ሀሳብ የሚመጣው በተለያየ አጋጣሚ ነው። ብዙ ጊዜ ግን ዘወትር ከምናሳልፍበት ጊዜ ለየት ያለ ሲሆን ነው። አዕምሯችን ሁሌም ከለመደው ነገር ወጣ ሲል እንደ አዲስ ይሆናል። ለምሳሌ የልቦለድና የግጥም ጸሐፊዎች አዲስ ሀሳብ የሚያገኙት ያልተለመደ ነገር ሲያዩ ነው። ግጥምም ሆነ ሌሎች የስነ ጽሑፍ ውጤቶች ሀሳብ ናቸው። ስነ ጽሑፋዊ ውበቱ ይለያያል እንጂ ማንም ሰው ከዘወትራዊ ነገሮች ወጣ ሲል አዲስ ሀሳብ ይመጣለታል። ለምሳሌ የሀይቅ አካባቢ ይወደዳል፤ የተወደደው አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው ሀይቅ አካባቢ ስላልሆነ ነው። ደመና ሲዳምን የተለየ ስሜት የሚሰማን የበጋ ወቅት አሳልፈን መዳመን ሲጀማምር ሰሞን ነው። ፀሐይ ብርቅ የምትሆንብንና አዲስ ነገር የሚሰማን ሙሉ ክረምት አሳልፈን መስከረም ላይ ፀሐይ ሲሆን ነው። የከተማ ነዋሪ ወደ ገጠር የገጠር ነዋሪ ወደ ከተማ ሄዶ የሚዝናናው ከለመደው ነገር ለመውጣት ነው።
የአንዳንድ ሰዎችን አንባቢነት ለመግለጽ ‹‹እገሌ እኮ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ያነባል›› ሲባል እንሰማለን። ይሄ አድናቆት ትክክል አይመስለኝም። መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማንም ያነባል። እንኳን የማንበብ ሱስ አለበት የሚባል ሰው ማንበብ የማይወድ ሰው መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሊያነብ ይችላል። ምክንያቱም እዚያ ውስጥ የተሰበሰበ ቀልብ ነው ያለው። ቦታውም የሚነበብበት ስላልሆነና የሰው ልጅ ደግሞ ወጣ ያለ ነገር ስለሚያስደስተው ነው እንጂ መጸዳጃ ቤት ለንባብ ምቹ የሚያደርጉት ባህርያት አሉት። አንዱና ዋነኛው ቦታው የጥሞና ጊዜ የሚወሰድበት መሆኑ ነው። ቤተ መጽሐፍ ውስጥ ግን የተለመደ ነው። ወይም ደግሞ ቤት ውስጥ ጠረጴዛ አስቀምጦ ሊያነብ ቢያስብ የተለመደ ነውና ሊሰለቸው ይችላል።
መጸዳጃ ቤት የምናነበው የተረጋጋ ቀልብ ያለን እዚያ ስለሆነ ነው። ሌላ ቦታ ወከባ ነው። ወከባ ሲባል የግድ ጩኸትና ጫጫታ ላይሆን ይችላል፤ ግን ቀልባችን የተበታተነ ነው። እንኳን ሥራ ቦታ ሆነን ምግብ ቤትና መጠጥ ቤት ውስጥ ራሱ ግርግር ነው። መስክ ላይ ወይም ጉዞ ላይ ከሆንን ደግሞ አይናችንና ጆሯችን በሌሎች ሥራዎች ይጠመዳል። እናያለን፣ እንሰማለን፤ ሌሎች ነገሮችን እያየንና እየሰማን ደግሞ ቀልባችን ሥራ ላይ ይሆናል ማለት ነው። በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ በየቦታው ወከባ ነው።
መጸዳጃ ቤት ውስጥ ግን ምንም የሚታይና የሚሰማ ነገር የለም። ለዚህም ነው አዕምሯችንን ሥራ ላለማስፈታት የተገኘውን ነገር የምናነበው። እንዲያውም ከዚህም አልፎ የሚጽፉ ሁሉ አሉ። ምንም እንኳን ድርጊቱ ነውር ቢሆንም የሽንት ቤቶች ግድግዳ ላይ ጽሑፎች ማግኘት የተለመደ ነው። ከዚህም የባሰ ነውር የሚሆነው ደግሞ ግድግዳ ማበላሸቱ ሳያንስ የሚጻፈው ነገር ቃሉ ራሱ ነውር መሆኑ ነው።
ሌላው የጽሑፍ ሀሳብ የሚገኝበት ደግሞ የመኖሪያ ቤት ግድግዳ ነው። ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ማግኘት ባይቻልም በትንንሽ ከተሞችና ገጠር ውስጥ ያሉ ቤቶች ግድግዳቸው ላይ ጥቅስ አይጠፋም። እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሑፎች ቤት ውስጥ ካለ ጋዜጣና መጽሔት የተሻለ የመነበብ ዕድል አላቸው።
ሌላውና ጥቅስ በስፋት የሚታይበት ደግሞ ታክሲ ነው። የታክሲ ውስጥ ጥቅስ አሁን ላይ በሰፊው እየታወቀና እየተለመደ ነው። በተለያዩ ተቋማትና በዩኒቨርሲቲዎችም ጥናት እየተሰራበት ነው። ለጥናት የበቃበት ምክንያት ደግሞ በውስጡ የያዘው ሀሳብ ነው። አብዛኞቹ መዝናኛ ተብለው የሚታለፉ አይደሉም፤ ጥልቅ ሀሳብ ያላቸውና የሚመረመሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ግን ለመዝናኛነት ብቻ ተብለው የሚጻፉም ናቸው። ችግሩ ግን ወደ ስድብ የሚጠጉም አሉ። ለምሳሌ ሴቶችን በተመለከተ በታክሲ ውስጥ ጥቅሶች ላይ በተሰራ ጥናት አንዳንዶቹ ነውር ናቸው። በተለይም አለባበሳቸውን በተመለከተና ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚለጠፉት በሴቶች ላይ የሚፈጥሩት ስነ ልቦና መጥፎ ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ሴቶች ቀን ሲከበር በዚህ ላይ ውይይት ተደርጎ እንደነበር አስታውሳለሁ።
እስኪ አንዳንድ አዝናኝና ቁም ነገር ያላቸውን የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች እንመልከት።
‹‹ነጋ ደግሞ ሰው ፍለጋ›› የሚል ጥቅስ በአንድ ታክሲ ውስጥ አይቻለሁ። ይሄ የሚያመለክተው የራሱ የባለታክሲውንና የረዳቱን ሕይወት ነው። ከነጋ እንቅልፍ አይኖራቸውም፤ ከማንኛውም ሰራተኛ ቀድመው መነሳት አለባቸው፤ ምክንያቱም እነዚህን ሰራተኞች የሚወስዱ እነርሱ ናቸውና። የፈለጉትን ያህል ተኝተው ማርፈድ አይችሉም።
አንዳንዶቹ መልዕክታቸው በጣም ግልጽ ስለሚሆን ብዙም ትኩረት አይስቡም። ለምሳሌ ጠንክረህ ሥራ፣ ታማኝ ሁን.. የሚሉ ጥቅሶች የማንንም ቀልብ አይዙም፤ ምክንያቱም ጠቅላላ እውነታ ናቸው። አንዳንዶቹ ግን በተቃራኒው ይሆኑና የኪነ ጥበብ ባህሪ ይኖራቸዋል። መልዕክታቸውንም በቀጥታ ከመንገር ይልቅ በጥበባዊ ባህሪ በማዋዛት እያሳቁ ያስተምራሉ። ለምሳሌ እግረኞችን ዜብራ ላይ አትቁሙ፤ ቶሎ እለፉ ከማለት ይልቅ እንዲህ የተባለ ጥቅስ ነበር። ‹‹ሟች ከመሞቱ በፊት ዜብራ ላይ ፍቅረኛውን ይስም ነበር›› ይሄን ያነበበ ሁሉ እውነተኛ ታሪክ እንዳልሆነ ያውቃል፤ መልዕክቱ ግን ጥልቅ ነው።
በታክሲ ውስጥ ያሉ ጥቅሶች መልዕክታቸው ዘርፈ ብዙ ነው። ለራሳቸው ለባለታክሲውና ለረዳቱ ሊሆን ይችላል፤ ለተሳፋሪው ሊሆን ይችላል፤ ለአገር መሪዎች ሊሆን ይችላል… በአጠቃላይ በየትኛውም ማህበራዊ ጉዳይ ላይም ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለፈገግታ ብቻም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ እንዲህ የሚል ጥቅስ አለ። ‹‹አንገትህ ቢቆረጥም ዋናው ጤና ነው›› የሰው ልጅ አንገቱ ከተቆረጠ በሕይወት ሊኖር አይችልም።
የአንዳንዶቹ መልዕክት ግልጽ ቢሆንም አገላለጻቸው ደግሞ መልዕክቱን እንድናብሰለስለው ያደርጋል። ስለ ስንፍና ብዙ ተነግሯል፤ በተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥም በብዛት አለ። በታክሲ ውስጥ ጥቅስ ደግሞ ‹‹የሰራ የእጁን፤ የተቀመጠ የቂጡን ያገኛል›› የሚል ነበር። ገና ስናነበው አገላለጹ መቀመጥም የሆነ ጥቅም ያለው ይመስላል፤ ልብ ብለን ስናየው ግን መቀመጥ ምንም አያስገኝም። ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ሌላኛው የታክሲ ጥቅስ ‹‹ከሰራህ ትበላለህ ካልሰራህ ሲበሉ ታያለህ››
‹‹መብትዎን ታክሲ ላይ ትዝ አይበልዎ›› የሚለው ጥቅስ ትክክለኛ መልዕክት ያለው ነው። ይሄ በብዛት ጊዜ ታክሲ ውስጥ ተለጥፎ የምናገኘው ጥቅስ ነው። ሰዎች የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ የሚሆኑት ታክሲ ውስጥ ነው። ምንም እንኳን ረዳቶች ላይ ብዙ መጥፎና ነውር ባህሪ ቢኖርም ተሳፋሪው ላይም የሚታዩ ነገሮች የሚያናድዱ ናቸው። አንዳንዱ ለብር ከሃምሳ መንገድ መቶ ብር ያወጣና ‹‹ዝርዝር የለህም?›› ተብሎ ሲጠየቅ ይደነፋል። አንዳንዱም ነገሩን በትህትና ማድረግ እየተቻለ ገና ከጅምሩ በቁጣ ይጀምራል። መውረድ የማይቻልበት ቦታ ላይ ሆኖም ‹‹ወራጅ›› የሚል አለ።
ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሌላኛው የታክሲ ውስጥ ጥቅስ ደግሞ ‹‹ሽሮና በርበሬ ሲወደድ ችላችሁ ታክሲ ውስጥ ታማርራላችሁ!›› የሚል ነው። ብዙ ዋጋ የሚያወጡት ነገሮች ሲወደድ ዝም ያላችሁትን ለ50 ሳንቲም ትከራካራላችሁ ለማለት ነው።
አንዳንዶቹ ፖለቲካ ናቸው። ልክ እንደ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሁሉ እዚህ ውስጥም ፖለቲካ ይነገራል። ከእነዚህ አንዱ ‹‹መንግስትና ተሳፋሪ ሊወርዱ ሲሉ ነገር ነገር ይላቸዋል›› የሚለው ነው። አምባገነን ሥርዓት ያላቸው አገራት መልካም አስተዳደር የላቸውም፤ አምባገነን መሪዎችም ከሥልጣን የሚወርዱት በህዝብ ቁጣ ነው። የታክሲ ውስጥ ተሳፋሪም እንደዚሁ ነው። ዝም ብሎ የቆየውን ሲወርድ ተሳድቦ ይወርዳል።
በነገራችን ላይ ሴቶችን በተመለከተ የሚጻፉ የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች አሉታዊ ብቻ አይደሉም፤ አወንታዊ መልዕክት ያላቸውና የሴቶችን ጠንካራነት የሚናገሩም ናቸው። ለምሳሌ ‹‹ምከረው ምከረው፤ እምቢ ካለ በሴት አስመክረው›› የሚለው ጥቅስ ነገር ፍለጋ ካላጣመምነው በስተቀር ሴቶችን የሚያደንቅ ነው። እንግዲህ ሴት ተመክሮ ተመክሮ ያልተመለሰን ሰው እንኳን ታሸንፋለች ማለት ነው።
‹‹ጠጋ ጠጋ በሉ በእኛ ታክሲ ተዋውቀው ብዙ ሰዎች ተጋብተዋል›› የምትለዋ ቀልድም ቁም ነገርም የያዘች ናት (ኧረ እንዲያውም ቁም ነገሩ ይበልጣል)። ልብ ብላችሁ ከሆነ ‹‹እንዴት ተዋወቃችሁ›› ሲባሉ ‹‹ታክሲ ውስጥ ነው የተዋወቅን›› የሚሉ ብዙ ባለትዳሮች ናቸው። በሬዲዮ እንግዳ የመሆን ዕድል ያገኙት እንዲህ ሲሉ ከሰማን ቃለ መጠይቅ የመደረግ ዕድል ያላገኙ ደግሞ ብዙ ይኖራሉ ማለት ነው። ታክሲ ውስጥ ነው ስልክሽን የተቀበልኩሽ፣ ታክሲ ውስጥ ነው ያወቅኩሽ ማለትም የተለመደ ነው። ‹‹ጠጋ ጠጋ በሉ የዓባይ ግድብ አለብን›› የምትለዋ ጥቅስም በልማት ስም የራስን ጥቅም ማስገኛ ናት። የጥቅሱ ተደራቢ ትርጉም ባለታክሲው ትርፍ ለመጫን እንዲያመቸው ነው።
አንድ ነገር ማለት አለብን። የታክሲ ውስጥ ጥቅሶችን እኛ እያጣመምን ተደራቢ ትርጉም እንሰጣቸው ይሆናል፤ እነርሱ ግን ይህን ያህል ተመራምረውና አስበውበት ላይሆን ይችላል። ለአንደኛው መልዕክቱ ወይም ለአዝናኝነቱ ብቻ ብለው ሊሆን ስለሚችል ያንንም ታሳቢ እያደረግን።
አንዳንዶቹ ጥቅሶች ከአገራችን ምሳሌያዊ አነጋገሮች የተወሰዱ ናቸው። ይሁን እንጂ ወደ ታክሲ ውስጥ መምጣታቸው ደግሞ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም ምሳሌያዊ አነጋገሮቹ በብዛት የሚነገሩት ገጠር አካባቢ ነው፤ ታክሲ የሚበዛው ግን ከተማ ውስጥ ነው። ስለዚህ ከተማ ውስጥ ለሚኖር መልዕክቱ መድረስ አለበት። በሌላ በኩል ምሳሌያዊ ንግግሮች እየተረሱም ስለሆነ መልዕክታቸው እንዲታወስ ያደርጋል።
ታክሲ ውስጥ ካየኋቸው የምሳሌያዊ አነጋገር ጥቅስ አንዱ ‹‹እግዚአብሔር ድሃን ማስደሰት ሲፈልግ አህያውን አጥፍቶ እንዲያገኘው ያደርጋል›› የሚል ነው። እጃችን ላይ ለረጅም ጊዜ (ምናልባትም ለብዙ ዓመታት) የቆየ ነገር ብዙም ጥቅሙ አይታየንም። አመስግነነው አናውቅም። ሲጠፋ ግን ምድር ይጠበናል። ያ የጠፋው ነገር ሲገኝ ደስታችን ከፍተኛ ይሆናል። ግን እኮ ያው የነበረው ነገር ነው እንጂ የተገኘ ሌላ አዲስ ነገር አልነበረም። አብሮን ሲቆይ ያልተደሰትነውን ጠፍቶ ስናገኛው እንደሰታለን።
‹‹በፍየል ዘመን በግ አትሁን›› የሚለው ምክር በብዙ ታክሲዎች ውስጥ ያየሁት ነው። እንስሳትን ገጸ ባህሪ ማላበስ የተለመደ ነው። በጎች ሞኛሞኝና የዋህ ተደርገው ተስለዋል፤ ፍየል ብልጣብልጥ ናት። የዚህ ጥቅስ መልዕክትም ዘመኑ የብልጠት ነው ለማለት ነው። ሁሉም ብልጥ ሆኗልና ከዘመኑ ጋር መራመድ አለብህ ለማለት ነው።
‹‹ሒሳብ ሳይከፍሉ ሐሳብ አይጀምሩ›› የሚለው ጥቅስ ማስጠንቀቂያም ጭምር ነው። በነገራችን ላይ አስፈላጊ መልዕክትም ነው። ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ሰዎች ታክሲ ውስጥ በሀሳብ ጭልጥ ብለው ይሄዳሉ። ‹‹ሒሳብ›› ሲባሉ አይሰሙም፤ ከጎናቸው ባለ ሰው ተጎስመው ካልሆነ አይነቁም። ለዚህም ነው ረዳቱ ይህን መልዕክት ያስቀመጠው።
ይህኛው ጥቅስ ለሁላችንም ነው። ‹‹ሐበሻ አንድ እግሩን ካልቆረጡለት የሁለተኛው እግሩ ጥቅም አይገባውም›› ብዙ ጊዜ ለአንድ ነገር ጥንቃቄና ክብካቤ የምናደርገው ካጣነው በኋላ ነው። ጤናችንን የምንጠብቅ ከታመምን በኋላ ነው፤ ለብዙ ነገሮች ትኩረት የምንሰጠው የሆነ አደጋ ካጋጠመ በኋላ ነው።
‹‹በጎ አሳቢ ከስድብ ምክር ያወጣል›› የምትለዋ ጥቅስ ትልቅ ፍልስፍና ናት። ከስድብ ራሱ ምክር ማውጣት ይቻላል። ያ የተሰደብነው ስድብ ትክክለኛና የሚመለከተን ከሆነ እንታረምበታለን ማለት ነው። ለምሳሌ የጫማዬ ሽታ የረበሸው ሰው የጫማውን ሽታ የሚገልጽ ነውር ስድብ ቢሰድበኝ ለጊዜው ላፍር እችላለሁ፤ ሁለተኛ ግን አይደገመኝም። እዚህ ጋ ልብ ማለት ያለብን እያወራን ያለነው ስለተሳዳቢው ሳይሆን ስለተሰዳቢው ነው። ተሳዳቢው ነውር ቃላት በመጠቀሙ ራሱም ባለጌ ሊሆን ይችላል፤ ተሰዳቢው ግን አካኪ ዘራፍ ብሎ እልህ ከመጋባት እንደ ምክር ሊጠቀመው ይችላል።
እነዚህ የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች ፍልስፍና ሊባሉ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ሀሳብ ናቸው። በአንድ ቅጽበት የምትወጣ አንዲት ሀሳብ ትልቅ ነገር ትፈጥራለች። እግረ መንገዳቸውንም ሰዎች ዘና እንዲሉ ያደርጋሉ። እርግጥ ነው ታክሲ ውስጥ የገባው ሁሉ ላያየው ይችላል።
ማስተዋል ጥሩ ነውና አካባቢያችንን እናስተውል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
ዋለልኝ አየለ