
በአልጀሪያ በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልመጂድ ቲቡን ማሸናፋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከሰሞኑ ገልጸዋል፡፡ ቲቡን ከሌሎች አራት ዕጩዎች ጋር ተወዳድረው 58 በመቶ ድምፅ በማግኘት ምርጫውን ማሸነፋቸውንም የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዋና ኃላፊ መሀመድ ሸሪፊ ይፋ አድርገዋል፡፡ ለመምረጥ ከተመዘገበው ህዝብ 40 በመቶ ያህሉ ድምፅ መስጠቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረገው መረጃ ያመለከተ ሲሆን የተገኘው ድምፅ በቂ በመሆኑ ውጤቱን በፀጋ መቀበል እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን የወረዱትና ለረጅም ዓመታት ሀገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩት የአብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ አጋር እንደነበሩ የሚነገርላቸው የ74 ዓመቱ ቲቡን፣ ሰፊ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ለአራት አስርት ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሠሩት ቲቡን፤ እ.ኤ.አ ከግንቦት 2017 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሹመው ከአራት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ እንዳገለገሉም ተጠቅሷል፡፡
በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትር የሥራ ዘመናቸው ከፈረንሳይ አቻቸው ኤድዋርድ ፊሊፒ ጋር በፓርስ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ራሳቸውን የቡተፍሊካ ተተኪ አድርገው አቅርበዋል በሚል ክፉኛ ተተችተዋል። የሀገሪቱ መንግሥት ሁኔታ አላምር ያላቸው ቲቡን ታዲያ ከኃላፊነቴ ሳያሰናብቱኝ እኔው ልቅደማቸው በሚል በገዛ ፍቃዳቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸውን መልቀቃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ በአንድ በኩል የስልጣን ዘመናቸውን ወደ 20 ዓመት ለማድረስ ሲያቅዱ የነበሩትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካን ውጥን የሚያመክንና የቡቶፍሊካ ቅሬቶችን ሙሉ ለሙሉ ጠራርጎ ለማስወገድ እንደ ትልቅ መሳሪያ ይጠቅማል የሚል እምነት ተጥሎበት እንደነበረ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው በተቃውሞ ሰልፍ ማዕበል ውስጥ መካሄዱ የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ረገድ እንከን ሊገጥመው እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡
ምርጫው ሀገሪቱ ዘጠኝ ወራትን ባስቆጠረ ህዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ በቆየችበት ወቅት የተካሄደ ቢሆንም፤ በምርጫው ዕለትም ምርጫው ወቅቱ እንዳልሆነና ዕጩዎችም የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች በሚል በተቃዋሚዎች ቢብጠለጠሉም፤ የቡቶፍሊካን መንግሥት ለመጣል ለወራት ተቃውሞውን ሲያሰማ ለቆየው ህዝብ ግን ካሰበው ይልቅ ያላሰበው ዱብእዳ እንደገጠመውና በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በኋላም የታዩት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ይህንኑ ሲያመለክቱ እንደሰነበቱ አልጀዚራን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡
እንደ መገናኛ ብዙሃኑ መረጃ ከሆነ ህዝቡ ምርጫው ወቅቱን የጠበቀ አይደለም በማለትና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን በመቃወም አደባባይ የወጣ ሲሆን የሀገሪቱ መንግሥት በምርጫው ዋዜማ ምንም ዐኣይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ፤ ቢካሄድም ዕርምጃ እንደሚወሰድ አሳስቦ ለዚህም የፀጥታ ኃይሎችን እንደሚያሰማራ ቢገልጽም ተቃዋሚዎችን ግን አደባባይ ከመውጣት ማገድ አልተቻለም፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴው የሀገሪቱ ዋና ከተማ በሆነቸው አልጀርስ ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሁለት ሰዓት አስቀድሞ እንዲዘጋ እስከማድረግ መድረሱንም ዘገባዎቹ አመልክተዋል፡፡ በአንዳንድ ከተሞችም በምርጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙንና የምርጫ አስፈፃሚዎች ላይም ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
በድምፅ መስጫው ዕለት በውጥረት ውስጥ በቆየችው የሃገሪቱ ርዕሰ ከተማ አልጀርስ ተቃዋሚዎች “ዛሬ ምንም ድምፅ የለም፤ ከቀማኛ ጋር ድምፅ የለም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል። ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት ውስጥ አንዱ የ54 ዓመቱ አርክቴክት ማጂድ በልግሆውት ‹‹ድምፅ አሰጣጡ ቀልድ ነው›› ሲሉ ገጸዋል፡፡ ‹‹ምርጫውንም አዛውንቱ ቡቶፍሊካ ራሳቸውን በድጋሚ በአዲስ መልክ ያቀረቡበት ነው›› ሲሉም አጣጥለውታል። ‹‹በአልጄሪያ ነፃ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ከዴሞክራሲ ሂደት በኋላ ነው፤ እኛ በሂደቱ ጅማሬ ላይ ነን›› ሲሉም ገልጸው፤ ይህ ብቻ አልጀሪያውያንን ካሰቡበት ደረጃ ሊያደርሳቸው እንደሚችልም ተቃዋሚው ጠቁመዋል።
ከምርጫው በፊት የተለያዩ መላምቶች ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም ምርጫው በተካሄደበት ዕለት ምሽት ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ቴቡን ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቴቡን ባደረጉት ንግግር አዲሲቷን አልጄሪያ ለመገንባት ተቃዋሚዎች ለውይይት እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን የቴቡን ማሸነፍ ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ እሳቸው እና በምርጫው የተወዳደሩ አራት ዕጩዎች የቀድሞው መንግሥት ጋሻ ጃግሬዎች ናቸው በሚል ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል፡፡
ቡቶፍሊካን ከፕሬዚዳንትነት ለማንሳት ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አዲሱ የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት ቴቡን ቀስ በቀስ ራሳቸውን ከተቃዋሚዎች ጎራ ነጥለዋል ተብለው የሚታሙ ሲሆን ለዚህም ጠንካራው የሀገሪቱ ጦር ጄነራል የሆኑት ጌይድ ሳላህ የቅርብ ሰው መሆናቸው ለአሸናፊነታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ሳያበረክት እንዳልቀረ ተጠቁሟል፡፡ ይህ አቋማቸውም በተቃዋሚዎች ዘንድ እንደ ቡቶፍሊካ ስርዓት አራማጅ እንዲቆጠሩ አድርጓቸዋል፡፡ የሀገሪቱን ጨረታዎች ጠቅልሎ በመውሰድ የሚታወቁ ባለሀብቶችም ቴቡን በምርጫው እንዲያሸንፉ እጃቸው እንዳለበት ይጠረጠራል፡፡
ምርጫውን አወዛጋቢ ሲል የገለጸው ዘ ጋርዲያን በበኩሉ የምርጫው ውጤት ይፋ እንደተደረገ በሺዎች የሚቆጠሩ አልጄሪያውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬዚዳንት ሆነው መምጣታቸውን በመቃወም ብካቶች አዳባባይ መውጣታቸውን ዘግቧል፡፡ በዋና ከተማዋ አልጀርስ አደባባይ የወጡት እነዚህ ተቃዋሚዎች ቴቡን ከስልጣናቸው በህዝባዊ አመፅ የተነሱት ‹‹የቡቶፍሊካ ታማኝ ሰው›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ ‹‹ቴቡን እንደውም ከቡቶፍሊካ ይብሳሉ፤የሀገሪቱን ሀብት በመመዝበር ከሚታወቁት ውስጥም አንዱ ናቸው›› ሲል ከተቃዋሚዎቹ ውስጥ አንዱ የሆነው የሠላሳ አንድ ዓመቱ አልጄሪያዊ የመንግሥት ሠራተኛ ገልጿል። ‹‹እኛ ድምፅ አልሰጠናቸውም፤ወደ ቀድሞው ስርዓት መመለስም አንፈልግም›› ሲልም የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል፡፡
ሪያድ ሜክርሲ የተባለው የ24 ዓመት ወጣት በበኩሉ ቡቶፍሊካን ለመጣል በተደረገው ተቃውሞ መሳተፉን ጠቅሶ፣ ማንም ያሸንፍ ማን ተቃውሞው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡ ‹‹ቡተፍሊካን አስወግድናል፤ በቀጣይ ደግሞ የቡቶፍሊካ ስርዓት ታማኞችን ለማስወገድ እንሠራለን፤ እጃችንን በፍፁም አጣጥፈን አንቀመጥም›› ሲልም ገልጿል፡፡
ዜይኔ ላቢዲይኔ ጌህቦውሊ የተባሉ የፖለቲካ ተንታኝ ደግሞ ‹‹ቴቡን በማይካድ መልኩ የአልጄሪያ ፖለቲካ ሥርዓት ውጤት ናቸው›› ሲሉ ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ ተንታኙ አዲሱ ፕሬዚዳንት የፖለቲካ እስረኞችን ከመልቀቅ እንስቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ዋስትና እንዲያገኝ ማድረግንና የፕሬስ ነፃነትን ማስከበርን ጨምሮ የአብዛኞቹን ተቃዋሚዎች ፍላጎት እንደሚያሟሉ አስታውቀዋል፡፡
ተንታኞች በበኩላቸው ‹‹የቀድሞው ባለስልጣን ህዝብ በከፈለው ዋጋ ራሱን ከፍታ ማማ ላይ አስቀመጠ›› ሲሉ የገለቱ ሲሆን ሁሉም ዕጩዎች የቀድሞው ስርዓት ባለስልጣናት እንደነበሩ በመጥቀስም ይህ ብቻውን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደማያስገኝላቸው ተናግረዋል፡፡ ያለፈው መንግሥት ቅሪቶች በምርጫው እስከተሳተፉ ድረስ ምርጫው ነፃና ተአሚኒ ሊባል እንደማይችልም አስታውቀዋል፡፡
በውዝግብ በተሞላው የአልጄሪያ ምርጫ አብዱልመጂድ ቴቡን አሸናፊ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ግን አሁንም በምርጫው አሸናፊ ሆኖ የመጣው የቀድሞው የአብዱላዚዝ ቡቶፍሊካ ስርዓት መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ተንታኞችም የህዝቡ ፍላጎት በምርጫ እንዳልተመለሰና አሁንም ተቃውሞው ሊቀጥል እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2012
ኃይለማሪያም ወንድሙ