“እነርሱው ጎትጉተው ለላኳቸው ሚዲያዎች ጥያቄ ምላሽ ሰጠን እንጂ መግለጫ አላወጣንም”
– የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን
“የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ እሰጣለሁ ጠብቁ ብሎን ሲያበቃ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጠው መግለጫ ተገቢ አይደለም” ሲሉ የኮርፖሬሽኑ ተከራይ ነጋዴ ተወካዮች ነን ያሉ ግለሰቦች አቤቱታቸውን አቀረቡ።
ኮርፖሬሽኑም “እነርሱው ጎትጉተው ለላኳቸው ሚዲያዎች ጥያቄ ምላሽ ሰጠን እንጂ መግለጫ አላወጣንም፤ ውሳኔም አላሳወቅንም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተከራይ ነጋዴዎች ተወካዮች እንደሆኑ በመግለጽ ዛሬ በድርጅታችን ተገኝተው ቅሬታቸውን ያቀረቡ ግለሰቦች እንደገለጹት፤ “ሰሞኑን በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በተከራዮች መካከል ባለው ቅሬታና አንዳንድ የሀሳብ ልዩነቶች መካከል በተፈጠረው ቅሬታ የድርድር ሂደት ውስጥ ባለንበት ሰዓት ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጠው መግለጫ ሚዛናዊነት እንዲኖረው እኛም ድምጻችን ሊሰማ ይገባል” በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
“የተሰጠው መግለጫ እኛ ካለን ቅሬታ ጋር የሚጣጣም አይደለም” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “እኛ ለኮርፖሬሽኑ ጥያቄዎቻችንን አቅርበን መልሱን ለታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ተቀጥረን የኮርፖሬሽኑን ምላሽ እየተጠባበቅን ባለንበት ሰዓት የተሰጠው መግለጫ የቅሬታችን ይዘት፣ እንዲሁም አጠቃላይ ያለውን የችግሩን ይዘት የሚገልጽ አይደለም” ብለዋል።
“ኮርፖሬሽኑ ለቅሬታችሁ ምላሽ እስክሰጥ ጠብቁ ብሎን የሰጠው መረጃ ውሳኔውን የሚያሳውቅ መስሎ ስለተሰማን እኛ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል” በማለትም ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያስረዱት።
በግለሰቦቹ ቅሬታ ዙሪያ ምላሽ ይሰጠን ዘንድ የጠየቅነው ኮርፖሬሽኑ በምላሹ፤ “እነርሱው ጎትጉተው ለላኳቸው ሚዲያዎች ጥያቄ ምላሽ ሰጠን እንጂ መግለጫ አላወጣንም፤ ውሳኔም አላሳወቅንም” ሲል አስታውቋል።
ተከራዮች ከኮርፖሬሽኑ ምላሽ ሳያገኙ በየሚዲያው እየሄዱ ባደረጉት ጉትጎታ ምክንያት ወደ ኮርፖሬሽኑ ለመጡ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ግዴታውን ከመወጣት በዘለለ ውሳኔውን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ አለመኖሩን የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ገብረመድህን ተናግረዋል።
“ተከራይ ነጋዴዎቹ ተመኑን አስመልክቶ ለኮርፖሬሽኑ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑም ቅሬታዎቻቸውን እየተመለከተ ሲሆን፤ የደረሰበትን ውሳኔ ሳያሳውቅና እነርሱም ውሳኔውን ሳያውቁ ወደሚዲያዎች ቀርበው በመጎትጎት ጋዜጠኞች ወደ ኮርፖሬሽኑ እየሄዱ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አድረገዋል። ኮርፖሬሽኑም ከጋዜጠኞች ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ግዴታ ስላለበት ይሄንኑ አድርጓል እንጂ ውሳኔውን የሚያሳውቅ መግለጫ አላወጣም፡፡ ምክንያቱም ኮርፖሬሽኑ ከሕዝብም ሆነ ከሌላ አካል ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠትና እውነታውን የማሳወቅ ግዴታ አለበት” በማለትም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
አሁንም ተከራይ ነጋዴዎች ኮርፖሬሽኑ ውሳኔውን በግልጽ እስኪያሳውቃቸው ድረስ ሚዲያውን ጨምሮ ወደተለያየ ቦታዎች ከመሄድ ይልቅ ውሳኔውን አውቀውና ይሄንኑ ይዘው ቅሬታቸውን ማቅረብ ቢችሉ የተሻለ ይሆናል ሲሉም ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
ኮርፖሬሽኑ የአብቱታ አቅራቢዎችን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔውን ታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ እንደሚደርግ መግለፁ ይታወሳል።