በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ ዞን ሆና የቆየችውና ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ክልልነቷን በከፍተኛ ድምጽ ያረጋገጠችው ሲዳማ በርካታ ባህሎችን አቅፋ ይዛለች። ከሚታወቁት ባህሎቿ መካከል የአመጋገብ ፣የቤት አሰራር፣ የሰርግ፣ የግጭት አፈታት፣እርቅና ይቅርታ… የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህ ባህሎች መካከል ለዛሬ ምግብም መመገቢያው ሆኖ አንድ አይነት ስያሜ ስላለው ‹‹ሻፌታ›› እናነሳለን።
‹‹ሻፌታ››ን ብዙዎች (ከባህሉ ባለቤቶች )ውጪ የሆኑት ያወቁት ወይም ሲጠራ የሰሙት ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሲዳማ ክልል ይሁን ለሚለው ምርጫ ምልክት ሆና ከቀረበች በኋላ እንደሚሆን እገምታለሁ። ያም ሆኖ ሻፌታ ምግብ ነው ወይስ የምግብ መያዣ የሚለውን የተረዳው ብዙም አይደለም። በመሆኑም በዛሬው የባህል አምዳችን ስለ ሻፌታ ከምንጩ ያገኘነውን መረጃ እነሆ ብለናል። በቅድሚያ መረጃውን የሰጡንን በሲዳማ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ውስጥ የሚሰሩትን አቶ ተፈራ ሌዳሞን እናመሰግናለን።
የሲዳማ ብሔር ባህላዊ ምግቦቹን በየዓይነቱ የሚያዘጋጅ ሲሆን፤ ምግቦቹ የሚዘጋጁትም ከእንሰት፤ ከበቆሎ፤ ከማሽላ፤ ከገብስ፤ ከአትክልትና ከእንስሳት ተዋዕጽኦ ነው።አዘገጃጀቱም ለየቅል ነው ። ለአብነት ምግቦቹ ሲዘጋጁ ለአባወራ፤ ለእንግዳ፤ ለድግስ፤ ለሀዘን፤… ተብሎ ነው። የማቅረቢያ ባህላዊ ዕቃዎቹም እንደየምግቡ ዓይነት፤ የሰው ቁጥርና የታዳሚዎች ሁኔታ ይለያል።
በሲዳማ ባህል የመመገቢያ ዕቃዎች በርካታ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል ሻፌታ፣ ጥልቴ፤ ሻቆ የሚባሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ዕቃዎቹ የሚሠሩት ከሸክላ ነው።ከእነዚህ መካከል በመጠን ትልቁ ደግሞ “ሻፌታ” ሲሆን፤ ድግስ ላይ ማለትም በግርዛት፤ በ‹‹ፍቼ ጫምባላላ” በዓል ጊዜ፤ በቤት ምርቃት፤ በዕርቅ ሥነ ሥርዓት፤ በጋብቻ፤ በጥሎሽ፤ በቁጥሩ በርከት ያለ ተወዳጅ እንግዳ ሲመጣ፤ ወዘተ በምግብ ማቅረቢያነት የሚያገለግልና ከሌሎች ምግብ ማቅረቢያ ዕቃዎች የሚለይ ነው።
‹‹ሻፌታ›› ከሸክላ የሚሠራ ዕቃ ብቻ አይደለም። ሻፌታ እየተባለ የሚጠራ ምግብም አለ። ይህ ምግብ በሲዳማ ባህል ከእንሰት ተዋጽኦ በሆነው በቆጮና በቡላ የሚዘጋጅ ነው።ቆጮው ውሃ ከውስጡ እስኪያልቅ ድረስ በደንብ ተጨምቆ መድረቁ ከተረጋገጠ በኋላ ባዕድ ነገሮችን ለመለየት በወንፊት ይነፋል። ከዚያ ጥራት ያለውን ቆጮ ለመፈርፈር በሚመች ሁኔታ በሸክላ ምጣድ በወፍራሙ ይጋገራል።በመቀጠልም የበሰለውን ከሸክላ በተሰራው መመገቢያ ዕቃ ጥልቴ (Xilte) ይደረግና በእጅ በደንብ ይፈረፈራል። በደንብ ተነጥሮ በተዘጋጀ ቅቤ ከረሰረሰ በኋላም ወደ ትልቁ ዕቃ ‹‹ሻፌታ›› ውስጥ ይጨመራል። ሻፌታው እስከአፉ ድረስ እስኪሞላ መጨመርም አለበት።
“ሻፌታ” በብሔረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ ምግብ ሲሆን፤ በጣም ተወዳጅና የተከበረ እንግዳ ሲመጣ “ዳኤ ቡሹ” /አፈር ይምጣልኝ/ ተብሎ የሚቀርብ ነው።ምግቡ ብዙ ቅቤ ስለሚገባበት በደንብ ተዘጋጅቶ ከእርጎ ጋር ነው የሚቀርበው። ምክንያቱም ለአመጋገብ ምቹ፤ ለሆድ የማይከብድ፤ ለሰውነት ተስማሚና በጣም ተወዳጅ ምግብ መሆን ስላለበት ነው።
በሲዳማዎች ዘንድ ታላቅ የሆነ ሰው እየተመገበ ታናሽ የሆነ ሰው መመገቡን ማቆም ወይም እየተመገበ ያለውን ቅጠል ምግቡን በያዘው ዕቃ/ጥልቴ/ ላይ ማስቀመጥ አይችልም፤ ባህሉም አይፈቅድለትም። ነገር ግን በጣም አጣዳፊና አስቸጋሪ የሆነ ጉዳይ ካጋጠመው የያዘውን ቅጠል ቀስ አድርጎ ምንም ዓይነት ድምጽ ሳያሰማ በዕድሜ ታናሽ በሆነው ሰው እጅ ላይ አስቀምጦ መሄድ ይችላል። በሻፌታ ግን በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ አይሆንም።ምክንያቱም መጀመሪያ በዕድሜ ወይም በሉዋ ታላቅ የሆነ ቀድሞ ይቁረስ አይባልም። ሁሉም ሁለቱንም እጆቻቸውን ወደ ማዕዱ በጋራ በመዘርጋት በእኩል ይቆርሳሉ። ስለዚህ ሻፌታ የእኩልነት ተምሳሌት ነው።
ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሀዋሳ ከተማ ብቅ ሲሉ በሁሉም ትላልቅ ሆቴሎች እንደልብ ማየትና ማግኘት የተለመደውን ሻፌታ ልዩ ባህሪያት እንዳሉት ያውቁ ይሆን? መልስዎ አዎ ከሆነ መረጃው የነገረንን ተመልከቱ። ሻፌታ የፍቅር ማዕድ ነው።ምክንያቱም የሚዘጋጀው በድግሶችና ተወዳጅ እንግዳ ሲመጣ አቀባበል ለማድረግ ነው። ሻፌታ ለሀዘን አይዘጋጅም። ሻፌታ ለደስታ፤ ለፍቅር፤ ለሠላም፤ ለፌሽታ ተዘጋጅተው ሁሉም በተናጠል ሳይሆን በአንድ ላይ ቀርበው የሚመገቡት ገበታ በመሆኑ የፍቅር ማዕድ ያስብለዋል።
ሻፌታ የሙሉነት ተምሳሌትም ነው። ምክንያቱም ተዘጋጅቶ ሲቀርብ በምንም ምክንያት ጎድሎ እንዲቀርብ አይደረግም። ሁሌም ከአፍ እስከአፉ ጢም ብሎ ተሞልቶ ነው የሚቀርበው።ጎዶሎ ማቅረብ በባህሉ እንደነውር የሚቆጠርበት ነው። ሻፌታ የሚቀርብበት ድግስም ይሁን የመጣ እንግዳ እንደ ገዳም ወይም ሙሉ ፍቅርና አክብሮት ያለው ተደርጎ ይወሰዳል። ሁሉ ነገር ሙሉ ይሆናል ተብሎም ይታመናል።
ሻፌታ አቃፊ ነው። በጣም ትልቅ ስለሆነ ለጥቂት ሰው አይዘጋጅም ወይም አይቀርብም።የሚቀርበው በጣም ብዙ ሰው ባለበት ነው። ሁሉም ፆታ፤ ዘር፤ ሀይማኖት፤ ዕድሜ ሳይለይ በሻፌታ ዙሪያ ክብ ሰርቶ እስኪጠግብ ድረስ በእኩልነትና በነፃነት ይመገባል። በሻፌታ ገበታ ላይ ማንም ወደኋላ እንዲቀር አይፈቀድም፤ ርቆ መቀመጥም ክልክል ነው። እንደአንድ ቤተሰብ ልጆች ፆታ፤ ዘር፤ ሀይማኖት፤ ዕድሜ ሳይገድባቸው በደስታ ጠጋ ብለው ይመገቡበታል።
ሻፌታ ለሁሉም የሚበቃ መሆኑም ሌላው መለያ ባህሪያቱ ሲሆን፤ በሻፌታ ገበታ ላይ ብዛት ያለው ሰው ቢቀርብም ለማንም አይገደብም። እስኪጠግብና እስኪበቃው ድረስ እንደልቡ መብላት ይፈቀድለታል። ለማንም ደግሞ አያንስም፤ ሁሉንም እኩል ያስተናግዳል።
ሻፌታ የክብር ምግብ ነው። ምክንያቱም በሲዳማ ባህል ሻፌታ የሚዘጋጀው በጣም ተወዳጅ ለሆነና ለክብር እንግዳ ነውና። ምግቡም ተወዳጅና ክብርን ይፈልጋል።ስለዚህ ለገበታ የቀረበ ሰው ብዛት ያለው ቢሆንም ምግቡ ሲጀመር አንድ ሰው አይደለም የሚያስጀምረው። ሁሉም እኩል በአንድ ላይ በሁለቱም እጃቸው ይቆርሳሉ። ይህም የሚያሳየው በሻፌታ ላይ ታላቅ፤ ታናሽ፤ ወንድ፤ ሴት የሚባል ነገር አለመኖሩን ነው።መስፈርቱ የሰው ልጅ መሆን ብቻ ነው። ስለዚህ ሁሉም እኩል ስለሆነ በእኩልነት ይስተናገዳል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው