በፈጠሩት አዲስ የሥራ መስክ ለበርካቶችም የሥራ ዕድል ማውጣት ችለዋል። የፀጉር መሸፈኛ እና ገዋናቸውን አድርገው በየዕለቱ በመሥሪያ ቤታቸው ቅጥር ወዲያ ወዲህ እያሉ ሲሰሩ ይውላሉ። በጥራት የሚያዘጋጇቸው የታሸጉ ምግቦች ከጥራታቸው በተጨማሪ ‹‹ጣት የሚያስቆረጥሙ›› ናቸው ተብለው በበርካቶች ተሞካሽቶላቸዋል። ምርታቸው ምስጋናን ብቻ ሳይሆን ግን ሰፊ ገበያንም እያመጣላቸው ይገኛል።
ወይዘሮ የምስራች አበራ ይባላሉ የዛሬዋ እንግዳችን። አባትና እናታቸው መምህራኖች ነበሩና አዲስ አበባ ለክረምት ስልጠና በመጡበት ወቅተ ለእስር ይዳረጋሉ። የእስሩ ምክንያት ደግሞ አንድን ሃይማኖት አራምዳችኋል በሚል ነው። በ1965 ዓም በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸው የታሰሩት ጥንዶች ታዲያ በቃሊቲ /ከርቸሌ/ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ወይዘሮ የምስራች የተወለዱት።
እናት አራስ መሆናቸውን ተከትሎ ደግሞ ለጥቂት ቀናት ከታሰሩበት ተፈትተው ልጃቸውን ይዘው ወደመኖሪያ ቀዬአቸው ባህርዳር ከተማ ያቀናሉ። አባታቸው ደግሞ ቆየት ብለው ተፈቱና ቤተሰቡን ተቀላቅለው ህይወታቸውን ቀጠሉ።
በባህርዳር ያደጉት እንግዳችንም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሰርፀድንግል ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ ፋሲሎ የተሰኘው ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ ጣና ሐይቅ የተሰኘው ትምህርት ቤት ገብተዋል። የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያን ወስደው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ባለማምጣታቸው የቋንቋ ትምህርትን በግል ኮሌጅ ለመከታተል ይወስናሉ።
የኮሌጅ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ በመዝገብ ቤት ሥራ ይቀጠራሉ። ለሁለት ዓመታት እንደሰሩ ትምህርታቸውንም በዲፕሎማ ተመርቀው አጠናቀቁ ። በወቅቱ ደግሞ የተቀጠሩበት ተቋም ከማስታወቂያ እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ጋር ሲቀላለቅል በተሰራው አዲስ መዋቅር በጋዜጠኝነት የሚሰሩበት ዕድል ተፈጠረላቸው።
በጋዜጠኝነቱም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በሚተላለፈው የሬድዮ ጣቢያ ላይ በዜና፣ ፕሮግራም አዘጋጅት እና ማስታወቂያ አንባቢነቱ ሰርተዋል። ከመጀመሪያዋ የሥራ ቀናቸው ጀምሮ ከአለቃቸው በአገኙት ማበረታቻ የተነቃቁት ወይዘሮ የምስራች ለ10 ዓመታት በሬዲዮ ጋዜጠኝነቱ እና በኩር ጋዜጣ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ከዚያ በኋላም አዲስ አበባ በሚገኘው የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ስር ተዛውረው ለአንድ ዓመት ያክል ሰርተዋል። በዚህ ሁሉ መሐል ግን ትዳር ይዘው ሁለት ልጆችንም ወልደው ነበር። እናም ቀን ለዘገባ ይወጣሉ፤ ልጆቻቸውን ለሠራተኞች ሰጥተው ማታ ደግሞ ይመለሳሉ፤ ባለቤታቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀኑን ያሳልፋሉ። ይህ ሁናቴ ግን የልጆቻቸው አስተዳደግ ላይ አደጋ እንደሚጥለው በመረዳታቸው ሥራቸውን ለቀው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ይወስናሉ።
ልጆችን ከማሳደጉ በተጓዳኝ የተለያዩ ቋንቋ እና የኮምፒውተር ስልጠናዎችን ቢጀምሩም የረጅም ጊዜ መክሊታቸውን ጋር ግን አልተገጣጠሙም ነበር። እየነገዱ በሐቀኝነት መሥራት ቢሆንም ፍላጎታቸው፤ ነጋዴ ከሆንኩ ሐጢያት ይሆንብኛል የሚል አስተሳሰብ ግን እነደነበራቸው ያስታውሳሉ። እናም ወደ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ሲያቀኑ ንግድን በሐቀኝነት ሠርቶ መኖር እንደሚቻል በብዙ የሚያስረዷቸው ሰዎችን ያገኛሉ።
<<ይህ ከሆነማ ሳልሰርቅ በዕውነተኛ መንገድ እየነገድኩ እራሴን መለወጥ እችላለሁ>> ብለው አዕምሯቸውን ያሳምናሉ። ከዚያም እንጀራ በሽሮ እየሰራሁ ማቅረብ አለብኝ ብለው ጦረኃይሎች አካባቢ የምትገኝ አንዲት አነስተኛ ቤት በ1 ሺህ 500 ብር ተከራዩ።
በሚሊኒየሙ መጀመሪያ በቤት ውስጥ የነበሯቸውን ቁሳቁሶች ይዘው እንጀራ በሽሮ ለሚመገቡ መንገደኞች ለመሸጥ ሲነሱ ጎረቤታቸው የነበረው ሲሊንደር መሸጫ ሱቅ በመሆኑ ማባያ ወጦችን በእሳት መሥራት እንደማይችሉ ይነገራቸዋል። ያጋጠማቸውን ችግር ለማለፍ ብለው ሳንቡሳ ወደማዘጋጀቱ ተሸጋገሩ።
አንዲት የሳነቡሳ መጥበሻ ማሽን ገዝተው በተጨማሪም አምባሻ እያዘጋጁ መሸጥ ጀመሩ። የሳንቡሳው ንግድ ጥሩ የያዘላቸው ቢሆንም እርሳቸው ግን ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ ስለፈለጉ አምባሻ እያዘጋጁ ማከፋፈሉን ብቻ ምርጫቸው አደረጉ። እናም ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ የጦርኃይሎች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደሲኤምሲ አካባቢ ገቡ።
በዚያም አንድ ግቢ ተከራይተው ግማሹን ከቤተሰባቸው ጋር ለመኖሪያ ግማሹን ደግሞ አምባሻ ለማዘጋጃነት አዋሉት። በመጀመሪያዋ ቀንም 24 አምባሻ አዘጋጅተው ቅመሱልኝ እያሉ በየሱቁ እየተዘዋወሩ አስተዋወቁ። በሂደትም ምርታቸው እየተወደደ እስከ መሪ እና ሾላ ገበያ እንዲሁም ወሰን አካባቢዎች ለሚገኙ መሸጫዎች ማከፋፈሉን ተያያዙት።
በወቅቱ አብረዋቸው ከሚኖሩት እህታቸው ጋር ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ተነስተው አምባሻ በመጋገር፤ ከጠዋቱ ከ12 ሰዓት ጀምሮ በእግር እና በታክሲ እየተዘዋወሩ በማከፋፈል የሚውሉት ወይዘዋ፤ የተቀረውን ጊዜያቸውን ደግሞ ለቀጣዩ ቀን ግብዓት የሚሆን ዱቄት ለመግዛት ወደ መርካቶ ጎራ ማለታቸው አይቀሬ ነበር። አንድ ቀን ግን አብረዋቸው ጠዋት ወጥተው ሥራውን የተመለከቱት ባለቤታቸው ድካማቸውን ይታዘባሉ። በመሆኑም አጋር እነደሚያስፈልጋቸው ይወስናሉ።
በመሆኑም ወይዘሮ የምስራች አምባሻውን ሲያዘጋጁ፤ አንድ ሚኒባስ የነበረው የቤተሰቡ አባል ደግሞ በማከፋፈሉ እንዲሰራ ስምምነት ተደረገ። ከዚህ በኋላ ወይዘሮ የምስራች ከአምባሻው በተጨማሪ፣ ህብስት እና ድፎ ዳቦ በማዘጋጀት ሲያቀርቡ አጋራቸው ደግሞ እያከፋፈለ ለአምስት ዓመታት በጋራ ሠርተዋል።
በወቅቱም በቀን እስከ አምስት ኩንታል ዱቄት ለምግብነት እስከ ማዘጋጀት የደረሰ ገበያ እንደነበራቸው አይዘነጉትም። በ2003 ዓ.ም ግን አንድ ሥራ ላይ መሰማራት እንዳለባቸው ቀንም ማታም ማሰብ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ። የተለያዩ ወጦችንም አሽገው መሸጥ እንደፈለጉ ለባለቤታቸው ሲያስረዱ በጊዜው ግርታን ቢፈጥርም ቆይቶ ግን ባለቤታቸውም ሐሳቡን ተቀበሉት።
በመሆኑም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምግብ አቅርቦት ምን መልክ እንዳለው ጉብኝት ካደረጉ እና አሰራሩን ከተገነዘቡ በኋላ የ2006 አዲስ ዓመት ኤግዚቢሽን ባዛር ላይ ያዘጋጇቸውን የታሸጉ ማባያ ወጦች አቀረቡ። የህብረተሰቡ ተቀባይነት ደግሞ ከፍተኛ መሆኑን ሲመለከቱ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት አድርገው ሥራውን ጀመሩ። በተደጋጋሚ ጊዜ ቢሰራም የተለየ ጣዕሙን እንዳይለቅ አድርገው ለእያንዳንዱ ማባያ የእራሱ የሆነ መዘርዝር አዘጋጁ።
ጉርድ ሾላ አካባቢ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ተከራይተው በቤት ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን አሟልተው በግላቸው የጀመሩት ሥራ ተወዳጅነቱ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ሄደ። የዶሮ ወጥ፣ ምንቸት እና ምስር ወጥ አዘጋጅተው ማሸግ ጀመሩ። ታፑ የበሰሉ ምግቦችን የተሰኘ አርማን ይዞ የሚዘጋጁ ወጦችም በርካቶችም በየዕለቱ የሚመርጡት ማባያ ሆነ ። ወይዘሮዋ በተጨማሪነት ድፎ ዳቦ እና እንጀራ አስጋግረው በፕላስቲክ አሽገው ይሸጣሉ።
ቀስ በቀስ ንግዱ እየተስፋፋ ሄዶ የመሸጫ ሱቅ ከፍተው እስከ መሥራት አደረሳቸው። ይህ አዲስ የሥራ መስክ ብዙ ደንበኛ በማፍራቱ አንድ ብለው የጀመሩት የምርት መሸጫ ሱቅ አምስት ደረሰ። መገናኛ፣ ሲኤምሲ፤ ቦሌ እና በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሱቆችን ከፍተው ታፑ ብለው በሰየሙት ድርጅታቸው ሥር የበሰሉ ምግቦች መሸጡን ተካኑበት።
አሁን ላይ ወሰን አካባቢ ባለው ሰፊ መሥሪያ ቦታቸው በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊነታቸው የጨመረውን ምርት እያዘጋጁ ይገኛል። በቀን እስከ አንደ ሺህ እንጀራ አስጋግረው አሽገው ይሸጣሉ። ምንም እንኳን የገበያ ሁኔታው ቢለያይም በቀን እስከ 1 ሺህ ስድስት መቶ በኮባ የተዘጋጁ ድፎ ዳቦዎችን ማቅረብ የሚችል 9 ዘመናዊ ማሽኖች አሏቸው። አንዱን በዘመናዊ መልኩ የታሸገ እና ለረጅም ጊዜ ፍሪጅ ውስጥ መቆየት የሚችል ሙሉ ዶሮ ወጥ በ1 ሺህ ሰላሳ ብር ያቀርባሉ።
ዶሮዎች ታርደው እስኪበስሉ እና እስኪታሸጉ ድረስ በማምረቻው ውስጥ ጣጣቸው ይጠናቀቃል። ማሸጊያዎቹም ከፋብሪካዎች በትዕዛዝ የሚሰራ ሲሆን የእያንዳንዱም ምግብ ንጥረ ነገር እና የድርጅታቸው አርማ ያዘለ ነው። ህብስት እና በ500 ግራም የታሸጉ ማባያ ወጦችንም በአምስቱም መሸጫ ሱቆቻቸው በቀጥታ ለደንበኞቻቸው ያቀርባሉ። የበሰሉ የታሸጉ ምግቦቻቸው ከፍሪጅ ወጥተው ለማዕድ ለመቅረብ የሚጠበቅባቸው በአግባቡ ሞቅ መደረግ ብቻ ነው። ይህ አይነቱ ምግብ በተለይ በቤት ውስጥ ለማብሰል ምቹ ላልሆነላቸው ሰዎች አማራጭ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ወይዘሮዋ ለድግስ እና ለተለያዩ ግብዣዎች የሚሆኑ የምግብ አቅርቦት ጥያቄዎች ሲቀርብላቸው ሙሉ ዝግጅቱን አሰናድተው ያቀርባሉ። ወይዘሮ የምስራች በጀመሩት የበሰሉ ምግቦች ሥራ 125 ሠራተኞችን ቀጥረዋል። ሥራ በሚበዛበት ወቅተ ቁጥሩ ከዚህም ሊያልፍ እንደሚችል ይገልፃሉ።
የእራሳቸው መሥሪያ እና መሸጫ የሌላቸው ሥራ ፈጣሪ ለቤት ኪራይ ግን በአጠቃላይ በወር 300 ሺህ ብር ይከፍላሉ። የወሰኑ ማምረቻቸው የግብት፤ የማብሰያ፣ የማጠቢያ እና የማቆያ እንዲሁም የሂሳብ ክፍል በሚል ተከፋፍሎ፣ እያንዳንዱ የሥራ ቦታ በጽዳትና በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው።
የመስሪያ ቦታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጊዜ ለከተማ አስተዳደሩ ባመለክትም ምላሽ የሚሰጠኝ ግን አላገኘሁም የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ቦታ አግኝተው ሰፋ ያለ ሥራ መሥራት ቢችሉ በርካታ ሰዎችን ቀጥረው የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ በሙሉ እምነት ይናገራሉ። በመሆኑም የሥራው ባህሪ ሰፊ ቦታን የሚፈልግ እና ለበርካቶችም ሥራ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን በመረዳት የቦታ ጥያቄያቸው ቢመለስ የተሻለ ሀገርን መጥቀም የሚያስችል ተግባር ማከናወን እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የበሰሉ ምግቦች አቅራቢዋ እንስት ለቤት ኪራይ በዓመት ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ቢያወጡም ሥራቸውን በጥራት እና ለጤና ተስማሚ በሆነ መልኩ በማቅረባቸው ግን ደንበኞች በማግኘታቸው እንዳልከሰሩ ያስረዳሉ። በተደራጀ መልኩ ታፑ የበሰሉ ምግቦች አቅራቢ ድርጅት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ ሲሆን፤ በሥሩም ሦስት ተሽከርካሪዎችን ገዝተው ሥራቸውን እያቀላጠፉ መሆኑን ይናገራሉ።
በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ የበሰሉ የኢትዮጵያን ምግቦች ወደ ውጭ አገራት በመላክ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ውጥን ይዘዋል። ምግቦቹን ወደ ውጭ ለመላክ ሲታሰብ ግን ደረጃ ያልወጣላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተቀባይነታቸው ሊቀንስ ስለሚችል መንግሥት የኢትዮጵያን ምግቦች ደረጃ አውጥቶ ቢሰጥ በርካታ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት ይቻላል።
ለወይዘሮ የምስራች ሥራ ማለት ሐቅን መሰረት አድርጎ በእግዚአበሔር ዕርዳታ ታግዞ ሌሎችንም መርዳትን ያካትታል። በዚህ አካሄድ ከእራሳቸው አልፈው ለበርካቶች ሥራ እንደመፍጠራቸው ነግደው ማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎችም ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ቢሰማሩ የተሻለ እንደሚሆን ይመክራሉ። እንደ እርሳቸው ማንኛውም ሰው በውስጡ ያለውን የሥራ ፍላጎት አውጥቶ መተግበር ከቻለ ለማደግ አስቸጋሪ አይሆንበትም።
ትንሽ ብር ነው ያለኝ መነሻዬ ለመነገድ በቂ አይደለም ብሎ መቀመጥ ሊገኝ የሚችለውን ትርፍ ከማግኘት ወደ ኋላ የሚያስቀር በመሆኑ ለሥራ መነሳሳት እና ከትንሽ ተነስቶ ስለማደግ አመኔታ ሊኖር ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ። እኛም የወ/ሮ ምስራችን ታታሪነት በማድነቅ የዛሬውን ጽሁፋችንን በዚሁ እንቋጫለን። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ጌትነት ተስፋማርያም