በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከ 1940 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠት እንደተጀመረ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዘመኑ ስልጣኔ እያደገ የመጣበት ወቅት እንደመሆኑ በርካታ ሙያዎችም እያደጉ የመጡበት ዘመን ነበር። በተለይ በምን አይነት መንገድ የክህሎት ሽግግር ይደረግ ነበር የሚለውን ስንመለከት ባህላዊ የአሰለጣጠን ሂደት ይከተሉ እንደነበር ይነገራል። ከዚህ አንጻር በክህሎት ሽግግር መንገድ እንኳ ብንመለከት ለሌሎች አገራት ሞዴል መሆን በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደነበርንም ይነገራል።
ነገር ግን ለሙያ ነክ ነገሮች ህብረተሰቡ የሚሰጠው ትኩረት እና ሙያውን ከማሳደግ አንፃር ክፍተቶች ነበሩበት። አገሪቱ የስልጣኔ ባለቤት እንድትሆን ያደረጓት በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ ባህላዊ ቤት አሰራሮች፣ የሸማና የሸክላ ስራ፣ የብረታ ብረትና የአንጥረኝነት ሙያ እንዲሁም ባህላዊ ህክምና መመልከት በቂ ነው።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ሰሞኑን በአገሪቱ ስላለው የቴክኒክና ሙያ ትም ህርትና ስልጠና ሁኔታ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ‹‹የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ከየት ወዴት›› በሚል መወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ ኃይለሚካኤል አስራት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናው አጀማመር፣ ከግብዓት ተኮር እስከ ውጤት ተኮር እንዴት እንደተሻገረ በዝርዝር አቅርበዋል።
ቴክኒክና ሙያ ስልጠና አጀማመር
በ1940ዎቹ አካባቢ አገሪቱ ከተለያዩ አገራት ጋር ከነበራት ጠንካራ ግንኙነት እና ከጣሊያን ወረራ ጋር ተያይዞ ግብዓት ተኮር የሆነው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተጀመረ። ስልጠናው በተቋማት ደረጃ ሲጀመር ዘገምተኛ ቢሆንም ህብረተሰቡን ለማዳረስ ተሞክሯል። ከ1972 እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መልሶ ማደራጀትና ማጠናከር ተጀመረ። በዚህም እንደ አገር አስራ ሰባት በተለያየ ሙያ የአስር
ሲደመር ሶስት (10+3) ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት የተደራጁበት ጊዜ ነበር። በተጨማሪም በወቅቱ የክህሎት ስልጠና የሚሰጥባቸው 25 ተቋማት ተከፍተው ስራ ጀምረዋል። ከ1993 እስከ 1999 ዓ.ም ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፖሊሲ ተቀርፆ እራሱን የቻለ የትምህርት አሰጣጥ ተጀመረ። በ1995 ዓ.ም የትምህርት ስትራቴጂ ተነድፎና በአዋጅ ተደግፎ ለዜጎች ስልጠናው የተዳረሰበት ወቅት ነበር። ይህ ሁኔታ ከባህላዊ አሰለጣጠን ዘይቤ ተወጥቶ ወደ ግብዓት ተኮር እንዴት እንደተሻገረ ያሳያል።
የቴክኒክና ሙያ አሰለጣጠን ውጤት ተኮር መሆን
ውጤት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና 1999 ዓ.ም ላይ እንዲጀመር ተደረገ። ከግብዓት ተኮር ወደ ውጤት ተኮር ሽግግር ሲደረግ በዋነኝነት ስልጠና የሚሰጠው የገበያውን ሁኔታ መሰረት ተደርጎ ነው። በስራ ቦታው ላይ የሚፈለገው ሰው በአይነት፣ በደረጃ እና በቁጥር ምን ያክል መሆን እንዳለበት ግምት ውስጥ የሚገባ ሲሆን ይህ አሰራር ለኢንዱስትሪ እድገት መሰረት ሆኗል። በሌላ በኩል ተቋማትን የሚመሩ አመራር የብቃት ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ማሰልጠኑ ገብተዋል።
የውጤት ተኮር አሰለጣጠን አፈፃፀሙ ሙሉ ለሙሉ በሚፈለገው ደረጃ ያለመተግበር እና ክፍተቶች ያሉበት ቢሆንም በርካታ ስኬቶች ተገኝተውበታል። በውጤት ተኮር ስልጠናው ላይ አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። እነሱም የስራ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ፣ የአሰልጣኞች ልማት፣ የተቋማት አቅም ግንባታ ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ብቃትን መሰረት ያደረጉ ስልጠና መስጠት፣ የሰልጣኞች ልማት በተለይ የስራ ቦታን መሰረት ያደረገ የትብብር ስልጠና ሂደት እንዲሰለጥኑ በማድረግ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲተሳሰሩ ማድረግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ናቸው።
ማንኛውም ሰልጣኝ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ የሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ይወስዳል። ፈተናው ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ልክ ብቁ ስለመሆናቸው የሚረጋገጥበት ሥርዓት ነው። ስልጠናው ግብዓት ተኮር በነበረበት ወቅት ይህ አሰራር ተግባራዊ አልተደረገም ነበር። የውጤት ተኮር ስልጠና ሲጀመር ግን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና መስጠት አስፈልጓል።
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
በዘርፉ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችን በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት ይቻላል። እነሱም የተቋማት ፍትሀዊ ተደራሽነት ችግርና የስልጠና ጥራትና አግባብነት ጉድለት ናቸው። ትምህርትና ስልጠናው በሁለቱ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ይገኛል። ፍትሃዊ ተደራሽነት ሲባል በተለያየ መልኩ መገለፅ ይችላል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከሚፈለገው የሙያ ስብጥር ጋር የተያያዘ ነው። ጥራትና አግባብነት ዙሪያ የግል ዘርፉ እየተሳተፈ አለመሆንም ችግሩን አባብሷል።
እንደ መፍትሄ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዲዋሳ አብዱላሂ እንደገለፁት፣ ዘርፉ አሁን ያለበትን ሁኔታ በማጤን የሚስተካከሉትን በማስተካከል ጥሩ ነገሩን ማስቀጠል ያስፈልጋል። በሌላው አገር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናውን እያንቀሳቀሱ የሚገኙት የግል ዘርፉ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የግል ተቋማት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሎ ሲታይ ጥሩ ጅማሮ ቢኖረውም መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉት። በመንግስት የተሰሩ ጥሩ ስራዎችን በመቀጠል ያጋጠሙ ችግሮችን ደግሞ በምን መልኩ መቅረፍ እንደሚቻል መታየት አለበት።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አብዛኛው በግል ተቋማት መያዝ እንዳለባቸው የጠቀሱት ዶክተር አብዲዋሳ፤ የግል ዘርፉ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ላይ እንዲሳተፍ ሲደረግ ከመንግስት ተቋማት ጋር ተመጋግቦ እንዲሰራ ለማድረግ መሆኑን ያመላክታሉ። የግል ዘርፉ ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ሲገባ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ነቅሶ የማውጣት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ።
እንደ ዶክተር አብዲዋሳ ገለፃ፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ከሁለተኛ ደረጃ የወደቁ ተማሪዎች የሚገቡበት ቦታ ነበር። ይህ አሰራር የተሳሳተ ነው። ችግሩን ለማስተካከል በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ቀድሞ የነበሩ የእጅ ስራ ትምህርቶችን መልሶ የማምጣት እና ተማሪዎች በምርጫቸው ቴክኒክና ሙያ ትምህርት እንዲያገኙ የሚደረግበት አሰራር ተዘርግቷል። ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር ጭምር ያስችላል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2012
መርድ ክፍሉ