በአዲስ አበባ ከ440 በላይ የተመዘገቡ ቅርሶች ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ሃውልቶች ሌሎቹ ታሪካዊ ቤቶች እና ሰፈሮች ሲሆኑ ጥቂት ደግሞ መካነመቃብሮችም በቅርስነት ተመዝግበዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የወላይታው ንጉስ ካዎ ጦና መካነመቃብር ይገኝበታል።
ካዎ ጦና በአዲስ አበባ በ1909 ዓ.ም ካረፉ በኋላ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሞ እቴጌ ጣይቱ በወቅቱ የነበረውን መካነ-መቃብር አሰርተውላቸዋል። መካነ-መቃብሩ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 440 ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ለጎብኚዎችም ክፍት በመሆኑ በርካቶች ታሪኩን ቦታው ድረስ በመሄድ ሊያውቁት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ባህላዊ ቅርሶች ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መክብብ ገብረማርያም ይጋብዛሉ።
የአዲስ አበባው የወላይታ ልማት ማህበር እና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም በጋራ ባዘጋጁት የጉብኝት መርሃ ግብር ሰሞኑን የወላይታ የመጨረሻው ንጉስ ካዎ ጦና መካነ መቃብር በሚገኝበት የአራት ኪሎ በዓለወልድ ቤተክርስቲያን አጠገብ ጉብኝት ተካሂደዋል። በወቅቱ ከ200 በላይ ሰዎች በተገኙበት ጉብኝት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት እና የቱሪዝም ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል።
ንጉስ ካዎ ጦና ማን ናቸው?
በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የወላይታ ህዝብ የራሱ ስርወ መንግስት መስርቶ ለበርካታ ዓመታት በመረጣቸው ንጉሶች ይተዳደር እንደነበር የአካባቢው ታሪክ አጥኚዎች በተለያየ ጊዜ ገልጸውታል። ነገሥታቱም በአጠቃላይ ካዎ(ንጉሥ) የሚል መጠሪያ አላቸው። ወላይታን የመሩት የመጨረሻው ንጉስ ደግሞ ካዎ ጦና ጋጋ ናቸው። እንደ ወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ከሆነ፤ ካዎ ጦና ጋጋ ጦና የቦሻሻ ጋጋ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው።
ካዎ ጦና በልጅነታቸው እንደማንም የነገስታት ልጅ በአያታቸው በካዎ ጎቤ ቤተመንግስት የፈረስ ጉግስ፣አደን፣ባህላዊ የእርሻ አሠራር፣የለቅሶ፣የሰርግና ሌሎችን ባህላዊ ሥርዓቶችን በሞግዚታቸው አቶ ባዳቾ (በኋላ ግራዝማች) አማካይነት ሙሉ እውቀት በማግኘት በድሎትና በእንክብካቤ አድገዋል።
ካዎ ጦና ከልጅነታቸው ጀምሮ በጣም ንቁ ጠንካራ ከመሆናቸው ባለፈ የወላይታ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ባህላዊ ህጎችንና ደንቦችን፣የጦር ስልትን፣አደንና የውሃ ዋናና የእርሻ አሠራርን፣ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትን እንዲሁም የንግድ ሥርዓትን ከሽማግሌዎችና ከባለሙያዎች በጥንቃቄ እንደተማሩ ይነገራል።
የንጉሱ አያታቸው ካዎ ጎቤ በጠና በመታመማቸው እና አስተዳደራዊ ሥራውን በሚገባ መፈጸም ባለመቻላቸው የወላይታ ሁሉንም ጎሳዎች የሚወክሉ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ቤተመንግስት/ካዎ ጋሩዋ/ በመምጣት ንጉሱ ቀጣዩን አዲስ ንጉስ እንዲያስታውቋቸው ይጠይቃሉ። በዚህን ጊዜ ካዎ ጎቤ ልጃቸውን ሀዳሮን እንዲያነግሱ ይነግሯቸዋል። ነገር ግን የወላይታ ሽማግሌዎች በመሉ ድምጽ የታላቅ ልጅ እያለ ታናሽ አይነግስም በማለት ጦናን ከንጉስ ጎቤ ይሁንታ ውጪ በሕዝብ ፍላጎት ብቻ በመስከረም /ግፋታ/ ወር 1866ዓ.ም የንግሥና ቀለበት በማጥለቅ አነገሷቸው።
ነገር ግን ጦና ገና የ12ዓመት ልጅ ስለነበሩ በዎንቤቶ(መስፍን) ሶራቶ ሞግዚትነት ሲመሩ ቆይተው ከሰባት ዓመታት የሞግዚት አስተዳደር በኋላ በሙሉ ኃላፊነት አገር መምራት እንደጀመሩ የብሔሩ አፈታሪክና የተጻፉ የጽሁፍ መረጃዎች ይገልጻሉ። በኋላም ከአጼ ምኒልክ ጋር በተደረገ ጦርነት የወላይታ ንግስናቸው አብቅቷል። ንጉስ ጦና በህይወት ዘመናቸው የወላይታን ህዝብ አንድ አድርጎ በመምራት ለፈጸሙት ተግባር የህዝቡ አንድነት ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉ።
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር