ቅድመ -ታሪክ
ተወልዶ ያደገባት ከተማ ሰፊና ዘመናዊ የምትባል ናት:: ለእሱ ግን ዕጣ ፈንታው አልሆነችም:: እንደ እኩዮቹ የመማር ዕድል ሳትሰጠው ዕድሜውን በችግር ሊገፋባት ግድ ሆነ:: በአካል መጎልበት ሲጀምር በጉልበቱ ከማደር ሌላ ምርጫ አልነበረውም:: አቅሙ የቻለውን እየሠራ ቤተሰቦቹን ማገዝና ራሱን መምራት ጀመረ::
ጥቂት ቆይቶ ደግሞ የታክሲ ረዳት ሆኖ የዕለት ገቢ ማግኘትን ለመደ:: ይሄኔ የገንዘብን ጥቅም አወቀ:: ገቢውን ከወጪው እያዛመደም ህይወትን በአግባቡ አጣጣመ:: ሥራው በርካቶችን ሲያስተዋውቀው ደግሞ አማራጮችን ፍለጋ በሃሳብ ባዘነ:: ከሚኖርበት የተሻለ ሆኖ ለመገኘት በብዙ መንገዶች ተመላልሶ አቅሙን ለማጎልበት ተሯሯጠ::
ሀጎስ በርሄ ከዕለታት በአንዱ ቀን ሲያሰላስል በከረመበት ጉዳይ ላይ ከውሳኔ ደረሰ:: ህይወቱን በተሻለ ለመምራት ካለበት ርቆ መሄድን አምኖበታል:: ይህን ሃሳቡን እውን ለማድረግም ከራሱ ሲመክር ቆይቷል:: ለዚህ ውጥኑ መዳረሻ ባደረጋት ከተማ ደግሞ ብዘዎቹ የአገሩ ልጆች ተመችቷቸው እንደሚኖሩ እያየ እነሱን ለመሆን ሲመኝ ነበር::
ከእነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት ኑሯቸው ተለውጧል:: በየዓመቱ ወደቤተሰቦቻቸው ሲመጡም አዲስ ለብሰውና በተለየ አምሮባቸው ነው:: ሀጎስ ይህን ባየበት አጋጣሚ ሁሉ በእነሱ ቦታ ራሱን ተክቶ ህይወታቸውን ሲመኝ ቆይቷል:: ዛሬ ግን ከምኞት በዘለለ በመንገዳቸው ሊቀጥል ጓዙን ሸክፎ ለጉዞ እየተዘጋጀ ነው:: ብዙዎች ወደሚመኟትና እሱም ወደሚናፍቃት አዲስ አበባ::
ሀጎስ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ በከተማው ስፋት እምብዛም አልተቸገረም:: የእንግድነት ስሜት ለቀናት ቢፈትነውም ጥቂት ቆይቶ ከሁሉ ተላመደ:: የአገሩ ልጆች በሚኖሩበት አካባቢ ተጠግቶም ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመረ:: ሀጎስ የአዲስ አበባን ህይወት ቀድሞ እንደገመተው አላገኘውም:: ኑሮ ውድ፣ ህይወትም ከባድ ሆነበት::
ገቢው እያነሰ ወጪው ሲበዛ ዳግም በአማራጭ ሥራዎች ራሱን አበረታ:: በየቀኑም ኑሮን ለማሸነፍ መታተር ያዘ:: አሁን በዚህ ስፍራ የሥራ ምርጫ እንደማይኖር ገብቶታል:: ህይወቱን ለማቃናት ደግሞ ቀን ከሌት መሮጥ እንዳለበት ካቀደ ቆይቷል:: እንዲህ ማድረጉ ለቤት ኪራይ ለዕለት ወጪውና ለሌላም ችግሩ በጎ ሆኖለት:: እያደር ሁሉን ችሎ ጊዜያትን እንደዋዛ ገፋ::
የሥራ ለውጥ
አሁን ሀጎስ የአዲስ አበባ ልጅ ሆኗል:: እንደትናንቱ የኑሮ ችግር እየፈተነው አይደለም:: ወደመሀል አገር የመጣበትን ዓላማ ቢያውቅም አንዳንዴ ወጣትነቱ ካልሆነ ስፍራ ያውለዋል:: ይህ አጋጣሚ ደግሞ የቀደመ ማንነቱን ለውጦ ታማኝነቱን አስቀይሮታል:: ለመኖር ሥራን ብቻ መምረጥ እንደማያዋጣ ሲገባው በሌብነት ድርጊት መሰማራትን እንደአማራጭ ተቀብሏል::
ስርቆትን እንደገቢ ምንጭ መጠቀም ሲጀምር ህይወት እየቀለለውና ኪሱ እየዳበረ ሄደ:: አጋጣሚው ለጊዜው ከሥራ ድካም አሳርፎ በየቀኑ ገንዘብ ያስቆጥረው ያዘ:: ሁኔታዎች ሲመቹት ስልቱን እየቀያየረ በድርጊቱ ገፋበት:: ይህን ማድረጉ እየጣመው ሲሄድም ሥራውን እርግፍ አድርጎ ተወ::
እንዲህ መሆኑ ግን እምብዛም አላራመደውም:: አንድቀን በፈጸመው የሌብነት ወንጀል ተይዞ ለክስ ተዳረገ:: ድርጊቱ በማስረጃዎች ተረጋግጦም ስምንት ወራትን በማረሚያ ቤት እንዲያሳልፍ ተፈረደበት:: እንጀራ ፍለጋ ከአገሩ የወጣው ወጣት መጨረሻ ሌብነት መሆኑ ብዙዎችን ማስገረሙ አልቀረም:: ለእሱ ግን የተለየ ስሜት አልነበረውም::
የፍርድ ውሳኔውን ጨርሶ ከአስር ሲወጣ ከጓደኞቹ ፈጥኖ ተቀላቀለ:: እንደ ቀድሞው በሥራ ለመሰማራት ፍላጎት አልነበረውም:: ያሳለፈውን እያሰበና ስለነገው እያቀደ ለቀናት መቀመጥን ምርጫው አደረገ::
ሀጎስ ከባልንጀሮቹ ሲገናኝ በመጠጥና በሙዚቃ መዝናናት ይወዳል:: አንዳንዴ በሚገኝበት ስፍራ ግብዣውና ጨዋታው እየጨመረ ሲሄድ ጠብና ግርግር ሊነሳ ይችላል:: ይሄኔ ፈጥኖ ለድብድብ የሚጋበዘው እሱ ነው:: ግልፍተኛ ዓመሉ ከብዙዎች ቢያጋጨውም በቀላሉ መተው አልሆነለትም::
እንግዳው ተማሪ
መቀሌ ተወልዶ ያደገው ወጣት ኪሩቤል ከጓደኞቹ በላይ የላቀ ውጤት በማምጣቱ ወደዩኒቨርሲቲ ለመግባት ተዘጋጅቷል:: ይህን ደስታ የተጋሩት እናት አባትም ልጃቸው እንዳይቸገር በማሰብ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተዋል::
ኪሩቤል ለትምህርት የተመደበበት ስፍራ አዲስ አበባ መሆኑን ካወቀ ጀምሮ የተለየ ስሜት ውስጥ ነው:: አስከዛሬ ከተማውን ለማየት ሲጓጓ ቆይቷል:: በዚህ ስፍራ የቅርብ የሚባሉ ዘመዶች ቢኖሩትም ምክንያት አግኝቶ የመጣበት አጋጣሚ አልነበረም::
መቀሌን አልፎ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ የዩኒቨርሲቲን ህይወት መላመድ አልቸገረውም:: ለእሱ ከቤተሰቦቹ መነጠል ቀላል ያለመሆኑን ያውቃል:: ትምህርት ጀምሮ ከብዙዎች ሲላመድ ግን ከሁኔታዎች ጋር ተዛመደ፤ አንዳንዴ ቤተሰቦቹ ውል እያሉት ይቸገራል:: ይህን ብቸኝነት ግን በቅርብ የሚያገኛቸው አጎቱ ዘንድ እየሄደ ለመርሳት ይሞክራል:: አጎቱ ከመቀሌ የመጣውን የእህታቸውን የአደራ ልጅ በስስት እያዩ ይንከባከቡታል:: እንደ ተማሪነቱ ያስፈልገዋል የሚሉትን በአቅማቸው እያሟሉም በየጊዜው ይጎበኙታል::
አውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ ኪሩቤልን ቸግሮት አያውቅም:: የቤተሰቦቹን ትዝታ ከአጎቱ ቤት እያቃለለ ቀኑን በደስታ አሳልፎ ወደግቢ ይመለሳል:: በየጊዜው በስልክ የሚያገኛቸው ወላጆቹ በእሱ ላይ የተለየ ተስፋ እንዳላቸው ያውቃል:: የእነሱን ውለታ በእጥፍ ለመመለስ የሚያስበው ወጣትም በትምህርቱ ላለመስነፍ ዘወትር እየተጋ ነው::
ጊዜ እየጨመረና ትምህርቱ እየገፋ ሲሄድ ኪሩቤል ከተማውን ተላምዶ ከበርካቶች ጋር ተዋወቀ:: አብረውት ከሚማሩት ውጪ ለመዝናናት የሚፈልጋቸው ጓደኞቹ በረከቱ:: እነሱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጭፈራ ቤቶችን አየመረጡ መዝናናትን ያዘወትራሉ::
ኪሩቤልም ባገኛቸው ጊዜ በመጠጥና በጭፈራ ማሳለፍ ምርጫው ነው:: ምሽቱን በየቤቱ እየዞሩና በጭፈራ እየተዝናኑ መታየትም በጓደኛሞቹ ዘንድ የተለመደ ሆኗል:: በዚህ አጋጣሚ የሚነሳ ጠብና ግርግር ቢኖር መምታትና መመታቱን ለምደውታል:: ይህን እውነት ደጋግሞ የሚያልፍበት ኪሩቤል ግን ከመጣላት ይልቅ መስማማትን እየመረጠ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ሲሞክር ቆይቷል::
አንዳንዴ ጠቡ አይሎ ድብድቡ ሲጀመር ኪሩቤል ከመሀል ገብቶ ይገላግላል:: ከአቅም በላይ በሆነ ጊዜም በፀጥታ ኃይሎች ተበትኖ ቤቱ እንደነበረው ይቀጥላል:: ተማሪው ኪሩቤል በዚህ ስፍራ መገኘቱ ተገቢ ያለመሆኑን ያምናል:: ከትውልድ አገሩ ርቆና ከወላጆቹ ተለይቶ የመጣበት ዓላማ ይህ አለመሆኑን ባስታወሰ ጊዜም ልቡ በጸጸት ተመልቶ ዳግመኛ በስፍራው ላለመገኘት ከራሱ ጋር ይማማላል::
ጥር 24 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት
ቦሌ አካባቢ ያለው የምሽት ጭፈራ ቤት በዚህ ቀን ሥራውን የጀመረው በተለመደው ሰዓት ነበር:: ሁሌም ቤቱን የሚያጨናንቁት ደንበኞች ዛሬም ከባንኮኒው ተደግፈው አንድ ሁለት ማለት ጀምረዋል:: በተለየ አለባበሳቸው ዓይን የሚስቡት ሴት አስተናጋጆች ከወዲያ ወዲህ እያሉ መጠጥ ያመላልሳሉ:: አብዛኞቹም ከአንድ ጥግ ሆነው ከውጭ የሚገቡትን ደንበኞች በዓይናቸው እየተቀበሉ ወደወንበራቸው ይጠቁማሉ::
ሙዚቃው ተጀምሮ መስተንግዶው ሲደራ አንዳንዶች ከወንበራቸው ተነስተው መደነስ ጀመሩ:: ሌሎችም ከሚፈልጓቸው አስተናጋጆች ጋር አፍ ለአፍ ገጥመው ጨዋታቸውን ቀጠሉ:: ከሚጨፍሩት ደንበኞች አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው:: ከእነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት በመጠጥ ናውዘው የሚያደርጉትን አያውቁም:: ሁሉንም እንደ አመጣጡ የሚያስተናግዱት ሴቶች ከብዙዎቹ ጋር መስለው ከሙዚቃው ጋር እየዘፈኑ ይደንሳሉ::
ድንገቴዎቹ ደንበኞች
በፈዛዛው መብራት መሀል አልፈው ወደ ውስጥ የዘለቁት ወጣቶች በዓይናቸው ወንበር እየፈለጉ ወደ ውስጥ ማለፍ ጀምረዋል:: ጥቂት ራመድ ብለው ካገኙት ጠረጴዛ ላይ ከበው እንደተቀመጡም ያሻቸውን አዘው መጠጣት ቀጠሉ:: አብዛኞቹ ሞቅታ ውስጥ በመሆናቸው ከሌላ ቦታ ሲዝናኑ እንደነበር ያስታውቃል::
ጥቂት ቆይተው የተወሰኑት ወደመሀል ገብተው መደነስ ጀመሩ:: ከአፍታ በኋላም ከዳንሰኞቹ ባልንጀሮች መሀል ከእስር የተፈታው ሀጎስ እየተወዛወዘ ተቀላቀላቸው:: ወዲያው ከሌላው ጠረጴዛ ላይ አንድ ወጣት ደናሽ ተነሳ:: ወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ኪሩቤል ነበር:: ጨዋታው ደምቆ ጭፈራው እንደቀጠለ ባልታሰበ ምክንያት ግርግር ተነሳ::
በደናሾቹ መሀል የተነሳው ግርግር ጠብ አስከትሎ ለድብድብ ሲዳርግ አፍታ አልቆየም:: ሁሉም በእጁ የጨበጠውን ጠረሙስና ብርጭቆ አጥብቆ ራሱን ለመከላከል አደፈጠ:: በሁለቱ ቡድኖች መሀል የተነሳው ድብድብም በስፍራው የነበሩትን አውኮ ትርምሱን አጎላው::
ጩኸትና ግርግር ማስተናገድ በጀመረው መጠጥ ቤት ውስጥ በሁለቱ ቡድኖች መሀል ድብድቡ ቀጥሏል:: ጠቡ በነኪሩቤልና በነሀጎስ መሀል የተፈጠረ ነው:: ሁለቱ ወገኖች ጎራ ለይተው ሲደባደቡ ከቆዩ በኋላ ወደውጭ ወጥተዋል:: ሀጎስ በመሀል ገብቶ ሲገላግል ቢታይም ከኋላው ድንገት ደርሰው በፈነከቱት ሰዎች ድርጊት በእጅጉ ተበሳጭቷል::
ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ድንገት የተወረወረው ድንጋይ ብዙዎቹን አልፎ በጥርሱ ላይ አረፈ:: ወዲያውም በድንጋጤ ደሙን እየጠረገ ወደፊት መሮጥ ጀመረ:: አጋጣሚ ሆኖ ከሚጣሉት ሰዎች መሀል ማንንም አላገኘም:: ወዲያው ግን ኪሩቤልን በርቀት አየው:: እሱ በድብድቡ ባይኖርበትም ከጓደኞቹ መሀል እንደነበረ አስታወሰ:: ከኋላው ሮጦ ሲደርስበት ጊዜ አልፈጀም:: ዝቅ ብሎ አንድ ትልቅ ድንጋይ በሁለት እጆቹ አነሳ:: ወዲያውም አነጣጥሮ ወደ ኪሩቤል ወረወረው::
የተወረወረው ትልቅ ድንጋይ ኪሩቤልን አልሳተውም:: መድረሻው ጆሮ ግንዱ ላይ ሆኖ በቁሙ ዘረረው:: ይህን ያየው ሀጎስ በድንጋጤ እንደተዋጠ ‹‹እግሬ አውጪኝ›› ሲል ወደፊት ገሰገሰ:: እየሮጠም አፉን በእጆቹ ዳበሰ:: ከፊት ጥርሶቹ መሀል አንደኛው በስፍራው አልነበረም::
በአካባቢው የነበሩ ክፉኛ ተመቶ የተዘረረውን ወጣት አንስተው ወደ ኮሪያ ሆስፒታል አመሩ:: ኪሩቤል ጉዳቱ የከፋ ሆኗል:: በሆስፒታሉ አስቸኳይ ዕርዳታ ቢደረግለትም ህይወቱን ለማትረፍ አልተቻለም::
የድርጊቱን መፈጸም ሰምቶ በስፍራው የደረሰው ፖሊስ ጉዳዩን ቀረብ ብሎ አጣራ:: በዕለቱ በቦታው የነበሩትን ለምስክርነት ጠርቶም የጠቡን ተካፋዮች በቁጥጥር ስር አዋለ:: ምሽቱን ከቤቱ ገብቶ የተደበቀው ሀጎስ ለጊዜው ባይገኝም ፖሊስ ካለበት ስፍራ ተገኝቶ በህግ ጥላ ስር አዋለው::
የፖሊስ ምርመራ
በፖሊስ የመዝገብ ቁጥር 676/08 መረጃው ተመዝግቦ መጣራት በጀመረው የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎች እየቀረቡ እያቀረበ እውነታውን ማውጣት ጀምረዋል:: በዋናሳጂን መንግስቱ አበበ የሚመራው ቡድንም የዕለቱን ግጭትና የተፈጠረውን ሁሉ በመለየት ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ አስተላልፎ ለፍርድ ውሳኔ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል::
ውሳኔ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት የተከሳሹን የተጣራ የወንጀል ድርጊት መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ዳኞቹን ሰይሟል:: በዚህ ሂደትም የተከሳሹን ጥፋተኝነት አረጋግጦ እንዲከላከል በሚል ዕድል ሰጥቷል:: ተከሳሽ ሀጎስ በርሄ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ በማመኑና በቂ የሚባል የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በመቅረቡም የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን ያስተምራል ያለውን የአስር ዓመት ጽኑ እስራት በይኖ መዝገቡን ዘግቷል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
መልካምስራ አፈወርቅ