ሁሉም ሰራተኛ በጥልቅ የደስታ ስሜት ውስጥ ገብቷል። የተደበላለቀ ስሜት ነበር የተስተዋለው፤ ጩኸት፣ ለቅሶ፣ ሳቅ በአንድ ላይ የታዩበት መድረክ። ምን አይነት መድረክ ቢሆን ነው? እንዲህ ያለ ድብልቅልቅ ስሜት የሚታይበት። ለቅሶ እና ሳቅስ እንዴት በአንድ መድረክ ላይ ሊታዩ ይችላሉ?
በአሜሪካ ሜሪላንድ የሚገኝ የአንድ ሪል ስቴት ኩባንያ በቅርቡ አመታዊ በአሉን ሲያከብር በሰራተኞች ዘንድ የታየው ይህ ስሜት ሰራተኞቹ ቀያይ ፖስታዎችን ታድለው ሲከፍቷቸው የመጣ ነው። ፖስታዎቹ ከተከፈቱ በኋላ ሁሉም ፈነደቁ፤ አነቡ፤ የሚይዙትን የሚጨብጡትንም አጡ። የዚህ ሁሉ ስሜት መነሻ ደግሞ ኩባንያው ለሰራተኞቹ የሰጠው ተአምር የተሰኘ ጉርሻ መሆኑን ሲ ኤን ኤን ሰሞኑን ይዞት የወጣ ዘገባ አመልክቷል።
‹‹ፖስታውን ስከፍተው የተመለከትኩትን ማመን አልቻልኩም›› ሲል ለሲ ኤን ኤን አስተያየቱን የገለጸው የዚህ ተአምረኛ ጉርሻ ተቋዳሽ ለመሆን የታደለው የኩባንያው የፕሮጀክት ረዳት ስራ አስኪያጅ ስቴፋኔይ ሪድግዌይ ያየውን ማመን አቅቶታል። የሆነውን የሚገልጽበት ቃልም አጥቷል። ጉርሻው በጣም የሚገርምና ለማመን የሚከብድ ሆኖበታል። ‹‹እስከ አሁንም ድረስ ሰውነቴ እየተብረከረከ ነው፤ ክስተቱ ህይወትን በወሳኝ መልኩ መቀየር የሚያስችል ነው›› ሲል ገልጿል።
እነዚህ 198 የሴንት ጆን ሪል ስቴት ኩባንያ ሰራተኞች ባልጠበቁት ወቅትና ሁኔታ በአማካይ 50 ሺህ ዶላር ጉርሻ ኩባንያቸው ስለሰጣቸው ይይዙት ይጨብጡት አጥተዋል። ሁሉም የተሰጣቸውን የጉርሻ መጠን ማመን ከብዷቸዋል። ኩባንያው ለሰራተኞች በአጠቃላይ ለጉርሻ ያወጣው 10 ሚሊየን ዶላር መሆኑን መረጃው ያመለክታል። የሆነው ነገር ጉርሻ ወይስ ልዩ ሎተሪ ያሰኛል?
ኩባንያው ምን ቢያገኝ ነው ይህን ያህል ገንዘብ ለጉርሻ ያወጣው? የኩባንያው ፕሬዚዳንት ላውሬንስ ማይካራንትዝ ሪል ስቴቱ 20 ሚሊየን ስኩዌር ፊት መሬት ለማልማት ጥሎት ከነበረው ግብ ዋናውን ማሳካቱን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙም በ14 አመታት ውስጥ እቅዱን በእጥፍ ማሳካት የቻለበት መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ግባችንን እንድናሳካ የረዱንን ሰራተኞቻችንን በሙሉ ማመስገን ፈለግን፤ በዚህም አንድ ታላቅ ተግባር ለማከናወን ወሰንን ››ሲሉ ለሽልማቱ እንዴት እንደተነሳሱ ያስረዳሉ።
እያንዳንዱ ሰራተኞች በኩባንያው በቆዩባቸው አመታት ልክ ጉርሻው የተሰጣቸው ሲን በትንሹ የ100 ዶላር ጉርሻ ተከፋይ ለመሆን በቅተዋል። ይህም ለአዲስ የተቀጠረና ገና ስራውንም ላልጀመረ ሰራተኛ የተሰጠ ጉርሻ መሆኑ ተገልጿል። ከፍተኛው ጉርሻ ደግሞ 270 ሺህ ዶላር መሆኑ ታውቋል። 270 ሺህ ዶላር እንዴት ጉርሻ ይባላል? እንል ይሆናል። እሱ እንደ ሀገሩ የሚለያይ ቢሆንም፣ በተጠቀሰው ሀገርም ቢሆን ጉርሻው የሰዎችን ስሜት የቀያየረ፤ አጉራሹንም ጭምር ያስደመመ ሆኗል።
ስምንት ቅርንጫፎች ያሉት የዚህ ኩባንያ ፕሬዚዳንትም በሰራተኞቹ ዘንድ የታዩት ድብልቅልቅ ያሉ ስሜቶች በእርሳቸው ላይም ልዩ ስሜት እንዳሳ ደረባቸው ተናግረዋል። በህይወት ዘመናቸው አይተውም ሰምተውም የማያውቅት የሰዎችን ደስታ እንደተመለከቱም ገልጸዋል።
‹‹ሰራተኞቹ በሰልፍ ሆነው ተጠመጠሙብን፤ ሳሙን፤ ጨበጡን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በጉርሻው ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ታሪካቸውን ጭምር እየጠቀሱ እንደገለጹላቸው አስታውቀዋል። ‹‹ሰራተኞቹ አሁን ከእዳ ነፃ ይሆናሉ። በጉርሻው እዳቸውን፣ የትምህርት ቤት ክፍያቸውን እና ብድራቸውን እንደሚከፍሉ ገለጹልን።›› ሲሉም ተደምጠዋል።
የ37 ሰባት አመቷ ሪድግዌይ በኩባንያው ለ14 አመታት አገልግላለች፤ ከኩባንያው ያገኘችውን ጉርሻ ለልጆቿ የኮሌጅ ወጪ ልታውለው እንዳሰበች ገልፃለች። ‹‹በሆነ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት፣መኖሪያ ቤቴን ደረጃ ለመቀየር ሀሳቡ አለኝ፤ አብዛኛውን ገንዘብ ግን ለልጆች የወደፊት ህይወት ማሻሻያ አውለዋለሁ›› ስትልም ተናግራለች።
የኩባንያው ፕሬዚዳንት ማይክራንትዝ በሰራተኞቻቸው በእጅጉ መኩራታቸውን ገልፀው፤ ‹‹ሰራተኞቻችን የኩባንያችን መሰረቶችና የስኬቶቻችን ምስጢሮች ናቸው›› እናም ምን ብናደርግላቸው ነው ልናመሰግናቸው የምንችልው በማለት ስናወጣ ስናወርድ ቆይተናል ያሉ ሲሆን ፤ባደረግነው ጉርሻም ስኬታማ ለመሆን በቅተናል ሲሉ አስታውቀዋል። ብዙ ባይባሉም ጥቂት ኩባንያዎች በሚያገኙት ትርፍ ልክ ለሰራተኞቻቸው ጉርሻ ወይም ቦነስ በመስጠት ያበረታታሉ። የሀገራችን ኩባንያዎች ከዚህ ምን ይማሩ ይሆን ?
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2012
ዘካርያስ