እጆቿ ገና ሰርተው አልደከሙም። በስሯ በርካታ ሰራተኞች ቢኖሯትም ሽርጧን አድርጋ ምርቶችን ማዘጋጀቱን የየዕለት ተዕለት ተግባሯ አድርጋዋለች። በአንድ እጇ ማስቲሽ በሌላ እጇ በወጉ የተዘጋጁ የቆዳ ቁራጮችን ይዛ ላያት አሰሪ ሳትሆን ተቀጣሪ ናት ብሎ ሊገምት ይችላል።
እርሷ ግን በወጣትነቷ የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትሆንም ሰፊ የማስተዳደር አቅም የሚጠይቀውን ድርጅቷን እየመራች ትገኛለች። ከሀገር ውስጥ አልፈው ወደውጭ ሀገራት የምትልካቸው ምርቶቿ የገቢዋ ምንጭ ብቻ ሳይሆኑ የውስጧን ፍላጎት አውጥታ ለሌላው የምታሳይበት የዲዛይነርነቷን ሙያዋን ያበለጸገችበት መንገድ በመሆኑ ትደሰትባቸዋለች።
ወይዘሮ ምስጋና ገብረእግዚአብሔር ትባላለች። ኤርትራ ነው የተወለደችው። ቤተሰቧ በተለይም አባቷ በደርግ ዘመነ መንግስት ስልጣን እንደነበራቸው ታውቃለች። በኤርትራም አለመረጋጋት ሲያይል እና ጦርነት ሲበረታ ግን አባቷ ቤተሰባቸው ላይ ችግር እንዳይደርስ በሚል ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ያኔ ምስጋና ገና የሶስት ዓመት ህጻን ነበረች።
አዲስ አበባ ሳርቤት እና ጨርቆስ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ቤት ተከራይተው ለመኖር ተገደዋል። በጨርቆስ አካባቢ እንዳሉም ምስጋና አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል እንዲመቻት ወንድማማቾች የተሰኘው ትምህርት ቤት ገባች። በጊዜው ከትምህርቱ ይልቅ ወደእጅ ስራው፣ ዲዛይነርነት እና ሞዴሊንጉ የምታደላው እንስት ታዲያ መጽሄቶች ላይ የሚወጡ ሞዴሊስቶች ቀልቧን ይስቡት እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህም ምክንያት የመጽሄቶቹን ምስሎች እያገላበጠች ማየቱን ታዘወትር ነበር።
ወደሁለተኛ ደረጃ ስትሸጋገር ደግሞ አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ከገባች በኋላ ይባስ ብሎ በቴሌቪዥን የሚቀርቡ የፋሽን ትርኢት እና የሞዴሎች ዝግጅቶች ላይ ትኩረቷን አደረገች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በወቅቱ የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ወስዳ ያጠናቀቀችው ምስጋና ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ባታገኝም የቴክኒክና ሙያ ለመግባት የሚያስችል ውጤት ግን አግኝታለች።
ተግባረዕድ የቴክኒክና ሙያ ተቋም ገብታ በብረታብረት ሙያ ስልጠናዋን መከታተል ጀመረች። በተግባረዕድ ለሁለት ዓመታት የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቃ ከተመረቀች በኋላ ግን ተቀጥራ አልሰራችበትም። ይልቁንም የተግባር ልምምድ/ አፓረንት/ ከወጣች በኋላ በቀጥታ ትኩረቷ የተሳበው ወንድሟ ቤታቸው ውስጥ የሚጠግናቸው ጫማዎች ላይ ነው።
ወንድሟ ቤተሰቡ በተከራየው ቤት ውስጥ ቀደም ብሎ የተለያዩ ጫማዎችን በመጠገን አነስተኛ ገቢ ያገኝ ነበር። እናም ምስጋና ለምን ቀለል ያሉ መጫሚያዎችን እያዘጋጀሁ የዲዛይነርነት ፍላጎቴን በዚያውም አላሳካም ብላ ተነሳች። የተወሰኑ የጨሌ ጌጦችን እና ቁርጥራጭ ቆዳዎችን በመሰብሰብ ነጠላ ጫማ /ሰንደል ጫማ/ መስራት ጀመረች።
በጥቂት ጊዜያት ክፍት ጫማውን ማዘጋጀት ከጀመረች በኋላ በቀጥታ ያመራችው ወደ ሴቶች የውበት ሳሎን ነው። በዚያም የመጀመሪያ ስሪቷ የሆነውን አንድ ጫማ ገዥ ከመጣ እንዲሸጡላት ነግራ ተመለሰች። ጫማውም በ35 ብር ተሸጠ። በውበት ሳሎኑ የነበሩ ሰዎች ምርቱን ስለወደዱት ተጨማሪ ሰርታ እንድታመጣላቸው ጥያቄ አቀረቡላት። ወዲያውም ከሽያጩ የተገኘችውን 35 ብር ይዛ መርካቶ በመሄድ ተጨማሪ የጨሌ ጌጦችን እና አነስተኛ ቆዳ በመግዛት በወንድሟ አጋዥነት ተጨማሪ 5 ክፍት ጫማዎችን አዘጋጅታ አቀረበች።
በሁለት ሺ የሚሊኒየሙ ክብረበዓል ወቅት የጀመረችው ስራ ቀስ በቀስ እየጎለበተ መጣ። እንዲህ እንዲህ እያለች በጥቂት ወራት ውስጥ የቆዳ ነጠላ ጫማዎቹን የሚፈልጉ ሰዎች በመበራከታቸው ምርቶቿን እያሳደገች ለመሄድ አልተቸገረችም። የወንድሟ የጫማ መስሪያ የእጅ መሳሪያዎች አነስተኛ አቅም ስለነበራቸው ወደመርካቶ እየሄደች ቆዳዎቹን በማሰንጠቅ እና ሶሎቹን በማሽን በማሰፋት በየጊዜው ለማደግ ጥረት ታደርግ እንደነበር አትዘነጋውም።
በልጅነት የነበራት የሞዴሊንግ እና የዲዛይነርነት ፍላጎት ደግሞ በሻማ ዲዛይኖች ላይ በማንጸባረቅ የእራሷን ይዘት አሻራ ያረፈባቸው ጫማዎችን ወደማምረቱ ገባች። በወቅቱ ደግሞ ኢንተርኔት ላይ የሞዴሊስቶች ውድድር የተመለከተ ማስታወቂያ ተመለከተች። እናም ውስጧ ያለውን ፍላጎት ለማርካት ተመዝግባ ውድድሩ ላይ አለፈች። በዚህም ምክንያት በርካታ መድረኮች እና ዝግጅቶች ላይ በሞዴሊነቱ እንድትሳተፍ እድል አግኝታበታለች።
የሞዴሎች ትምህርት ቤት ገብታም ተጓዳኝ ሙያዋን በትምህርት አበለጸገችው። የጫማ ምርቷን ሳትለቅ በምትሰራው የሞዴል ተሰጥኦ ማስታወቂያዎች ላይ ጭምር ተካፍላ ክፍያዎችን እንድታገኝ ረድቷታል። ይህን ሁሉ ስትከውን ግን የጫማ ምርቶቿን በቤተሰብ የኪራይ ቤት ነበርና ቤቱ ለመኖሪያ እንጂ ለንግድ አልተፈቀደም የሚል ፈተና ገጠማት።
ችግሩን ለማለፍ ለእናቷ ቀደም ብሎ የተሰጠ የመንገድ ዳር ተለጣፊ ሱቅ ነበርና እዚያ ገብታ መስራት እንዳለባት ወሰነች። ገነት ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው ሁለት በሁለት የሆነ ጠባብ ሱቅ ውስጥ ከእህቷ ጋር አጸዳድታ ስራዋን ቀጠለች። በ2001 ዓ.ም ተለጣፊ ሱቋን በ400 ብር ተከራይታ ከእህቷ ጋር በመሆን የተለያዩ ጫማዎችን ማምረቱን ተያያዘችው።
በሶስት ሺ ብር አንድ መስፊያ ማሽን እና ለጫማ መስሪያ የሚሆን መሞረጃ ማሽን ገዝታ አነስተኛ መስሪያ ቦታዋን አጠናከረች። የወንድማቸው እግዛ ሳይለያቸው ወይዘሮ ምስጋና እና እህቷ ለሁለት ዓመታት በገነት ሆቴል መንገድ ዳር የነበረችው ተለጣፊ ሱቅ ውስጥ ከሰሩ በኋላ ሱቋ ስላነሰች ሌላ መፈለግ ነበረባት፡፡ እናም ፍላሚንጎ አካባቢ ሰንሻይን ወንዙ ዳር የተሰራ ሼድ ሰፋ ያለ መስሪያ ቦታ በክፍለ ከተማ አማካኝነት አገኘች።
ሰፋ ወዳለው መስሪያ የተሸጋገረችው ጫማ አምራች ታዲያ ስራውን በማለማመድ ተጨማሪ አንድ ሰራተኛ ቀጥራ ምርቶቿን አሳደገች። በወቅቱ ሙያተኛ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለነበር በመኖሪያ አካባቢዋ የምታውቀውን ሰው አሰልጥና ወደስራ መግባቷን ወይዘሮ ምስጋና ትናገራለች። ለሁለት ዓመታት በሼዱ ውስጥ እንደሰራች ግን ምርቶቿ በማደጋቸው ወደሌላ ቦታ ለመዘዋወር ተገደደች።
በጊዜው መስሪያ አካባቢዋ ለሌላ ልማት በመፈለጉ ጨርቆስ አካባቢ የሚገኝ ህንጻ ውስጥ በኪራይ መልክ እንድትገባ ይደረጋል። በዚያም ከሴት ክፍት ጫማዎች በተጨማሪ የወንድ እና የሴት ሽፍን የቆዳ ጫማዎችንም ጭምር በማዘጋጀት ወደተሻለ አምራችነት ተሸጋገረች።
በተለይ ከመኪና ጎማ የምታዘጋጃቸው የጫማ ሶሎች እና ከአሮጌ ጅንሶች የምትሰራቸው ጫማዎች ታዋቂነቷን ጨምረውላታል። የተለያዩ ያገለገሉ የሶፋ ጨርቆችን እና ከአካባቢዋ የሚገኙ ምርቶችን በመጠቀም በእራሷ ዲዛይን ሰርታ የምታመርታቸው ጫማዎች ሰፊ ገበያንም ይዘውላት መጡ። ብዙዎች ያረጀ ጅንስ ሱሪያቸውን ይዘው እየመጡ ጫማ ስሪልን ሲሏት ፋሽን የተከተሉ ምቹ መጫሚያዎችን በማዘጋጀት የንግድ ፈጠራዋን አሻሻለችበት።
አቅሟ እየጠነከረ ሲመጣ ደግሞ የተለያዩ የጫማ ሶሎችን በምትፈልገው ዲዛይን መሰረት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር እያስመረተች መጠቀም ጀመረች። ምርቶቿን በጥራት እና በውበት ረገድ ለማሻሻል ሁሌም እንደምትለፋ የሚያውቋትና የሚመሰክሩላት ወይዘሮ ምስጋና አሁን ላይ በተለያዩ መደብሮች እና ቡቲኮች ምርቶቿን ማግኘት ቀላል ነው።
በተደጋጋሚ ጊዜ ስለምቾት እና ጥንካሬው እንዲሁም ዲዛይኑ ማማር ፍተሻ አድርጋ ለገበያ የምታቀርብ በመሆኑ ምርቶቿ በነጋዴውም ሆነ በተገልጋዩ ዘንድ ተቀባይነታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መሆኑን የሚያውቋት ይመሰክራሉ። በከተማው ውስጥ በርካታ ሰዎች እግር ላይ ጫማዎቿን ማየት የተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጣቷ ነገም የበለጠ ሰርታ ለማደግ የሚያስችላትን ስም እየገነባች መሆኑንም የሚናገሩ በርካታ ናቸው።
በቀን እስከ 100 ጫማዎች የማምረት አቅም ላይ የደረሰችው እንስት አንዱን ጫማ ከ 800 ብር ጀምሮ ወደታች ባሉ ዋጋዎች ምርቶቿን እንደምትሸጠው ትናገራለች። በተለይ ደግሞ 95 ከመቶው የምርት ግብዓቷ በሀገር ውስጥ የሚሟላ በመሆኑ እስከአሁን ሰፊ የውጭ ምንዛሬ ችግር አልገጠማትም።
በቦሌ አየር ማረፊያ የእንግዳ መቀበያ በሚገኙ ሱቆች ውስጥ ምርቶቿን በማቅረብ ለውጭ ደንበኞቿን ፍላጎት ለማሟላት መንገዱን የጀመረችው ወይዘሮ ምስጋና በሀገር ውስጥ ደግሞ በመቀሌ እና ናዝሬት ቀጥታ ምርቶቿን የምታስረክባቸው ጅምላ ነጋዴዎች ጋር አብራ ትሰራለች። በቀጣይ ደግሞ የምስጋናን ብራንድ የያዙ መሸጫ ሱቆችን በአዲስ አበባ ስለመክፈት ዝግጅት እያደረገች ይገኛል።
ዛሬ ምስጋና ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ጫማዎቿን ወደውጪ መላክ ጀምራለች። በሶስተኛ ወገን ወደአየርላንድ የተላኩት የምስጋና ጫማ ምርቶች ጥሩ ገበያ አግኝተዋል። በእራሷ ስም የላኪነት ፈቃድ አውጥታ ደግሞ ወደጃፓን ለሙከራ ያህል ምርቶቿን ልካ ተቀባይነት አግኝታለች። በቀጣይም የተለያዩ ሀገራት ጫማዎችን በመላክ ገቢዋን ለማሳደግ ውጥን ይዛለች።
አሁን ላይ ወይዘሮ ምስጋና በማምረቻ ቦታዋ በጊዜያዊነት እና በቋሚነት የሚሰሩ 25 ሰራተኞችን ቀጥራለች። በሱቋ የሚሰሩ ወጣቶችም ገንዘብ ከማግኘት ባለፈ ለቀሪው ህይወታቸው የሚሆን ልምድ ማካበት መቻላቸው ለእርሷ ደስታ ነው። አንድ የስራ ተሽከርካሪ እና 20 የተለያዩ የጫማ መስሪያ ማሽኖች ባለቤት የሆነችው ምስጋና፤ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነ ጫማ ፋብሪካ የመገንባት ፍላጎት አላት።
አሁን ላይ በምርቶቿ የተገኘው ወጤት እራሷን እና ቤተሰቦቿን ከመርዳት አልፎ ለበርካታ ሴቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር በመሆኑ የተምሳሌትነት /የሮል ሞዴል/ እና የጠንካራ ሰራተኝነት ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝታበታለች። በሴትነቷ ሳትበገር ሰርታ ማሰራት መቻሏ ደግሞ ለሌሎች እንስቶችም አርዓያ ተግባር መሆኑን መመስከር ይቻላል። የእናት እንክብካቤ የሚሻ አንድ ልጅ ቢኖራትም የእናትነት ተግባሯን ሳታስታጉል በማምረቻ ቦታዋ ደግሞ አጠቃላይ የስራ ሂደቱን በመቆጣጣር ጭምር ጠንካራነቷን እያሳየች ትገኛለች።
የሰው ልጅ ፍላጎቱን መሰረት አድርጎ እራሱን እያስተማረ እና ዕውቀቱን እያሳደገ መስራት ከቻለ መለወጥ ይቻላል የምትለው ወጣት ምስጋና፤ ወጣቱ በትንሽ ገንዘብ ተነስቶ ለበርካቶች ስራ ስለመፍጠር ማሳብ እንደሚያስፈልገው ትናገራለች። ማንም ሰው ገንዘብ ይዞ አልተወለደም፤ በመሆኑም ወጣቱ ሰርቼ ያልፍልኛል ደክሜ ይሳካልኛል የሚል አስተሳሰብ በማኖር ለቀጣዩ ህይወት ስንቅ የሚሆን ስራ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል የሚለው ደግሞ ምክሯ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
ጌትነት ተስፋማርያም