እ.ኤ.አ. የካቲት 2003 ነበር የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ (ኢኤምኤም) የተሰኙ ሁለት አማጺ ቡድኖች በጋራ በመሆን የሱዳን መንግስትን መፋለም የጀመሩት። እንዲፋለሙ ምክንያት የሆናቸው ደግሞ የኦማር ሀሰን አልበሽር መንግስት “አረብ ያልሆነውን የዳርፉር ነዋሪ ህዝብ ጨቁኗል” የሚል ነበር። የሱዳን መንግስትም በዳርፉር የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂዎች ለማጥፋት በሚል ከባድ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ጀመረ።“ላንድ ክሩዘር ዋር” የሚል ቅጽል ስም በተሰጠው በዳርፉር ጦርነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጦርነቱ እና ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ርሃብና በሽታ ምክንያት ሞተዋል።
ጦርነቱ ሚሊዮኖችን ለመፈናቀል እና ለአስገዳጅ ፍልሰት በመዳረግ በአካባቢው በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንዲታጎሩ ምክንያት ሆኗል። ሚሊዮኖች ድንበር በማቋረጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ በማድረግ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጆች ላይ በተፈፀመ ወንጀል በዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲከሰሱም ምክንያት የሆነው በዚሁ ግዛት ውስጥ የተከሰተው እልቂት ነበር፡፡
የሱዳን መንግስት እና አማጺያን በዳርፉር ሰላም ለማስፈን እና አካባቢው ከፊል ራስ ገዝ እንዲሆን እ.አ.አ በ2010 ከጊዜያዊ ስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም የስምምነቱ የፊርማ ቀለም ሳይደርቅ ዳግም ወደ ጦርነት በመግባት የዳርፉር የዋሻው ጫፍ ብርሃን እንዲጨልም አደረጉት።ወደ ጦርነቱ ዳግም እንዲገቡ ያደረጋቸው ደግሞ የሱዳን መንግስት ስምምነቱን በመጣስ በአንድ መንደር ላይ የአየር ድብደባዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶችን አድርሷል በሚል አማጺያኑም ወደ ፍልሚያ በመመለሳቸው ነው። በዚህም ወደ ዘላቂ ሰላም ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የስምምነት ሂደት ተቀጨ፡፡
ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ሱዳንን ያስተዳደሩት ኦማር ሀሰን አልበሽርን ያስወገደው የሱዳን አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ ግን በምዕራብ ሱዳኗ ዳርፉር የሰላም ንፋስ መንፈስ ጀምሯል።ታዋቂው ዘ ታይምስ መጽሄት ሰሞኑን ስለ ዳርፉር ባተተበት የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ጉዳዮች አምዱ እንዳስነበበው ባለፈው ነሃሴ ወር በታጠቁ ኃይሎችና በጄኔራሎች መካከል የተደረሰው የስልጣን ክፍፍል ስምምነት ለዳርፉር ሰላም መሰረት መጣሉን አትቷል።
ስምምነቱን ተከትሎ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕገ-መንግስትም በዳርፉርና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች መንግስትን ሲፋለሙ ከነበሩ አማጺያን ጋር ወደ ሰላም የሚያደርሱ ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነቶች መጀመር እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም የሽግግር መንግስትና አማጺያኑ መነጋገር ጀምረዋል።የምጣኔ ሀብት ሊህቁና የአሁኑ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ሰላም ኮሚሽን በማቋቋም በዳርፉር ከሚንቀሳቀሱ አማጺያን ጋር መነጋገር ጀምረዋል። የሽግግር መንግስቱ ከኃይል ይልቅ ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ ፍላጎት ማሳየቱ ለዳርፉር አዲስ የሰላም ብስራት ሆኗል፡፡
አዲሱ መንግሥት በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ አማጺያን ጋር የተኩስ አቁም ያወጀ ሲሆን፤ አማጺያን ቡድኖች መሪዎችም ከውጭ ሀገር እንዲመለሱ ጥሪ ተላልፎላቸዋል። መንግስት ሰብዓዊ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች በአካባቢው ያለውን ሁኔታ የሚመለከቱበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት በዳርፉር የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል መሪ ኤርሚያስ ማባሎ በመንግስት እና በአማጺያን መካከል በመጪው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ የሰላም ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለዘ ኢኮኖሚስት ይፋ አድርገዋል። በአማጺያንና በመንግስት መካከል የሚደረሰው ስምምነት ስኬታማ እንዲሆን ግን የአብደል ዋዲ አልኑሪ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። አብደል ዋዲ አልኑሪ ከአስር ዓመት በላይ በፈረንሳይ ፓሪስ ሆነው አማጺያኑን ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ በሱዳን ነጻ አውጪ ግንባር አባል የሆኑትንና በዳርፉር ጄቤር ማረራ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን ሁለት ሺህ የሚሆኑትን ታጠቂዎችን ይመራሉ። ለዚህም ነው የአብዱል ዋዲ አልኑሪ ድጋፍ ወሳኝ የሆነው፡፡
እንደ ዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ በዳርፉር ያለውን ሁኔታ በመቀየር ወደ ሰላም ቀጣናነት ማምጣት ቀላል አይሆንም። በተለይም ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በነበረው ጦርነት የተጎዱ ዜጎች ብስጭትና ምሬት ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል። በቅርቡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዳርፉር ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን መጠለያዎች ሲጎበኙ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ተፈናቃዮች ምሬታቸውን ከመግለጽ አልፈው የተቀሙት መሬታቸው እንዲመለስላቸውና ለደረሰባቸው በደልም ካሳ ጠይቀዋል። ዜጎቹ ለደረሰባቸው በደል ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውን የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በህግ ፊት ቀርበው ሲጠየቁ ማየት እንደሚሹም ተናግረዋል። ለዚህም የቀድሞ ፕሬዚደንቱ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድቤት እንዲቀርቡ እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል፡፡
ተጎጂዎች ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሰጡት ምላሽ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ በጄኔራሎችና በሲቪሎች መካከል ባለው የኃይል ሚዛን ላይ የተመሠረተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በአብዛኛው የሲቪል አስተዳደርን የሚመሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሌፍተነንት-ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው 11 አባላት ያሉት ሉዓላዊ ምክር ቤት ቁጥጥር ይደረግበታል። ሌፍተነንት ጄኔራሉ ደግሞ የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት ለዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡
በዳርፉር የሚንቀሳቀስ የአማጺ ቡድን መሪ የሆኑት እስኒፍ ሴይድ ሻሪፍ እንደሚሉት፤ በመንግስትና በአማጺያን መካከል የሚደረገው የሰላም ስምምነት ብቻውን በዳርፉር ዘላቂ ሰላም አያረጋግጥም። የሱዳን መንግስት ከአማጺያን ጋር ከሚያደርገው ሰላም ስምምነት ባሻገር ለሀገሪቱ አለመረጋጋት ተጽዕኖ እያደረጉ ያሉ ክፍተቶችን መሙላት አለበት። ከሀገሪቱ ሀብት አብዛኛው የሚፈሰው በካርቱም አካባቢ ነው። በቀድሞ ፕሬዚደንት በኦመር ሀሰን አልበሽር ዘመን ከመንግስት ወጪ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው በጀት ለጸጥታ ስራ ሲውል ነበር። ከካርቱም ራቅ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ትምህርት ቤትን የመሳሰሉ መሰረታዊ ልማቶችን ለማስፋፋት የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ እጅግ አነስተኛ ነው።
የዳርፉር ነዋሪዎች ነጻ ትምህርትንና የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለመንግስት እያቀረቡ ነው። የሱዳን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት። ከዚህ ቀደም በሱዳን የተደረጉ ለውጦች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሳያመጣ አልፏል። በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጥ አልፏል። በመሆኑም ለውጦቹ ቀጣይ ሊሆኑ አልቻሉም። አሁንም የሱዳን አብዮት ተመሳሳይ መጨናገፍ እንዳያጋጥመው ጥንቃቄ ያሻል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2012
መላኩ ኤሮሴ