ጠዋትና ማታ የሚብሰለሰልበት ጉዳይ ዕንቅልፍ ከነሳው ቆይቷል። ግድ ሆኖበት እንጂ ከቤት ውሎ ባያድር ፈቃዱ ነው። ውጭ ቆይቶ ወደ መኖሪያው ሲዘልቅ ደርሶ የሚያበሽቀውን እውነት ጠንቅቆ ያውቀዋል። በግቢው አንድን ሰው በፍፁም ማየት አይፈልግም። የህይወት አጋጣሚ ዓመታትን በአንድ ቢያኖራቸውም በውስጡ ያደረውን ቂምና ጥላቻ በቀላሉ መርሳት አልሆነለትም።
ጌታነህ ከእንጀራ አባቱ ጋር ዓመታትን የዘለቀው አለመግባባት ሥር ከሰደደ ቆይቷል። በየምክንያቱ ጥላቻውን ለመግለጽ የሚያደርገው ሙከራም የብዙዎችን ዓይን የሚስብ ሆኖ ከርሟል። በመሐላቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሞከሩ አንዳንዶች በእሱ እምቢ ባይነት ልፋታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ከነዚህ መሐል ጥቂቶቹ ደግሞ እልህና ንዴቱን ታዝበው ገለልተኛ ለመሆን ሞክረዋል።
ሰሞኑን ደግሞ ከወትሮው በተለየ ጥላቻው ብሶ ይብሰለሰላል። በወጣና በገባ ቁጥርም ጥርሱን እየነከሰ እጁን ከእጁ ያጋጫል። እንዲህ ባደረገ ጊዜ ዓይኖቹ ወደ እንጀራ አባቱ ዓይኖች ያፈጣሉ። ከሰውዬው ጋር ድንገት ከተያዩ ደግሞ ንዴቱ ግሎ የግንባሩ ሥር ይግተረተራል። ቁጭት ብሽቀትና ጥላቻ በየተራ ይፈትኑታል።
ጌታነህ የሰሞኑ ሁኔታው ከሌላው ጊዜ ባስ ማለቱን ብዙዎች አይተው ታዝበዋል። እንዲህ የመሆኑን ሚስጥር የሚያውቀው ግን እሱ ብቻ ነው። ሌሎች እንደያሚስቡት ይህ ጥላቻና ጥርስ መንከስ የወትሮው አይነት አልሆነም። ደርሶ ቱግ የሚያደርገው ስሜት ዛቻና ማስፈራሪያ ታክሎበታል። ግልምጫና ራስ መነቅነቅ ተጨምሮበታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጤና ያጡ እናቱን ጠበል እንደሚያመላልስ መንደርተኛው ሁሉ ያውቃል። አሁን ደግሞ እናት መክረሚያቸውን እዛው በማድረጋቸው ከእሳቸው ዘንድ እየዋለና እያደረ ብቅ ማለት ጀምሯል። ይህ በሆነ ቁጥር ግን ለእናቱ ጤና ማጣት እንጀራ አባቱን ተጠያቂ ከማድረግ ቦዝኖ አያውቅም። ለዚሁ ሁሉ ችግር የዳረጋት እሱ ብቻ ነው የሚለው እምነቱም ዓመታትን በእርግጠኝነት አሻግሮታል።
እናቱና የእንጀራ አባቱ ሃያ ሦስት ዓመታትን በትዳር ዘልቀዋል። ጥንዶቹ ንብረት አፍርተው ክፉ ደጉን አብረው ቢገፉም የጋራ የሚሉትን የልጅ ፍሬ ለማግኘት አልታደሉም። ጌታነህን ጨምሮ ሌሎች እህትና ወንድሞቹ ከሌላ አባት የሚወለዱ ናቸው። በጥንዶቹ ድካም በቆመው ጎጆም እነሱን ጨምሮ ሌሎች ዘመዶች በሰላም እየኖሩ አሳልፈዋል። በግቢው በተሰሩ አነስተኛ ክፍሎችም ዓመታትን በኪራይ የተጎዳኙ ነዋሪዎች አብረዋቸው ዘልቀዋል።
የሰባ አንድ ዓመቱ ኣዛውንት አቶ ተስፋሁን ከሌሎች የእንጀራ ልጆቻቸው ጋር ያላቸው ቅርበት ሰላማዊ የሚባል ነው። እሳቸው የጌታነህ ጥላቻ ሥር የሰደደ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህ እውነታም ዘወትር በተለየ ጥርጣሬ እንዲያዩት ሲያደርጋቸው ቆይቷል።
አዛውንቱ አብሯቸው በዘለቀው የስኳር ህመም ዓመታትን ሲሰቃዩ ዘልቀዋል። አልጋ እያስያዘ የሚያስነሳቸው በሽታም ከመድሃኒት አልፎ በሐኪም ቤት ደጃፍ ሲያመላልሳቸው ኖሯል። አንድቀን ግን የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ ክፉኛ ሊታመሙ ግድ ሆነ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ያልታሰበ ሁኔታ ፈጥሮ አንደኛውን እግራቸውን ለመቆረጥ ዳረገ።
አቶ ተስፋሁን በህመሙ ሳቢያ የቀኝ እግራቸውን ካጡ ወዲህ ከቤት መዋል ልምዳቸው ሆነ። ለመንቀሳስ የሚጠቀሙት የእንጨት ክራንች ያሰቡትን ያህል አላራምድ ባላቸው ጊዜም በየትኛውም ሰዓት ከቤት ከግቢው አልታጣ አሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ ዘወትር ከጌታነህ ጋር የመገናኘት ዕድሉን አሰፍቶ በየቀኑ ያፋጥጣቸው ያዘ።
ጌታነህ እናቱ ዘንድ ጠበል ውሎ ሲመለስ የእንጀራ አባቱን ከግቢው ውስጥ ያገኛቸዋል። ወዲያውም የተዳፈነ ጥላቻው ተቀስቅሶ በእልህ እየገላመጣቸው ያልፋል። ሰሞኑን ደግሞ ከአንድ ጓደኛው የሰማው ወሬ የነበረውን ቂምና ጥላቻ የሚያብስበት አጋጣሚን ፈጥሯል። ባልንጀራው ስለእንጀራ አባቱ ሹክ ያለው ያልተሰማ ወሬም ዕንቅልፍ ነስቶት ከርሟል።
እስከዛሬ የእንጀራ አባቱን እንደማይወድ ልቦናው ቢያውቅም ጥላቻውን በግልጽ ከማሳየት ውጭ የተለየ ሐሳብ ገብቶት አያውቅም። ሰሞኑን ግን ‹‹በል›› የሚል አንዳች ስሜት እየፈተነው ነው። በተለይ እንጀራ አባቱ ‹‹አድርገውታል›› የተባለውን ክፉ ጉዳይ ደጋግሞ ባሰበው ቁጥር ስሜቱ ግሎ ራሱን መቆጣጠር ያዳግተዋል።
ባልንጀራው ሰሞኑን ባመጣለት አሉባልታ የእንጀራ አባቱ በአርሱ ላይ መተትና ድግምት አድርገውበታል። ጓደኝዪው ሰማሁት እንዳለውም ይህ የተደረገው ሆን ተብሎ ጌታነህን ለመጉዳትና ለማሳደድ ሲባል ነው።
ጌታነህ ወሬውን የሰማውና ያወቀው እናቱን ይዞ ጠበል በሄደበት አጋጣሚ በመሆኑ ለጉዳዩ የተለየ ትርጉም ሰጥቶታል። እንጀራ አባቱ ይህን ማድረጋቸው እሱን ለማጥፋት መሆኑን ከገባው ወዲህም ከቀድሞው የተለየ ጥላቻ ውስጡን ሲሸነቁረው ከርሟል።
ጌታነህ ተማሪ ሳለ ‹‹ደህና ውጤት አመጣለሁ›› የሚል ግምት ነበረው። ያሰበው እንዳልሆነ ባወቀ ጊዜ ግን በተለያዩ ሥራዎች ራሱን ሲያግዝ ቆየ። ቀለም እየቀባና ጂብሰም እየሰራ በሚያገኘው ገቢም ከእኩዮቹ ሳያንስ ዓመታትን አሳለፈ። ከግቢው ጓሮ ከሚገኙ ክፍሎች በአንደኛው እየኖረም ወጣትነቱን አጋመሰ።
አሁን የጌታነህ ጥላቻ ከወትሮው በተለየ በእጥፍ ጨምሯል። በወጣ በገባ ቁጥርም እንጀራ አባቱን ማየት እየፈተነው ከራሱ ስሜት ጋር መታገል ይዟል። አቶ ተስፋሁን የእንጀራ ልጃቸው በእሳቸው ላይ የሚያሳየውን ግልጽ ጥላቻ ለምደውታል። የሰሞኑ ድርጊትና አስተያየቱ ግን ከሌለው ጊዜ ለየት ማለቱ ፈጽሞ ሊገባቸው አልቻለም።
ሁለቱ ድንገት በተገናኙ ጊዜ አዛውንቱ የእንጨት ክራንቻቸውን ተደግፈው ከዓይኑ ለመራቅ ይሞክራሉ። አጋጣሚ ሆኖ ከደረሰባቸው ግን በተለየ ግልምጫና ስድብ እያሽቆጠቆጠና እጁን በእጁ እየመታ በአጠገባቸው ያልፋል። ይህን የሚያዩ ብዙዎችም በነገሩ ጣልቃ ላለመግባት እንዳላየ ሆነው ይታዘባሉ።
ታህሳስ 14 ቀን 2011 ዓም
በዚህ ቀን ጌታነህ እንደተለመደው እናቱ ዘንድ ሄዶ ጠበል ሲያስጠምቃቸው ቆይቷል። ድንገት ግን እናት ልጃቸው ‹‹ከዚህ ነኝ›› ሳይልና ሳይሰናበታቸው ከአጠገባቸው ስለመራቁ አወቁ። ‹‹ይመለሳል›› ብለው ሲጠብቁትም የውሃ ሽታ ሆነባቸው። እንዲህ ማድረጉ ያልተለመደ ነበርና ወይዘሮዋ መጨነቃቸው አልቀረም።
ጌታነህ መኖሪያ ግቢው እንደዘለቀ በረንዳውን አልፎ ወደቤቱ ገባ። አሁንም በሐሳቡ እየተመላለሰ የሚያስጨንቀው የመተት ጉዳይ ሰላም ነስቶታል። በተለይ ብቻውን ከሆነ ጉዳዩን በቀላሉ ለመተውና ለመርሳት ይቸግረዋል።
ምሽቱን በቤቱ ማሳለፍ የመረጠው ወጣት በጊዜ ካገኘውና በቤቱ ካስተናገደው ወንድሙ ጋር እየተጨዋወቱ ራት ሲበሉና ቡና ሲጠጡ አመሹ። ሰዓቱ መግፋት ሲጀምርም ወንድሙ ተሰናብቶት ወደመኖሪያው አመራ። ጌታነህም እስከ ደጅ ሸኝቶት በሩን ዘግቶ ተመለሰ።
ምሽት 5፡30
ጌታነህ ወንድሙን ሸኝቶ ወደቤት ከገባ ጥቂት ሰዓታት ተቆጥረዋል። አሁንም ግን አይምሮው ሰሞኑን ሲያስበው በሰነበተበት ጉዳይ እየተብሰለሰለ ነው። የቀን ውሎው ያሳደረበት ድካም ደግሞ ዓይኖቹን ለዕንቅልፍ አነሳስቶ ያንጎላጀው ጀምሯል። ይህ በሆነ ጥቂት አፍታ ግን የቤቱ በር ደመቅ ብሎ ተንኳኳ። ጌታነህ ወዲያውኑ ፈጠን ብሎ የተዘጋውን በር ከፈተ። ከመዝጊያው ጀርባ የቆመውን ሰው ባየ ጊዜ ተደናገጠ።
ገና በጊዜ ‹‹ደህና እድር.›› ብሎ የሸኘው ወንድሙ ተመልሶ የመጣበት ምክንያት አልገባውም። ወንድምዬው የመመለሱን ምክንያት ማስረዳት ሲጀምር ከወቀሳ ጋር ሆነ። የእንጀራ አባቱን ከቤት ማስወጣቱን ሰምቶ መመለሱንና ይህን ማድረጉም ተገቢ ያለመሆኑን እየመከረ ሊነግረው ሞከረ።
ጌታነህ የወንድሙን ስሞታ በሰማ ጊዜ በዕንቅልፍ መደብዘዝ የጀመረው ንዴቱ ዳግም ተጋጋለ። በእልህ እየጮህና እየተበሳጨም ሰውዬውን እንደማይለቃቸው ደጋግሞ መዛት ጀመረ። ወንድሙ የጌታነህን ዳር የወጣ ንዴት እንዳየ ሊያረጋጋው ሞከረ። ጉዳዩን ቀለል እንዲያደርገው ነግሮም ለመሄድ ተነሳ። ወደ ውጭ ሲወጣ አቶ ተስፋሁን ፍራሸ አንጥፈው በረንዳ ላይ ነበሩ።
ወንድሙ ይህን እንዳየ ፍራሹን አብሮት ከመጣ ጓደኛው ጋር ተጋግዞ ወደቤት መለሰና ለመሄድ ተዘጋጀ። ይህኔ ተስፋሁን እጃቸውን ወደጌታነህ እየጠቆሙ አንድቀን እንደሚገላቸው ስጋታቸውን ተናገሩ። ጌታነህ ወዲያው ሰዎቹን ሸኝቶ የውጩን በር ዘግቶ ተመለሰ። እግሮቹ የቤቱን ደረጃ አልፈው በረንዳውን መርገጥ ሲጀምሩም ሁኔታውን ያዩት አዛውንት ብርክ ያዛቸው።
በጥላቻ መንፈስ ተሞልቶ ሲጮህባቸው ከአንገታቸው ቀና ብለው ሊሞግቱት ሞከሩ። እሱ ግን ትዕግስት ኖሮት ሊያስጨርሳቸው አልፈቀደም። በሁለቱ መሐል ጭቅጭቁ አይሎ አለመግባባቱ ቀጠለ። ይህኔ ጌታነህ በውስጡ ሲብላላ የቆየው ቂምና ጥላቻ ሲያገረሽ ተሰማው። በልቦናው ተዳፍኖ የሰነበተው የመተት ታሪክም ነፍስ ዘርቶ መላ አካሉን በግለት ሲያቀጣጥለው በፍጥነት ወደ እንጀራ አባቱ ተንደርደረ።
ወዲያው አካሄዱን ቀይሮ ወደ ጓዳ ዘለቀና እጀታው ብረት የሆነ መጥረቢያ ይዞ ተመለሰ። አዛውንቱ በእጁ ላይ ያለውን ስል መጥረቢያ ባዩ ጌዜ በድንጋጤ እየተንቀጠቀጡ ራሳቸውን ለመከላከል ሞከሩ። ዓይኖቻቸው ከወዲያ ወዲህ እየቃበዙ የሚያድናቸውን ፈለጉ። ሁሌም ድጋፍ የሚሆናቸው የእንጨት ክራንች ግርግዳውን ተደግፎ ቆሟል። ተስፋ ቆርጠው፡ ዓይናቸው በዕንባ ተሞላ።
ጥርሱን ነክሶ ፊት ለፊት በቆመው የእንጀራ ልጃቸው በስለቱ በኩል አናታቸውን ሲመቱ የእንግላል ወደቁ። ፊታቸው በትኩስ ደም መሸፈን ሲጀምር ጌታነህ አስተካክሎ የያዘውን መጥረቢያ በደረታቸው ላይ ደጋግሞ አሳረፈው።
ስለቱ ከላይ ወደታች እየሰነጠቃቸው ሲያልፍ ለሁለት የተገመሰውን አካል ቁልቁል እያስተዋለ ቀጣዩን ድርጊት ለመፈፀም ወደ ጓዳ ተንደረድሮ ከፌሮ የተሰራ ትልቅ ቢላዋ ይዞ ተመለሰ። ወዲያው በደም ተሞልቶ እኩል የተሰነጠቀውን ደረት በስል ቢላዋው እያሰፋ እጆቹን እስከ ክንዱ አስገብቶ ወደውስጥ መቦርቦር ጀመረ።
እጆቹ አንዳች ነገር ይፈልጉ ይመስል ወደውስጥ ዘልቀው ግራናቀኝ ይሰረስሩ ያዙ። አስሩም ጣቶቹ እያንዳንዳቸው የያዙትን አንቀው ላይና ታች፣ ግራና ቀኝ እያሉ የሆነ ነገርን ከነበረበት ስፍራ አላቀቁ። ወዲያው ዓይኖቹ ሲሻው የቆየው ጉዳይ እውን መሆኑን አረጋገጡለት። ልብ። አዎ! አሁን የእንጀራ አባቱ ልብ በትኩስ ደም ተነክሮ ከመሐል እጁ ተቀምጧል።
ጌታነህ የሰውዬውን በድን አካል በፈገግታ እየተመለከተ ነፍስ አልባውን ልብ ሲያስተውል የእርሱ ልብ በእርካታ ሲረሰርሰ ተሰማው። በስለቱ እንዳሻው እየሸረከተ መቆራረጥ ሲጀምር ደግሞ ለየት የሚል አንዳች ስሜት በውስጡ ሲመላለስ ታወቀው።
ከሰውዬው ደረት ውስጥ ቦርቡሮ ያወጣውን ልብ በአንድ እጁ እንደያዘ ከአጠገቡ ባገኘው ሰማያዊ ማስታጠቢያ ላይ አስቀመጠውና ቢላዋውንና ደም የነኩ እጆቹን አለቀለቀ። ወዲያው የሆነ ነገር ትውስ ሲለው ዓይኖቹን ባሻገር ወደሚታየው ጃኬት ላይ አነጣጠረ። ጊዜ አልፈጀም። የኪሱን ገበር ገልብጦ አንድ ሁለት ሲል ዘጠኝ ሺህ ብር ቆጠረ።
ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ልብሶቹን በሻንጣ ይዞ በሩን ከፍቶ ወጣ። መንገድ ከመጀመሩ በፊት መላ አካሉን በጥንቃቄ ቃኘው። በልብሱ ላይ ምንም የደም ጠብታ አይታይም። በሩን ከውጭ ቆልፎ ወደ አውቶቡስ ተራ ሲያመራ ደጅ ከተቀበለው ቅዝቃዜ በቀር የረበሸው ስሜት አልበረም።
ወደ ባህርዳር ትኬት ቆርጦ ጉዞ ሲጀምር ፊቱ በፈገግታ እንደበራ ነበር። አምስት ቀናትን እዛው አሳልፎ ጎንደር፣ ሑመራና ትግራይ ሲዘዋወር ቆየ። ውሎ አድሮ ኪሱ ባዶ ሲሆን በጎዳና እያሳለፈ ቀናትን ቆጠረ።
አንዳንዴ ዕንቅልፍ ሸለብ ሲያደርገው እንጀራ አባቱ በህልሙ እየመጡ ያለመሞታቸውን ይነግሩታል። በዚህ ደንግጦ ሲባነንም ነገሮች ሁሉ ግራ ያጋቡታል። ይህን የሸሸ ቢመስለው አገር እየቀረ እስከ ኤርትራ ድንበር ተጓዘ። የአዛውንቱ ሙት መንፈስ ግን በየሄደበት እየተከተለ ምቾትና ሰላም አሳጣው።
የፖሊስ ምርመራ
ኮልፌ ቀራንዮ ልዩ ቦታው ካራ ቆሬ ከተባለ ስፍራ የሰማውን ጥቆማ ተከትሎ የደረሰው ፖሊስ የአዛውንቱን ቤት በተመሳሳይ ቁልፍ ከፍቶ ሲገባ ያገኘው እውነት ከተገመተው በላይ ነበር። ይህን የጭካኔ ድርጊት የፈፀመውን ሰው ለማውቅ ባደረገው ሙከራ ከብዙዎች የደረሰው መረጃ ተመሳሳይ በመሆኑ ጌታነህን ለመያዝ ፍለጋውን ቀጠለ። በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 788/11 የተከፈተው መዝገብ በመርማሪ ዋና ሳጂን አማረ ቢራራ እየታገዘም ጠቃሚ የሚባሉ መረጃዎች ሰፈሩበት።
ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ የረገጣቸው ከተሞች አድራሻ እንደታወቀ ፍለጋው ቀጠለ። ማንነቱን የሚጠቁሙ መለያዎች በፖሊስ እጅ እንደገባ ግን ሌላ ጥቆማ ደረሰ። ጌታነህ በመታወቂያ ምክንያት ታስሮ ከቆየበት መቀሌ ከተማ ተፈቶ አዲስ አበባ እንደገባ አራት ኪሎ አካባቢ በእግሩ ሲዘዋወር በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ፖሊስ ማንነቱን እንዳረጋገጠ ምርመራውን ቀጠለ። ጌታነህም የዕምነት ክህደት ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነ። ድርጊቱንም በትክክል ስለመፈፀሙ ተናገረ። በንግግሩ መሐል ግን ደጋግሞ የሚናገረው ቃላት ብዙዎቹን አስገረመ። እሱ የእንጀራ አባቱን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ መቼውንም ቢሆን ፈጽሞ እንደማይፀፅተው ደግሞ ደጋግሞ መናገሩ።
ውሳኔ
ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓም የተሰየመው የልደታ ምድብ 20ኛ የወንጀል ችሎት የእንጀራ አባቱን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ የፍርድ ወሳኔ ለማሳለፍ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ የቀረቡ ሰነዶችን መርምሮ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጡ ግለሰቡ የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርብም ጠይቋል። ተከሳሹ የተባለውን ወንጀል በትክክል ስለመፈፀሙ በማረጋገጡና ለውሳኔ የሚያደርሰ በቂ ማስረጃ በመገኘቱ በዕለቱ በሰጠው ውሳኔ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የ21 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
መልካምስራ አፈወርቅ