ክፍል አንድ
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ታሪክ የሚጀምረው የሰው ልጅ ዕርምጃውን አንድ ብሎ የጀመረበትን የዘፍጥረት መነሻ ታሪኩን መሠረት በማድረግ መሆኑን የዘርፉ ልሂቃን አበክረው ሲጽፉና ሲያስተምሩ ኖረዋል። የሺህ ማይል የረጂም ታሪኩ ጉዞ መድረሻው የሀሌታ ዕርምጃው ስለመሆኑም በቻይናዊያን የተዘወተረ ጥንታዊ አባባል ተደጋግሞ ሲጠቀስ ኖሯል።
የሕዝብ ለሕዝብ መገናኛ፣ መዋሃጃ፣ መዋለጃ፣ መዛመጃና መጋመጃ መንገዱና ዘዴው የተዥጎረጎረው፣ ዓይነቱም ሊበረክት የቻለው በሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የዝውውር ነፃነት አስገዳጅነትና ተጽዕኖ ጭምር ነው። ግንኙነቱና እንቅስቃሴው ገደብ ቢበጅለትም ሊበገር በማይችል ትስስር የተቆራኘ መሆኑን በህዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም የዚሁ ጋዜጣ እትም ላይ አጠቃላዩን እውነታ ለማሳየት ሞክሬያለሁ።
በንግድና በጦርነት፣ በሃይማኖትና በትምህርት፣ በስደት፣ በዕውቀትና በጥበብ አሰሳ፣ በአድቬንቸርና በቱሪዝም ምክንያት ሕዝብ ከሕዝብ ሲገናኝና ሲሰባጠር ኖሯል። ግንኙነቶቹ የሰላም መቀራረቦች ብቻ ናቸው ተብሎ የሚደመደም አይደለም። ሕዝብን ከሕዝብ ክፉም ያገናኛቸዋል፤ ፍቅርም ያቀራርባቸዋል፤ ጦርነት የዕልቂት ሰበብ ቢሆንም በተሸናፊውና በአሸናፊው ወገን መካከል በካሣም ሆነ በእርቅ ሰላም ሲሰፍን ግን አጨባብጦ ያቀራርባል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ምድር ላይ በሚገነባና በሚታጠር የሾህ አጥር፣ ባህር ላይ በሚዘረጋ ወጥመድና በሰማይ ላይ በሚምዘገዘግ ሚሳይል መገደብም ሆነ ማቆም አይቻልም። ልክ የወንዝን የውሃ ፍሰት ለአፍታ ካልሆነ በስተቀር ለዘለዓለም ገድቦ መገተር እንደማይቻል ሁሉ። የመሪዎች ቁጣና ዛቻ፣ ልምምጮሽና ማባበያ፣ የቀማኞች ጭካኔና ዘረፋ፣ የፖለቲካ ክፋትና ግፍትሪያ፣ የግፈኞች ግፍና ግፊያ፣ የመደለያ መሸንገያዎችና ማታለያዎች ወዘተ. የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ጥላ ያጠሉ ካልሆነ በስተቀር ሰንሰለቱን ከነጭራሹ ሊበጥሱት አይችሉም። እንደ ትናንቱ ዛሬ፣ እንደ ዛሬም ነገ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱና ዝውውሩ በደግም ሆነ በክፉ መቀጠሉ አይቀርም።
የዛሬውና የነገው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምናልባትም እንደ ትናንቱ “ይሄና ያ” ተብሎ በውስን ዙሪያ ገብ ድንጋጌ ላይወሰን ይችል ይሆናል። ለምን ቢሉ ዘመኑና ትውልዱ ተራቋል፤ የብሱ፣ ባህሩ፣ ውቂያኖሱና ጠፈሩ ለመጓጓዣነት ተመቻችቷል፣ ዲፕሎማሲው ረቅቋል፣ ፖለቲካው መጥቋል፣ ንግዱና ሃይማኖቱ ተመሰቃቅሏል፣ ግጭቱና ጦርነቱ ጦዟል የተለመደው የሕይወት ሽክርክሪት በፍጥነቱ ከንፏል። ስለሆነም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በምንም ዘዴና ብልሃት በማይቆምበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል – ያውም እስከ ዕለተ ምጽዓት ድረስ።
ወደ መነሻ ጉዳያችን እናቅና፤
የኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ልዑካን ቡድን ከህዳር 16 እስከ 21/ 2012 ዓ.ም በዩጋንዳ ቆይታ ያደረገው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በታሪክ መቆራኘታቸውን፣ በሁለቱ የዓባይ ወንዞች የተፈጥሮ በረከት መታደላቸውን መሠረት በማድረግ ለቅርብ ጎረቤታችን ለዩጋንዳ ሕዝብና መንግሥት የሰላምና የምሥጋና መልዕክት ለማድረስ ነበር። ሰላምታው የኢትዮጵያን ወንድምና እህት ሕዝቦችን ንፁሕ ፍቅር ለዩጋንዳ ወንድም እህቶቻችን አጉልተን ለማሳየት ሲሆን ምሥጋናው ደግሞ የዩጋንዳ መንግሥትና ሕዝብ በታላቁ የህዳሴ ግደባችንና በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ላይ ከሀገራችን ጎን ቆመው ድምፃችንን ድምፃቸው፣ ወሳኔያችንን ወሳኔያቸው አድርገው አጋርነታቸውን ስላረጋገጡልን በኢትዮጵያዊ ባህል ደስታችንንና አክብሮታችንን መግለጽ እንደሚገባን ስለታመነበት ነበር።
ሁለተኛው የተልዕኮው መሠረታዊ ጉዳይ በዩጋንዳ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መሃል ተገኝቶ ሕዝባችንን በመወከል ቤተሰባዊ ፍቅርንና ናፍቆትን በጋራ ለማጣጣም ነበር። በጸሐፊው እምነት ሁለቱም ተልዕኮዎች ያለምንም መሰናክል ተከናውነው ቡድኑ በሰላም ወደ ሀገሩ ሊመለስ ችሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤታችን ሥር የተቋቋመው የዚህ የሕዝብ ለሕዝብ የልዑካን ቡድን (ፐብሊክ ዲፕሎማሲ) አባላት ስብጥር በተቻለ መጠን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲወክል ተደርጎ የተዋቀረ ነው። ስብጥሩና ውክልናው ፍጹም ነበር ባይባልም “መልካም” ለመባል የሚበቃ መሆኑን ግን ማረጋገጥ ይቻላል። ቡድኑ የተመራው በሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባዔ በተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ ሲሆን ከልዑካን ቡድኑ ጋር የተንቀሳቀሱት የብሔራዊ ቴያትር የባህል ቡድን አባላትም ለተልዕኮው ፈርጥ ነበሩ ማለቱ ሃሳብን ይጠቀልላል። ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከጂቡቲ ቀጥሎ በአራተኛነት የሚጠቀሰው የዩጋንዳ ጉዞ በእጅጉ የተሳካና ፍሬያማ እንደነበር ለማሳየት በተከታታይ በሚቀርቡት ጽሑፎች ለማሳየት ይሞከራል።
ስለ ዩጋንዳ አጠቃላይ የመንደርደሪያ መደላድል አኑሮ ማለፉ አግባብ ስለሆነ በጥቂት ቃላት ለመጭዎቹ ሰፋፊ ጽሑፎች ጥቁምታ የሚሰጡ ሃሳቦችን ፈነጣጥቄ ልለፍ። ልምላሜ የሚለው ቃል ይገልጸው ከሆነ እርግጠኛ ባልሆንም ዩጋንዳ በአጠቃላይ ለምለም ሀገር ነው። ሕዝቡ በአብዛኛው ቅንና ገር ሲሆን በተለይም ለሀገሬ ልጆች ያላቸው አክብሮትና ፍቅር በቀዳሚነት ይመሰገናል። ብዙ ዩጋንዳዊያን ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራን መነሻችን ከኢትዮጵያ ነው ሲሉ ማድመጥ ልብን ያሞቃል። “ዩጋንዳ የስደተኞች ገነት ነች” እያሉ ሲያሞግሱ ያደመጥኩት ባለሀገሮቹ ሳይሆኑ የእኔው የራሴ ወገኖች ናቸው። ሙገሳቸው የምር መሆኑንም በተግባር ማረጋገጥ ችለናል።
ከክቡር የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ጋር የተወያዩት ጥቂት የልዑካን ቡድኑ አባላት ደርሶ መልሳቸው ከፕሮቶኮል ቋንቋና ከዲፕሎማሲ ጥንቃቄ ነፃ እንደነበር ዕድሉን ያገኙት አባሎቻችን በመገረምና በመደነቅ ሪፖርት አድርገውልናል። ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ራሳቸውን የሚገልጹት “የግብርና ባለሙያና የተፈጥሮ ወዳጅ ፕሬዚዳንት” በማለት ሲሆን ለእርሻና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልዩ አክብሮት ብቻ ሳይሆን ልዩ ፍቅርም እንዳላቸው ተወካዮቻችን አስረግጠው የነገሩን እንዳለ ሆኖ የሀገራቸው እውነታ አፍ አውጥቶ የመሰከረልንም ይህንኑ ነው። ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ በሺዎች ስለሚቆጠሩት ስለ ባለ ረጃጅም ቀንድ የግል እንስሳቶቻቸው ተናግረው አይጠግቡም ተብለናል። ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም ይህንንው እንደነገሯቸውና በአካልም እንዳስጎበኟቸው የእኛ ሚዲያዎች ባይገልጹልንም የፎቶግራፍ መረጃ ያየነው ካምፓላ ውስጥ ነበር። መቼም የሌላ አካባቢ ጉብኝት እንዳልሆነ እንረዳለን።
ፕሬዚዳንቱ በመንበረ ሥልጣናቸው ላይ ለሦስት አሠርት ዓመታት መቆየታቸው ይታወቃል። ይህንን ንግሥና አንዳንዶች በአምባ ገነንነት ሲፈርጁት በርካታ ዩጋንዳዊያን ግን “ክፉ አይንካብን!” እያሉ መመረቃቸውን በወሬ ሳይሆን በጆሯችን ደጋግመን አድምጠናል። በተለይም በ2020 ዓ.ም ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ፈጣሪ ከሽንፈት እንዲታደጋቸው በስዕለት ቀረሽ ተማጽኖ እንደሚቃትቱ የጋራ ማረጋገጫ ሰጥተውናል። ከነአባባሉስ “ለገቢህ ተንገብገብ” አይደል። እንዴታውን በዝርዝር እመለስበታለሁ።
ከተከበሩ የሀገሪቱ አፈጉባዔ ከፍልቅልቋ ወ/ሮ ርብቃ ካዳጋ ጋር የነበረን የጋራ ምክክር በእጅጉ ውጤታማ ነበር። ድባቡ ከብዶ አልተጫነንም። ውይይቱም አልጠነነብንም። ፈገግታ ከፊታቸው ላይ የማይጠፋውና ቅንነትና ቀለል ብሎ የመታየት “Simplisity” ባህርይ የሚታይባቸው የልዑካን ቡድኑ መሪ የተከበሩ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ውይይቶችን ፈታ የማድረግ ችሎታቸውንና አሳታፊነታቸውን የቡድኑ አባላት በእጅጉ አድንቀውላቸዋል፤ በአመራር ብቃታቸውም ከልብ ወደዋቸዋል።
ከሀገሪቱ የኢነርጂና የማዕድን፣ የውሃና የአካባቢ ሁለት ሚኒስትሮችና ባለሙያዎች ጋር፣ ከሀገሪቱ የሃይማኖቶች ጉባዔ ተወካዮች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከተዘጋጁት የፓናል ውይይቶች በርካታ ዕውቀቶችንና ግንዛቤዎችን ለመቅሰም ተችሏል። በተለየ ሁኔታ ግን ከአንጋፋውና ከተከበረው የማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ መሪዎችና ፕሮፌሰሮች ጋር የነበረው ቆይታ ሙያዊ፣ አካዳሚያዊና ምሁራዊ ስለነበር ጸሐፊው ዳግላስ በእጅጉ ተደስቶበታል።
የነጭ አባይን መነሻ ሥፍራና የቪክቶሪያ ሐይቅን በጎበኘንበት ዕለት ግን በግሌ የተሰማኝ ስሜት ቁጭትና መድበን ነበር። የሀገሬ የዓባይ ወንዝ መነሻ የተጎሳቆለ አካባቢ፣ አስተዋሽ አጥቶ እንደስሙ በእውነትም በጭስ እየተጨናበሰ ስላለው “ጢስ ዓባይ”፣ እና የእንቦጭ አረም አጥንቱንና ሥጋውን እያመነዠከ ህመም ላይ የጣለውን የጣናን ሕይቅ በተመለከተ ቪክቶሪያ ሐይቅ ዳር ቆሞ ማነፃፀር ባያሳብድም ውስጥን ይፈትናል፤ “ያልታደልን!” አሰኝቶም ያስቆዝማል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሚገባ ተመልሼበት ራስ ምታቴ በአንባቢያንም ላይ እንዲጋባ ዝርዝሩን ወደፊት አስነብባለሁ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ዩጋንዳ በመሠረተ ልማት እጅግም አልበለፀገችም። ግን ተፈጥሮና ዜጎቿ ተስማምተውና ተፋቅረው በመከባበር እየኖሩ ነው። እንደ ዝርክርኳ ሸገር ዩጋንዳዊያን ከቆሻሻ ጋር ፍቅር ላይ አልወደቁም። የአውራ ጎዳናዎቿ ጥበትና የትራፊክ ጭንቅንቁ ግን ሀገሬ በስንት ጣዕሙ ያሰኛል። የካምፓላን የትራፊክ ጃም ያየ ከአያት አደባባይ እስከ መገናኛ ያለውን የማለዳ የመኪኖች ሰልፍ እንደ ቅንጦት ቢቆጥር አይፈረድበትም። የካምፓላ እውነታ ይህንን ይምሰል እንጂ ዜጎቿ የሕዝብ ትራንስፖርት ጥበቃ በኪሎ ሜትር ርዝመት ተሰልፈው ፈጣሪንም መንግሥትንም እያማረሩ እንባቸውን ወደ ሰማይ አይረጩም። ዕድሜ “ለቦዳ ቦዳ” አዳሜ ባለመኪና በመኪና መሪው ላይ ተደፍቶ ቆሽቱ እርር እያለ በቆመበት ሲያዛጋ እግረኞች ያሰቡበት ቦታ ለመድረስ ደቂቃ ዝንፍ አይልባቸውም። “የቦዳ ቦዳ”ን ምስጢር ይፋ የማደርገው በቀጣዩ ጹሑፌ ይሆናል።
የነጋዴዎችን እንባና ምሬት የጠገቡት የሀገሬ የንግድ ፈቃድ መስጫ ተቋሞችና የገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ምነው መንግሥት ያወጣውን ወጪ አውጥቶ ዩጋንዳን ባስጎበኛቸውና ቅንነትን ለምደውና ንስሐ ገብተው በተመለሱ ብዬ ያማኋቸው መሰናክሉ በዝቶብን አላሠራ ያለንን የኩባንያ የንግድ ሥራ ፈቃድ ለመመለስ ዶኪዩመንታችንን መልክ እያስያዝኩ በነበረበት ወቅት ነው። እንባና ሣግ እየተናነቀኝ ጭምር።
በሀገሬ የንግድ ሥራዎች ፈቃድ አሰጣጥና አመላለስ ላይ የተቆጣጣሪነትና የውሳኝነት ሥልጣን የተሰጣቸውን መ/ ቤቶች ለሚመሩ ሕዝብ አስለቃሽ ሹማምንትና ሠራተኞች ቀና ልብና ትህትና በለገሳቸው እያልኩ ምሬት ይሁን ጸሎት በውል ልለየው ያልቻልኩት ስሜት ውስጤን አመሳቅሎ መተከዜንም አልሸሽግም። ዩጋንዳ እንኳን ለዜጎቿ ቀርቶ እንነግድና ሕይወትን እናሸንፍ ለሚሉ የሀገሬ ስደተኞች ሳይቀር በሩ ወለል ተደርጎ የተከፈተና የተመቻቸ እንደሆነ “እምዬ ዩጋንዳ” በማለት እያንቆላጰሱ ሀገሩንና ሕዝቡን የሚመርቁት ወገኖቼ በኩራት ሲናገሩ እያደመጥሁ ከምድሬ ጋር በማነጻጸር “እኛንስ የረገመን ማን ነው? ተረግመንስ ከሆነ ለምን?” ብዬ ራሴን በራሴ ጠይቄ መልስ ባጣ ትዝ ያለኝ የጌታቸው ካሣ የቆየ እንጉርጉሮ ነው፤
እመኛለሁ፣ እመኛለሁ፣
ዘወትር በየዕለቱ ላይሳካ ኑሮና ብልሃቱ።
ልክ ብለሃል ጌታቸው።
«ዩጋንዳ የስደተኞች ገነት»
ይህንን ምስክርነት አፋቸውን ሞልተው ያረጋገጡልን ስደተኞችና በዚያ ነዋሪ የሆኑ የተሳካላቸውና በስኬት ጎዳና ላይ መራመድ የጀመሩ የእኛው ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ናቸው። ስለ ቃል ምስክርነታቸው እኔን ዳግላስንና የሕዝብ ለሕዝብ ልዑካን አባላትን ጠይቁ። የጽሑፍ ምስክርነት ካስፈለገ ግን ከኬኒያው ካኩማ የስደተኞች ካምፕ ጅምሮ ለስደትና ለመንከራተት ሳይበገር ሕይወትን ለማሸነፍ ከሚተጋው ከናትናኤል ጋሻው (ናቲ ቪሎፒያ) ጽሑፍ ማስረጃዬን እጠቅሳለሁ። ናቲ ከጋዜጠኛነት ሙያው ጋር በተያያዘ አሳዳጆች በርትተውበት ከሀገሩ ያስኮበለሉት ልበ ብርሃን ወጣት እንደሆነ በነበረን ቆይታ ለማረጋገጥ ችያለሁ። ንቁ አዕምሮ፣ የሰላ ብዕር ባለቤቱ ናቲ “ፍም ሃሳብና ሌሎች” በሚል ርዕስ ካሳተመው ድንቅ መጽሐፍ ውስጥ ዩጋንዳንና የኬኒያ ስደቱን እያነጻጸረ ከገለጸበት ሃሳብ ጥቂት ቆንጥሬ ላስነብብ።
“ዩጋንዳ ብዙም መሠረተ ልማት ያልተሟላላት ግን በጣም የምትመች ሀገር ነች። ምንም እንኳ መሠረተ ልማቷ ያልተሟላ ቢሆንም እንደ አዲስ አበባችን የታክሲ ሰልፍ አለ ብለህ አትሳቀቅ። ምክንያቱም ካለህበት ስፍራ ወደ ፈለግህበት የሚወስድ ትራንስፖርት አለና ዘና በል። ዩጋንዳ ወስጥ እንደ ኬኒያ በየመንገዱ እያስቆመ ስደተኛን ለገንዘብ ብሎ የሚያስጨንቅ ፖሊስ የለምና በዚህ በኩል ሰላም ይሰማህ።”
“ለምለሚቱ ሀገሬ ተብሎ የተዘፈነላት እምዬ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንኳን ልጆቿና ለምለም ሜዳዋ እና ጫካዋ የት ሄዶ ነው እንዲህ “ሲና በረሃ” የመሰለችው ከተባልክ ደናችን በተፈጥሮ የፖለቲካ ጥገኝነት ምክንያት ዩጋንዳ ተሰዶ ነው በል። አዎ ዩጋንዳ አረንጓዴ ናት። ልምላሜዋን ለማየት ብዙ መጓዝ የለብህም። ከተማዋ በረሷ አረንጓዴ ናት። አየሩ ምቹ ነው። አትሰደድ! ከተሰደድክ ግን ከኬኒያ ናይሮቢ የበለጠ ካምፓላ ትመችሃለች። በካምፓላ ሃበሾች በብዛት እንደሚኖሩና የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ስነግርህ በኩራት ነው። ስደት ድክም ቢያደርገውም ሃበሻ ፊት አይነሳህም። ሃበሻ ለመኖር የሚሮጥ፣ የስደት ኑሮውን ለማሳመር የሚታገል ብርቱ ኢትዮጵያዊ ነው። አትሰደድ ከተሰደድህ ግን ካምፓላ ትመችሃለች።” (ፍም ሃሳብ፤ ከገጽ 81-86)
ናቲ በጽሑፉ እንደመሰከረው ስደት አይበረታታም። መሰድደ ግድ ሆኖ በባዕድ ምድር እግር ከጣለ ግን የተሰደዱበትን ሀገርና ሕዝብ ማመስገን መቻል የታላቅ ስብዕና መገለጫ ነው። ብዙዎቹ የዩጋንዳ ስደተኛ ወገኖቻችን ዩጋንዳን የሚገልጹት “እምዬ” እያሉ ነው። እንደ እንጀራ እናት ሳይሆን ልክ እንደ እናት ሀገር።
ከዓመታት በፊት በጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት ያስተማርኳትና ስደት አንከራቶ ዩጋንዳ ያደረሳትን ተማሪዬን ፍቅርተንም ሳላነሳ አላልፍም። ፍቅርተ የስደቷን መራራ የሬት ታሪክ ስትተርክ ልብን በኀዘን ትደልቃለች። ተንከራታለች ብቻ አይበቃም። የስደቷን ሕይወት ስትተርክ ፊልም እንጂ በውን በእሷ ላይ የተፈጸመ አይመስልም። ስደቷን ብቻም ሳይሆን በብሩህ ገጽታ የካምፓላ ስኬቷን ታሪክ ጭምር ስታጋራም አድማጯን ታፈዛለች። የፍቅርተ የባህል ዕቃዎች መሸጫ ሱቅ በካምፓላ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ቸርነቷና ደግነቷ ደግሞ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ብዙዎች “እናታችን ነች” እያሉ ያሞግሷታል። ከደግነት መገለጫዎቿ መካከል ለበርካታ የልዑካን ቡድን አባላት ያደረገችውን በጎነት መተረኩ ለጊዜው አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም። በሀገራችን ባህላዊ ሬስቶራንት ከበር መልስ የጋበዘችንን ጠቅሼ ባላመሰግን ግን ጓደኞቼ ይታዘቡኛል። ታታሪዋ ፍቅርተ ለብዙዎች ምሳሌ የምትሆን እህትና ለችግር ደራሽ መሆኗን ገልጾ ማለፉ ባይበቃም ይብቃ።
በአጭር ጊዜ የዲፕሎማቲክ ስኬታቸው ከአለቆቻቸውና ከባልደረቦቻቸው ምስጋና የሚዥጎደጎድላቸው በዩጋንዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ስለሆኑት ስለ ክብርት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረትና እንደ እንዝርት እየሾሩ ያስተናገዱን የኤምባሲያችን ወጣት ዲፕሎማቶች በልዩ አክብሮት ሊመሰገኑ ይገባል። በተለይ “በአሳዳጅኛ በተሳዳጅነት ክፉ የፖለቲካ ተፅእኖ” ለዓመታት ሆድና ጀርባ ሆነው ከኤምባሲያችን ጽ/ ቤት ጋር የጎሪጥ እየተያዩ የኖሩት የሀገሬ ስደተኞችና ነዋሪዎች ዛሬ አርቀ ሰላም ወርዶ በኤምባሲያችን ቅጥረ ግቢ ውስጥ እኛን በፍቅር እያስተናገዱ ለሀገራችን ምን አስተዋጽኦ እናበርክት እያሉ በጥያቄ ሲያጣድፉን ማስተዋል ምንኛ ደስ ይላል። “ሀገር ሲጠብ የኤምባሲ ጽ/ቤት ይሆናል” እንዲሉ በጠባቡ የኤምባሲያችን ጽ/ቤት ውስጥ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያ ነገሠው ያመሹበት የአንድ ምሽት ትዝታ ለአንድ ምዕተ ዓመት ቢተረክ የሚደበዝዝ አይደለም። እናመሰግናለን ወገኖቻችን።
«ወገኔ ሲከፋው ውጭ ሀገር ይመኛል፣
እዚህ ያላደለው እዚያ ምን ያገኛል።»
የሚለው ተስፋ አስቆራጭ እንጉርጉሮ በዩጋንዳ ባይሠራም ስደት ግን በራሱ የሚበረታታ አይደለም። በቀጣዮቹ ጽሑፎቼ የምነካካቸውንና የሚነካኩንን በርካታ ብርቱ ጉዳዮች እንደማነሳሳ ቃል እየገባሁ እሰናበታለሁ። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ