እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው ሲያገባ የመጀመሪያው ትኩረት ፍቅር እና ስምምነት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ ምርምሮች በተለይም የኤችአይቪ ምርመራ አስፈላጊነት ግዴታ ነው፡፡ የደም ወገን (ምድብ) ምርመራ አድርጎ የሚያገባ ሰው የለም፤ አይመከርምም፡ ፡ ይሁን እንጂ አጋጣሚ ሆኖ አልፎ አልፎ ባል ደሙ አርኤች ፖዘቲቭ (Rh +ve) ሆኖ የሚስት ደግሞ አርኤች ኔጌቲቭ (Rh-ve) በሚሆንበት ጊዜ በሆድ ውስጥ በሚገኝ ህፃን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያደርሳል፡፡ ይህም በአማርኛ አጠራሩ ሾተላይ ይባላል፡፡
ሾተላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልና ህፃኑን ማህጸን ውስጥ እስከ መሞት (still birth) ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህንን ችግር እንዴት እንደሚያመጣ ከማየታችን በፊት አስቀድመን የደማችንን አይነት ማለትም አር ኤች ኔጌቲቭ (Rh -ve) ወይም አር ኤች ፖዘቲቭ (Rh +ve) ማለት ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
የሰው ልጅ ካሉት 4 የደም አይነቶች ውስጥ አንዱ ይኖረዋል፡፡ እነዚህ የደም አይነቶችም በትልልቅ (ካፒታል) የእንግሊዝኛ ፊደሎች የተሰየሙ ሲሆን ምድብ A የደም አይነት፣ ምድብ B የደም አይነት፣ ምድብ AB የደም አይነት እና ምድብ O የደም አይነት ይባላሉ:: ደም እንደሚታወቀው የተለያዩ አይነቶች በውስጡ ያሉት ሲሆን በተለያዩ አይነቶች የሚከፋፈለው ደግሞ ቀይ የደም ሴሎችን (ህዋሶችን) መሰረት በማድረግ ነው፡፡
ከላይ A፣ B፣ AB እና O በመባል የተከፋፈሉት እያንዳንዳቸው እንደገና Rh የሚባል አካል ከቀይ የደም ሴላቸው (red blood cell) ላይ መኖራቸው እና አለመኖራቸውን መሰረት በማድረግ ይካፈላሉ፡፡ ይህም ማለት “A” የደም ወገን (ምድብ) በሁለት ቦታ ይካፈላል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት “A ፖዘቲቭ የደም አይነት እና A ኔጌቲቭ የደም አይነት” ብለን በሁለት ቦታ እንከፍላቸዋለን፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ሊኖረው (ሊኖራት) የሚችለው ከዚህ በታች ካሉት የደም አይቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ሲሆን እሱም፡-
– A ኔጌቲቭ የደም ቡድን /ምድብ/ (A -Ve)
– A ፖዘቲቭ የደም ቡድን/ምድብ/ (A +Ve)
– B ኔጌቲቭ የደም ቡድን /ምድብ/ (B -Ve)
– B ፖዘቲቭ የደም ቡድን /ምድብ/ (B +Ve)
– AB ኔጌቲቭ የደም ቡድን / ምድብ/ (AB -Ve)
– AB ፖዘቲቭ የደም ቡድን/ምድብ (AB-Ve)
– O ኔጌቲቭ የደም ቡድን/ምድብ (O-Ve)
– O ፖዘቲቭ የደም ቡድን/ምድብ (O-Ve)
አንድ ሰው ይህንን የደም አይነት /ምድብ/ የሚያገኘው በእድል ሳይሆን ከአባቱ እና እናቱ የሚወረስ ነው፡፡ እናቱ A የደም አይነት (ምድብ) ያላት እና አባቱ ደግሞ B የደም አይነት (ምድብ) ሊኖራቸው የሚችሉት ልጅ የደም አይነት (ምድብ) አይነት ከ(A)፣ (B)፣ (O) እና (AB) ውስጥ አንዱ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከአራቱም ውስጥ የትኛውም ሊኖረው እንደሚችል መለየት በመጠኑ በጥልቀት ማየት ስለሚጠይቅ አሁን አናነሳውም:: ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ ላይ የሁለቱም ወላጆች የደም አይነት ቢታወቅ የልጃቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ ማየት ይችላል፡፡
በሀገራችን በርካታ ሰዎች የደም አይነታቸውን ለማወቅ ብቻ ምርመራ ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ይልቁንም ለሌላ በሽታ ወይም ለሌላ አገልግሎት ተፈልጎ የደም አይነት ምርምራ እንዲያደርጉ ሲገደዱ ብቻ ነው የደም አይነታቸውን የሚያውቁት:: ነገር ግን የራስን የደም አይነት (ምድብ) አይነት ማወቅ አስፈላጊ ነው:: ሰው በሚታመምበት ጊዜ ወደ ሀኪም ቤት ሄዶ የደም ልገሳን ማግኘት የሚችለው የደሙ አይነቱን ሲያውቅና ተመሳሳይ ደም አይነት ማግኘት ሲችል ብቻ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ድንገተኛ አደጋ አጋጥሞ ሀኪም ቤት ደርሶ የደም አይነቱ እስኪታወቅ ድረስ ጊዜ የሚወስድ ስለሚሆን አስቀድሞ ማወቁ ወዲያውኑ የደም ልገሳ ለማግኘት ይረዳል ማለት ነው፡፡
የወንድ የቀይ ደም አር ኤች አይነት (ምድብ) የሚለያየው (ፖዘቲቭ እና ኔጌቲቭ) ሆኖ ቢጋቡ ምን አይነት ችግር ይፈጠራል ?
– የባል የደም አይነት (ምድብ) አር ኤች ኔጌቲቭ (RH -Ve) ቢሆን በጽንስ ላይ ምንም ችግር አያመጣም (ሚስት ኔጌቲቭም ፖዘቲቭም ብትሆን ማለት ነው)
– የባል እና የሚስት ማለትም የሁለቱም የደም አይነት (ምድብ) አር ኤች ፖዘቲቭ (RH +Ve) ከሆነ በፅንስ ላይ ምንም ችግር የለውም፡፡
– ነገር ግን የባል የደም አይነት (ምድብ) አር ኤች ፖዘቲቭ ሆኖ የሚስት ደግሞ አር ኤች ኔጌቲቭ ከሆነ ጽንስ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ስለሚያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና በቂ ህክምና ያስፈልጋል፡፡
ተፅእኖ የሚደርሰው እንዴት ነው?
አንድ የደም አይነት (ምድብ) ከሌላ የደም አይነት (ምድብ) ጋር ሲደባለቅ እንደ ባእድ በመተያየት ይጣላሉ፡፡ ለምሳሌ የደሙ አይነት “A” የሆነ ሰው የደሙ አይነት “B” ከሆነው ጋር ሲደባለቅ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ የ “A-ve” እና “A+ve” የሆነም እንደዚሁ ነው፡፡ የደሟ አይነት (ምድብ) ኔጌቲቭ (Rh-ve) ያላት ሴት የደሙ አይነት (ምድብ) ፖዘቲቭ (Rh+ve) ካለው ወንድ ጋር ጋብቻ ፈፅማ ብታረግዝ ይህ የደም አይነት (ምድብ) በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያለው ህፃን አርኤች ፖዘቲቭ (Rh +ve) የደም አይነት (ምድብ) የመኖር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በማህፀን ውስጥ የሚገኝ ህፃን ደም Rh +ve ከሆነ የእናት Rh -ve እንደ ባእድ በማየት የህፃን ደም ሴልን መጣላት ይጀምራል፡፡
ይህንም ሊሆን የሚችለው በእናት ማህፀን ውስጥ ከሚገኝ የፅንስ (የህፃን) ደም ጋር ሲደባለቅ ነው፡፡ ደሙ በሚደባለቅበት ጊዜ የቀይ ደም (red blood cell) የእናታዊ የመከላከል ሥርዓትን (maternal immune system) የቀይ ደም ሴል ይህንን ፅንስ የሚጣላን (maternal antibody) ያዘጋጃል፡፡ የመጀመሪያው ፅንስ ሳይጎዳ የመወለድ እድል አለው፡ ፡ ይህም ከህፃኑ ጋር የሚጣላው ሥርዓት (maternal antibody) እና በእናት ደም ውስጥ የሚፈጠረው ችግር ወደ ፅንሱ (የህፃን) ከመድረሱ በፊት ቶሎ ሊወለድ ስለሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ሁለተኛውን እና ተከታዩን ፅንስ በትክክል ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቅ በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል፡፡ በጽንስ (በእርግዝና) ላይ ሊመጡ ከሚችሉ ጉዳቶች ውስጥ፡-
– የጽንስ መጨንገፍ (Abortion)
– በህፃን ላይ ደም ማነስ መከሰት (Fetal Anemia)
– በማህፀን ውስጥ የህፃን መሞት (Still birth)
– በህፃን ሰውነት ውስጥ የውሃ ማጠራቀም (hydrops fetalis) እና ሌሎች ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ይህንን ችግር እንዴት መከላከል እንችላለን?
በእርግዝና ጊዜ ኢሚኖግሎቡሊን (Anti D) የሚባል መድሃኒትን ለእናት በመስጠት ሊመጣ የሚችለውን ችግር ማስቀረት ይቻላል፡፡ ይህ ኢሚኖግሎቡሊን (Anti D) ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ችግር ላላቸው ሴቶች ካረገዙ በኋላ የመጀመሪያው በ7ኛው ወር ወይም በ28ኛው ሳምንት ላይ የሚሰጥ ሲሆን 2ኛው ደግሞ የህፃኑ የደም አይነት (ምድብ) አር ኤች ፖዘቲቭ (Rh +Ve) ከሆነ ከወለደች በኋላ በ72 ሰአታት ውስጥ የሚሰጥ ነው::
ይህንን አግልግሎት ወይም መድኃኒት ሊያገኙ የሚችሉት የእርግዝና ክትትል (antenatal care) ሲኖራቸው ነውና የህክምና ክትትል ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው:: ተመርምረው የደም አይነታችን ማወቅ፤ ለነፍስ ጡሮች ቢቻ ሳይሆን፤ ለሁሉም የሰው ልጆች በተለይ በአደጋ ጊዜ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ፤ ተመርምረን የደማችንን አይነት እንወቅ፡፡
ዶ/ር ጉርሜሳ ሂንኮሳ
አርሲ ዩኒቨርሲቲ
ሆራ ቡላ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012