ክፍል ሁለት
ኅዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ብዕሬ ቤትኛ በሆነበት በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ ዓምድ ላይ “የሕዝብ ለሕዝብ ልዑካን የካምፓላ ቆይታ” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ ማቅረቤ ይታወሳል። በዚያ የጉዞ ዘገባ ውስጥ ጠቋቁሜ ያለፍኳቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ፈታ አድርጌ ለማብራራት የይደር ቀጠሮ መስጠቴም ይታወሳል። “የተናገሩት ከሚጠፋ” እንዲሉ እነሆ ሁለተኛውን ጽሑፍ ቃሌን አክብሬ ዳግም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ተመልሼበታለሁ።
ከዚያ በፊት አንድ ወቅታዊ ቁጭት፤
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለተሸለሙት የሰላም ኖቤል በአንደበቴ ዕልልታ፣ በእጆቼ ጭብጨባ፣ በብዕሬ ሙገሳ ደስታዬን እገልጻለሁ። የሀገሬ ሰው ደስታውን ቃላት አልገልጽለት ሲለው “አሹ!” በማለት የአድናቆት ስሜቱን ይዘረግፋል። እኔም ይህንን ድንቅ ገለጻ ተውሼ አሹ! ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከኢትዮጵያ የተነሳችው የሰላም ርግብ ከአጥናፍ አጥናፍ እየበረረች የደስታዋን ብስራት ለዓለም አድርሳለች። እንኳን ደስ ያለዎት! ብዬ ደስታዬን በመግለጥ እንደረደራለሁ።
ሽልማቱ ያስታወሰኝ ታሪካዊ ክስተት፤
ከ1957 – 1966 ዓ.ም ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ያህል ለሀገራችን፣ ለአፍሪካና ለተቀረው የዓለም ማሕበረሰብ ታላላቅ ተግባራትን ላከናወኑ ምርጥ ልሂቃን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት እጅግ የተከበረና ብዙዎች ይጓጉለት የነበረ ሽልማት ይሸልም ነበር። ከሀገራችን ደራስያን መካከል ከበደ ሚካኤል፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ መንግሥቱ ለማ፣ ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል፣ ደስታ ተክለ ወልድን የመሳሰሉ በርካታ ጎምቱ ደራሲዎቻችንና የቋንቋ ምሁራን የሽልማቱ ተካፋይ ነበሩ። በሥነ ጥበቡም ዘርፍ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌንና እስክንድር ቦጎሲያንን የመሳሰሉ ዝነኛ ሰዓሊያን ለሽልማቱ ታድለው ነበር።
በንግድ፣ በእርሻ፣ በሰብዓዊ አገልግሎት፣ በትምህርትና በምርምር ዘርፍም በቀለ ሞላ፣ ሰይፉ ፈለቀ፣ አስፋው የምሩ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበርና ሌሎች በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት ተሸላሚዎች ነበሩ። ከአፍሪካ አህጉርም በርካታ ፕሮፌሰሮች፣ ተመራማሪዎችና የጤናና የሰብዓዊ መብት ትጉሃንና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሴዳር ሴንጎርን ጨምሮ በፊስቱላ በሽታ የሚሰቃዩትን የሀገራችንን ሴቶች በመርዳት የሚታወቁት ዶ/ር ሐምሊንን ጨምሮ ከአውሮፓ፣ ከሰሜን አሜሪካና ከሌሎች በርካታ ሀገራት የተመረጡ ጠበብት በተለያዩ ዓመታት ሽልማቱን ተቀብለዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል በልዩ ሁኔታ የሚዘከሩ፤
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በተጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት በ1957 ዓ.ም በግርማዊት እቴጌ መነን ስም የተሰየመውን የብር ሰላሣ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት (በወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ ነበር) ከወርቅ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ጋር የተሸለመው በቀደም ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የሰላም ኖቤል የሸለመው የአልፍሬድ ኖቤል የሽልማት ድርጅት ነበር። ሽልማቱን በአካል ተገኝተው ከንጉሠ ነገሥቱ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ የተቀበሉት የወቅቱ የኖቤል ሽልማት ድርጅት ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቲ. ሲሲያስ ነበሩ።
የኖቤል ድርጅቱ የተሸለመበት ዋና ምክንያት በአጭሩ የተገለጸው እንዲህ ተብሎ ነበር። “በአሁኑ ክፍለ ዘመን በሙሉ የአልፍሬድ ኖቤልን ሃሳብና ዓላማ በመከተል መልካም ሥራ ላበረከቱት ሰዎች ሽልማት በመስጠት ከፍ ባለ ደረጃ ያከናወነ በመሆኑና ድርጅቱ በትክክልና ተመጣጣኝ በሌለው ደረጃ ሥራውን ለረጅም ዘመናት በመስራቱ የአብዛኛውን ሕዝብ አድናቆት በማግኘቱ እንዲሸለም ተወስኗል። ” የሚል ነበር።
ጸሐፊውን ዳግላስን የቆጨው፤
በንጉሠ ነገሥቱ እጅ ኢትዮጵያ የኖቤል ሽልማት ድርጅትን የሸለመችው የ2019 ዓ.ምን መቶኛ የሰላም ኖቤል ሽልማት ያሸነፉት የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመወለዳቸው 55 ዓመታት አስቀድሞ ነበር። ታላቋ ሀገሬ ታላቁን ተቋም ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት አስባ መሸለሟ በርግጥም የቀዳሚ መሪዎቻችንን ታላቅ ርዕይ የሚያሳይ ተግባር ነበር። በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትና ከንጉሡ እጅ ያን የመሰለ ሽልማት ማግኘት ታላቅ ክብር የሚያጎናጽፍ ነበር። ታሪካችን ይህንን መሰሉን ክብር ለመመስከር ተሽኮርማሚ ቢሆንም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማታቸውን ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ ሲቀበሉ ይህንን ታሪክ ቢያስታውሱ ኖሮና ከዋናው ንግግራቸው አስቀድመው፤ “እናንት የኖቤል ኮሚቴ አባላት ለእኔና ለሀገሬ ይህንን የከበረ ሽልማት ለመሸለም ከመወሰናችሁ በፊት፤ ያውም ከዛሬ 55 ዓመት አስቀድሞ እኔ ባልነበርኩበት ዘመን ይህንን የተከበረ የኖቤል ሽልማት ድርጅት፤ ያውም በመጀመሪያው የሽልማት ዓመት፤ ሀገሬና መንግሥቴ በክብር አሽሞንሙነው ሸልመውት ነበር። እኔና ሀገሬን ዛሬ ይህንን ሽልማት በመሸለማችሁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማኝ እየገለጽሁ ውለታ እንደማትረሱም ጭምር ጥሩ ማሳያ እንደሆነ ሳገልጽ አላልፍም። ” (ሳላስበው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢናገሩት ኖሮ ብዬ የተቆጨሁበትን የንግግር ሃሳብ እንዳለ አሰፈርኩ መሰለኝ። )
በርግጥም ይህ ታሪካዊ ማስታወሻ በዚያ የከበረ የሽልማት መድረክ ላይ በተሸላሚው አንደበት ቢገለጽ ኖሮ ድምቀቱና ሞገሱ እንደምን ይበልጥ ይጎላ እንደነበር ለመገመት አይከብድም። እንዲሁ ሳስበው ግን የዓለም መገናኛ ብዙኃን ተሽቀዳድመው ለዜናቸው የሚሰጡት ርዕስ “ኢትዮጵያ ውለታዋ ተከፈላት!” የሚል ይመስለኛል። ለማንኛውም “ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም” አሰኝቶ ካላስተረተ በስተቀር ይህ ታሪክ በዚያ ደማቅ የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ቢገለጽ ኖሮ አቤት ይገኝ የነበረው ተጨማሪ ክብር! ከሽልማቱ አንድ ቀን አስቀድሞ በግል በምጠቀምበት የፌስ ቡክ ገጼ ላይ ይሄንንው ጥቆማ ሰንዝሬ የነበረ ቢሆንም ያለመታደል ሆኖ ግን በሚመለከታቸው ሰዎች የተነበበ አይመስለኝም። “ወይ ነዶ!” ይላል ቁጭት የገባው የሀገሬ ደጉ ሰው። ምን ያደርጋል ዕድሉ አመለጠን።
ወደ ካምፓላ ዋና ጉዳያችን እንመለስ፤
የካምፓላው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዋነኛ የተልዕኮ ዓላማ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋርና በሌሎች የጋርዮሽ ጉዳዮች የዩጋንዳ መንግሥት ለሀገራችን ስላሳየው ቀና አመለካከትና ትብብር ለማመስገንና በዚያ ሀገር ከሚገኙ ዜጎቻችን ጋር ቤተሰባዊ ቆይታ ለማድረግ መሆኑን በሳምንቱ ጽሑፌ አብራርቼ ገልጫለሁ። የተልዕኮው ዓላማም ሙሉ ለሙሉ የተሳካ እንደነበር የግሌን ማረጋገጫ ሰጥቻለሁ። የተማርንባቸውና የተቆጨንባቸው በርካታ ሁኔታዎች አንዳጋጠሙንም ነካክቼ አልፌያለሁ።
የዛሬው ጽሑፌ የሚያተኩረው በክፍል አንድ የነካካኋቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ጫን ብሎ ለማፍረጥ ይሆናል። እኔ እንደተረዳሁት አስተዋዩ፣ ዕድሜና ሥልጣን ጠገቡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ክቡር ዩዌሪ ሙሴቪኒ ፕሮቶኮል ባልተጫነው ቋንቋ እኛን ወክለው ላነጋገሯቸው የተወሰኑ የልዑካን ቡድን አባላት ያጫወቷቸው የልባቸውን ሃሳብ እንዲህ በማለት ነበር። “በዘመነ ወጣትነታችን ኢትዮጵያን የምንመለከታት ለመላው አፍሪካዊያን ኩራት እንደሆነች እያመንን ነበር። ሀገራችሁ ለእኛ ዘመን አፍሪካዊያን ወጣቶች ኩራት ብቻ ሳትሆን እንደ ክብርም በመቁጠር የነፃነቷን ታሪክ እየተረክን ጣሊያንን ደጋግማ በማሸነፏም በድል ተምሳሌትነቷ ተማርከንባት እንደ አርማ እንቆጥራት ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የአገዛዝ ዘመን ሶሻሊዝም/ኮሚኒዝም እያሉ ያበዱለትን ሥርዓታቸውን ጥቂት እንዲያሰክኑ መክሬያቸው ነበር፤ አልሰሙኝም። ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላም ሀገር ይመሩ ለነበሩት መሪዎቻችሁ በጎሳ ላይ ያማከለውን ሥርዓት በድርበቡ ያዙት ብዬ መክሬያቸውለሁ፤ የሰሙኝ አልመሰለኝም። ምክሬን ቢሰሙ ኖሮ እወድ ነበር” በፍቅር የወዛው የፕሬዚዳንቱ መልዕክትና ምክር እጅግ ብዙ ቁምነገሮች የተገበየበት ነበር። “ሁሉን ቢናገሩት” እንዳይሆን ስለሰጋሁ ለአብነት ጠቅሼዋለሁ።
“ልብ ያለው ልብ ያድርግ፤ የቦርከና ወንዝ ማለት ይሄ ነው!” አለ ይባላል በክፉ የርሃብ ዘመን ምን ይሉኝን ከቁብ ሳይቆጥር ሚስቱን ሸጦ የእርሱንና የልጆቹን ነፍስ ለመታደግ የጨከነ አባወራ። ምሥጢሩ ከገዢዎችሽ አምልጠሽ ወደ ቤትሽ ብትመለሽ እንኳን የቦርከና ወንዝ ምልክት ይሁንሽ ማለቱ ነበር። የፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ንግግርም ልብ ያለው ልብ ያድርግን ያስታውሰናል። እናመሰግናለን ክቡር ፕሬዚዳንት።
ስለ ዩጋንዳ መንገዶች ጠቆም አድርጌ ማለፌ አይዘነጋም። ከዋና ከተማዋ ከካምፓላ ውጭ የሚገኙት የሀገሪቱ መንገዶች በአብዛኛው መልካም በሚባል ይዞታ ላይ የሚገኙ ናቸው። በተለይም በኢንቴቤ ከተማና በካምፓላ መካከል የተዘረጋው ዘመናዊው ፈጣን መንገድ ከአካባቢው ልምላሜና ጽዳት ጋር ተዳምሮ የሾፌሮችን መንፈስ በሃሴት ያስደንሳል፤ ተሳፋሪንም ያዘምራል። መንገዱን የሠሩትና እየሰሩ ያሉት በእኛ ሀገር ድንኳናቸውን የተከሉ የቻይና ኩባንያዎች መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ።
የካምፓላ ከተማ ጠባብ መንገዶች፣ የትራፊክ ጃም፣ ጭንቅንቁና ትርምስምሱ ግን ሀገሬ በስንት ጣዕሟ ያሰኛል። በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓትማ ያለማንሳቱ ይመረጣል። በዚያ ጭንቅንቅ መሃል አንድ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ምናልባትም ሰዓታት ሊገድል ይችላል። በካምፓላ በራስ መኪና ከመጓዝ ይልቅ በእግር መጓዝን ያስመኛል። የሕዝብ ትራንስፖርት ጠብቄ ልጓዝ ማለትማ አይሞከር።
ደግነቱ ዕድሜ ለቦዳ ቦዳ። ቦዳ ቦዳ የካምፓላ ነዋሪ ከልጅ እስከ ሽበት የሚጓጓዝባቸው የሞተር ብስኪሌት አማራጮች ናቸው። ሞተር ብስኪሌቶቹ አንድም ሁለትም ተሳፋሪ እያሳፈሩ የታክሲና የአውቶብስ አገልግሎት ይሰጣሉ። የሞተር ብስክሌቶቹን ቁጥር ግን እንኳን ሕዝቡ ቀርቶ ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት እንኳ በውል ያውቃቸው እንደሆን እርግጠኛ አይደለሁም። የቁጥራቸውን ብዛት በጉንዳንና በአሸን መመሰሉ ይቀላል። ቦዳ ቦዳ በካምፓላ ባይኖርስ ብሎ ማሰቡ በራሱ ጭንቅላት ያዞራል። የፈለጉበት ቦታ ተሳፋሪዎችን ለማድረስ ግን ሹልክልክ እያሉ ስለሚያመልጡ ተሳፋሪያቸውን የሚያደርሱት ደቂቃ ዝንፍ ሳይል ነው። የመዲናችን አስተዳደር በቅርቡ ሞተር ብስኪሌቶችን እንዳገደው ሁሉ ካምፓላም ልሞክር ብላ እኛን ብትኮርጅ ኖሮ ሰበቡ ለትውልድ የሚተላለፍ ቀውስ እንደሚፈጥር ስለሚተዋወቁ የሚኗኗሩት በመከባበር ነው። ለአንድ ሰዓት ያህል የቦዳ ቦዳ አገልግሎት በካምፓላ ቢቋረጥ የከተማዋ እስትንፋስ በሰከንድ ቀጥ ብሎ ሲጥ ያደርጋት ነበር። “የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ!” ይላል የሀገሬ ሰው።
በዩጋንዳ ልነግድ ያለ ዜጋም ሆነ መጤ በሕጉ ስርዓት እስከተመራ ድረስ ይበረታታል፣ ይደገፋል፣ ይታመናል እንጂ እንደ ሀገሬ የንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣትና ቢከስርም ፈቃድ ለመመለስ ደም እንባ አያስለቅሱም። የግብርና የቀረጥ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤትም ሳትዋሸኝ ያመንከውን ክፈል ብሎ ያበረታታል እንጂ እንደ ሀገሬ መሰል ተቋማት ተስፋውም ህሊናውም በጅራፍ እየተገረፈ “ያላተረፍከውንም ቢሆን አምጣ” እየተባለ እንጦሮጦስ አይወረወርም።
ስደተኞች ወገኖቻችን ሳይቀሩ እየተበረታቱ ወደ ንግድ ሥራ ሲገቡ በአጭር ዓመት በስኬት የሚባረኩት በዚሁ የምድሪቱ ርህራሄ መንስዔነት ነው። የሀገራችንን የንግድ ሥርዓት ትብታብ ለመፍታት በቅድሚያ የአእምሯችንን የሸረሪት ድር ማጽዳት እንደሚገባን በሚገባ አምናለሁ። ንግዳችንና እንባችን መቼ ነጻ ወጥቶ እንደሚታበስ አዋቂው ፈጣሪ ብቻ ነው።
ጂንጃ በሚባለው አካባቢ የጎበኘነውን የነጭ አባይ መነሻና የቪክቶሪያ ሐይቅን በተመለከተ ግን የተሰማንን ቁጭትና መብገን ለመግለጽ ቃላት አቅም አይኖራቸውም። የእኛው ጥቁር አባይ ከሚነሳበት ከከሰላና ግሸ አባይ ጋር እና ከጣና ሐይቅ ጋር እናነጻጽራቸው ከተባለማ ባይሞከር ይሻላል።
የዩጋንዳ መንግሥት ነጭ አባይንና ቪክቶሪያ ሐይቅን የሚያለማውና የሚያስጠብቀው በልዩ እንክብካቤ ነው። ወንዙም ሆነ ሐይቁ ንፁህና ከብክለት የጸዳ ነው። የዓሳ ሀብቱም በባህላዊ ዘዴ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ኢንዱስትሪም ተደራጅቷል። የወንዙ መነሻ (Zero Point) ተለይቶ ተመልክቷል። ቪክቶሪያን አገኙ የሚባሉ የባዕዳን አሳሾች ሳይቀሩ በሐይቁ ውስጥ በሚገኝ ደሴት ላይ መታሰቢያ ቆሞላቸዋል። የሐይቁ ዙሪያ ገብ ማራኪና ውብ ነው። በሐይቁ ዳር የምግብና መጠጥ አቅርቦቱ ገንዘብን ካልጨነቀው በስተቀር በዘመናዊ ሆቴሎችና ሎጆች እንደ ልብ መስተናገድ ይቻላል። እዚያ አካባቢ ቆሞ ጣናንና የእምቦጭ አረምን ማሰብ አእምሮ ያቃውሳል። የእንቦጭን ምልክት በቪክቶሪያ ሐይቅ ዳር በትንሹ ምልክቱን አይተን የእኛ ክፉ ዕጣ እንዳይደርስባቸው በጸሎት አግዘናቸዋል። አይ እኛ! ማን ይሆን አዚም ያደረገብን? ማንስ ይሆን ከተፈጥሮም ይሁን ከራሳችን ጋር እንድንጣላ የፈረደብን። ሆድ ይፍጀው ብሎ ማለፉ ይቀላል።
ወደ ራሳችን ጉዳይ እንመለስ፤
ጉራጌዎች አውከሬ እንደሚሉትና በማሳ መሃል እንደሚቆመው የወፎች ማስፈራሪያ ምስለ ሰው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት፣ ስደተኞችና ነዋሪዎች ለዓመታት የኖሩት እየተፈራሩና እየተጎሸማመጡ ሆድና ጀርባ ሆነው ነበር። የኤምባሲ ጽ/ቤታችን እንኳንስ በሀገሩ ልጆች ሊጎበኝ ቀርቶ በአካባቢው ቢታለፍ እንኳ እከሌ ምን ፈልጎ ነው በኤምባሲ አካባቢ የታየው እያሰኘ ያስጠረጥር ነበር።
ዕድሜ ለጊዜና ለታሪክ ለዋጮቹ መሪዎቻችን ይሁንና ዛሬ የኤምባሲው ጽ/ቤት ለዜጎቻችን የመኖሪያ ቤታቸው እስኪመስል ድረስ የግላቸውና ቅርባቸው ሆኗል። ክብርት አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሠረት ተሹመው ከሄዱ ጊዜ ጀምሮ ታሪክ ተለውጧል። እንደ እናት፣ እንደ ታላቅ እህትና እንደ ታላቅ ዲፕሎማት የሦስትዮሽ ሚና በመጫወታቸው የጥሉን ግድግዳ ደረማምሰው ኤምባሲያችንን ነፃ አውጥተውታል። ይህንንም እውነታ በዓይናችን አይተን አረጋግጠናል። የኮሚዩኒቲው አባላት የኤርፖርት አቀባበልና መስተንግዶ ውለታም በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።
ላደራጀንና ላሰማራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ ቤት ታላቅ ምስጋና፣ ለዩጋንዳ መንግሥት ልባዊ አክብሮት፣ ለኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ በዩጋንዳ ለሚገኙት ክብርት አምባሳደርና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለምድር ለሰማይ የከበደ አድናቆት፣ በግል ላስተናገዱን ወዳጆቻችን ልዩ በረከት እየተመኘሁ ለዳግም ጉብኝት ያብቃን እላለሁ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)