ሶስቱ ጎረምሶች ጫት እየቃሙ ይመክራሉ። የያዙት ጉዳይ ከሌላው ቀን ጨዋታቸው የተለየ ሆኗል። ከሶስቱ አንደኛው ጉዳዩን በዋነኛነት ይዞ ትዕዛዝና መመሪያ እየሰጠ ነው። ከቀናት በኋላ ሊያደርጉት ባሰ ቡት ዕቅድ ላይ ሀሳብ እየሰጡ መወያየት ከጀመሩ ቆይተዋል። ዕቅዱ ከተሳካ ሁሉም ኑሯቸው እንደሚለወጥ አምነው ያሰቡትን ለመፈጸም ተጣድፈዋል።
ኢብራሂም ታናሽ ወንድሙን በጉዳዩ እንዲሳተፍ ሲጠይቀው ፈቃደኛ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበር። የሚሉት ጉዳይ ከተሳካ በርካታ ገንዘብ ያገኛሉ። ድርጊቱን ከደጋገሙት ደግሞ ቤትና መኪና ይኖራቸዋል። ይህ ምኞ ት ዕንቅልፍ የነሳቸው ሶስቱ ሰዎች በጉዳዩ እየመከሩ ስልትን ከቦታ ያማርጣሉ።
የኢብራሂም ወንድም ሁሴን እስከዛሬ አያቶቹ ቤት ይኖር ስለነበር የሰማውን አዲስ ሃሳብ ለመቀበል አላንገራገረም። ከዚህ በኋላ እነሱን ማስቸገር እንደሌለበት አምኖ ወንድሙ በሚለው ነገር ሁሉ ለመስማማት ተዘጋጅቷል። ነገ በሚፈስለት የሀብት ሲሳይም አያቶቹን መጦር እንደሚችል እያለመ ነው።
ኢብራሂም መኪኖች እየተሰረቁ እንደሚ በለቱ ያውቃል። በዚህ ሽያጭም በርካቶች ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደያዙ መረጃው አለው። ሁሌም ኑሮው ፈቅ ያለማለቱን ባሰበ ጊዜ እንደሌሎች በዚህ ድርጊት መሳተፍን ሲሻው ኖሯል። ከትውልድ አገሩ ርቆ አዲስ አበባ ከከተመ ወዲህም የእሱን ኑሮና የበርካቶችን ህይወት አነጻጽሮ ጸጉሩን በንዴት ነጭቷል። ከንፈሩን በቁጭት ነክሷል።
ከአሁን በኋላ ይህ ዓይነቱ ምራቅ መዋጥ እንደማይኖር በገባው ጊዜ ደግሞ ለሀሳቡ ስኬት ሁለቱን አማክሮ ዕቅዱን ነደፈ። አጋሮቹ ውጥኑን ሲሰሙ ለስርቆት ይሆናሉ ያሏቸውን መኪኖች ለይተው ለምርጫ አቀረቡለት። ከቀረቡት መኪኖች መካከል ሚዛን የደፋው ደግሞ የሚኒባስ ታክሲ ሆነ።
ኢብራሂም ለዓመታት የታክሲ ሾፌርና ረዳት ሆኖ ሰርቷል። አሁን ደግሞ የራሱ ታክሲ የሚገዛበት በቂ ገንዘብ እንዲኖረው ይፈልጋል። ኑሮን ለማሸነፍ ከዚህ በፊት በቀን ሥራና በሌሎች አድካሚ ውሎዎች ያሳለፋቸውን ጊዜያቶችም አሁን ላይ መድገምን አይሻም።
የሚፈለገው የመኪና አይነት ከታወቀ በኋላ እየተጣደፈ ለአንድ ሰው ፈጥኖ ስልክ ደወለ። ሰውዬው ሶማሌ ተራ አካባቢ የተሰረቁ መኪኖችን እየበለተ በመሸጥ ይታወቃል። ኢብራሂም ይህን አሳምሮ ስለሚያውቅ ቀደም ሲል ስለመኪና ሽያጭ ያማከረውን አስታውሶ በድጋሚ ሃሳቡን አነሳለት። ሰውዬው ጉዳዩን ሲሰማ በደስታ ተፍለቀለቀ። መኪናውን ባሻው ጊዜ ካመጣለትም ያለማወላወል እንደሚረከበው ቃል ገባለት።
ኢብራሂም የምስራቹን ለአጋሮቹ ለማካፈል አልዘገየም። የሰማውን ሁሉ አንድም ሳያስቀር ዘረዘረላቸው። ጥቂት ቆይ ቶ በጋራ ማድረግ ስለሚገባቸው ቀጣይ ዕቅድ በትኩረት መከሩ። ምክክራቸውን እንዳ ጠናቀቁ በሁሉም ፊት ላይ ሞቅ ያለ ፈገግታ ተነበበ። በዕለቱ ቦታ ወስነው፣ ሰዓት ለይተው ወዳሰቡት ስፍራ ሲንቀሳቀሱ ጊዜው ለዓይን መያዝና መጨለም ይዞ ነበር።
ነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓም
ቀኑን ሙሉ ሲጥል የዋለው ዝናብ አመሻሹንም በርትቶ ቀጥሏል። ቅዝቃዜው ከመንገዱ ጭቃ ጋር ተዳምሮ አላላውስ ያላቸው መንገደኞች በላያቸው የሚወርደውን ካፊያ ለማምለጥ በዣንጥላና በዝናብ ልብስ ተከልለው እየተጓዙ ነው። ሰዓቱ ገና የሚባል ቢሆንም የክረምቱ ባህርይ ያለጊዜው እንዲጨልም አስገድዶታል።
ኮልፌ ቀራንዮ በተለምዶ ‹‹ወይራ›› ሰፈር በተባለው አካባቢ ያሉ ባለታክሲዎች እንደወትሮው ደንበኞቻቸውን ሲያመላልሱ ውለዋል። ከአውጉስታ ማዞሪያ እስከ ቤቴል ሆስፒታል ያለው መንገድ ተሳፋሪዎች ስለሚበዙበት ሁሌም ግፊያና ትርምስን ማስተናገድ ልማዱ ነው። በተለይ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ችግሩ ጎልቶ ይስተዋላል።
የታክሲ ሾፌሩ ኤፍሬም ተሾመና ትንሹ ረዳት ሰለሞን አድነው ከጠዋት እስከማታ አብረው ይውላሉ። ግንኙነታቸው የታላቅና ታናሽ ወንድም አይነት ነው። ሁሌም ማለዳ ለሥራ ሲሰማሩ ደንበኞቻቸውን በወጉ ተቀብለው በማስተናገድ ይጀምራሉ። ኤፍሬም መልካም ሥነምግባር ያለው ወጣት ነው። ብዙዎች ስለ ማንነቱ ሲናገሩ በጎ ባህሪውን አጉልተው ነው።
የታክሲ ረዳቱ ተሾመ አስራ አራተኛ ዓመቱን የደፈነው በቅርቡ ነው። ከትውልድ ሀገሩ አዲስ አበባ የመጣው ከቤተሰቦቹ ተደብቆና ጠፍቶ ነበር። ከተማ ከገባ በኋላ ግን የአቅሙን እየሰራ ትምህርቱን መማር ቀጠለ ። ስድስተኛን አልፎ ሰባተኛ ክፍል ሲደርስም የነገውን መልካምነት እያሰበ በተስፋ መራመድ ጀመረ።
ትንሹ ልጅ ከብዙዎች ለመግባባት ጊዜ አይወስድበትም። ያዩትና በቅርብ የሚያው ቁትም ልጅነቱን እያስተዋሉ በቅ ልጥፍናው ይገረማሉ። በተለይ ከተማ እየሰራና እየተማረ ገጠር ለሚገኙ ቤተሰቦቹ የሚያደርገው እገዛ የ‹‹እደግ ተመንደግ›› ምርቃትን አስገኝቶለታል።
ምሽት 2፡00 ሰዓት
ቀኑን ሙሉ በሥራ ላይ የዋሉት ኤፍሬምና ተሾመ በጊዜ ገብተው ለማረፍ አስበዋል። የቀኑ ዝናብ መሆንና የተሳፋሪው መበራከት ግን እንዳሰቡት ለማድረግ አላስቻላቸውም። ከወይራ ሰፈር ቤቴል የመጨረሻዎቹን ተሳፋሪዎች ይዘው ሲጓዙ ስለነገው ውሏቸው አንስተው በጠዋት ለመገናኘት ተቃጥረዋል።
ኤፍሬም ተሳፋሪዎቹን አራግፎ ታክሲ ውን ወደሰፈሩ አቅጣጫ ማዞር ሲጀ ምር ከመኪናው ግንባር ቆመው እጃቸውን ለል መና ከዘረጉ ሶስት ሰዎች ጋር ተፋጠጠ። ሰዎቹ እያለቀሱ መሆኑ ሲገባው ሩህሩህ አንጀቱ አላስችል አለውና መኪናውን ቀጥ አድርጎ አቆመ። ወዲያው መስኮቱን ከፍቶም ሰዎቹን ማነጋገር ጀመረ።
ከሶስቱ አንደኛው በጉንጮቹ የሚወርድ ዕንባውን እየጠረገ ጉዳዩን ማስረዳት ያዘ። ሌሎቹም ከጎኑ ቆመው በሀዘን የተከፋ ፊታቸውን አስነበቡ። ኢብራሂምና ሁለቱ አጋሮቹ የመጡበትን ጠንቅቀው ያውቃሉና ጉዳዩን ተራ በተራ እያስረዱ ነው። በዚህ ስፍራ ድንገት መገኘታቸው የወንድማቸውን ሚስት መታመም ሰምተውና የታማሚዋን ህይወት ለማትረፍ እንደሆነም ማብራራት ጀምረዋል።
ሆስፒታል ለማድረስ መኪና እየፈለጉ መሆኑንና ከእነሱ ጋር የመገናኘታቸውን አጋጣሚ በበጎ እንደቆጠሩት ሲናገሩ በሁ ሉም ገጽታ ላይ ደማቅ ፈገግታ ይነበብ ነበር። ኤፍሬም ንግግራቸውን ተከትሎ ምን ልርዳችሁ ሲል ጠየቀ። እነሱም በአንድ ድምጽ ታማሚዋን ወደሆስፒታል እንዲያ ደርስላቸውና ለአገልግሎቱም የሚገባ ውን ያህል እንደሚከፍሉት አሳወቁት።
ኤፍሬም ወደሰፈሩ አቅጣጫ የዞረውን ታክሲ መልሶ ውጭ የቆሙትን ሰዎች ለማሳፈር ፈቀደ። ትንሹ ረዳት ተሾመ ደግሞ በሩን አንሸራቶ በመክፈት ተሳፋሪዎቹን ቦታ አስይዞ ለጉዞ ተዘጋጀ። ኢብራሂም የታክሲውን በር ከፈተና ከሾፌሩ ጎን ተቀመጠ። ሁለቱ ደግሞ ከረዳቱ ጋር ከኋላ ተቀምጠው ጨዋታ ቢጤ ጀመሩ።
ሞተሩ ተነስቶ ጉዞው እንደቀጠለ ታማሚዋ በቅርብ ትገኝበታለች ወደተባለው ሰፈር ለማቅናት ጋቢና የተቀመጠው ኢብራሂም መንገድ ማመላከት ጀመረ። የኋለኞቹም ለጉዳዩ የቸኮሉ በማስመሰል ጭንቀ ታቸውን አሰሙ። ታክሲው ከአስፓልቱ እንደወጣ ቤቴል ሆስፒታል ጀርባ ወዳሉት መንደሮች እንዲያመራ ምልክት ተሰጠው።
ኤፍሬም ተሳፋሪዎቹ የነገሩትን ምልክት ይዞ ወደ ኩርባው ታጠፈ። አካባቢው ጨልሟል። ጭርታ ውጦታል። ሲጥል የዋለው ዝናብም ስፍራውን በጭቃ ለውሶ በእግር ለመራመድ ያዳግታል። ወደ ጨለማው እየገቡ ሳለ የኋለኞቹ ሁለት ሰዎች የተለየ እንቅስቃሴ አሰሙ። ወዲያው ከፊት የተቀመጠው ኢብራሂም በእጁ ምልክት ሲያሳያቸው ያዘጋጁትን የፍራሽ ማሰሪያ ገመድ አንስተው ወደሾፌሩ ተጠጉ።
የሚሆነው ሁሉ ያልገባው ኤፍሬም በድንጋጤ ዞር ከማለቱ ገመድ በአንገቱ ጠልቆ ለሁለት እየታገሉት መሆኑን አወቀ። እንዲተውት እየተማጸነ ራሱን ለማዳን ሲፍጨረጨር ትንሹ ረዳት ተሾመ እያለቀሰና እየጮኸ እንዲተዋቸው ለመነ። ሰሚ ጆሮ አልነበረም። በኤፍሬምና በሶስቱ ሰዎች መሀል ያለው ትግል ቀጠለ።
በጨለማውና ጭር ባለው መንደር ከታክሲው ጣራ ስር የተፈጠረውን እውነት የታዘበ አልነበረም። በአንገቱ ላይ ጠብቆ የታሰረውን ገመድ ታግሎ ለማስጣል የሞከ ረው ኤፍሬም የሶስት ጎረምሶችን ጡንቻ መቋቋም ሳይሆንለት ቀርቶ ትንፋሹ ተቋረጠ። ይህን ያረጋገጠው ኢብራሂም አስከሬኑን ከአጋሮቹ ጋር ተሸክሞ ወደ ኋላ ወንበር ጣለና ጋቢናውን ለቆ የሾፌሩን ቦታ ተረከበ ።
የመኪናውን የሞተር ቁልፍ በፍጥነት አስነስቶ እንቅስቃሴውን ከመጀመሩ በፊት በታክሲው ውስጥ ስለተገኙ ንብረቶች ጠየቀ። ከረዳቱ ኪስ የነበረ ጥቂት ገንዘብና በብር ላስቲክ የታሰረ አሮጌ ሞባይል ስለመኖሩ አሳወቁት።
ኢብራሂም ታክሲውን ካቆመበት አስነስቶ ከጨለማው መንገድ እየወጣ ቀጣዩን ዕቅድ አማከራቸው። የራሳቸውን ሀሳብ ከመሰንዘራቸው በፊትም በአይምሮው የመጣለትን አጋራቸውና በሀሳቡ ተስማምተው ጉዞውን ቀጠሉ።
ጥቂት አለፍ እንዳሉ ትንሹ ረዳት ተሾመ ትውስ አላቸው። ያሰቡትን ለመፈጸም ምንም አይነት እማኝ እንደማያስፈልግ ያውቃሉ። እሱን አዝነው ቢተውት ደግሞ እንደሚያጋልጣቸው እርግጠኞች ሆነዋል። ይህን እየተነጋገሩ ዞር ሲሉ ተሾመን እያለቀሰ ተመለከቱት። ሀሳባቸው የገባው ይመስል ያደረጉትን ለማንም እንደማይናገርና እሱን እንዲምሩት በጭንቀት ለመናቸው። ቤተሰ ቦቹ እንደናፈቁትና እነሱም ሊያዩት እንደጓጉ ለመስቀልም አገሩ ለመሄድ እንዳሰበ ጭምር እያስተዛዘነ በልጅነት አንደበቱ ተማጸናቸው።
ይህን ሁሉ ልመና የሰሙት ሶስቱ ሰዎች እንባው ተዝረክርኮ በብርክ የተያዘው ህጻን ተማጽኖን ከምንም አልቆጠሩም። እሱንም እንደሾፌሩ በማሰናበት ያሰቡትን ለመፈጸም መፍጠን እንዳለባቸው በመስማማት ሌላ ገመድ አነሱ። አፍታ ሳይቆዩም ገመዱን በህጻኑ አንገት ሸምቅቀው ጸጥ አደረጉት ። ተሾመ እነሱን የሚታደግ አቅምና ጉልበት ስለሌለው ሊታገላቸው አልቻለምና ግድያው ቀላል ሆነላቸው።
ጉዞ ወደ ገፈርሳ
ሶስቱ ህልመኞች ያሰቡትን ለማሳካት ትልቁን መንገድ እንደተሻገሩት አምነዋል። ታክሲው በእጃቸው በመሆኑ ደስታቸው ወሰን አጥቶ የነገውን ማለም ጀምረዋል። ሁለቱን አስከሬን ይዘው የሚጥሉበትን ሲነጋገሩ የገፈርሳ ግድብ ምርጫቸው ነበር። በኢብራሂም አሽከርካሪነት ከስፍራው ሲደ ርሱም የሰዓቱ መጨለም አመችቷቸው ያሰቡትን ለማድረግ ቀላል ሆኖላቸዋል።
አሁን ሁለቱን ሟቾች ከግድቡ ጥልቅ ባሀር በድልድዩ በኩል ወርውረው ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ነው። ከዛሬ በኋላ በርካታ ሥራዎች ስለሚኖራቸውም የድርሻቸውን ከወዲሁ ተከፋፍለዋል። አዲስ አበባ ሲደርሱ ሰዓቱ ገፍቶ ነበር። ኢብራሂም ግን ለመኪና አራጁ ጓደኛው በእጁ ያለውን ሲሳይ ሳይናገር ማደር አልሆነለትም። መኪናውን እያመጣው ስለመሆኑ አሳወቀው። ጓደኛው አሁንም ሊቀ በለው ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ ስልኩን ዘጋ።
ኢብራሂም ሸጎሌ አካባቢ ሲደርስ ሁለቱን ከመንገድ አውርዶ ወደ አንድ መንደር ዘለቀ። ወዲያውም ከሚፈልገው ሰው ተገናኝቶ መኪናውን አሳየው። ሰውዬው በማግስቱ ገንዘቡን ከባንክ አውጥቶ እንደሚሰጠው ነግሮትም ተሰነባበቱ።
ሲነጋ ኢብራሂም የተባለውን አስታውሶ ወደባልንጀራው ስልክ ደወለ። እንዳሰበው ግን ስልኩ በፍጥነት አልተነሳም። አሁንም ደጋግሞ ሞከረ። ለውጥ አልነበረም። ጥቂት ቆይቶ ሲደውል የስልኩን የመጥፋት ምልክት አሰማው። ቀኑን ሙሉ ሲደውል ቢውል ምላሽ ያጣው ኢብራሂም ሲመሻሽ መኪናውን ካቆመበት ጋራዥ አውጥቶ በተለያዩ ስፍራዎች ሲያቆመው ከረመ። ስልኩን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየሞከረም በተስፋ ሲጠባበቅ ቆየ።
ኢብራሂምና አጋሮቹ ያሰቡት ዕቅድ አንዳችም ሳይሳካ ሶስት ቀናት ተቆጠሩ። ታክሲዋ በተባለው መልኩ ተበልታ ካልተ ሸጠች ችግሩ የከፋ እንደሚሆን የገባው ኢብራሂም አንድ ቀን ከነበረችበት ጋራዥ አውጥቶ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ጉራራ ወደተባለ አካባቢ ወስዶ አቆማት።
ባልተለመደ መልኩ በስፍራው ቀናትን ያስቆጠረችው ኮድ3 53978 አአ የሆነች ታክሲ የአካባቢውን ሰዎች ትኩረት ስትስብ ሰነበተች። ብዙዎችም በተለየ ጥርጣሬ እያስተዋሉ በዓይነ ቁራኛ ሲቃኟት ከረሙ። አንድ ቀን ምሽት ግን እነ ኢብራሂም መኪናውን ወዳቆሙበት ስፍራ ሲሄዱ ከሰዎች አይን ገቡ። ሁኔታቸውን የተጠራጠሩም ማንነታቸውን ጠየቁ። ወዲያው የአካባቢው ፖሊስ ደርሶ ኢብራሂምን በቁጥጥር ስር አዋለው።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪውን ይዞ በጥያቄ አፋጠጠ። ኢብራሂም በአካባቢው ለግል ጉዳዩ በመምጣቱ ከመኪናው ባለቤት ሸሽጎ ያቆማት መሆኑን ተናገረ። ፖሊስ ቤተሰቦች ስለልጆቻቸው መጥፋት ያመለከቱትን አስታ ውሶም ባለቤቱን እንዲያቀርብ ጠየቀ። የመጣ ሰው አልነበረም። ከጥቆማው አካባቢ በተገኘ መረጃ ከድርጊቱ ጋር የሚገናኝ ፍንጭ በመገኘቱ ምርመራው ተጠናከረ። በመጨረሻ ኢብራሂም ያደረገውን መካድ አልሆነለትምና የሆነውን ሁሉ ተናገረ።
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 285/08 የተያዘው መረጃ በመርማሪ ዋናሳጂን መንግስቱ ታደሰ እየተመራ ምርመራው ቀጥሏል ። እነኢብራሂም ሟቾቹን የጣሉበት የገፈርሳ ግድብ በመታወቁም አስከሬናቸውን ለማውጣት አሰሳው ቀጥሏል። ፍለጋው ግን በዋዛ የሚጠናቀቅ አልሆነም። በተለመደው መልኩ ፈልጎ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ ከ20 ቀናት በላይ የፈጀ ፈታኝ ጥረት ተደርጎ በመጨረሻ የሟቾቹን አስከሬን ለማግኘት ተቻለ።
ውሳኔ
ከፖሊስ በምርመራ ተጣርቶ በአቃቤ ህግ ከሳሽነት መዝገቡ የደረሰው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሾቹን ጉዳይ መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ ከአንድ እስከ ሶስት ስማቸው የተጠቀሰው ተከሻሾች የፈጸሙት ድርጊት ነውረኛና ከባድ ነፍስ የማጥፋት ወንጀል መሆኑን ጠቅሶም ጥፋተኝነታቸውን አረጋግጧል። በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ኢብራሂም መሀመድ የዕድሜ ልክ እስራት ሁለተኛና ሶስተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው የ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲበየንባቸው ወስኖ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
መልካምስራ አፈወርቅ