እለተ ቅዳሜ፣ ታህሣሥ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ማለዳ ከአራት ኪሎ የጀመረው ጉዞዬ፤ አራት ሰዓት ከሃያ ላይ ሰበታ ከተማ በሚገኘው የሰበታ ሃዋስ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ጊቢ አድርሶኛል። ገና ወደ ቅጥር ጊቢው ሲዘልቁ እዚያም እዚህም የተከማመሩ የድንጋይና አፈር ቁልሎች ምቾት ይነሳሉ። በጊቢው ውስጥ ከአራት ያላነሱ የወረዳው የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እለቱ ቅዳሜ እንደመሆኑ ከአንዲት ክፍል ውጪ ሁሉም ዝግ ናቸው። ክፍት ሆና በምትታየው አንዲት በር እንዲሁም ከአንድ አነስተኛ ዛፍ ጥላ ስርና በሌላ በረንዳ ጥላ ስር ሰብሰብ ብለው በተቀመጡ አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች አቅራቢያዎች በርከት ያሉ ሰዎች ከጸሐይ ለመከለል ያክል በየበረንዳው ደረጃና በየድንጋዩ ላይ ቁጭ ብለው ይታያሉ።
ጉዳዩ ለአዲስ ደራሽ ሰው እንግዳ ቢሆንም፣ ለአካባቢው ነዋሪ ግን የተለመደ ክስተት ነው። ምክንያቱም እለቱ የሰበታ ሀዋስ ወረዳ እና የሰበታ ከተማ አካባቢ አባ ገዳዎች ችሎት ተሰይመው እውነቱን ከውሸት ገለባ ለይተው ፍርድ የሚሰጡበት፤ ህብረተሰቡን በገዳ ስርዓት የጨፌ ህግ መሰረት የሚዳኙበት ነው። በዚህ በኦሮሞ እሴት ታግዞ በሚከናወነው የአባገዳዎች ችሎት፣ ፎሌዎች እንደ ፖሊስ፤ አባ ቦኩ ወይም ኃላፊነታቸውን ለተተኪዎች ያስረከቡ አባ ገዳዎች አማካሪ ሆነው ያገለግላሉ።
በኦሮሞ ባህል ደግሞ በተለይም የአባ ገዳና ሀደ ሲንቄዎች ፊት እውነትን ይዞ መመረቅ የሚናፈቀውን ያክል፤ እውነትን ክዶ መረገም በእጅጉ ይፈራል። ለምን ቢሉ፣ ምርቃታቸው ያለመልማል፤ በህይወት ጉዞ ስኬትን ያጎናጽፋል። በአንጻሩ እርግማን አጥንት ይሰብራል፤ የህይወት ጉዞን ጣዕም አሳጥቶ የሞት ጥላ እንዲያጠላ ያደርጋል። እናም ሰዎች በዚህ ችሎት ሲቀርቡ፣ ስለእውነት ልባቸው ሀሴት አድርጋ፤ ስለ ሀሰት ደግሞ የአባ ገዳን አለንጌ እንኳ ይዞ ለመማል ጉልበት እስኪከዳቸው በፍርሃት የሚቆሙበት መሆኑን ተገንዝበው ነው። ችሎቱም ሁሉም ያለልዩነት የሚዳኝበት የአባገዳዎች የሚዛን መድረክ ስለመሆኑ በስፍራው ያገኘናቸው የአካባቢው ተገልጋዮች ይናገራሉ።
አቶ ወርቁ ጌታሁን፣ የአካባቢው ሽማግሌ ሲሆኑ፤ አባ ገዳዎች ለሽማግሌ የሚመሯቸው ጉዳዮች ሲኖሩ በሽምግልና ወስደው ጉዳዮች እንዲፈቱ ከሚሰሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የአባ ገዳዎች ችሎት የፍርድ ቤቶችን ስራ ያቃለለ፤ የአሁን ሁነቶችን ብቻ ሳይሆን እማኝ ጠፍቶና ፍርድ ተዛብቶባቸው ዓመታትን ያስቆጠሩ የተሰወሩ እውነቶችን ጭምር እያስገኘ ያለ ነው። ለምሳሌ፣ በሀሰት ምስክር ምክንያት ከአስር ዓመት በላይ የተቀጡ ሰዎች፤ በአባ ገዳዎች ችሎት አማካኝነት በሀሰት የመሰከሩ ግለሰቦች በመሃላ እውነቱን እንዲያወጡ፤ ታሳሪውም ነጻ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። ምስክሮቹም በሀሰት መስክረው ለእስር የዳረጉትን ሰው እንዲክሱ አባ ገዳዎች ፈርደውባቸዋል። በመሆኑም የአባ ገዳዎቹ ችሎት የእውነት ፍርድ ማግኛ ትክክለኛ ቦታ ለመሆን የቻለ፤ እንደ ፍርድ ቤቶች ቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ሳይኖረው በአጭር ጊዜ ፍርድን የሚሰጥ፤ ሰዎች እውነትን ብቻ አስበው በእውነት ብቻ እንዲጓዙ ትምህርት እየሰጠ ያለ ነው።
በዛፍ ጥላ ስር ሰብሰብ ብለው በአባገዳዎች ፊት ለፊት ከነበሩ ተከራካሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ ሲሳይ ስንታየሁ፣ ችሎታቸውን ጨርሰው ሲነሱ ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው በነገሩን መሰረት፤ አባታቸው ካገቧት ሁለተኛ ሚስት የንብረት ክፍፍል ሲያደርጉ ለአቶ ሲሳይም የእናታቸው መሬት ተከፍሎ እንዲሰጣቸው ይሆናል። መሬቱም በስማቸው ይዞርና ለአስራ ሁለት ዓመታት እየገበሩ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አባት መሬቴን መልስ የሚል ጥየቄ ቢያቀርቡም፤ ልጅ መሬቱ የእናቴ ድርሻ በመሆኑ የራሴ ነው፤ በማለት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። አባትም መሬቴን ሊመልስልኝ ይገባል በሚል ለአባ ገዳዎች ችሎት አቤት ይላሉ።
የአባገዳዎች ችሎትም የባህሉንም የህጉንም ሚዛን ይዞ የግራ ቀኙን ሀሳብ ካዳመጠ በኋላ፤ መሬት ለአባት ሳይሆን ለልጅ የሚገባ መሆኑን ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ አባት ምንም ቢበድል ወላጅ ነውና ልጅ አባቱን እንዲደግፍ መክረው፣ ቃል አስገብተውና አስታርቀው በባህሉ መሰረት መርቀው የህጉንም የባህሉንም እውነት አስጨብጠው በአንድነት ሸኝተዋቸዋል።
‹‹ይህ የአባ ገዳዎች ችሎት ከተጀመረ ወዲህ ፈጣሪም ቀርቦናል›› የሚሉት ደግሞ በእለቱ ለሌላ ጉዳይ መጥተው በስፍራው ያገኘናቸው አቶ ታደሰ ኩማ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በ2011 ዓ.ም ልጃቸው ተደብድባና ጭንቅላቷ ተጎድቶ ፍትህ ለማግኘት ቢጥሩም፤ በመደበኛው የሕግ አካሄድ መፍትሄ ስላጡ ለአባገዳዎች ችሎት ይዘው ይቀርባሉ። ችሎቱም በአገሩ ደንብና በገዳ ስርዓት መሰረት በዳይና ተበዳይን አቀራርበው ፍርድ በመስጠት ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋሉ። በመሆኑም ይህ ችሎት እውነት ጠምቷቸው በሀሰት ቀንበር ለሚንገላቱ ወገኖች የእውነት ፍርድ መድረክ ሆኖ የልብ ስብራታቸውን እየጠገነ ይገኛል። በፍርድ ቤቶች ከሚደርስ የሀሰት ምስክሮች ሴራ እና በዚህ ምክንያት ከሚፈጠር ያልተገባ ተግባር ታድጓቸው እውነትን ተናግረው እውነትን አግኝተው የሚሄዱበት ነው።
ሀደ ሲንቄ ወለቦ ጡሬ እና አባ ገዳ በዳዳ ነጋሳ፣ በዚህ ስፍራ ለህዝቡ እውነትን ለማስገኘት የሚተጉ የችሎት ተሰያሚ ሀደ ሲንቄና አባ ገዳዎች መካከል ናቸው። ሀደ ሲንቁ ወለቦ ጡሬ እንደሚሉት፤ ችሎቱ ሁሉም እውነትን አገኝበታለሁ ብሎ የሚመጣበት እንደመሆኑ በገዳ ስርዓት መሰረት ሚዛናዊ ፍርድ የሚገኝበት ነው። ችሎቱ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ሴቶች የጥበብ ባለቤትነታናቸው ታምኖበት ሀደ ሲንቄዎች ሙሉ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ነው። ሀደ ሲንቄዎችም ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እንዲሁም አቅመ ደካማ እናቶች ቶሎ እንዲስተናገዱ ጭምር የሴቶች መብት ተሟጋች ሆነውም የሚቀርቡ ናቸው። ይህ ግን ለሴቶች ሲባል ፍርድ ይዛባ የሚል ሳይሆን፤ ሴቶች ካለባቸው ኃላፊነትና ጫና አንጻር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ ለማስቻል ያለመ ነው።
ኦሮሞ ሰፊና ጥልቅ እሴት ያለው ነው የሚሉት ሀደሲንቄ ወለቦ፤ ‹‹ከረገመ ያጠፋል፤ ከመረቀም ያበለጽጋል›› ይላሉ። ከዚህ አንጻር በዚህ ችሎት እውነትን የማውጣት ሂደቱ ከእውነት ጋር ያለ የሚመረቅበት፤ እውነትን በሀሰት ለመቅበር የሞከረም የሚረገምበት ስለመሆኑ ይገልጻሉ። ምክንያቱም ከጅምሩ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ስለሚከራከሩበት ጉዳይ እውነት ይዘው ስለመሆኑ በመሃላ አረጋግጠው የሚያካሂዱት ስለመሆኑ፤ ክዶ የሚከራከርም ካለ የአባገዳ አለንጌን ይዞ በፈጣሪው ስም በገዳና ጨፌ ስርዓት መሰረት እንዲምል የሚደረግ እንደሆነም ያስረዳሉ። በመሆኑም ችሎቱ እውነት ተደብቃ እንዳትቀር የሚያደርግ፤ ሰዎች በፍርድ ቤቶች የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድና በሀሰት ምስክር ምክንያት የሚገጥማቸውን የተዛባ ፍርድ የሚያስቀር እንደሆነም ያብራራሉ።
አባገዳ በዳዳ ነጋሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ይሄን ችሎት በገዳ ስርዓትና በጨፌ መመሪያ መሰረት እያከናወኑት ሲሆን፤ የተጣላን የማስታረቅ፣ የተበደለን የማስካስ፣ ነፍስ የተጠፋፋ ቢኖር እንኳ በጉማ ህግ መሰረት እውነተኛ እርቅ የሚፈጸምበትና ከቂም በቀል በጸዳ መልኩ ከልብ የሆነ የአንድነትና የዝምድና ትስስር እንዲፈጽሙ ጭምር የሚደረገበት ነው። በዚህ ሂደት ግን ይህ ችሎት እንደ መደበኛው ፍርድ ቤት ምስክሮችን አይፈልግም፤ ሰዎችን ለማስታረቅና ለማስማማት እንጂ ወደ እስር ቤት የመላክ ዓላማም የለውም።
ምክንያቱም አንደኛ፣ አንዳንድ ወንጀሎች ምስክር ስለማይገኝላቸውና ምስክሮችም ዋሽተው የተሳሳተ ፍርድ ላይ ሊያደርሱ ስለሚችሉ ሲሆን፤ ሁለተኛም፣ ሰው ምንም እንኳን ለበደሉ በእስር ቢቀጣም የተጎጂ ወገን ከቂም በቀል ሊነጻ ስለማይችል ታሳሪው ሲለቀቅ ችግሩ ዳግም ሊከሰት የሚችልበት እድል የሰፋ በመሆኑ ነው። በመሆኑም የአባገዳዎች ችሎት ምስክሩ የመሃላ ቃል ሲሆን፤ ተከራካሪዎች የሚናገሩት እውነት ስለመሆኑ ‹‹የተናገርኩት ሀሰት ቢሆን ‹የወለድኩት አይደግ፣ ዘሬ አይባረክ፣ ከወጣሁበት አይመልሰኝ፣ እጄ ሰርቶ አያብላኝ፣ ምግብ ቆርሶ ቢያበላኝና ውሃም ቀድቶ ቢያጠጣኝ እንኳ የጠጣሁት ከደሜ አይወሃድ የበላሁትም ከስጋዬ አይሁን፤ እግሬም ይታሰር፣ ተራምዶም ያሰብኩበት አያድርሰኝ፤ የዘራሁት አይብቀልልኝ፤›› እና ሌሎችንም ለማዩ ቀርቶ ለሰሚው የሚከብዱ መሃላዎችን በመፈጸም እውነትነቱን የሚረጋግጥ ይሆናል።
ይህ ህግ ገና ከጅምሩ ፈጣሪ ለፍጡራኑ የሰጠው የቃልኪዳን ሕግ እንደመሆኑም ይሄን መሃላ በሀሰት የማለ፣ በመሃላ የገባውን ቃልም ያፈረሰ ሰው ልጅ አያገኝም፤ ዘሩም አይባረክም፤ ንብረት አይበረክትለትም፤ ጤና አይኖረውም፤ እድሜውም ያጥራል። በዚህ መልኩ በሀሰት ምለው የካዱ አራት ያክል ሰዎችም በማሉ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደወጡ ቀርተዋል። አምና እንኳን እንዲሁ ሶስት ያክል ሰዎች በሀሰት ምለው ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተለያየ አደጋ ሞተዋል። ሰውም ይሄን ስለሚያውቅ እውነቱን ተናግሮ ይቅርታ ይጠይቃል፤ ካሳም ከሶ ይታረቃል እንጂ አይዋሽም። አባ ገዳዎችም ቢሆኑ እውነትን ሳይሸሽግ ተናግሮ ለመፍትሄ ያገዘን መርቀው ሲሸኑ፤ እውነትን በውሸት ሸፍኖ አሻፈረኝ ያለን ረግመው ያሰናብታሉ። ይህ ደግሞ ለችሎቱ መከበርና መፈራት፤ ለተገልጋዮችም እውነትን ይዞ መቅረብ አግዟል።
የገዳ ስርዓት ፍልስፍናው በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና ሌላም ጉዳይ ልዩነት ሳይፈጥር ሁሉም የፈጣሪ ፍጡር እኩል ነው የሚል ነው። በዚህም የገዳ ስርዓት ሴትና ወንድን እኩል ያያል፤ የሰው ልጆችን በሙሉ በእኩል ይመዝናል፤ ስለዚህ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በዚህ ችሎት እኩል ይገለገላሉ። አባ ገዳዎቹም በችሎቱ በፈጣሪ ክብር የተሰጠውን የሰው ልጅ በእምነትና ማንነት ብሎም በጾታ ሳይለዩ በገዳ ስርዓት መሰረት በእኩልነት ማገልገልና ማስተናገድ፤ እውነትን ለባለእውነት መስጠት እንደሚገባ አምነው የሚተጉ ናቸው።
‹‹ሰውን የሚጎዳው ተፈጥሮ ሳይሆን የራሱ ተግባር ነው›› የሚሉት አባ ገዳ በዳዳ፤ ሰዎች በዚህ መልኩ ለችሎት ሲቀርቡ እውነትን ይዘው መሆን እንዳለበትና በሀሰት መማልም ውጤቱ የከፋ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ አባገዳዎች እውነትን ለማውጣትና ፍትህን ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት አጋዥ በመሆን ከእርግማን ይልቅ ምርቃትን ሊያተርፍ፤ ይሄን እውነትና ፍትህን አስተሳስሮ በሀሰት እየተበደሉ ያሉ ዜጎችን እንባ ለማበስ የሚሰራውን የገዳ ስርዓትና የጨፌ ህግ ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ይመክራሉ።
አባ ገዳ በዳዳ ነጋሳ እና ሀደ ሲንቄ ወለቦ ጡሬ እንደሚሉት፤ የአባ ገዳ ችሎት ተሰያሚዎች ሁሉም የየራሳቸው የኑሮ ውጣ ውረድ አለባቸው። ይሁን እንጂ ከገዳ በተቀበሉት አደራ መሰረት ህዝባቸውን በፍትህ አደባባይ በእውነት ለማገልገል እየሰሩ ናቸው። ወደ ችሎቱ ሲመጡም የግል ስራቸውን ትተው ቢሆንም ጠዋት ወጥተው ማታ ድረስ ሲሰሩ ለትራንስፖርት፣ ለምግብና ውሃ ከራሳቸው ወጪ እንጂ የተለየ የገቢ ምንጭ ወይም ድጎማ የላቸውም። በሌላ በኩል ችሎቱ ማክሰኞና ቅዳሜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ረቡዕ ደግሞ የችሎት ቀጠሮ መስጫና መጥሪያ ደብዳቤዎች ወጪ የሚያደርጉበት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ አንድም አባ ገዳዎች የራሳቸውን ስራ ማከናወን ስላለባቸው ሲሆን፤ በዋናነት ግን ችሎት የሚቀመጡበት ቦታ የወረዳው ጽህፈት ቤቶች ጊቢ ውስጥ በመሆኑ በስራ ቀናት ችሎቱን ለማከናወን የሚያስችል ስፍራም ሆነ የጸጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው።
ምክንያቱም ይሄን ችሎት ሲያከናውኑ የመቀመጫ ቦታ እንኳን የላቸውም፤ አሁን ያሉበት ቦታም ቢሆን በወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት መልካም ፈቃድ ነው። ሆኖም የችሎት ስራቸው ከነፍስ ግድያ ጀምሮ ያሉ በርካታ ጉዳዮች የሚመለከቱበት እንደመሆኑ አንዳንዱ ሚስጢራዊነትን ይፈልጋል። የችሎት ማስቻያ ቦታቸው ደግሞ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ከሚያውሳቸው አንዲት ጠባብ ክፍል ውጪ ሌላው በየዛፍ ጥላና በረንዳው ስለሚካሄድ ስራቸውን አዳጋች አድርጎባቸዋል።
ተገልጋዮችም ቢሆኑ በጸሃይና አቧራ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ሲንገላቱ ማየቱ እረፍት አልሰጣቸውም። በመሆኑም ባለሃብቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የመንግስት አካላትና የአካባቢው አስተዳደሮች የችሎቱን አስፈላጊነት በአካል ጭምር ቀርበው በመመልከት፤ አንደኛ፣ ምቹ የሆነ ችሎት የማስቻያ ቦታ፤ ሁለተኛም ለተገልጋዮች ተራ መጠበቂያ የሚሆን አነስተኛ አዳራሽ እንዲሰራ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውንም፣ ኃላፊነታቸውንም እንዲወጡ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አቶ ሲሳይም ሆኑ አቶ ታደሰ እና ሌሎችም በስፍራው ያገኘናቸው ተገልጋዮች በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አባ ገዳዎች ክብር አላቸው። በክብራቸው ልክም ስለ እውነት እየሰሩ የእውነት ፍርድንም እያስገኙ ናቸው። ይሁን እንጂ የክብራቸውና የስራቸውን ቦታ አላገኙም። ይልቁንም ጥላ ፍላጋ ከቦታ ቦታ እየተንቆራጠጡ፤ በሁካታ መሃል ሆነው ስለሚሰሩም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለመናገር እንኳን እየተሳቀቁ፤ በድንጋይ መቀመጫ ላይ ሆነው እየሰሩ ነው።
በመሆኑን እነዚህን የእውነት ችሎት ባለቤቶች፤ አንድም ተገቢ ቦታና ችሎት እንዲኖራቸው በማድረግ፤ ሁለተኛም አቅማቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉበት ስልጠና በመስጠት፤ ሶስተኛም ስራቸውን ትተው ችሎት የሚሰየሙ እንደመሆኑ ለእለት እንኳን በልተው የሚውሉበትን ወጪ የሚሸፍን የኪስ ገንዘብ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያለ የመንግስት አካል፤ ከግለሰብ እስከ ድርጅት ያለ ዜጋ የድርሻውን ሊያበረክት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የእረፍት ቀን ሲሆን በአንድ ቢሮ ቁልፍ ስለሚገኙ ቢሮዋንም የበረንዳና የዛፍ ጥላንም ይጠቀማሉ፤ የስራ ቀን ሲሆን በየዛፍ ጥላው ስር ይሰየማሉ። ይህ ደግሞ በስራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። በተለይም ሚስጢራዊነታቸው ሊጠበቁ የሚገባቸውን የችሎት ጉዳዮች ለማየት በእጅጉ ተቸግረዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ወንድወሰን ሽመልስ