የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ዘጠኝ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ፎረም ፎር ፌዴሬሽን ለበርካታ ዓመታት በመመካከር እና የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር ሀገራችንን ከገባችበት ቅርቃር ያወጣል ያሉትን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከነዚህም ጥረቶች አንዱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እና ኢትዮጵያን ይወክላሉ ተብሎ የታመነባቸውን 50 የሴናሪዎ / የዕድል ፈንታ / ቡድን አባላት ለስድስት ወራት ለሶስት የተለያዩ ጊዜያት ተገናኝተው በኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ላይ በዝግ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመክሩ አድርገዋል።
በውይይቶቹ መጨረሻ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊገጥሟት የሚችሉትን አራት ሴናሪዮዎች ለይተው አመላክተዋል። እነዚህ አራት ሴናሪዮዎች የተዘጋጁት አገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በመተንተን፣ የባለሙያ ምክር በማድመጥና አስፈላጊ ነጥቦችን ለውይይት ማዳበሪያነት በመውሰድ ነው። የሴናሪዎ ቡድን አባላት እነዚህን እድል ፈንታዎችን / ሴናሪዎችን / መለየት የቻሉት በብዙ ምክክር ፣ ሙግት እና ማንሰላሰል መሆኑን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ወደፊት የምትደርስበትን ሁኔታ የሚወስኑ የተለያዩ መንገዶች አሉ። የሴናርዮ ቡድኑ ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ መጪውን ዘመን በሚገባ ያመላክታሉ ብሎ ያመነባቸውን አራት ሴናሪዮዎች ቀርጾአል። ስለወደፊት በእርግጠኝነት መተንበይ ባይቻልም ስለተወሰኑ ጉዳዮች ግን አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ፣ ከተሞች እንደሚስፋፉ ፣ የወጣቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድና ይህም ብዙ የሥራ ዕድል ፍላጎት ጥያቄን እንደሚያስነሳ፣ እንዲሁም የፌዴራሊዝም ሥርዓት የተወሰኑ ይዘቶች ወደፊት እንደሚቀጥሉ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በመነሳት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።
በሌላ በኩል አሁን እርግጠኛ መሆን የማይቻልባቸው ጉዳዮች አሉ ። የዴሞክራሲ ባህርይ ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ፣ የኢኮኖሚ ዕድገታችን እና ሁሉን አቃፊነቱ ፣ የግጭትና ብጥብጥ አዝማሚያ ፣ ለአካባቢ መጎሳቆል የምንሰጠው ምላሽ ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻላችን ፣ ዓለም አቀፋዊና ከአገር ውጭ የሚፈጠሩ ክስተቶች በአገር ላይ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ፣ እንደ አገር የመቀጠላችን ጉዳይ እና መሰል ጉዳዮች ናቸው።
የቀረቡት አራት የወደፊት ሴናሪዮዎች እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን ከምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች እንደምንሰጣቸው ምላሾች የተለያዩ አራት መዳረሻዎችን ያመላክቱናል ። እነዚህ መዳረሻዎች በ2032 ዓ ም ሊከሰት የሚችሉ ሴናሪዮኖች ናቸው። እነሱም ፦ ሰባራ ወንበር፣ አፄ በጉልበቱ ፣ የፉክክር ቤት እና ንጋት ናቸው ።
1. ሰባራ ወንበር
የመጀመሪያው ሴናሪዮ ሠባራ ወንበር ሲሆን ለችግሮቻችን የምንሰጠው ምላሽ ጥንቃቄ የተሞላበት እና አሁን ባሉብን የአቅም ውስንነቶች ልክ የተገደበ መሆኑን ያሳያል። የሰባራ ወንበር ሴናርዮ ጠንካራ በሚመስል ፣ ነገር ግና ገና ሲነኩት እንደሚሽመደመድ ፣ ቀላል ክብደትን እንኳን የማይሸከም ወንበር የተመሰለ ነው ። የአቅም ዕጦቱ በማሕበረሰቡ ውስጥ በየደረጃው ለሚነሱ የልማት ፍላጎቶች ተግባራዊ ድጋፍ ለመስጠት እንዳይቻል ያደርጋል ። በመጀመሪያ ሰሞን ብሩህ ተስፋዎች ይታያሉ ። ሆኖም በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ እያደገ ለሚሄደው ሕዝብ ይህን ተከትሎ የሕዝብ ፍላጎት ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት አለመቻል በሥርዓቱ ላይ ጫና ይፈጥራል ። የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ግልጽ ቢሆኑም ፣ ውጤታማና ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ለመስጠት አለመቻላችን ውሎ አድሮ ባለንበት ቦታ ተቸንክረን እንድንቀር ምክንያት ይሆናል።
2. አፄ በጉልበቱ
አጼ በጉልበቱ የሚባለው ሁለተኛው ሴናሪዮ ግዙፍ የሆኑት የአገራችን ችግሮች ቆራጥ አመራር ያስፈልጋቸዋል ከሚል እሳቤ በመነሳት ለችግሮቻችን ፈላጭ ቆራጭ የሆነ እና በጥብቅ ቁጥጥር የተሞላ ምላሽ የሚሰጥ ነው ። በዚህ የማንአለብኝነት ሴናሪዮ የችግሮቻችን ምላሽ ብለን ያመንነው ፈላጭ ቆራጭ የሆነ እና ጥብቅ ቁጥጥርን ያማከለ ሥርዓትን ነው ። ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የኢኮኖሚውን አካሄድ ፣ የአካባቢ መጎሳቆልንና የሕዝብ እድገት ጫናዎችን ለመመከት ቁጥጥር ተኮር ሥርዓትን መከተል ወሳኝ መሆኑን ያምናል ። በጊዜ ሂደት የሚታየው እድገት ሁሉን አቀፍና አሳታፊ እንዳልሆነ በመረዳት፣ በመሰላቸትና ተስፋ በመቁረጥ አመፅ ይቀሰቅሳል።
3 የፉክክር ቤት
ሶስተኛው አማራጭ ሴናሪዮ የፉክክር ቤት የሚባለው ነው ። የተለያዩ ቡድኖች በነጻነት እና ባልተማከለ መልኩ የመለሷቸውን ምላሾች በተናጠል በመሰንዘራቸው ሳቢያ የሚፈጠረውን የተሸራረፈና የቡድን ፉክክር የሞላበትን ምላሽ መልክ የሚያሳይ ነው። ይህ ሴናሪዮ ልክ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው የአገራችን ተረት የተለያዩ ቡድኖች እና ክልሎች ያገኙትን አዲስ ነጻነት እነርሱ እንደፈለጉትና እንደመሰላቸው መጠቀማቸውን የሚያሳይ ሲሆን ከመንግሥት አንስቶ እስከ ቤተሰብ ደረጃ በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚመጡ ክፍተቶችንና ክፍፍሎችን የሚያሳይ ነው። ኢኮኖሚው ጥሩ እድገት ያሳያል ማሕበራዊ እድገት ግን በቂ ትኩረት አልተቸረውም። ዘርፈ ብዙ ቀውሶች የፌዴራል መንግሥቱን ሊፈረካክሱት ተቃርበዋል። አንዳንድ የክልል መንግሥታት ሙሉ በሙሉ የራሳቸውን ነጻነት ማወጅ እስከሚያስችላቸው ደረጃ ድረስ ጡንቻቸውን አፈርጥመዋል ።
4 . ንጋት
ንጋት አራተኛው ሴናሪዮ ሲሆን ቀስ በቀስ በሚደረግ የተቋማት ግንባታ ልንደርስበት የምንችለውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያሳይ ነው ። የንጋት ሴናሪዮ የኢትዮጵያ እድገት ደረጃ በደረጃ ዕውን የሚሆንበትን ተስፋ ያዘለ ነው። የሙሉ ቀን ብርሃን አልሆነም። ነገር ግን የአዲሱ ቀን ወገግታ ጀምሯል። ኢትዮጵያውያን ሕጋዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እና የዕርቅ ሂደቶችን አጠናክረው በመተግበር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እያስቀጠሉ ነው። በአገሪቱ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሥር የሰደዱ ማሕበረሰባዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እልባት ማግኘት ጀምረዋል። ከቅራኔ እና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታና እርቅ አስተሳሰቦች በማሕበረሰቡ ዘንድ እንዲሁም በመደበኛ እና ማሕበራዊ መገናኛዎች በየዕለቱ ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቶአል። የዴሞክራሲ ተቋማትና ኢኮኖሚው ደረጃ በደረጃ እየተገነቡ ፣ በጋራ ራእይ ላይ የተመሠረተ አንድነት በመፍጠር ላይ ይገኛል።
እንደ ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ሰላም ብልፅግና ምትሀት አይደለም ። ዝም ብለን እጃችንን አጣጥፈን የምንጠብቀው አይደለም። የምንገነባው እና ሰርተን የምናገኘው ነው ። ተሸንፈን የምናሸንፍበት ነው። አሸንፈን የምንሸነፍበት ነው። ሰጥተን የምንቀበልበት ፣ ተቀብለን የምንሰጥበት ነው። የምንተባበርበት ነው። ልክ እንደ ጋብቻ የሚቆጠር ነው። ጋብቻ ውስጥ አሸናፊ ተሸናፊ የሚባል ነገር የለም። ሁለቱም አሸናፊ ናቸው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም እንደ ጋብቻ አይነት ግንኙነት ላይ ነው ያለነው። ሰዎች የተሻለ የተባለ ሲናሪዎን ላይ ለመድረስ የትኛው መንገድ ነው የሚያስኬደኝ የሚል ጠቢብ የሆነ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል ። …” የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ሀሳብ አመንጪ እና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ከፍ ብለው እንዳስገነዘቡት ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት መስቀለኛ መንገድ ወደ ብሩህ ተስፋ የማሸጋገር ጉዳይ ቁጭ ብሎ እጅን አጣጥፎ በመጠበቅ ወይም በፍላጎት ብቻ ሊሳካ አይችልም ። ስለሆነም የሁሉንም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ። ይህ ተሳትፎ ግን በግዕብታዊነት እና በአቦሰጥ ዘው ተብሎ የሚገባበት አይደለም ። በሰከነ አእምሮ በጥሞና የተተለመውን መንገድ መከተል ያሻል ። ይህን መንገድ 50ዎቹ የዴስቲኒ ቡድን አባላት ለስድስት ወራት የሀገራችንን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ እና መጻኢ እድል ወይም አደጋ በጥልቅ ተጠየቃዊ እና አመክኖአዊ በሆነ አግባብ ተንትነው ከላይ የተዘረዘሩትን እድል ፈንታዎች ተንትነው አስቀምጠዋል። “ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓም “ ከላይ በተዘረዘሩት እድል ፈንታዎች ፣ ቢሆኖች ፣ ሊሆን ይችላሎች scenarios በአንዱ ይወሰናል። በሰባራ ወንበር ወይም በአፄ በጉልበቱ አልያም በፉክክር ቤት ወይም በንጋት። የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ቢሆኖች ሀገራችንን ከገባችበት የቀውስ አዙሪት ፣ የግጭት አረንቋ ፣ ልዩነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት ፣ ኢፍትሐዊነት ፣ ኋላቀርነት፣ ወዘተ. . . ሊታደጓት የሕዝቧንም ተስፋ ሊያለመልሙት አይችሉም። ሶስቱም ሴናሪዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በንጉሳዊው ፣ በወታደራዊው ወይም በቀዳማዊ ኢህአዴግ ተገልጠው ዛሬ ለደረስንበት ውስብስብ ችግር የዳረጉን ናቸው ። ዛሬ ላይ ከሶስቱ አንዱን አልያም ሶስቱን ሴናሪዎች በአንድነት ብንመርጥ ወዳለፍናቸው አገዛዞች እና አበሳዎች የሚመልሱ ናቸው ።
በአንጻሩ 50ዎቹ የዴስቲኒ አባላት በአንድ ድምፅ ሀገርን እና ሕዝብን በማስቀደም የመረጡትን እድል ፈንታ “ ንጋትን “ ብንመርጥ መፃኢው ዘመን እንደ ጎህ የሚቀድ እንደ ንጋት ወገግ እያለ የሚሄድ ይሆናል። ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ ፣ እኩልአዊ ፣ ሀገር መመስረት እንችላለን። ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጉን በረከቶች ላይ የሚያተኩር ዜጋ ለማነፅ እና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት ያስችላል። በአጠቃላይ በ2032 ዓ.ም የተሳካ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ይሆናል – ይነጋል። ኢትዮጵያ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጠንክራ እየሠራች ትገኛለች። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥምር ፓርቲ ሥርዓት ውክልና፣ ከጾታ፣ ከእድሜ፣ ከችሎታና ከማሕበራዊ መደብ ስብጥር ጋር በጽኑ ተሳስሯል። የብሔር ለብሔር ግንኙነቱ ፍትሐዊና በስምምነት ላይ የተመሰረተ ሆኗል። በዚህ ጊዜ ልዩነትን የማስተናገድ ባህል ዳብሯል። አዲስ የአንድነት እና የጋራ ብሔራዊ ማንነት ጽንሰ ሀሳብ ብቅ ብሏል። የፌዴራል ሥርዓቱ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አንድነትን በሌሎች ላይ ደግሞ ብዝሃነት እንዲኖር አስችሏል። ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በአመራር ላይ ጽኑ ተፎካካሪ ሆነዋል። የሥርዓተ ጾታ እኩልነትና ማሕበራዊ ፍትሕ የአገራችን ልዩ መገለጫዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። የሕዝብ እድገት ምጣኔ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል። በዚህ ጊዜ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ባህል እና ጠንካራ መሪዎች ስላሉን በክፍለ አህጉሩና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወትን እንገኛለን። አቋማችን በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ውሎች ረገድ ጠንካራ የመደራደር አቅም ፈጥሮልናል። ኢትዮጵያ የተሻለ የሥራ እድል ያለባት አገር ስለሆነች ባልታሰበ ሁኔታ የአጎራባች አገራት ዜጎች ወደ አገራችን በስደት ይመጣሉ።
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ቢሆን ተግዳሮቶች አሉብን። በኢኮኖሚውና በአስተዳደሩ የደረስንበትን እመርታ ያህል በማህበራዊው ዘርፍም የሚጠበቀውን ያህል እድገት አላመጣንም። ሁልጊዜም ተመሳሳይ አቋም ከማይኖራቸው ፓርቲዎች የተለያዩ አቋሞችን ስለምንሰማ የውሳኔ አሰጣጥ አስቸጋሪና የተጓተተ ነው። ሆኖም በዚህ ደረጃ ላይ መቻቻል የዴሞክራሲ ሂደቱ አንዱ አካል ነው። ቀስ እያለ በሚፈስ የማሕበራዊ እድገት ጉዞ ላይ ነን።
የዴሞክራሲ መሠረት ለመጣል እጅግ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል። ይሁን እንጂ አሁንም በረጅሙ ጉዞአችን መልካም እድሎች እና ተግዳሮቶች ይጠብቁናል ። የዴሞክራሲ ጉዞአችን እየተሻሻለ የሚሄድ ነገር ግን ያላለቀ ፕሮጀክት ነው ።
ለዚህ ነው ከድቅድቅ ጨለማ ንጋትን የመረጥሁ ። እናንተስ ! ?
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳይን )