በአማርኛ ሪሕ ተብሎ የሚጠ ራው በሽታ በአንጓ ወይም በመገጣጠሚያዎች ላይ ብርቱ የሆነ ሕመም የሚፈጥርና ምቾት የሚነሳ በሽታ ነው። ይህ በሽታ አዲስ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው። የዚህ በሽታ አመጣጥ ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ስለሚገመት የነገስታት በሽታ ተብሎ ይጠራም ነበር። ነገስታቱ በድሎት ከሚመገቧቸው ምግቦች በመነሳት ማለት ነው። ሆኖም ይህ በሽታ ሌሎችን ሰዎች ሊያጠቃ እንደሚችል በግልፅ ይታወቃል። ወደ በሽታው ስንመለስ የመጀመሪያ ስሜቶች ወይም ምልክቶች የሚጀምሩት አልፎ አልፎ በሚነሳ ብርቱ የሆነ የመገጣጠሚያ ሕመም ነው። አብዛኛውን ጊዜ በተናጠል አንድ መጋጠሚያ ላይ በተለይ የእግር አውራ ጣት ላይ ይከሰታል።
የዩሪክ አሲድ ክምችት አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው በአውራ ጣት አካባቢ ነው
በሰውነታችን ውስጥ ዩሪክ አሲድ(Uric acid) የተባለ በተፈጥሮ የሚገኝ የሂደቶች የመጨረሻ ውጤት ሲሆን ይህ አሲድ በሰውነታችን ውስጥ በተወሰነ መጠን የሚገኝና ከዚያም በተፈጥሮ በሽንት በኩል የሚወጣ ውጋጅ ነው። ከመጠን አልፎ በሰውነት ውስጥ ከተከማቸ ግን በመገጣጠሚያዎቻችን መሃከል በሚገኝ ፈሳሽ ውስጥ እንደ ትንንሽ መርፌ የሰሉ ዝቃጮች ይፈጥራል። እነዚህ ዝቃጮች ናቸው እንግዲህ ለእብጠትና ለሕመም የሚዳርጉት። የዩሪክ አሲድ ከመጠን ማለፍ ሊከሰት የሚችለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ሁለት ዐብይ ምክንያቶች የሚሆኑት ዩሪክ አሲድ ከመጠን በላይ ሲከማች ወይም ኩላሊቶቻችን የተከማቸውን የዩሪክ አሲድ መጠን በበቂ ሁኔታ ከሰውነት ማስወገድ ሳይችሉ ሲቀሩ ነው። ከመጠን በላይ የዩሪክ አሲድ መፈጠር የተለያዩ ምክንያቶች ውስጥ የምግብና የመድኃኒት ዓይነቶች ይገኙባቸዋል። ከመጠን በላይ የተከማቸው የዩሪክ አሲድ በመገጣጠሚያዎች አካባቢ ዝቃጭ ከመፍጠሩ በላይ በኩላሊት ውስጥና በሽንት ማመላለሻ መስመሮች ላይ በመዝቀጥ የኩላሊት ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል።
በሪሕ የሚያዙ ሰዎች እነማን ናቸው?
አብዛኛውን ጊዜ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በሪሕ በሽታ ይያዛሉ፤ የኩላሊት በሽታ ያለባቸው ሰዎችም በሪሕ በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው። ሪሕ በዘር ስለሚተላለፍ በርከት ባሉ ቤተሰብ አባላት ላይ ሊታይ ይችላል። ከሪሕ በሽታ መከሰት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ስንመለከት ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የደም ግፊት በሽታ፣ የስኳር በሽታ በተጨማሪም በሰውነት የጮማ መጠን መጨመር ይገኙበታል። ሪሕ በሕፃናት ላይ እምብዛም አይታይም።
ሪሕ እንደያዘን እንዴት ነው የሚታወቀው?
ብዙ የተለያዩ የቁርጥማት በሽታዎች ሪሕ የሚመስል ጠባይ አላቸው። ስለዚህ የቁርጥማት በሽታ ሲኖር በትክክል ሪሕ ለመሆኑ ትክክለኛ ምርመራ መደረግ ይኖርበታል። የቁርጥማት በሽታ ሪሕ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚጠረጠረው በአንድ ወይም በሁለት የመገጣጠሚያ አካላት ላይ የእብጠት ምልክትና ጠንከር ያለ ሕመም ሲፈጠር፤ ይህ ሕመም ደግሞ በመሃል ፋታ የሚሰጥ ከሆነ ነው። የመጀመሪያ የሪሕ ሕመም አብዛኛውን ጊዜ የሚነሳው በማታ ነው። እንደዚሁ ልክ ሪሕን የሚመስል ግን ያልሆነ ሪሕ(Pseudo gout) ተብሎም የሚጠራ በሽታም አለ። ትክክለኛ ሪሕ መሆኑ የሚታወቀው ሐኪሞች ካበጠው መገጣጠሚያ በመርፌ ፈሳሽ በመቅዳት ፈሳሹን በማይክሮስኮፕ በመመልከት ለሪሕ በሽታ መንስኤ የሆኑትን የዩሪክ አሲድ ዝቃጮች በማየት ነው። ከሽንት በሚወሰድ ምርመራም ሊታወቅ ይችላል
ሪሕ የከፋ ደረጃ ሲደርስ በቆዳ ላይ እብጠት ይፈጥራል፤ ይህ እብጠት በእንግሊዘኛው ቶፋይ( Tophi) ተብሎ ይጠራል። የዩሪክ አሲድ ዝቃጭ በቆዳ ውስጥ በሚፈጠረው እብጠት ውስጥም ይገኛል። በሌላ በኩል በደም ውስጥ የዩሪክ አሲድ መጠን መለካት ሊረዳ የሚችል ቢሆንም የሚያሳስት ሁኔታ ግን ሊፈጥር ይችላል። ይህም የሚሆነው የሪሕ ቁርጥማት በተነሳበት ጊዜ በደም ውስጥ የሚገኘው የዩሪክ አሲድ ሲለካ ትክክለኛ መጠን አልፎ አልፎም ዝቅ ያለ መጠን ሊያሳይ ስለሚችል ነው። እንግዲህ የሪሕ በሽታ የሚታወቀው ከመጠን በላይ የዩሪክ አሲድ መጠን ከፍ በማለቱ ነው። ስለዚህ ቁርጥማት ባገረሸበት ሰዓት የደም ምርመራው ሊያሳስት የሚችል ውጤት ሊያሳይ ይችላል ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሪሕ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች በደማቸው ውስጥ ከመጠን ያለፈ የዩሪክ አሲድ መጠን ሊገኝባቸውም ይችላል። ለረዥም ጊዜ የቆየ የሪሕ በሽታ ከሆነ ራጅ በማንሳት የተጎዳውን የመገጣጠሚያ አካል በማየት ሊታወቅ ይችላል። ሲቲ ስካን የተባለውን የውስጥ አካላት ማንሻ ዘዴን በመጠቀምም ማየት ይቻላል፤ እንደውም ይህ መሳሪያ ገና አዲስ የሆኑ በሪሕ ምክንያት የሚፈጠሩ የመገጣጠሚያ አካላት ጉዳቶችን ማየት ሊቻል ይቻላል።
ከፍተኛ የዩሪክ አሲድ ክምችት ሲኖር አብጦ በግልፅ ሊታይ ይችላል
የሪሕ ሕክምና
የሪሕ ቁርጥማት በሚነሳበት ጊዜ የሚታዘዙ መድኃኒቶች አሉ፤ ከነዚህ ውስጥ በዋነኛነት ኮልቺሲን (Colchicin) ተብሎ የሚጠራው መድኃኒት ነው። ይህ መድኃኒት ቁርጥማት ገና ሲጀምር ከተወሰደ እፎይታን ይሰጣል። መድኃኒቱ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ትውኪያ፣ ተቅማጥ ወይም የማቅለሽለሽ ሁኔታ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊፈጥር ይችላል። መድኃኒቱን ከሐኪም ጋር በመማከር በዝቅተኛ መጠን በመውሰድ የጎንዮሽ ጉዳቶቹን መቀነስ ይቻላል። የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ የዚህን መድኃኒት መጠን ቀነስ አድርገው እንዲወስዱ ይመከራሉ። ሌላ የሚወሰድ መድኃኒት ካለም ከምንወስደው መድኃኒት ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሌሎች የመድኃኒት ዓይነቶች ደግሞ ሕመምና ብግነትን (inflammation) የሚቀንሱ ሲሆን እነሱም ኢንዶሜታሲን (indomethacin, indocin)፣ ናፕሮሲን (naprosyn) የተባሉ ናቸው። እነዚህ መድኃኒቶች ቁርጥማቱ በሚነሳ ጊዜ የሚወሰዱ ናቸው። የነዚህ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት የጨጓራ ቁስለት እና ተቅማጥ ማስከተል ነው። ሆኖም ለአጭር ጊዜ ከተወሰዱ ብዙም ጉዳት ሳያስከትሉ ልንጠቀም እንችላለን።
ለሪህ በሽታ የሚወሰዱ መድኃኒቶች
በተለያዩ ምክንያቶች ከላይ የተጠቀሱትን መድኃኒቶች መውሰድ የማይችሉ ሰዎች አሉ፤ እነሱም የጨጓራ ቁስለት ያለባቸው፣ የኩላሊት በሽታ ያለባቸውና የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ናቸው። ለነዚህ ሰዎች (Corticosteroid) ተብለው የሚጠሩ መድኃኒቶችን መጠቀም ይቻላል። እነዚህ መድኃኒቶች በእንክብል መልክ በአፍ ወይም በመርፌ መልክ በታፋ መሰጠት የሚችሉ ናቸው። አንዳንዴም መድኃኒቱ ቀጥታ እብጠቱ ያለበት ቦታም በመርፌ ሊሰጥ ይችላል። ከመድኃኒቱ ውጪ የተጎዳ ወይም የታመመውን መጋጠሚያ ማሳረፍ፣ ቀዝቃዛ ወይም በረዶ በላዩ ላይ ማድረግ ሕመሙን ሊያስታግስ ይችላል።
ማስታወሻ፡- ማናቸውንም መድኃኒቶች ስንወስድ ሐኪምን በማማከር መሆን እንዳለበት መዘንጋት የለብንም። በሪሕ የሚጠቁ ሰዎች ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲመገቡ ይመከራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
ዋለልኝ አየለ