ማንኛውም ሰው ማንበብ አለበት፡፡ የሰው ልጅ ምግብ ሳይመገብ እንደማይኖር ሁሉ አዕምሮም ክፉውን ከደጉ ለመለየት ምግብ ይስፈልገዋል፡፡ የንባብ ምግብ ማለት ነው፡፡ ያለንባብ ማንም ሰው የትም አይደርስም፡፡ በተለይ ደግሞ አርቆ ማሰብ፣ ነገሮችን በጥልቀት መመርመር፣ ጠያቂ መሆን፣ ታሪክን ማወቅና መረዳትም ሆነ አስተዋይ መሆን አይችልም፡፡ አንባቢ ሕዝብ ሀገሩን በጥበብ ያንፃሉ። በሁሉም ዘርፍ ለማደግ ጊዜ አይወስድበትም፡፡ የማደግና የመለወጥ ዘዴው በእጁ መዳፍ ላይ ነው። ይጠይቃል፣ ይመራመራል፤ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ይሞግታል፡፡ በሀሳብ የበላይነት ይረታል ወይ ይረታል፡፡ ይሄ አለምን የሚያስማማ፣ ሰውን ከሰው የሚያግባባ ነው፡፡ ያለንባብ ሙሉ ሰውነት አይገኝም።
ምክንያቱም የማያነብ ሰው ችኩልና ከጥበብ የራቀ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ በጥንት ጊዜ አባቶቻችን ሳይማሩ ሳያነቡ በተፈጥሮ በታደሉት ጥበብ ቅርሶችን አንጸው እና ጠብቀው፣ ሀገራቸውን አልምተው እንዲሁም አስተዳድረው ኖረዋል፡፡ ሳይማሩ፣ ሳያነቡ ጥበበኞች ነበሩን ብንልም ዛሬ ግን ዘመኑ፣ ቴክኖሎጂው እና የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ግን የሚጠይቀው ያነበበ ያወቀ ትውልድን ነው፡፡ ንባብ ሙሉ ሰው ያደርጋል የሚለው አባባል ነው ተቀባይነት ያለው፡፡ አንብቦ ነገሮችን የሚያገናዝብ ለዛሬ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ ሀሳብ የሚያፈልቅ ትውልድ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ በየአመቱ በየክልሎች እየተዘዋወረ የንባብ ሳምንት እንዲከበር ያደርጋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ‹‹ህዳር ሲታጠን፤ መጽሐፍ ሲተነተን›› በሚል መሪ ቃል በባህርዳር ከተማ የንባብ ሳምንት አካሂዷል፡፡ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ መላኩ አላምረው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ‹‹መጽሐፍት የሚፃፉት ለሰነፍ አንባቢ ነው፡፡ የአሁን ጊዜ ትውልዶች ሰነፍ አንባቢም መሆን አልቻልንም፡፡”ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት” በጥንት ጊዜ ሰዎች ሰማይና ምድርን በማንበብ በገባቸው ልክ ታሪክን ከትበው አስረክበዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገራችን የብዙዎችን ቀልብ ስትስብ ቆይታለች፡፡ እኛ ግን እንደ አባቶቻችን ታሪክ መስራት ይቅርና የአባቶቻችንን ታሪክ ማስቀጠል እንኳን ተስኖናል፡፡ ሀገራችንን እንደ ቀደመው ጊዜ ብዙዎች የሚመኟት ማድረግ አልቻልንም፡፡ ዋናው ችግር ደግሞ ማንበብ አለመቻላችን ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ ሄኖክ ስዩም ‹‹ህዳር ሲታጠን፤ መፅሐፍ ሲተነተን›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጹሑፍ ያቀረበ ሲሆን፤ የህዳር መታጠንና የመፅሐፍ መተንተንን ግንኙነት እንደሚከተለው አስረድቷል። ‹‹የህዳር ወር ወረርሽኝ በሽታ የሚበዛበት ነው። በኢትዮጵያ ታሪክም በአንድ ወቅት በርካታ ሰዎች በህዳር ወር በተነሳ ወረርሽኝ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ታዲያ ወረርሽኙን ለማጥፋት ህብረተሰቡ ቆሻሻን በመሰብሰብ ያቃጥላል፤ አካባቢውንም መልካም መአዛ ባላቸው ቅጠሎች ያጥናል፡፡
ያሁኑ ትውልድም አስተሳሰቡ በመወላገዱ ምክንያት ለሀገር ስጋት ከሆነ ቆይቷል፡፡ ልክ እንደ ህዳር ወረርሽኝ ብዙ ሰዎችን እያጠፋ ነው፡፡ ያላነበበ አዕምሮ ክፉ ነው። በመሆኑም ክፉ አስተሳሰብን ለማስወገድ ልክ ህዳር መልካም መአዛ ባላቸው ቅጠሎች እንደሚታጠነው ሁሉ፤ ክፉ አስተሳሰባችንንም በመፅሐፍት እንጠነው›› ሲል አስረድቷል፡፡ ህዳርን ማጠን ከወረርሽኝ እንደሚከላከለው ሁሉ ማንበብም ከድንቁርና ከክፉነት ያድናል፡፡
በሀገራችን ንባብን የሚያበረታታ የለም ብሎ ለመናገር ያስደፍራል፡፡ አንባቢዎችን ከመንግስት እስከ ወላጅ የሚያበረታታ የለም፡፡ መጽሀፍትንም ከመማሪያ መጽሐፍት ጀምሮ ያለው አይበረታታም። በዚህም የተነሳ ለተለያዩ ፕሮግራሞች ለሰዎች ስጦታዎችን ስናበረክት መፅሐፍትን ግምት ውስጥ አናስገባም፡፡ መጽሀፍትን ስጦታ አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች ካሉም በጣም ጥቂት መሆናቸውን ይናገራል፡፡
‹‹ቢሮዎች ያለ ካፌ አይገነቡም፡፡ ነገር ግን ያለ ቤተመጽሀፍ ይገነባሉ፡፡ ያላነበበ አዕምሮ መልሶ ካፌውን ያፈርሳል›› ይላል ጋዜጠኛ ሄኖክ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ተደራርበው የንባብ ባህል እንዳይኖርና በጠባብ አስተሳሰብ ተሸብሽበን እንድንቀመጥ አድርጎናል፡፡ ትውልዱም የነበረውን መልካም መስተጋብር በመዘንጋት መጨካከንን ልምድ እየሆነ ጥላቻ እየገነገነ መጥቷል፡፡ አዋቂ ሰዎች ዝም እንዲሉ፤ መድረክ እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ምክንያቱም በአስተሳሰብ ያልበለፀገ ሕሊና የቱ መድረክ ለማን ይገባዋል የሚለውን መለየት ስለማይችል ነው፡፡
ይሄ ሁኔታ ያለንን ድንቅ ሀገር ለትውልድ ማስተላለፍ እንዳንችል እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ ንባብ ውጤታማ አድርጎኛል የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ፤ የተሳካና ተወዳጅ ስራ ለመስራት ማንበብ ወሳኝነት እንዳለው ይናገራል፡፡ ባለማንበባችን ሙሉ ሰው መሆናችን ቀርቶ ሰው መሆን አቅቶናል፡፡ የሰውነት ትርጉሙ ጠፍቶብናል፡፡ አልኮልና የመፅሐፍት ዋጋ እኩል በሆነበት ሀገር ሁሉም አልኮል መጠጣትን ሲያስቀድም መፅሐፍት ለመግዛት የሚያስብ የለም። እንዲህ አይነት ትውልድ ተይዞ ሀገርን አንድ ማድረግ አይቻልም የሚል ሀሳብ አለው፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ማንበብን የሚያበረታቱ በመሆናቸው ብዙ አንባቢያንና ደራሲያንን ፈርተዋል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ‹‹ምላስና ምራቅ›› ያለው ሁሉ ጋዜጠኛ ሆኖ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች በርካታ ችግር ያለባቸው ከመሆናቸውም በላይ ለሕዝብ የሚያስተላልፉትን መረጃ ከየት እንዳገኙት መጥቀስ ግዴታ እንዳለባቸው እንኳን አይረዱም፡፡ ይህም የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ ስላለው መገናኛ ብዙሀን ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡ በመንግስት በኩል ትውልድን ሊጠቅሙና ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን በመለየት ትውልድ ቀረፃ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ድጎማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
“በደርግ ዘመን መንግስት ለንባብ ከፍተኛ ቦታ ይሠጥ ስለነበር ወጣቱ አንባቢ ነው፡፡ ወታደሮች ከወርሀዊ ደመወዛቸው እየተቆረጠ በስልጠና ቦታቸው ከባሩድ ሽታ ጋር ያነቡ ነበር፡፡ ሀገር ወዳድ ትውልድ መፍጠር ተችሎ ነበር፡፡ በአሁን ጊዜ ደግሞ ብዙ ሰዎች አሜሪካ የተሻለች ሀገር ስለሆነች ለመሄድ ብዙ መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ብርቅ መሆን የቻለችው በሚያነቡ ሰዎች ስለተገነባች ነው፤ ስለዚህ የሚሰደደውን ትወልድ ለማስቆም ንባብን ባህል በማድረግና ከግጭት የፀዳች ሀገር በመፍጠር ብዙዎችን መሳብ ይቻላል”ይላል፡፡
ጋዜጠኛ ሄኖክ እንደሚለው አለማንበብ በሽታ ነው፡፡ ይህን በሽታ ለመከላከል ደግሞ ለቲቪና ለካንሰር የምናወጣውን ወጪ ያህል ሳናወጣ ንባብን ወደ ሕብረተሰቡ ማስረፅ ይቻላል፡፡ ያነበበና ያወቀ ትውልድ ጤናውን ይጠብቃል፡፡ ነገር ግን እውቀት ማጣት በቅድሚያ ግለሰብን፣ በመቀጠል ሀገርን ያጠፋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እውቀት ሀገርን አስጠብቆ የማቆያ ሚስጥር ነው፡፡ የንባብ ልምድ ያለው ሰው ጠንካራ የሆነ የሞራል ስብዕና ይገነባል፡፡ ምክንያታዊ ትውልድ እንዲፈጠር በማድረግ ሞጋችና በሀገሩ ጉዳይ ለምን ባይ ትውልድን ይፈጠራል፡፡ እንዲሁም ያለማጥፋት መንገድን ይከተላል፡፡
ብዙ ችግሮቻችን እውቀት ከማጣት የመነጩ መሆናቸውን የሚናገረው ጋዜጠኛ ሄኖክ አሁን የሚስተዋሉ ለሀገራችን የማይመጥኑ ነገሮችን የምንፈታው ከንባብ በምናገኘው እውቀት ነው። ሀገር የሚሰራው በሰው ነው፤ ሰዎች የሰሩትን ሀገር መመኘት ብቻ ሳይሆን እንደሰው ሀገራችንን ማነፅ አለብን፡፡ ባለማንበባችን ከአለም አንሰናል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ሀገሩን መጠበቅ የሚችለውም የእውቀት ባለቤት ሲሆን ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል ሲል አስረድቷል፡፡
ከግማሽ በላይ የሀገሪቱ የሕብረተሰብ ክፍል መፃፍና ማንበብ በማይችልበትና የንባብ ባህል በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማሸጋገርም ይሁን ሰላምን ማምጣት አስቸጋሪ መሆኑ የሚገልፁት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ማረው አለሙ ናቸው። ዶክተር ማረው ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ባቀረቡት ትንታኔና መደምደሚያ መረዳት የምንችለው ኢትዮጵያ ከ 100 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚኖርባት አገር ብትሆንም አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መፃፍና ማንበብ አይችልም፡፡ ይህም እንዳለ ሆኖ በቀለም ትምህርት ያለፈው እና ሳይንሳዊውን ትምህርት የቀሰመውም ቢሆን በየጊዜው እራሱን ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር የማያገናዝብ እና የማንበብ ልምድን ባለማዳበሩ ምክንያታዊ የሆነ ትውልድን መፍጠር አልተቻለም።
የንባብ ባህልን ያልዳበረ ትውልድ ለሀገር ግንባታና ለሰላም እጦት ምክንያት ከመሆኑም በላይ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አቅም እንደሌለው በጥናታቸው ላይ ያገኙትን ውጤት ተንተርሰው የሚጠቅሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ብልፅግናና እድገት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይናገራሉ፡፡
እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ የማያነብ ሕብረተሰብ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት ከመፍታት፣ በጥልቀት ከማሰብና ከመመርመር ይልቅ በስሜታዊነት መመራት ይቀናዋል፡፡ ማንበብ የመጠየቅን ፍላጎትን ያሳድጋል፤ ለሀገር እድገትና ለሰላም ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ በተለይ ተማሪዎችና ወጣቶች ንባብን ልምድና አንዱ የሕይወታቸው አካል በማድረግ በጭፍን መረጃ ከመውሰድ ተላቀው አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሆን ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡
ይህን ሀሳብ እና የጥናት ውጤት ደራሲና መምህር ኃይለመለኮት መዋዕለ ይጋሩታል። ‹‹የተሟላ ሰው ለመሆን ማንበብ ወሳኝነት አለው›› በማለት ማንበብ የሕይወት ብርሀን መሆኑን በጠንካራ ቃላቶች ያስቀምጡታል፡፡ የአንድ ሀገር ትልቅ ሀብት መፅሀፍትና አሰላሳይ አንባቢያን ናቸው የሚል አመለካከትም ያንፀባርቃሉ፡፡ ‹‹አንባቢ ሕዝብ ካለ ሀገር ትገነባለች፤ የችግሮች ሰለባ አትሆንም›› እያሉ አገር እና የአገር ብልፅግናና ከፍታ ከመፅሀፍ ውስጥ እንደሚፀነስ ይነግሩናል፡፡
መጽሐፍትን ማንበብ የእውቀት መነሻና መድረሻ በመሆኑ ወጣቱ ሊያዘወትር ይገባል የሚለውን ሀሳብ በወጣቱ ውስጥ እንዲሰርፅ ይሻሉ፡፡ የንባብ ልምድን ባለማዳበራችን ‹‹የአስተሳሰብ ድሀ ከመሆንም በላይ ልዩነታችን ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የእርስ በእርስ ችግር ውስጥ ገብተናል›› በሚል እንደ እሳት የሚምቦገቦግ ቁጭት ከፊት ገፅታቸው ላይ እየተስተዋለ የንግግራቸውን አፅንዖት ጉልህ አድርጎ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዩ ደግሞ የወጣቱ የንባብ ባህል ባለማደጉ እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር እየደረሰ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ትውልዱ አንባቢ ባለመሆኑ በአስተውሎት ከመመርመር ይልቅ በሀሰተኛ መረጃ እየተመራ ለሀገር አንድነት እንቅፋት እየሆነ ነው የሚል ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ በተለይ ጥራዝ ነጠቅ በሆኑ ፀሀፊዎች በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ብቻ የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎችን ይዘው በግብታዊነት ያለምንም ማረጋገጫ እንደ እውነት መያዛቸው ያሳስባቸዋል። የተሟላ መረጃ ለማግኘት አንባቢ መሆን አንዱና ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ሳይጠቁሙ አያልፉም፡፡ ‹‹ወጣቱ ባለማንበቡ የእውቀት ባለቤት ካለመሆኑም በላይ እንዳያስብና እንዳይጠይቅ ሆኗል›› የሚለውን እሳቤ እርሳቸውም ይጋሩታል፡፡
‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ታይተው የማይታወቁ እኩይ ተግባሮች እየተፈፀሙ ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ለሀገር ግንባታ ከወጣቱ ብዙ ነገር ይጠበቃል ይላሉ፡፡ ወጣቱ ንባብን በማዳበር ስሜታዊነትን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት በመቋጫቸው ያሰመሩበት ሀሳብ ነው፡፡
አንባቢ ትውልድ የእውቀት ምንጭ ነው። ያለፈውን ታሪክ ያውቃል፤ የአሁኑን ይረዳል፤ ስለመጪው ጊዜ ይተነብያል፡፡ እያንዳንዱን ጉዳይ ይመረምራል፡፡ በምክንያት ላይ የተመሰረተ ሀሳቡን ለትውልዱ ያሳውቃል፣ ከጥፋት ይቆጠባል፤ የጠፋውን ያርማል፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ አለም በደረሰችበት የዕድገት ዘመን ላይ ይደረሳል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2012
ሞገስ ፀጋዬ