የአማራ ክልል ፍ/ቤት ዳኞች የሙያ ማህበር በባ/ዳር ከተማ ተመስርቷል፡፡
የማህበሩ ዋና ዓላማ በክልሉ የሚገኙ ፍ/ቤቶችን እና ባለሙያዎችን አቅም በማጠናከርና በማሳደግ የባለሙያዎችን ጥቅምና ደህንነት በማስከበር ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም ነፃና ጠንካራ የዳኝነት ስርዓት እንዲኖር መስራተ መሆኑን የማህበሩ አስተባባሪ አቶ ፈቃዱ አንዳርጌ ተናግረዋል።
በምስረታ በዓሉ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ኘሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ የክልሉ ፍ/ቤት ዳኞች የሙያ ማህበር መቋቋሙ ፋይዳው ለዳኞች ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች እና በዳኝነት አገልግሎት የሚታዩ ክፍተቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት፣ ዳኞች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ፣ የዳኝነት ነፃነት በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር እና ፍ/ቤቶች ራሳቸዉን ችለው እንዲቆሙ ያስችላል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ፍ/ቤት ዳኞች የሙያ ማህበር በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ነፃ፣ ጠንካራና ገለልተኛ ፍ/ቤቶች እንዲኖሩ፣ ተቋማዊ አሰራር እንዲዳብር እና ለአሁኑ ትውልድ ብቻ በቂ የሆነ የፍትህ ጥያቄ የሚመልስ ሳይሆን ለቀጣዩም ትውልድ አስቦ የሚሰራ ኃላፊነት የሚሰማው ማህበር ይሆናል ሲሉ አቶ የኔነህ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የዜጐችን የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የዳኝነት ሙያና ተቋማዊ ነፃነት እንዲከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ከጐኑ ሆኖ እንደሚሰራ አቶ የኔነህ አክለው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም 15 አባላት ያሉት የክልል ስራ አስፈፃሚ የተመረጡ ሲሆን አቶ ፀጋየ ወርቅአየሁ ኘሬዝዳንት፣ አቶ ፈቃዱ አንዳርጌ ምክትል ኘሬዝዳንት አቶ ሀይለየሱስ ተስፋማረያም ፀኃፊ ሆነው መመረጣቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡