በቡና ፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት 287 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት 104ሺህ 666 ነጥብ 51 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት በመላክ 349 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 102ሺህ 916ነጥብ 5 ቶን ምርት በመላክ 287 ነጥብ 59 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።
የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጻር 82 በመቶ በላይ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል። አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ27 ነጥብ 1 በመቶ በገቢ ደግሞ የ9 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።፡
የቡና አራት ወራት ኤክስፖርት አፈጻጸምን በተመለከተ ከሀምሌ 2011 እስከ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ወደ ውጭ አገር ሊላክ የታቀደው የቡና ምርት 96,826.00 ቶን ሲሆ 339 ነጥን 85 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ነበር። ሆኖም ግን አፈጻጸሙ ሲታይ 100ሺህ 452ነጥብ 4 ቶን ቡና ተልኮ 284 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሊገኝ ችሏል። በ2012 በጀት ዓመት አራት ወራት የተላከው ቡና በመዳረሻ ሀገራት በገቢ ሲታይ ጀርመን ፣አሜሪካ እና ሳኡዲ አራቢያ ቀዳሚዎቹ መዳረሻዎች ናቸው።
እንደ ባለስልጣኑ መረጃ፤ በገቢ በኩል ከእቅዱ አንጻር ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ያልተቻለበት ዋነኛው ምክንያት የአለም ገበያ ዋጋ ባለፉት 13 አመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ቅናሽ በማሣየቱ ነው። አሁንም ይኸው ሁኔታ እንደቀጠለ ሲሆን የዋጋ ቅናሽን ለማካካስ ኢትዮጵያ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው። ከጥረቶቹ መካከል የሚላከውን ምርት ከመጨመር ጀምሮ ፣ የአለም አቀፍ ቡና ሁነት እና የባለልዩ ጣዕም ቅምሻ ውድድርን ማዘጋጀትን እንዲሁም ጨምሮ ቻይናን እና ሩሲያን የመሳሰሉ የገበያ አማራጮችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 700 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ
በ2012 የበጀት ዓመት ሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 700 ሚሊዮን ዶላር ማሳካት መቻሉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የኢንቨስትመንት ኮሚሺነር አቶ አበበ አበባው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባቀረቡት ሪፖርት የኮሚሽኑ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑም በሩብ ዓመቱ 1 ሺህ 307 የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ምዝገባ የማከናወን እና ፍቃድ የመስጠት አገልግሎቶችን አቅዶ ከ2 ሺህ 500 በላይ ምዝገባ እና ፈቃድ ማከናወኑን ተናግረዋል።
በ2012 በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ዞኖች ለ23 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶም ከ24 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ እገዛ እያደረገ ነው
የአፍሪካ አገራት የአገር ውስጥ ቦንድ የፋይናንስ ዘርፍ ልማት 8ኛው አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት ተካሂዷል። በወቅቱ የብሔራዊ ልማት ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት የሆኑት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የአፍሪካ ልማት ባንክ እየደገፈው ይገኛል። በተለይ በአገር ውስጥ ቦንድ ገበያ ዙሪያ አማካሪ መድቦ ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራ ይገኛል።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱና ቁልፉ ጉዳይ የአገር ውስጥ ቦንድ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ገዥው፤ ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚን ማጠናከር ረገድ አዲስ አበባ አውደ ጥናቱ ላይ ከተገኙ ባለሙያዎች እና ሀገራት ልምድ መውሰዷን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ፍቃዱ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እንድታስመዘግብ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ወሳኝነት አለው። በዚህ ረገድ የአውደ ጥናቱ መካሄድ የአፍሪካ አገራት ልምድ በመቅሰም በአገር ውስጥ ቦንድ ገበያ ዙሪያ ያሉትን አካሄዶች ለመቅሰም ይረዳል።
የተወለዱት በምስራቅ ሀረርጌ ጉርሱም ውስጥ ነው፡፡ ወይዘሮ ክብሬ ሙላት ይባላሉ። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። ወላጅ አባታቸው በሥራ ምክንያት ወደተለያዩ ሥፍራዎች ይንቀሳቀሱ ስለነበር እሳቸውም ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ለማደግ ተገደው እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ላይ ስራቸው ከግመል እና የደለቡ በሬዎች ንግድ ውስጥ ቢከታቸውም በልጅነታቸው ከብቶችን በጣም ይፈሩ እንደነበር ግን አይረሱትም። ስለግመል ማወቅ የጀመሩት ገና አፍ መፍታት እንደጀመሩ ነው። የተለያዩ ኮተቶችን ያዘሉ ግመሎች ከጅግጅጋ ተነስተው ጉርሱምን አቋርጠው በኤጀርሳ በኩል ወደሐረር ያመሩ ነበር። ያኔ የግመል ነጋዴዎች ወደ ገበያ ሲሄዱ በእርሳቸው ቤት በረንዳ ላይ አርፈው ሙቀቱን ለማስታገስ ውሃ ጠጥተው ነበርና ጉዟቸውን የሚቀጥሉት ስለባህሪያቸው በልጅነታቸው መማራቸው አልቀረም።
ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ በመጠነኛ የንግድ ስራ ይሳተፉ ነበር። በሸቀጣሸቀጥ ሱቅ እና የልብስ መደብር እንዲሁም አነስተኛ ካፍቴሪያ ነበራቸውና ወይዘሮ ክብሬ ም ከትምህርት መልስ የንግዱን ስራ ያግዛሉ። በዚህ ወቅት ታዲያ እንስቷ ስለንግድ እና ገንዘብ አያያዝ በመጠኑም ቢሆን ያወቁበት እና ጠንካራ ሰራተኝነት አዋጭ መሆኑን የተማሩበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ።
የዛሬዋ እንግዳችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ወይም ኮሜርስ ተከታትለዋል። በጽህፈት እና ቢሮ አስተዳደር በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ በመንግስት ስራ ላይ ነበር የተቀጠሩት። በሙያቸውም በአዲስ አበባ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በ700 ብር ተቀጥረው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በወቅቱ ግን ደመወዛቸው ለጥሩ ኑሮ የሚበቃ ስላልነበረ በንግድ ተሰማርተው እራሳቸውን ለመደጎም ያስባሉ። እናም ከደመወዛቸው የቆጠቧትን ጥቂት ገንዘብ ከማጥፋት ይልቅ ለአንድ አላማ ሊያውሏት አቀዱ። የመንግስት ስራቸውን ሳይለቁ አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ንግድንም ጀመሩ። አንድ ሁለት እያሉ የሸቀጣሸቀጥ ንግዳቸው ትርፍ ሲጨምር ደግሞ ገንዘባቸውን ጠርቀም አድርገው ያገለገሉ መኪናዎችን እየገዙ ወደመሸጥ ተሸጋገሩ። የአሮጌ መኪናው ንግድ ግን ከሸቀጣሸቀጡ ይልቅ የተሻለ ትርፍ የሚገኝበት ነበርና የተሻለ ገቢ ሲያገኙ ደግሞ ሌላ የስራ አማራጭ ላይ ቀልባቸው አረፈ።
ለመጠጋት የሚፈሯቸውን ከብቶች ገዝተው እያተረፉ ለመሸጥ በማቀዳቸው የቁም እንስሳት ንግድ ውስጥ ገቡ። በመጀመሪያ ቀንም ከብቶቹን ገዝተው በረት ውስጥ ካስገቡ በኋላ እንዳይወጓቸው ሲፈሩ እና ሲቸሩ ለመጠጋት አልቻሉም ነበር። እናም ከብቶቹን ሸጠው የተወሰነ ትርፍ ካገኙ በኋላ ሌሎችንም እንስሳትን ከሸጡ በኋላ ቀስ በቀስ እየተላመዷቸው መጡ።
ቀስ እያሉም ከከብት ንግድ በተጨማሪ ግመሎችን እራሳቸው ገበያ ሄደው ገዝተው ማትረፍ ጀመሩ። ለሴት ልጅ ይከብዳል ተብሎ የሚታሰበውን ስራ በብቃት በመወጣት ከ11 ዓመታት በፊት በጀመሩት ንግድ ለብዙዎች ተምሳሌት በመሆን ስራቸውን ማስፋፋቱን ተያያዙት።
አቅማቸው ጠንከር ሲልም በኦሮሚያ ክልል ሉሜ አካባቢ የእንስሳት ማቆያ ስፍራ በመገንባት ከገበያ የሚገዟቸውን ግመል እና ሌሎች የቁም እንስሳት እየተንከባከቡ ያቆያሉ። ከዚያም በመኪና አጓጉዘው ወደጅቡቲ ከወሰዱ በኋላ ለተለያዩ ሀገራት ተቀባዮች በውጭጥ ምንዛሬ ይሸጣሉ።
ወይዘሮ ክብሬ በባሌ፣ ሃረርጌና ሞያሌ አካባቢዎች ባሉ ገበያዎች ብዙ ጊዜ ተመላልሰው ግመሎችን ገዝተዋል። በሬ እና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ የቁም እንስሳትንም በመሸመት ወደ ሉሜው ማቆያቸው ማስገባትን የሁልጊዜ ተግባራቸው አድርገዋል። ከዚያም እስከ ጅቡቲ ድንበር ድረስ በስራቸው ባገኙት ትርፍ የገዟትን መኪናቸውን እያሽከረከሩ ንግዳቸውን ያቀላጥፋሉ። ሲመለሱ ደግሞ በአዲስ አበባ በሚገኘው ቢሯቸው አሊያም በእንስሳት ማቆያቸው ቀሪውን ስራ ማከናወናቸው የማይቀር ነው።
ስራቸው ዕውቅና ሲያገኝና እና ደንበኞቻቸውም እየጨመሩ ሲመጡ እስከ ግብጽ እና ሱዳን ድረስ የቁም እንስሳት ተፈላጊ እየሆኑ መጡ። አቅማቸው ጠንከር ሲልም በተለያዩ ጊዜ ከተለያዩ አካባቢዎች የገዟቸውን ከአንድ ሺህ በላይ ግመሎችም በአንድ ጊዜ ወደ ጅቡቲ በመላክ ወደ መነገዱ ተሸጋገሩ።
ስራው ከፍ እያለ ሲመጣም በአንድ ጊዜ 3ሺህ 500 ግመሎችን ያጓጓዙበት ወቅት እንደነበረ አይዘነጉትም። እያንዳንዷን ትርፍ ወደ ተጨማሪ እንስሳት ንግድ ስራ ላይ የሚያውሉት ወይዘሮ ክብሬ በጥቂት ዓመታት ከፍተኛ ነጋዴ መሆን ችለዋል።
በተለይ ግመሎችን ወደ ሱዳን፣ ግብጽ እና ኦማን በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለእራሳቸውም ለሀገራቸውም በማስገባት ጠንካራ ነጋዴ መሆናቸውን አሳይተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጉዟቸው በሙሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ ነው የሚናገሩት።
ሥራውን ሲጀምሩት ወደ ቄራ ንግዱም እገባለሁ ብለው ቢሆንም የውሃ እጥረት ሲያጋኝማቸው ሱዳን በተገኘ የቁም እንስሳት ገበያ አማካኝነት እንስሳቶችን ከነህይወታቸው ወደመነገዱ መሸጋገራቸውን ያስረዳሉ። በመሆኑም እንስሳቱን ከዝተው በማቆያ ክትባት እየሰጡ እና እየመገቡ ካቆዩ በኋላ ገበያ አጥተው የተቸገሩባቸው በርካታ ጊዜያት መኖራቸውን ያስታውሳሉ።
በዚህ ወቅት የእንስሳቱ መኖ ወጪ ከፍተኛ ስለሚሆን አንዳንድ ጊዜ ችግር ይፈጥራል። ገበያ በማጣታቸው ደግሞ ያደለቧቸውን ከብቶች በዱቤ የሸጡበት ጊዜም እንደነበረ ይናገራሉ። ይባስ ብሎም አንዳንዶች በዱቤ የወሰዱትን እዳ በመካዳቸው እርሱን ለማስመለስ ተጨማሪ ጊዜ እና ወጪ ያወጡም ነበር።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ሥራውን እርግፍ አድርጎ መተው እንዳለባቸው የተሰማቸው ወቅትም ነበረ። የእንስሳት ገበያ የጠፋበት ወቅት ነበርና ለዘጠኝ ወራት ያክል ያለምንም ስራ እንስሳቶችን እየመገቡ ማቆየት ግድ ሆነባቸው። የመኖው ወጪ ሲያይልባቸው ቢናደዱም ፈጽሞ ግን ተስፋ አልቆረጡምና ገበያው እስኪገኝ ጥረታቸው ቀጠሉበት። በወቅቱ ያጋጠማቸው የገበያ እጦት ለወትሮው አራት ዙር ኤክስፖርት የሚያደርጉበትን ጊዜ ነው የወሰደባቸው። ባላቸው ጥሩ የመግባባት እና ችሎታ እና ቅልጥፍና ግን በስተመጨረሻ ገበያ አፈላልገው የቁም እንስሳቶቹን መሸጥ ቻሉ።
ያ ሁሉ ጊዜ ታልፎ ግን ገበያ አፈላልገው ወደተለያዩ ሀገራት በሚልኳቸው ግመል እና የደለቡ በሬዎች አማካኝነት የተሻለ ጥቅም ማግኘት ችለዋል። ሰፊ የእንስሳት ገበያ በሚገኝበት ወቅት በዓመት እስከ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ያስገቡበት ወቅት ነበር። አንዱን ግመል ከ1ሺ100 እስከ 1ሺህ 300 ዶላር ድረስ ለግብጽ ገበያ በማቅረብ የሚሰሩት ወይዘሮ ክብሬ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ላይ በመሳተፍም የገበያ አማራጫቸውን ለማስፋት በየጊዜው ጥረት ያደርጋሉ። ለስራ ካላቸው ታታሪነት የተነሳና እየተሯሯጡ በመስራታቸው በቂ ምግብ እንኳን ሳይወስዱ እራሳቸውን ስተው የወደቁበትን ጊዜ እንደነበረ ያስታውሱታል። ሴትነታቸው ሳይበግራቸው በይቻላል መንፈስ ሰረተው የሚያሰሩ መሆናቸውን ደግሞ የሚያውቋቸውም ይመሰክራሉ።
የግመል ንግዱ አሁን ላይ በእንስሳት እጥረት ምክንያት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተቀዛቀዘ ቢመጣም ስራ በሚኖርበት ወቅት ግን ከ80 እስከ 120 ሰራተኞችን ቀጥረው ያሰራሉ። በሉሜው የእንስሳት ማቆያ ደግሞ ጥበቃዎችን ጨምሮ ደግሞ ሰባት ሰራተኞች አሏቸው።
የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ የሚፈጥረው የስራ እድል ሰፊ ነው የሚሉት ወይዘሮ ክብሬ፤ ለአብነት ግመሎችን ወደግብጽ ገበያ ለመላክ ሲዘጋጁ እንስሳቱን ለሚያቀርበው ከአርብቶ አደሩ ጀምሮ፣ መኖ አቅራቢው፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው፤ ጫኝና አውራጁ፤ ሃኪሙና መጋዘን አከራዩ የገቢው ተቋዳሾች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ከዚህ ባለፈ ለቤተሰባቸውም ታላቅ በመሆናቸው ወንድምና እህቶቻቸውን የመደገፉን ነገር አልተውትም ነበር። ሁለት የሚያሳድጓቸው ልጆችም አሏቸው። በተጨማሪ ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር በመሆን በደብረሊባኖስ አካባቢ የአረጋዊያንና የህጻናት መርጃ ድርጅት አቋቁመው ለህጻናት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
በጋምቤላ አካባቢ 200 ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ ማምረት ጀምረው አላዋጣ ቢላቸው ጣጥለው የወጡት ወይዘሮ ክብሬ፣ በቀጣይ ደግሞ ከቁም እንስሳቱ ባለፈ የቄራ ፋብሪካ ገንብተው ለመስራት ነው ውጥናቸው። የቁም እንስሳት ንግዱ በበርካታ ችግሮች የተያዘ በመሆኑ መንግስትም ከደገፈው የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚችል ቢሆንም የቄራ ስራው ደግሞ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት አቅርቦ ገቢንም ለማሳደግ የሚያመች ነውና መሰማራቴ አይቀርም ባይ ናቸው።
ሴት መስራት እንደምትችል አሳይቻለሁ የሚሉት ወይዘሮ ክብሬ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን አስወግዶ በጥንካሬ ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይናገራሉ። የንግድ ሃሳብን ወደ ተግባር መቀየር እና በ የጊዜው የሚገኝ ፈተናዎችን በጽናት እያለፉ መስራት ከተቻለ እራስን ጠቅሞ ሀገርንም ማገልገል ይቻላል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ጌትነት ተስፋማርያም