ሄፕታይተስ ለብዙ የቫይረስ ልክፍት የተሰጠ ስም ነው። እንደ ሄፐታይተስ ኤ፣ ሄፐታ ይተስ ቢ፣ ሄፐታይተስ ሲ ያሉ ጉበትን የሚያጠቁ በሽታዎች ማለት ነው። በሀገራችን በተለምዶ የወፍ በሽታ ተብሎ የሚጠራው ሄፐታይተስ ኤ ሲሆን ይህ ስያሜ ከወፍ ጋር ምንም የሚያዛምደው ነገር የለም። በሽታው በአብዛኛው ትኩሳት የሚያስከትል ሲሆን፣ ሲጀምረን የምግብ ፍላጎት ይቀንሳል። ትኩሳት ሲቀንስም ዐይን ቢጫ መልክ ይይዛል። ይህ በሽታ በሕፃናትና በልጆች ላይ ቀለል ቢልም በአዋቂዎች ላይ ግን ይጠናል። ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት በዚህ ሕመም ከተያዙ ይጠናባቸዋል፤ እስከ ሞትም ሊያደርስ ይችላል።
ሄፐታይተስ ኤ በተለምዶ የወፍ በሽታ
በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቻችን ገና በልጅነት በሄፐታይተስ ኤ የመያዝ ዕድላችን ከፍተኛ ቢሆንም ሕመሙ ቀላል ስለሆነ ያን ያክል ጉዳት አያደርስም። ሰውነታችን በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ የዚህን በሽታ መከላከያ አብዛኛውን ጊዜ ይፈጥራል።
• ሕመምተኛው ምንም ምግብ መብላት አይፈልግም፤ ለበርካታ ቀኖችም ሳይመገብ ሊቆይ ይችላል።
• በቀኝ በኩል ጉበት አጠገብ ወይም ከጎድን አጥንት በታች አንዳንድ ጊዜ ሕመም ይኖራል።
• መላ ሰውነትን ሊያሳክክ ይችላል።
• ትኩሳት ሊኖረው ይችላል።
• ከጥቂት ቀናት በኋላ ዐይን ቢጫ ይሆናል።
• ምግብ በማየትና በማሽተት ብቻ ሊያስመልስ ይችላል።
• ሽንት ጠቆር ብሎ ቢጫ ይመስላል። ዐይነምድር ግን ነጭ ሊመስል ይችላል።
በአጠቃላይ በሽተኛው ለሁለት ሳምንታት በጣም ይታመማል፤ ከአንድ እስከ ሦስት ወራትም ገመምተኛ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም እነኝህን ነጥቦች ማስታወስ ያስፈልጋል፡-
• ፀረ ተሃዋስያን መድኃኒቶች ለሄፐታ ይተስ ሕክምና አይጠቅሙም። እንዲ ያውም አንዳንድ መድኃኒቶች በጉበት ላይ ተጨማሪ ጉዳትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
• ሕመምተኛው በቂ ዕረፍት ማግኘትና ብዙ ፈሳሽ መጠጣት አለበት። በተለይ የፍራፍሬ ጭማቂዎች።
• ሕመምተኛው የምግብ ፍላጎቱ እየተመለሰ ሲመጣ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ መደረግ አለበት።
• ሕመምተኛው ለረዥም ጊዜ አልኮል መጠጣት የለበትም።
• ጮማና ቅባት የበዛበት ምግብም መውሰድ የለበትም።
የመከላከያ ዘዴው
የጉበት በሽታ (ሄፐታይተስ ኤ) ቫይረስ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፈው በምግብ ወይም በውሃ ብክለት ነው። ስለዚህ ሕመምተኞች የሚፀዳዱበት ቦታ ዝንቦች ሊደርሱበት በማይችል ቦታ መሆን አለበት። እንዲሁም ማንኛውም እርዳታ ሰጪ ወይም አስታማሚ ምንጊዜም እጁን በሳሙና ሙልጭ እያደረገ መታጠብ አለበት።
ሕፃናት በሽታው ቢኖርባቸውም የበሽታውን ምልክት ሳያሳዩ ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ስለዚህ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የግል ንፅህና አጠባበቅ ላይ የጥንቃቄ መመሪያዎችን መተግበር አለባቸው። ለበሽታው የተጋለጡ ግለሰቦች ብቻቸውን እንዲበሉና የተለየ መጠጫ ብርጭቆ እንዲሰጣቸው መደረግ አለበት። ነገር ግን የበሽታው ምልክቶች ከጠፉ ከ3 ሳምንት በኋላ በሽታው መተላለፍ የማይችል ስለሆነ ችግር የለውም።
በሽታው እንዳይተላለፍ ወሲብ በሚፈፀምበት ጊዜ በኮንዶም መጠቀም ይገባል፤ እንደውም ቢቀር ይመረጣል።
የጉበት በሽታ (ሄፐታይተስ ኤ) ቫይረስ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፈው በምግብ ወይም በውኃ ብክለት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012