“ ቃሌ ፊርማዬ ነው:: “
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት በመጡ ጥቂት ቀናት ውስጥ በተለያዩ መድረኮችና በብዙኃን መገናኛዎች ስለ ኢህአዴግ ውህደት በልበ ሙሉነትና እርግጠኝነት አበክረው ሲናገሩ ብዙዎቻችን ከልብ ማመን ተቸግረን ነበር:: ሆኖም ውህደቱ አንድ ቀን በተአምር እውን ሊሆን እንደሚችል ብንገምትም እንዲህ በአጭር ጊዜ ለዛውም በየቀኑ የምንሰማው ቅስም ሰባሪ መርዶ አየሩን መልክዓውን በተቆጣጠረበት ሰሞን ይሆናል ብለን ግን አልጠበቅንም::
መልህቃቸውን የጣሉት እና በምንም አይነት ማዕበል የማይናወጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ባለፉት 20 ወራት የሚያዩት የሚሰሙት ሁሉ ፈታኝ ቢሆንም አይናቸውን ከትልቁ ስዕለ ኢትዮጵያ ለአፍታ ሳያነሱ በተለያዩ ጊዜያት ስለውህደቱ አስቀድመው ይህን ብለው ነበር::
– በኢህአዴግ ውህደት የሚፈጠረው አዲስ ፓርቲ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚወከልበት ይሆናል::
– አንድ ሁላችን ያለንበት ኢትዮጵያዊ ፓርቲ በመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚነጋገርበት መድረክ
ይሆናል ::
– እኩል የሚወስንበት ድምፁ የሚሰማበት ከየትኛውም ጫፍ ብቃት ያለው ሰው ለየትኛውም ኃላፊነት የሚበቃበት ሥርዓት ለመፍጠር ለውጡ በትጋት እየሰራ ይገኛል::
– ወደ አንድ ስንመጣ መራገፍ ያለበትን አራግፈን መጨመር ያለበትን እንጨምራለን::
– ሶማሌውም አፋሩም ጋምቤላውም ኦሮሞውም አማራውም በእኩልነት በልማት በዴሞክራሲ ይችን ሀገር ማሸጋገር የሚችል ሃሳብ ያለው ፓርቲ መፍጠር አለብን::
ሆኖም የውህደቱ ጉዳይ ቢያንስ ከኢህአዴግ የ1991 ዓ ም 4ኛው ጉባኤ ጀምሮ ግንባሩን በሂደት ወደ ሕብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ ለማሸጋገር ተወስኖ ነበር:: ከዚህ በፊትም ሆነ ከዚህ በኋላ አምስቱ አጋር ድርጅቶች በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ እስከ መቼ በሀገራችን ጉዳይ ባይተዋር ሆነን እንቀጥላለን ? የሚል ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበር ይታወቃል:: የቀድሞው የሶህዴፓ ሊቀ መንበር አብዱልመጅድ ሁሴን ( ፒ ኤች ዲ) ይህን ጥያቄ ሲያነሱ ከነበሩ የአጋር ድርጅቶች አመራሮች አንዱ ናቸው::
ህወሀት እንዲህ ዛሬ ላይ በ180 ዲግሪ ተከርብቶ ውህደቱን አምርሮ ሊቃወመው በተጋዳላይ ስዩም መስፍን ፊት አውራሪነት የውህደቱ ደጋፊ ነበር:: የሚገርመው ይህን የውህደት ጥያቄ የቀድሞው የግንባሩ ሊቀ መንበር “ ጓድ “ መለስ አጋር ድርጅቶች የሚመሯቸው ክልሎች አርብቶ አደሮች በስፋት የሚኖሩባቸው ስለሆኑ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር መሰረት ሊሆኑ ስለማይችሉ ግንባሩን መቀላቀል አይችሉም ብለው ነበር:: አመክንዮው ውሃ ባይቋጥርም እሳቸው ካሉ አሉ ነበር:: ጫናው ሲበዛና ጥያቄው ሲደጋገም ደግሞ አቋማቸውን አለዝበው ጊዜው ሲደርስ ይፈፀማል እስከ ማለት ደርሰው ነበር::
ሆኖም ህወሀት በ1977 ዓ.ም ወርዒ በተባለ አካባቢ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ን ሲመሰረት ገበሬውን እንጂ ላብ አደሩንና ምሁሩን ታሳቢ መነሻ በማድረግ አልነበረም:: ይህ በአለማችን በገበሬው ላይ ብቻ የተመሰረተ የመጀመሪያው ማርክሳዊ ፓርቲ ያደርገዋል:: በማሌሊት ምስረታ ወቅት በጀርመኑ የማሌ ፓርቲ ተወክሎ መጥቶ የነበረው ካፍካ አንድ ላብ አደር በሌለበት እንዴት ማርክሳዊ ፓርቲ ይመሰረታል በሚል እጅግ ግራ ተጋብቶ እንደነበር አይተ ገብሩ አስራት” ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ “ በሚለው መፅሐፋቸው አስነብበውናል:: ህወሀት ለጊዜአዊ ድርጅታዊ ጥቅም እንጅ ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅምም ሆነ ለመርህ መከበር ግድ እንደሌለውም ጥሩ ማሳያ ነው::
የኢህአዴግ መስመር እንደሆነ ሌት ተቀን ሲለፈፍለት የኖረው “ አብዮታዊ ዴሞክራሲ “ ም በዚህ ወለፈንዲ መንገድ ያለፈ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው:: የቻይናው ኮምኒስት ፓርቲ መስራችና የቀድመው ሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም አድርጎት ማኦይዝም ብሎ ሲነሳ ታሳቢ መሰረቱ ገበሬው ነበር:: ሆኖም ሌኒን ለጥቅምቱ አብዮት እንዲስማማ የርዕዮቱን መሰረት ላብ አደር አድርጎ ቀምሮታል:: ኢህአዴግም ይሄን ድቅል አስተሳሰብ ነው እንዳለ ገልብጦ የወሰደው፡፡ እንግዲህ ይህ እንደ እስስት ተለዋዋጭ ድርጅት በአጋር ድርጅቶች በሚመሩ ክልሎች በስፋት የሚኖረው አርብቶ አደር እንጂ አርሶ አደር ስላልሆ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ታሳቢ መሰረት ሊሆን ስለማይችል የግንባሩ አጋር ድርጅቶች አባል ሊሆኑ አይችሉም በሚል መናኛ አመክንዮ ውህደቱን ለ30 ዓመታት ሲያንከላውሰው የኖረው::
ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በebs ቴሌቪዥን የTeckTalk አዘጋጅ “ ግርምተ ሳይቴክ “ በተሰኘው ድንቅ መፅሐፉ እንዳስነበበን ኢላን መስክ ጊዜንና እርቀትን ሊሽር “ Hyperloop “ን ፈጥሮ በከተሞች መካከል ያለ ጉዞ እጅግ ፈጣን በሰዓት 1ሺህ 126 ኪሎ ሜትር መንጎድ የሚችል እንደቱቦ ባለ በተዘረጋ መስመር ውስጥ ልዩ አይነት መጓጓዣ በፈጠረበት ዘመን እኛ ከግንባር ወደ ፓርቲ ለመለወጥ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ፈጅቶብናል::
ኢህአዴግ በጊዜአዊ የትግል ስልት ማለትም በግንባርነት ለዚህን ያህል ጊዜ መቆየቱ ነገሮቻችንን የምንከውንበት አግባብ ምን ያህል እንደ ኤሊ ቀርፋፋ እንደሆነ አንዱ ተምሳሌታዊ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ከባልደረቦቻቸው ጋር ውህደቱን አጀንዳ አድርገው በትጋት በመስራት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እውን አድርገውታል:: ለዚህም ያለኝን አክብሮት ከመቀመጫዬ ብድግ በማለት ባርኔጣየን ከፍ በማድረግ እገልጻለሁ::
የኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ እንደገና መነሳት ከጀመረ ወዲህ መላው ኢትዮጵያዊ ዳር እስከ ዳር በአንድነት በጥፍሩ ቆሞ በጉጉት ሲጠባበቀው የነበር ጉዳይ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፣ ተፎካካሪ ፣ ደጋፊ ፣ ተሟጋች (አክቲቪስት) ፣ የሃይማኖት መሪ ፣ የሀገር ሽማግሌ ሁሉም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፈታኝ ወቅት የኢህአዴግ ነገር ከድርጅት በላይ ነውና:: ለዚህ ነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “…ውህደቱን በሰላም ማጠናቀቅ ይጠቅማል:: …”ሲሉ አበክረው ያስጠነቀቁት:: አዎ ! በቋፍ ላይ ለምትገኝ ሀገር የኢህአዴግ ሰላም ለእሷም ሰላሟ ነው:: ሰላሙ ሀቀኛ ከሆነ፡፡ በኢህአዴግ ቤት የሚፈጠር ውህደትም ሆነ መርሀዊ አንድነት ለሀገራዊ አንድነት ከቡድ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡
በተቃራኒው በኢህአዴግ ቤት የሚፈጠር አለመተማመንና መጠራጠር እንደ ተስቦ ወደ ሕዝብ ወደ ሀገር ይጋባል፡፡ የግንባሩም ሆነ የእህት ድርጅቶች መሰረት በማንነት ላይ የተጣለ ስለሆነ ይሄ መሰረት በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ሲናጋ በአባላቱና በደጋፊው ከፍ ሲልም በሕዝቡ ዘንድ ስንጥቅ መፍጠሩ አይቀርም:: በዚህ ፈታኝ ሰዓት የሚፈጠር ስንጥቅ ደግሞ ከሌሎች ሰሞነኛ ቀውሶች ጋር ተደምሮ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እጅግ የሚያባባና የሚያስፈራ ያደርገዋል፡፡
የተጀመረውን ለውጥም ሊያጨናግፈው ተስፋችንንም ሊያጨልመው ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለ ውህደቱ አብዝቶ የተጨነቀው የስቶክሆልም ሲንደረም / stockholm syndrome /ሰለባ ፣ ታማሚ ሆኖ አይደለም:: በነገራችን ላይ ሕመሙ ታጋቾች ለአጋቾች የሚሰማቸው አይነት ስነ ልቦናዊ ሀዘኔታ ነው፡፡ በአንድም በሌላ በኩል ወደድንም ጠላንም ተቀበልነውም አልተቀበልነውም አመንም አላመንም ቴክኒካሊ ሁላችንም እስከዛሬ የቀዳማዊ ኢህአዴግ ታጋቾች ነበርን:: ሆኖም ሁላችንም ስለውህደቱ ስንጨነቅ ስንጠበብ የነበረው ለኢህአዴግ በማዘን ሳይሆን ለራሳችን ለሀገራችን ግድ ስለሚለን ነው:: ለዚህ ነው የድርጅቱ ሊቀ መንበር “ ጓድ “ ዐቢይ የብልፅግናን ፓርቲ መመስረት አስመልክተው ፈካ ብለው በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው በሰጡት መግለጫ “ እንኳን ደሳለን ደስ አላችሁ !!! “ ሲሉን በአንድነት “ እንኳን አብሮ ደስ አለን !!! “ ያልነው::
የቀደመውን ፣ ነባሩን ፣ ያለውን status quo ይዞ መቀጠል ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን አይዋጅም፡፡ ይህን ተጨባጭ ነባራዊ እይታ prgmatic view የቻይናው ኮምኒስት ፓርቲ በከፊል ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ቅይጥ በመቀየር ፣ የአሜሪካዊ ሪፐብሊካን በትራምፕ ጎታችነት ወደ ቀኝ አክራሪነት በመሳብ ተግብረውታል::
በተመሳሳይ በአውሮፓ ፣ በእስያ ፣ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ ያሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት የአሰላለፍ ሽግሽግ አድርገዋል፡፡ ዘመን ተሻጋሪው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አነስታይን ከታላላቅ ግኝቶቹ ከአንጻራዊ እይታ ፣ ለአቶሚክ ቦንብ መገኘት ፈር ቀዳጅ ከሆነው ቀመርና ከሌሎች ፈጠራዎቹ ባልተናነሰ እኩል የሚታወሱለት ድንቃ ድንቅ አባባሎች አሉት:: ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት” ችግሩን በፈጠረው በዚያው አስተሳሰብ ፤ ችግር መፍታት አይቻልም:: “ የሚለው ተደጋግሞ ይጠቀስለታል::
ከፍ ብሎ ለመግለፅ እንደሞከርሁት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከኢህአዴግ ቤት የሚሰማው መልካም “ ዜና “ ይህን የአነስታይንን ዘመን ተሻጋሪ አባባል እና “ ቁሞ ቀር “ ርዕዮት ጠል የሆነውን የቶኒ የብሌየርን ምክረ ሀሳብ ምርዝ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል:: የለውጥ ኃይሉ ዘመኑንም ትውልዱንም የሚዋጅ የ” መደመር ፅንሰ ሀሳብ “ ን በመፅሐፍ ሰንዶ አቀረብሁ ባለ በአጭር ጊዜ ይሄን ፅንሰ ሀሳብ ይመጥናል ያለውን አደረጃጀትና አሰራር ይዞ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው:: ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ከመከረ በኋላ ወደ ሕብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ መዋሀዱን አብስሮናል::
ምስር ይብላና:: አዴፓ ፣ ኦዴፓና ደኢህዴን ውህደቱን በሙሉ ድምፅ እንደደገፉት መገመት ይቻላል:: ህወሀት ከዘጠኙ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ ስንቱ በስብሰባው እንደተገኙ እርግጠኛ ባንሆንም ውህደቱን የተቃወሙት ስድስቱ ግን የህወሀት አባላት ሳይሆኑ እንደማይቀር መጠርጠር ይቻላል:: ይህ ደግሞ የሚጠበቅና መብትም ነው:: እኛ አምርረን ጠልተነው የነበረው ከመማፀኛ ከተማው ሆኖ የሚወረውረውን የፕሮፓጋንዳ ጦር እና የሚጎሽመውን የጦር አውርድ ነጋሪት እንጂ እንዲህ በጠረጴዛ ዙሪያ በልዩነት የሚወስደውን አቋም አይደለም:: አምስቱ አጋር ፓርቲዎች ማለትም ጋሕአዴን ፣ አብዴፓ ፣ ቤጉሕዴፓ ፣ ሶህዴፓና ሀብሊ ከ2ኛ ዜግነት ፣ ከመገለል ፣ ከመገፋት ፣ ከባይተዋርነት ፣ ከሞግዚት ተላቀው የውህደቱ ዋልታና ማገር ሆነዋል::
የመደመር ፅንሰ ሀሳብ የማዕዘን ድንጋዮች ማለትም መሰብሰብ ፣ ማከማቸትና ማካበት ከቀዳማዊ ኢህአዴግ አሰራርና አደረጃጀት ጋር ጀርባና ሆድ ነበሩ:: በእነዚህ የመደመር አላባውያን ስር በውስጠ ታዋቂነት ፍትሕ ፣ አካታችነት ፣ እኩልነት ፣ ነፃነት ፣ ዴሞክራሲያዊነትና ሌሎች ሰብዓዊ እሴቶች አንዳሉ ይታመናል:: በተለይ በቀዳማዊ ኢህአዴግ የ28 ዓመታት አሰራርና አደረጃጀት ፍትሐዊነት ፣ እኩልነት ፣ ፣ ነፃነትና ዴሞክራሲያዊነት ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታዎች ነበሩ:: ህወሀት ኢህአዴግን ቀዶ የሰፋው በእሱ ልክ ስለነበር ውህደቱ በአዲስ ለሁሉ እንዲበቃ ተደርጎ ተቀዶ መሰፋት ነበረበት፡፡ ሂደቱም በዚህ ውህደት አሀዱ ተብሎ ተጀምሯል ማለት ይቻላል::
ከሀገሪቱ ግማሽና ከዚያ በላይ የሚሆነውን መልክዓ ምድር የሚወክሉ አምስት ክልሎችን ገዥ ፓርቲዎች በሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ሆነ በሞግዚት በሚያስተዳድሮአቸው ክልሎች መፃኢ እድል የመምከርና የመወሰን መብት አልነበራቸውም:: አሁን ይህ አድሎአዊ ገፊ ጥቁር መጋረጃ ተቀዷል:: ከአሁን በኋላ በክልላቸውም ሆነ በሀገራቸው ጉዳይ ባይተዋር አይሆኑም:: የድርጅታቸው “የብልፅግና ፓርቲ “ ፕሬዚዳንት የመሆንም ሆነ ፕሬዚዳንቱን የመምረጥ መብትን ተቀዳጅተዋል:: ከአሁን በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የመወዳደርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን የመምረጥ መብታቸው ተረጋግጧል:: ይህ ውህደት የፈጠረውን ስሜት በደንብ ለማጣጣም ከእህት ፓርቲዎች ይልቅ በአጋር ፓርቲዎች ጫማ ቆሞ ፍትሐዊነትን መቅመስ ይጠይቃል::
ግንባር ታክቲካዊ የጋራ አላማን ለማሳካት ማለትም ፖለቲካዊ ሕብረትን እውን ለማድረግ የሚቀየስ ጊዜአዊ ስልት እንደሆነ ቢታወቅም ህወሀት ግን ስልጣን ላይ የሚያቆየው ብቸኛ ስትራቴጂ ስለነበር በዓለማችን የፖለቲካ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ለዓመታት የሙጥኝ ብሎት መኖሩ ሳያንስ ይህን ግትር አቋሙን እስከ መጨረሻው ገፍቶበታል:: ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ጅማሬ ማብሰሪያ ላይ “ የኢትዮጵያን ሕልውና እና ብልፅግና ጉዞ የሚያቆም ምንም ኃይል የለም !!! “ ካሉ በኋላ በማስከተል “ ዶሮዋ የእንቁላሉ ባለቤት ብትሆንም ሰብሮ ጠብሶ ከመብላት ግን ልታግደን አትችልም:: “ ባሉት መሰረት እንቁላሏ ተጠብሶ በእኩልነት ለመቋደስ ማዕዱ ቀርቧል:: ዜጎችን 1ኛ ፣ 2ኛ ፣ … ዜጋ የሚያደርገው ኢፍትሐዊ ፣ ኢዴሞክራሲያዊ ፣ አድሎአዊ ፣ አግላይ ፣ ገፊ ፣ ወዘተ . የኢህአዴግ አሰራርና አደረጃጀት ላይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሸኝቷል ማለት ይቻላል::
እንግዲህ የለውጥ ኃይሉ ግንባሩ ሲከተለው የነበረ አሰራርም ሆነ አደረጃጀት ፍትሐዊም ዴሞክራሲያዊም ካለመሆኑ ባሻገር ግንኙነቱ በእኩልነትና መርህ ላይ ያልተመሰረተ ስለነበር ይህን የሚያስተካክል አሰራርና አደረጃጀት ለማስፈን የሚያግዝ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዳር እስከ ዳር በእኩልነት ፣ በፍትሐዊነት የሚያሳትፍ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ግልፅ አድርገዋል::
ፓርቲ ተመሳሳይ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ፖለቲካዊ ስልጣን ለመያዝ ብለው የሚመሰርቱት ድርጅት መሆኑን ስናስብ ግንባሩ ወደ ፓርቲነት ለመለወጥ መወሰኑ በራሱ ትልቅ እመርታ ቢሆንም የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን ግን አበክሮ ማመን ግድ ይላል:: የለውጥ ኃይሉ ወደ ውህደቱ ለመምጣት ካደረገው ትግል ባልተናነሰ ትክክለኛውን የትውልዱን ድምፅ ፣ ጥሪ ለይቶ በማድመጥ ሁለንተናዊ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ምላሽ የመስጠቱ ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑን ሊያጤነው ይገባል::
ከሁሉም በላይ አዲስና ተግባራዊ እይታን የግድ የሚያደርገው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘውት የመጡት የመደመር ፍልስፍና በታላቁ መፅሐፍ የማቲዎስ ወንጌል ላይ “ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም:: ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል:: ….ይቀጥላል )
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012