ጋንግሪን በጣም አደገኛ የሆነ የቁስል መመርቀዝን የሚያስከትል በሽታ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው በእግርና በእጅ እንዲሁም በእግርና በእጅ ጣቶች ላይ ቢሆንም በማንኛውም የአካል ክፍል ላይ ሊከሰትም ይችላል።ከቁስሉም የሚከረፋ ግራጫ ወይም ቡናማ ዓይነት ፈሳሽ ይወጣል።ቁስሉ አካባቢ ያለው ቆዳ ጠቆር ብሎ ውሃ ሊቋጥር ይችላል። የቁስሉ ሥጋም እንደአረፋ ያኮፈኮፈ ይመስላል።የቁስል መመርቀዝ አደጋ ከተከሰተ ከ6 ሰዓት እስከ ሦስት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጀምራል።በአጭር ጊዜ ውስጥም በሽታው እየከፋና ቁስሉም እየሰፋ ይሄዳል።አስፈላጊው ሕክምና በፍጥነት ካልተሰጠ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሞት ይዳርጋል፡፡
ጋንግሪን ማለት ከሙሉ አካላችን ተለይቶ የተወሰነ የሰውነታችን ክፍል እየሞተ ወይም በድን እየሆነ መምጣት ማለት ነው።ጋንግሪን፣ መጀመሪያ ከነበረበት ቦታ ሊስፋፋ የሚችል የጤና ችግር ስለሆነ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል። በእግር ጣቶች መሐል እንዲሁም በሌላ የሰውነት ክፍል ላይ የሚፈጠርን አነስተኛ ቁስለት ችላ ማለት የለብንም፤ በተለይ የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ቁስለቶችን ችላ ሳይሉ ተከታትለው እንዲድን ማድረግ አለባቸው፡፡
የጋንግሪን በሽታ መከሰቻ ምክንያቶች
የጋንግሪን ክስተት በደም እጥረት የሞተ የሰውነት ክፍል እንደማለት ነው፤ የጋንገሪን በሽታ አንድ የሰውነት ክፍል ደም አጥሮት ምግብና ኦክስጅን አልደርሰው ብሎ ሲጠቁርና ሕይወት አልባ ሆኖ በድን ሲሆን፣ ጋንግሪን ይዞታል ወይም ተፈጥሯል ይባላል።ለምሳሌ በተለያዩ አደጋዎችና ሌሎች ምክንያቶች በአካላችን የተለያዩ ክፍሎች የደም ዝውውር ቢቋረጥ፣ የተቋረጠበት የሰውነት ክፍል ጋንግሪን ይፈጥራል።እንዲሁም አንዳንዴ የልብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ደም ይረጋና ከልብ ወደ ደም ስሮች ይሄዳል፤ በጣም ትንሽም ብትሆን የረጋች ደም የደም መተላለፊያ ትቦዎችን ትዘጋለች፤ በዚህ ጊዜ ይህ ደም ይመግበው የነበረው የሰውነት ክፍል ምንም ማግኘት ስለማይችል ጋንግሪን ይፈጥራል፤ ምክንያቱም አካሉ በምግብና አየር እጥረት ምክንያት ይሞታል። ከዚህ በተጨማሪ በደም ሥር ጥበት ምክንያትም ጋንግሪን ሊፈጠር ይችላል። ለረጅም ጊዜ የስኳር ሕመም የገጠማቸው ሰዎች፣ የደም ግፊት ችግር ያለባቸው እንዲሁም ከፍተኛ የደም ቅባት ያለባቸው ሕሙማን የደም ሥራቸው ሊጠብ ይችላል።ሌላው ምክንያት ደግሞ የቁስል ማመርቀዝ ወይም ኢንፌክሽን ነው፤ የሰውነት ክፍል አመርቅዞ ሲያብጥና በባክቴሪያ ሲጠቃ አካሉ በደም ሥር ደም አይደርሰውም።ስለዚህ ምግብና አየር ስለማይደርሰው ጋንግሪን ይፈጠራል።እንደ እጅና እግር ያሉ አካላትንም ደም እንዳይዘዋወር ጠፍንገን ለረዥም ሰዓት ካሰርናቸው ጋንግሪን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ጋንግሪን ማለት ከሙሉ አካላችን ተለይቶ የተወሰነ የሰውነታችን ክፍል እየሞተ ወይም በድን እየሆነ መምጣት ማለት ነው
አብዛኛውን ጊዜ የችግሩ ተጠቂዎች እነማናቸው?
በሽታው የሚከሰተው አብዛኛውን ጊዜ በስኳር፣ በልብ እንዲሁም በደም ግፊት ሕሙማን ላይ በመሆኑ እነኝህ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች የተለየ ክትትል ማድረግ አለባቸው፤ በተለይ ማንኛውንም ቁስለት ችላ ማለት የለባቸውም፤ ጋንግሪን የሞተ የአካል ክፍል በመሆኑ ሕክምናው የተጠቃውን በድን አካል ማስወገድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ምርጫ ደስተኞች አይሆኑም፤ ሐኪሞችንም ለመቁረጥ ይፈጥናሉ የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፤ ሌሎች አማራጮች ካሉ በማለትም መፍትሔ በማፈላለግ ጊዜ ይሰጣሉ፤ ይህ ሁኔታም በሽታው ሥር እንዲሰድ ክፍተት ይፈጥራል፤ ይህ ሁኔታ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ታካሚውን ይሆናል።በጋንግሪን በሽታ ላይ ሐኪሞች ነገር ሥር ሳይሰድ የሚሰጡትን የመዳን ውሳኔ በጊዜ መቀበል ህይወትን ሊያድን ይችላል፡፡
በጋንግሪን በሽታ ላይ ሐኪሞች ነገር ሥር ሳይሰድ የሚሰጡትን የመዳን ውሳኔ በጊዜ መቀበል ህይወትን ሊያድን ይችላል
ሕክምናው ምንድን ነው?
እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ስፋት ሕክምናው ሊለያይ ይችላል፤ ሁኔታው በጊዜ ከተደረሰበት በሕክምና ሊድን ይችላል፤ ነገር ግን የተስፋፋ ከሆነ በሕክምናው አብዛኛውን ጊዜ የተጎዳውን በድን አካል ቆርጦ እስከ ማስወገድ ሊደርስ ይችላል።አነስተኛ የሚመስሉ ቁስለቶችን ወደ ሕክምና ተቋማት ሳናቅማማ ሄደን በማሳየት መፍትሔ ማግኘት የመጀመሪያ አማራጫችን መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012