አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች አዲስ ሥራ ለመጀመር በሚያስቡበት ወቅት በቀና መንገድ ተመልክተው ድጋፍ እንደሚያደርጉ በርካቶች ይናገራሉ። የተረጋጋው ስብዕናቸው ለተሻለ ስኬት እንዳደረሳቸው ደግሞ የሚያው ቋቸው ይመሰክራሉ። በዱቤ እቃዎችን ተረክቦ ከማከፋፈል የተነሳው የንግድ ህይወታቸውን አሁን ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት እያንቀሳቀሱበት ይገኛል።
አቶ ወንድወሰን ሃብታሙ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው አዳማ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው ሦስተኛ ልጅ ናቸው። በልጅነታቸው ደግሞ ብዙም ሥራ አይበዛባቸውምና ኳስ መጫወትን ያዘወትሩ ነበር። ይሁንና ከስፖርቱ ይልቅ ሲያድጉ የህክምና ሙያተኛ ሆነው ማገልገል ነበር ምኞታቸው።
አባታቸው በመንግሥት ሥራ ምክንያት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይሰሩ ስለነበር በዝውውር ወደምንጃር ሸንኮራ ተመድበው እንዲሠሩ ሲደረግ ቤተሰባቸውንም ይዘው ተጓዙ። አቶ ወንድወሰንም ወደምንጃር ሸንኮራ ሄደው ቀኛዝማች መኩሪያ ወልደስ ላሴ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ ግን ምንጃር ሸንኮራ የነበረው ቤተሰው ወደአዳማ በመመለሱ እርሳቸውም በተወለዱባት አዳማ ከተማ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
የጤና መኮንኑ
ሁለተኛ ደረጃ እንዳጠናቀቁ ደግሞ በጤና ረዳትነት ወደ ሻሸመኔ የህክምና ማሰልጠኛ የሚገቡበት እድል ተፈጠረ። በማሰልጠኛው የጤና ረዳትነት ትምህርት ለሁለት ዓመታት ተከታትለው እንዳጠናቀቁም አዳማ ከተማ ዙሪያ በሚገኝ አንድ ውስጥ መመደባቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ በጤና ጣቢያዋ የነበሩት ባለሙያዎች እርሳቸውን ጨምሮ አራት ብቻ ስለነበሩ ከጤና ረዳትነት ሥራቸው ባለፈ እናቶችና ህፃናት ህክምናዎች ላይና በአዋላጅነት ጭምር በመስራት ለአምስት ዓመታት እንዳገለገሉ አይዘነጉትም።
በሥራ ላይ እያሉ ደግሞ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለተጨማሪ የትምህርት ዕድል በአሁኑ ወቅት ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተሰኘው ተቋም መግባት የሚያስችላቸው አጋጣሚ ተፈጠረ። ይሁንና የእርሳቸው ፍላጎት የጤና ትምህርትን መከታተል ቢሆንም ቅሉ የተመደቡት በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል በመሆኑ ደስተኛ አልነበሩም። በዚህ ምክንያት ሁለተኛ ዓመት ላይ ትምህርቱን አቋርጠው በራሳቸው ወጪ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ህይወታቸውን ለመቀጠል ወሰኑ። የፋርማሲስትነትን ሙያ እየተከታተሉ በጎን ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ሥራ ባለው የጅማ ግብርና ኮሌጅ የተማሪዎች ክሊኒክ ኃላፊ ሆነው ይሰሩ ጀመር። ቀን በክሊኒኩ የተለመደ ስራቸውን ሲከውኑ ውለው ማታ ደግሞ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አምስት ዓመታትን በጽናት አሳለፉ።
የሽያጭ አስተባባሪነት
ከምረቃ በኋላ ግን በቀጥታ ያመሩት ወደአዲስ አበባ ከተማ ነበር። በአዲስ አበባም ላቦራ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በተሰኘ የህክምና አስመጪ ድርጅት ውስጥ በሽያጭ አስተባባሪነት ተቀጥረው መስራት እንደጀመሩ ያስታውሳሉ።
በሽያጭ አስታባባሪነታቸው የሌሎች ባለሙያዎችን ሥራ ሲከታተሉ እርሳቸው ደግሞ የተለያዩ የህክምና መገልገያዎችን በማሻሻጥ ኮሚሽንም ያገኙ ነበር። በስራቸው ደግሞ የተደሰቱት የድርጅቱ ባለቤቶች አቶ ወንድወሰን ማበረታታቸውን ቀጥለዋል። አቶ ወንደወሰን ግን የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የድርጅቱን ዕቃዎች በዱቤ እየተረከቡ ለደንበኞች ለማከፋፈል በማሰብ ስራቸውን ለመልቀቅ ፈልገዋል።
በዚህ መሃል አሰሪያቸው አቶ ወንድወሰንን ለማቆየት አራት ጊዜ ያህል የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ ደመወዛቸውን 5ሺ500 ብር አደረሱላቸው። አቶ ወንደወሰንም በጎን የፋርማሲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ዲግሪያቸውን ያዙ፤ አንድ የቤት መኪና በአነስተኛ ዋጋ ገዝተውም እየተዘዋወሩ የድርጅቱን ምርቶች መሸጡን ተካኑበት።
ለሦስት ዓመታት ተኩል በድርጅቱ እንደሰሩ ግን የህክምና እቃዎችን በራሳቸው ፈቃድ እያቀረቡ ለመስራት መወሰናቸውን ለላቦራ ኃላፊ ሲገልጹ በምላሹ እርሳቸው ደግሞ በዱቤ እቃዎችን በቅናሽ ዋጋ እንደሚያገኙ ተነግሯቸው በመልካም ፈቃድ ስራቸውን ለቀቁ።
የግል ሥራ ጅማሮ
ቀድሞ ሲሰሩ ያጠራቀሟትን ጥቂት ገንዘብ በመያዝ ቄራ አካባቢ ከ12 ዓመታት በፊት በሦስት ሺህ ብር ቢሮ ሲከራዩ የቀድሞ አሰሪያቸው ደግሞ ጠረጴዛ እና ወንበር በስጦታ ተበረከተላቸው። በወቅቱ ደግሞ የህክምና መሳሪያዎችን ለመነገድ ከባለቤቱ በተጨማሪ ተጨማሪ ባለሙያ ያስፈልግ ነበርና በ700 ብር አንድ ፋርማሲስትና ጥበቃ በ400 ብር ቀጥረው መስራት ጀመሩ። ከቀድሞ አሰሪያቸው የ25ሺ ብር የላብራቶሪ መሳሪያዎችን በዱቤም ተረክበው ሎፋ ፋርማሲውቲካል የተሰኘ ድርጅት ከፍተው መስራቱን ተያያዙት።
አቶ ወንደወሰን ብድራቸውን ለመክፈል የወሰደባቸው ጊዜ ሁለት ወራት ብቻ ነበር። እናም በትርፋቸው ሌሎች መሳሪያዎችን በመግዛትና በዱቤ ተጨማሪ የህክምና እቃዎችን በመረከብ እየተዘዋወሩ መሸጡን ቀጠሉበት። እራሳቸውን የግዥ ባለሙያ ሆነው፤ እራሳቸው እየተሸከሙም፤ እያደረሱም የሚሰሩት እኝህ ሰው፤ የተለያዩ የህክምና መገልገያዎችን ከአስመጪዎች ላይ በመቀበል ለተጠቃሚው በመሸጥ ትርፋቸውንም እንዳያሳድጉ ምንም አላገዳቸውም።
ስራቸው እያደገ ሲመጣ ደግሞ አንድ ተጨማሪ ለእቃ ማጓጓዣ የሚሆን ተሽከርካሪ ገዝተው ሹፌር ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ። እንዲህ እንዲህ እያሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ደንበኞቻቸውን በማስተናገድ የንግዱን ዓለም በስፋት ገቡበት።
ወደአስመጪነት
የንግድ አቅማቸውም ጠንከር እያለ ሲመጣ ደግሞ አንዳንድ ደንበኞቻቸው ደግሞ በከተማው ውስጥ ያጧቸውን የ ህክምና መሳሪያዎችን እንዲያፈላልጉና እንዲያመጡላቸው ሲጠይቁ ለምን ከውጭ ሀገራት እያስመጣሁ አልሸጥም የሚል ሃሳብ እንደመጣላቸው ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት የአስመጪነት ፈቃድ አውጥተው በመጀመሪያ ቢያስገቧቸው ስለሚያስፈልጉ ምርቶች ጥናት አካሄዱ። ቢሯቸው ውስጥ የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች ላይ የተለጠፉ አድራሻዎችንም በመመልከት ከአምራቾቹ ጋር በኢሜይል ግንኙነት እንደፈጠሩ ያስረዳሉ።
ከአምራቾቹ ጋር ከተስማሙ በኋላ አፍሪ ሜድ ብለው በሰየሙት የአስመጪ ድርጅታቸው አማካኝነት የተወሰነ የህክምና ዕቃዎችን ወደማስመጣቱ ተሸጋገሩ። በአስመጪነታቸው ህንድ እና ቻይና ድረስ በመሄድና ማምረቻ ፋብሪካዎቹን በአካል ተገኝተው በመጎብኘት ለኢትዮጵያ የሚስማማውን መገልገያዎች በማሰራት ወደሃገር ውስጥ እንዳስገቡ ይናገራሉ።
በተለይ የአጥንት ህክምና ዕቃዎች፣ የህክምና ማስተማሪያ አካላት ላይ በማተኮር ለበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችንና የህክምና ተቋማትን ምርቶችን አቅርበዋል። አሁንም የህሙማን ተጣጣፊ አልጋዎችን እና ‹‹ስፔሻል ፕሮቲን አናላይዘር›› የተሰኘ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን እያስመጡ ይሸጣሉ።
‹‹የህክምና ዕቃዎች ንግድ ከትርፉ በተጨማሪ ለጤናው ዘርፍ የሚያበረክተው አገልግሎት ትልቅ ነው›› የሚሉት አቶ ወንድወሰን፤ ሰዎች ለጤናቸው የሚገለገሉባቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች በማቅረባቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን ነው የሚናገሩት። የሉም የተባሉ አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎችንም በማቅረብ ጭምር ከንግድ ጥቅም በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎቱን ላይም እየተሳተፉ መሆናቸውንና በዚህ የተነሳ በከተማው ውስጥ የጠፉ መሳሪያዎች ካሉ እርሳቸው ጋር አይጠፋምና ካለ ፈልጉ እስኪባል ድረስ ጥሩ ስም ማትረፋቸውን ያስረዳሉ።
እራሳቸው ከሚቆጣጠሩት የአስመጪው ድርጅታቸው በተጨማሪ ሎፋ የተሰኘውን ድርጅታቸውን ደግሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሥራሽወርቅ አሰፋ እያስተዳደሩ ጥሩ የትዳር አጋር ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የንግድ ሰው መሆናቸውንም እያሳዩ ይገኛል። አቶ ወንደወሰን በሁለቱም ድርጅታቸው ውስጥ በአጠቃላይ 23 ቋሚ ሰራተኞችን ቀጥረው ያሠራሉ። እቃዎች ሲገቡና ሲወጡ ደግሞ እንደየአስፈላጊነቱ ቁጥራቸው የሚጨምሩ ጊዜያዊ ሠራተኞች በመኖራቸው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ጠንክረው በያዙት የህክምና ዕቃዎች ንግድ የራሳቸው ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ወንድወሰን፤ በስራቸው አማካኝነት ስድስት የሥራ ተሽከርካሪዎች እና አንድ የቤት መኪናም ባለቤትም መሆን ችለዋል። ምርቶቻቸውም ከአሶሳ እስከ አክሱም፣ ከሐረር እስከ ጅግጅጋ እና ጋምቤላ በሚገኙ ተቋማት ግልጋሎት ላይ ናቸው። በተጨማሪ በአዳማ ከተማ ባለ ሦስት ወለል ህንጻ ላይ ክሊኒክ ከፍተው እየሰሩ ይገኛል።
እርሳቸው ስራውን ሲጀምሩ የቀድሞ አሰሪያቸው እንደደገፏቸው ሁሉ አቶ ወንድወሰንም አብረዋቸው የሰሩ ወጣቶች የህክምና መሳሪያዎችን በግላቸው ወደመነገዱ ሲሸጋገሩ ደግሞ ሁልጊዜም በቀናነት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አብረዋቸው የሚሰሩ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
በተለይ ከእርሳቸው ጋር ሲሰሩ የነበሩ 11 ወጣቶች አሁን ላይ የእራሳቸውን ንግድ ጀምረው መሳሪያዎቹን ከአስመጪዎች እየተረከቡ በማከፋፈል ላይ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንደኛው ነጋዴ ወደሥራ ሲገባ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገውለት እንደነበርና አሁን ላይ ወደአስመጪነት ደረጃ በመሸጋገሩ ደስታ እንደሚሰማቸው ይነገራሉ።
የህክምና መሳሪያዎች እጥረት ባለባት ሀገር በዘርፉ የበኩሌን መወጣት መቻሌ ለእኔ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖኛል የሚሉት ነጋዴው፤ ከዚህ ባለፈ ግን በልብ ህመምና በኩላሊት ዲያሊሲስ የህክምና ዕቃዎች እጥረት ሰዎች ተቸገሩ ሲባል ብዙ ትርፍ ባይገኝበት እንኳን መሳሪያዎቹን ስለማምጣት እንደሚያስቡ ይናገራሉ።
ቀጣይ ውጥኖች
ቀጣይ እቅዳቸው ደግሞ የህክምና መገልገያዎችን ከውጭ ሀገራት ከማስመጣት ባለፈ እዚሁ ሀገር ውስጥ የሚፈበረኩበትን መንገድ ስለማመቻቸት ነው። ለዚህም እንዲረዳቸው በሱሉልታ ከተማ 1ሺህ500 ካሬ ሜትር ቦታ ገዝተው ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ለህክምና እቃዎች ከሚያመርቱ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገርም አብረው ስለሚሰሩበት መንገድ ውይይት በማድረግ ጥናት በማካሄድ ላይ ናቸው። ፋብሪካው ዕውን ሲሆንም የውጭ ምንዛሬ ወጪን ሊቀንሱ የሚችሉ ከህክምና መማሪያ ቁሶች ጀምሮ የተለያዩ መሳሪያዎችን ወደማምረት እንደሚሸጋገሩ ተስፋ ሰንቀዋል።
ወደአምራችነት ከመሸጋገሩ ባለፈ ደግሞ ትልቅ የህክምና ተቋም ገንብተው መስራት የሚፈልጉት አቶ ወንድወሰን፤ በተወለዱባት አዳማ ከተማ ያቋቋሙትን ክሊኒክ ወደሆስፒታል ደረጃ የማድረስ እቅድ አላቸው። ክሊኒኩ በአሁኑ ወቅት እየሰጠ ከሚገኘው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ትልቅ ሆስፒታል አድርገው ለመስራት የሚያስችላቸውን የገንዘብና የመሳሪያ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል።
ከዚህ ሁሉ ሥራ ባሻገር ደግሞ ንግድን እየከወኑ መማርም እንደሚቻል በተግባር በማሳየት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚ ኒስትሬሽን ዘርፍ መከታተል ችለዋል። በትም ህርት ቆይታቸው ወቅት ደግሞ የሰሩት ጥናት በህክምና እቃዎች ሽያጭ ወቅት ደንበኛ ለመሳብ ስለሚቀርቡ የስጦታ እቃዎች የገበያ ተጽዕኖ ላይ ያተኩራል። ጥናቱም ላምበርት በተሰኘው ጥናት አቅራቢ ተመርጦ በአማዞን የኢንተርኔት ገበያ እንዲቀርብ በመደረጉ ከጽሁፉ ሽያጭ ወደፊት ገንዘብ የሚያገኙበት እድል ተመቻችቷል።
ይህ ሁሉ ስኬት የመጣው ከጠንካራ ሥራ ጋር በታጀበ የንግድ እንቅስቃሴ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ወንድወሰን፣ ማንኛውም ሰው በአዕምሮው ያለውን የሥራ እድል ወደተግባር ለመቀየር ሳይፈራ በትጋት ቢሰራ ውጤታማ መሆኑ አይቀርም ይላሉ። አንድ ቀን ያለሙት ቦታ ላይ ለመገኘት ዛሬን በሥራ ማሳለፍ ትልቅ ስንቅ በመሆኑ ወጣቱም ጊዜውን ሳያባክን ንግዱን ቢቀላቀል ውጤታማ መሆን ይችላል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
ጌትነት ተስፋማርያም