ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር « …ኢትዮጵያ መሐፀነ ለምለም ናት። … “ በማለት አገራችን በታሪኳ ከገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በክብር አቅፈው ደግፈው የሚታደጓት የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳሏት መናገራቸው ይታወሳል።
ዛሬም ልጆቿ በማንነት እና በሴራ ኀልዮት የተነሳ ተቃቅረው አይንህን ለአፈር በተባባሉበት፤ አይንና አፍንጫ በሆኑበት፤ ሀገር ፅንፍ በወጡ ሐሳቦች እየተላጋች መንታ መንገድ ላይ ቆማ እያለ የሚያሻግር ሐሳብ ያላቸው ልጆቿ ደርሰውላታል።
ድፎ ባልቆርስም እኔ “ ቲም ንጉሱ “ ብያቸዋለሁ። በአስተባባሪያቸው አቶ ንጉሱ አክሊሉ ስም። አቶ ንጉሱ የኢኒሽየቲቩ ጠንሳሽና ዋና አስተባባሪ በሙያቸውም ታዋቂ ማህበራዊ ተሟጋችና የግሎባል ገቨርናንስ ባለሙያ ናቸው። የቀረቱ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቭ አባላት እውቅና ስለሚገባቸው ስማቸውን እንደሚከተለው ዘርዝሬአለሁ። ወንድወሰን ስንታየሁ የኢኒሽየቲቩ ምክትል አስተባባሪ፣ መስፍን ጌታቸው የኢኒሽየቲቩ ምክትል አስተባባሪ፣ እንዳልካቸው ስሜ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል፣ ማህሌት ተሾመ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል፣ ሙሉጌታ መንግሥት የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል፣ ብሌን ፍፁም የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል፣ ያስሚን አብዱልዋሴ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል፣ ሞነኑስ ሁንደራ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪ ቡድን አባል እና ማእረጉ ሀብተማርያም (የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር) ናቸው ። እናመሰግናለን።
ዛሬ በሀገራችን የተፈጠረውን ንቃቃት በመጠቀም የፖለቲካ ነጋዴዎች ሌት ተቀን ግጭት፣ ቀውስና ሴራ እየቀፈቀፉ እስፖንሰር እያደረጉ በድሀ ልጅ ደም ሸቅጦ ለማትረፍ ደፋ ቀና በሚሉበት ሰዓት” ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቮች “ ደግሞ ሀገራችንን ከጥፋት ለመታደግ ሐሳብ በማፍለቅ ተስፋችንን እንደገና አለምልመዋል። የተሰበረውን ቅስማችንን ሊጠግኑ አሐዱ ብለዋል።
ጠቢቡ ሰለሞን ቤተክርስቲያንን እና ፈጣሪን በለሆሳስ በሚሰማ መዝሙር እንዳመሰገነው እኔም እነ “ ቲም ንጉሱ “ን ፣ 50ዎቹን ንጋቶች እና የሰላም ሚኒስቴርን ለማመስገንና እገረ መንገዴን ከአንባቢያን ጋር ለማስተዋወቅ የመጣጥፌን ርዕስ “ መኀልዬ መኀልዬ ዘዴስቲ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቭ“ ብየዋለሁ።
በተከታታይ መጣጥፎቼ አበርክቶአቸውን ይዤ የምመለስ ሲሆነ ለዛሬ ዴስቲኒዎችን እና ንዑድ ሐሳባቸውን በወፍ በረር አስተዋውቃለሁ ።
ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቭ አገራችን ለምትገኝበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መፍትሄ ለማቅረብ የተጠነሰሰ አገር በቀል እንቅስቃሴ ነው። የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች (Core Team) ዘጠኙ ያገባኛል ብለው የተነሱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እነዚህም ልዩ ልዩ ብሔሮችን፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን፣ እምነትንና የሙያ ስብጥርን ይወክላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በመሥራት ላይ የሚገኘው ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ የተሰኘውና መቀመጫውን በካናዳ ያደረገው ዓለም አቀፍ ተቋም በገዥውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ እንደገለልተኛ አካል ስለሚቆጠር ተቋሙ ኢኒሽየቲቩን በፕሮጀክትነት እንዲይዘው ተመርጧል።
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ቡድን የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመፈተሽ አገራችን ካለችበት ቅርቃር ልትወጣ የምትችልባቸውን አማራጮች ሲያፈላልግ ቆይቷል። ፈተናውን ከወደቁ አገራት ተሞክሮ ማግኘት እንደሚቻል የማይካድ ቢሆንም፣ መሠል የፖለቲካ አጣብቂኝን በስኬት ጠርምሰው ካለፉት አገራት ግን የተሻለ ገንቢ ትምህርት ማግኘት እንደሚቻል የቡድኑ ጽኑ አቋም ሆኖ ቆይቷል። የደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያና መሠል አገራት ልምድ እንደሚያሳየው መጪው ዘመን ላይ ልዩ ትኩረት ያደረጉ ወሳኝ አካላት ተቀራርበው በመጪው ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲመክሩ የሚያግዙ አሠራሮች አገሮቹን ከአጣብቂኙ ለማሾለክ ከማስቻላቸውም በላይ ለሌሎች የሠላም እና የዕርቅ ጥረቶች ዕገዛ አስተዋጾ ማድረግ እንደቻሉ ታሪክ ይመሰክራል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ እ.ኤ.አ. በ1991 ደቡብ አፍሪካ ረዥም ዘመን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቀውሷን ለመፍታት በተቸገረችበት ወቅት እንደ አንድ የብሔራዊ ሠላም ግንባታ መሣሪያ ተደርጎ ተግባራዊ የተደረገው የትራንስፎርሜሽን ሴናሪዮ ዕቅድ ነበር። በጊዜው በሁለት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ጠንሳሽነት በቁጥር ወደ 30 የሚጠጉ ተጽዕኖ አምጪ እና ገዥ አመለካከትን የሚወክሉ ሰዎች ከመላው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ መስኮች በጥንቃቄ ተመርጠው በደቡብ አፍሪካ ሊከሰቱ የሚችሉ መፃኢ ዕድሎችን (scenarios) እንዲቀርፁ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ተደረገ።
ከገዥው ፓርቲ፣ ከተፎካካሪዎች (ለምሳሌ – የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ወይም ኤ.ኤን.ሲ. ፓርቲ፣ ፓን አፍሪካን ኮንግረስ እና መሰል ፓርቲዎች) እና ከሌሎች መስኮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተቀራርበው በሂደቱ ተሳታፊ በመሆን ሴናሪዮዎቹን በጋራ ቀረፁ። ሂደቱም በተሳታፊዎች መካከል ወዳጅነትን፣ ቅብብሎሽንና መተማመንን እንዲፈጥሩ አዲስ መንገድን ጠርጎላቸው ነበር። በተጨማሪም ይህ ሂደት እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በአቋሙ ላይ ክለሳ እንዲያደርግና አገሪቱ የምትገኝበትን የከፋ የፖለቲካ ቀውስ አስተውሎ በሰላም የምታልፍበትን የጋራ ውሳኔ እንዲያሳልፍ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ይህንን ሂደት አስመልክቶ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ይህ ሂደት ተሳታፊዎቹ በግላቸው ከፍ ሲልም በአገር ደረጃ የነበራቸውን አልሸነፍ ባይነት እና ግትርነት እንዲተውና ሽግግር እንዲያደርጉ በማገዝ ደቡብ አፍሪካ ደጃፍ ላይ ቆመው የነበሩ ብጥብጦችና የመበታተን አደጋዎች በመጡበት እግራቸው እንዲመለሱ በማድረግ አገሪቱ ወደቀጣዩ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ይህ ተሞክሮ ላይ በመመርኮዝ ይህ ልምድ እንደ ኮሎምቢያ፣ ጓቲማላ፣ ታይላንድ፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች አገሮች ተወስዶ ጥቅም ላይ ውሏል።
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ የዚህ ዘዴ ጠንሳሽ እና በደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች አገሮች ሂደቱን በማስተባበር የተሳተፈውን ሪዮስ ፓርትነርስ የተባለውን ድርጅት ዋነኛ መስራች አዳም ካህንን በማግኘት፣ በተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ በመምከር ለበርካታ ዓመታት ዕቅድ ሲያቅድ እና የሌሎች አገራትን ልምድ ሲያሰባስብ ቆይቷል። ከዚያም ከሌሎች የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች ጋር በመመካከር ሐሳቡን በኢትዮጵያ የመተግበር ዕቅድ ተያዘ። አስተባባሪ ቡድኑ አስቀድሞ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የፖለቲካ አመለካከቶችን እና ክልሎችን የሚወክሉ ቁልፍ ተጽዕኖ አምጪ ሰዎች ለመለየት እንዲቻል ሁሉን አካታች የሆነ የመመዘኛ ማዕቀፍ (multi-criteria assessment framework) ቀርጿል።
ይህ ቡድን የሚመለምላቸውን የሴናሪዮ ቡድን አባላት አመራረጥ ተአማኒነት ለማጉላት ደግሞ የፆታ፣ የዕድሜ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ እና የሙያ ስብጥርን የመሳሰሉ ሚዛን ማስጠበቂያዎችን (sensitivity markers) ተጠቅሟል። በእነዚህ መሥፈርቶች በመጠቀም በአመለካከት ደረጃ የአሁኗ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ይወክላሉ ብሎ ያሰባቸውን ወደ 50 ገደማ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን (ሁለት የዳያስፖራ አባላትን ጨምሮ) መልምሏል። ኢኒሽየቲቩን ለመጀመር የመንግሥት እውቅና ያስፈልግ ስለነበር ከሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው አካላት ዘንድ ቀርቦ በመወያየት ይሁንታንና ድጋፍን አግኝቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን፣ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ኃላፊዎች ጋር ቀርቦ ስለ ሂደቱ በማስረዳት ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን አረጋግጧል። በዚሁ መንፈስ የሂደቱ አስተባባሪዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችን በማነጋገር ድጋፍ አሰባስበዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ታዋቂ የመገናኛ ብዙኃን፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና የሲቪክ ማሕበረሰብ ወኪሎችንና ምሁራንን ቀርቦ በማነጋገር በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓል።
የአስተባባሪ ቡድኑ የሚመራበትን የሥነ ምግባር ደንብ በጋራ የወሰነ ሲሆን ገለልተኝነት ዋና የሥራችን መርህ ሆኖ እንዲቀመጥ ተስማምቷል። ኢኒሽየቲቩ ገለልተኛ እና አካታች ሲሆን አብዛኛውን ፖለቲካዊና ፖለቲካዊ ያልሆነውን አመለካከት የሚወክሉ፣ ያገባኛል የሚሉና ተጽዕኖ አምጪ የሆኑ ሰዎች በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተለያዩ ሴናሪዮዎች እንዲቀርፁ ማስቻል ነው። ምንም እንኳን ለድርድር እና ለእርቅ ሂደቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ሊኖረው ቢችልም ሂደቱ ድርድርም፣ እርቅም አይደለም። ዋነኛ ግቡም የተለያየ አመለካከት ባላቸው መሪዎች ዘንድ የወንድማማችነት መቀራረብ፣ መግባባት እና መተማመንን ለማበረታታት እና ቢቻል ደግሞ ብዙሃን የሚስማሙበት ርዕይ በመቅረጽ ዘላቂ ሰላም እና ዋስትና በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።
ሂደቱ ሦስት ምዕራፎችን አልፏል፤ እነዚህም
1) ለሴናሪዮ ቀረፃው አባላትን መመልመል፣
2) ሴናሪዮዎቹየሚቀረፁባቸውን ሦስት ለሕዝብ
ክፍት ያልሆኑ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ፣ እና
3) ውጤቱን ለሕዝብ ማሰራጨት ናቸው። ሦስቱ የሴናሪዮ ቡድን የምክክር መድረኮች ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት በአርባ ምንጭና በቢሾፍቱ ከተሞች በዝግ ተካሂደዋል ። በሁሉም መድረኮች የሴናሪዮ ቡድን አባላቱ በሚገባ ተሳትፈዋል። በእነዚህ መድረኮች ላይ የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮንን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ፣ እና የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሤ አስተያየቶቻቸውን በመለገስ ተሳትፈዋል። እንዲሁም በሴናሪዮ ቡድኑ ጥያቄ መሠረት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ምጣኔ ሀብት፣ ሕገ መንግሥታዊና የፌዴራል ሥርዓት፣ በሥነ ሕዝብ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ሊሰጡ የሚችሉ ምሁራን ተጋብዘው መረጃ እንዲሰጡ ተደርጓል።
ከዚህ ረጅም ውይይት እና ክርክር በኋላ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚውክሉ እነዚህ 50 የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት በ2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ምን አይነት መልክ ሊኖራት እንደሚችል የሚተነትኑ አራት አማራጭ ሴናሪዮዎችን በስምምነት ቀርፀው በሪፖርት መልክ አቅርበዋል።
እያንዳንዱ ሴናሪዮ እንደ አገር ምን አይነት ጉዞ ብንከተል ወደ የት ልናመራ እንደምንችል ያመላክታል፤ የእያንዳንዱ የጉዞ መስመር መጨረሻም ምን እንደሆነ በገልፅ ያሳያል። በዚህ ሂደት አጠቃላይ ጉዞ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች ሚና ሂደቱን ማቀላጠፍ እና ከጀርባ ሆኖ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ብቻ የተገደበ እንደነበረ፣ እያንዳንዱ የሴናርዮ ቡድን አባል ይወክለዋል ተብሎ የሚታሰበውን የማህበረሰብ ክፍል መድረስን ዋነኛ ኢላማ ያደረገና በዓይነቱ ለየት ያለ አቀራረብ ያለው የሥርጭት ስልት ከቡድኑ አባላት ጋር በመመካከር ተነድፏል። በዚህም የሥርጭት ሂደት የሴናሪዮ ቡድን አባላት እንደሚያመቻቸው ተቀናጅተው ይሠራሉ። ከሌሎች አገሮች እንደተማርነው የሴናርዮ ቀረፃው ሂደት የሴናሪዮ ቡድን አባላትን አስተሳሰብ በመቅረፅና እርስ በራሳቸው ያላቸውን መተማመን በማጠናከር አዎንታዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
በተጨማሪም በመጪው ሕዝባዊ ምርጫና እርቅ ሂደቶች ላይ አዎንታዊ አሻራ ለማኖር ቡድኑ ከብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን እና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመምከር ላይ ይገኛል።
እንደ መውጫ
ከሳምንታት በፊት በአዲስ ዘመን እና በሪፖርተር ጋዜጦች በተከታታይ ለአንባቢ ባደረስኳቸው መጣጥፎች በሰከነ አዕምሮ ቁጭ ብሎ በጥሞና ስለመመካከር እና ማንሰላሰል አስፈላጊነት የሚከተለውን ብዬ ነበር ። “… በሰው ልጅ ታሪክ ፅንፈኝነት፣ ዋልታ ረገጥነትና አክራሪነት በጊዜአዊነት የሚጠቅመው ጥቂት ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን እንጂ አገርንና ሕዝብን አይደለም። አገርን የሚጠቅመው በጥሞና በእርጋታ መመካከር ማንሰላሰል ነው። ዜጎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ማንኛውንም ልዩነት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት ይችላሉ ። …”
ዛሬ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ እና ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ይህን ሐሳብ እውን አድርገውታል። ኢህአዴግ፣ ኦነግ፣ ኢዜማ፣ አብን፣ ኦብነግ፣ ወዘተ . በአንድ ጣራ ሥር መክረው ዘክረው “የምንመኛት ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም“ ራዕይ ይዘው መጥተዋላ። እውነቱን ለመነጋገር እስከ እዚች ዕለት ድረስ ይህ ይሆናል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።
በክፍል ሁለት መጣጥፌ ስለ እዚህ ራዕይ እና ስለ “ ንጋት “ እና ሌሎች ሴናሪዮኖች በስፋት ይዤ እመለሳለሁ። ፈጣሪ እንደ “ ቲም ንጉሱ “ ቅን አሳቢዎችን ያብዛልን ! አሜን ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳይን )