አመልካች፡- የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
ጉዳዩ፡- የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄን በተመለከተ
አመልካቹ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የሥራ ዘመናቸው ካበቃ በኋላ ‹‹ይገባኛል›› ያሏቸውን ልዩ መብትና ጥቅማጥቅሞችን አስመልክቶ መጋቢት 28 ቀን 1997 ዓ.ም ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን አቅርበዋል::
የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ አቅራቢው የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ያቀረቡት አቤቱታ
ለኢፌዴሪ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ
በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 255/94 ውስጥ ያሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች ሕገመንግሥቱን የሚቃረኑ ስለሆነ አጣሪ ጉባኤው ጉዳዩን በተገቢው መልኩ አጣርቶ ለፌዴሬሽን ምክርቤቱ ለውሳኔ እንዲያቀርብልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ
ነጋሶ ጊዳዳ /ዶክተር/
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለሕገመንግሥት ትርጉም አጣሪ ጉባኤው ባቀረቡት አቤቱታ የሚከተሉት የሕግ ድንጋጌዎችና ነጥቦች እንዲመረመሩላቸው ጠይቀዋል::
-የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 9፣29፣30፣31፣38፣70፣(1)(2)፣83 እና አንቀጽ 84
– የአዋጅ ቁጥር 255/94 አንቀጽ 6፣7፣10፣12፣13፣14
ዶክተር ነጋሶ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 9 ጥያቄ ያቀረቡበት ጉዳይ ዝርዝር ይዘት የሕገመንግሥትን የበላይነት የሚያሳይ ነው::
* ሕገመንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ስለመሆኑ፣
* ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገመንግሥቱን የማስከበርና ለሕገመንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው፣
* በዚህ ሕገመንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማንኛውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ የተከለከለ መሆኑንና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የሀገሪቱ ሕግ አካል ስለመሆናቸው በግልጽ አስፍሯል::
በአንቀጽ 29 ላይ የተጠቀሰውም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጠቁም ሆኖ የአመለካከት፣ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት ስለመደንገጉ የሚጠቁም ነው::
በዚህም መሠረት ዶክተር ነጋሶ በዝርዝር የተቀመጡትን ሌሎች ነጥቦች መሠረት በማድረግ የዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚገልጽ መልኩ የሰፈሩትን ፍሬ ሀሳቦች ከሚያቀርቧቸው ፍላጎቶች ጋር በማገናዘብ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄን አቅርበዋል:: ዶክተር ነጋሶ ከጠቀሱትና በአንቀጽ 29 ላይ ከሰፈሩ ዝርዝር ነጥቦች መካከልም፡-
*ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል::
* ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ መብት አለው::
*ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ፣ ወይም በህትመትና በሥነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል::
*የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን ነፃነት ስለመረጋገጡ በመግለጽም የቅድሚያ ምርመራ ስለመከልከሉና መረጃ የማግኘት መብት ስለመፈቀዱ ጭምር ያስቀምጣል::
በተመሳሳይ መልኩ ዶክተር ነጋሶ የሕገ መንግሕት ትርጉም ጥያቄ ባቀረቡበት አንቀጽ 30 የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብቶች ሰር ከተደነገጉት ነጥቦች መካከል ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብቶች እንዳለው ይጠቁማል::
ዶክተር ነጋሶ ማብራሪያ በጠየቁባቸው ሌሎች አንቀጾችም የመደራጀት፣ የመዘዋወር፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዝርዝሮችን አስፍረዋል:: በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 70 ላይ የሰፈረው የፕሬዚዳንቱ አሰያየም የሚለው አበይት ጉዳይም በቀጥታ ከማንነታቸው ጋር የሚዛመድ በመሆኑ በጥያቄያቸው ላይ የተካተተ ፍሬ ሀሳብ ሆኗል::
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በተለይ በዚሁ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ የተቀመጡትን ሁለት ነጥቦች በመለየት የአቤቱታቸው መሠረት አድርገዋቸዋል::
በአንቀጽ 70 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ለፕሬዚዳንቱ ዕጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስለመሆኑ ሰፍሯል:: በተመሳሳይ ሁኔታ በንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተቀመጠው ነጥብም የቀረበው ዕጩ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትና በፌዴሬሽን ምክርቤቱ የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ከተደገፈ ፕሬዚዳንት ይሆናል በማለት አስቀምጧል::
ዶክተር ነጋሶም በአንቀጽ 83 እና 84 ላይ የተጠቀሱትን የሕገ መንግሥቱን ትርጓሜና የአጣሪ ጉባኤውን ስልጣንና ተግባራት ፍሬ ሀሳቦች በአቤቱታቸው ላይ አካተዋል::
በነዚህ ሁለት አንቀጾች ስር የሰፈሩት ዝርዝር ሀሳቦችም ሕገ መንግሥታዊ ክርክር ሲነሳ በፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ያትታሉ:: ውሳኔ በማሳወቂያ የጊዜ ገደብም በሰላሳ ቀናት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥበት አስቀምጧል::
የሕገመንግሥቱ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሥልጣንና ተግባርን አስመልክቶ በቀረቡ ዝርዝር ነጥቦችም ጉባኤው ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን እንደተሰጠው ተቀምጧል::
ዶክተር ነጋሶም በነዚህ አንቀፆች ስር የተብራሩትን ሌሎች የጉባኤውን ሥልጣንና ኃላፊነቶች መነሻ በማድረግ ለአቤቱታቸው መሠረት አድርገው ተጠቅመውባቸዋል:: የዶክተር ነጋሶን አቤቱታ የመረመረው የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤም ለአመልካቹ ተገቢ ይሆናል ባለው ሀሳብ ከድምዳሜ ደርሷል::
የኢፌዴሪ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሰጠው ውሳኔ
የአዋጁ ድንጋጌዎች ከሕገመንግሥቱ አንቀጾች 29፣30፣31 እና 38 ጋር የሚጋጩ አይደሉም:: በመሆኑም የአመልካቹ አቤቱታ ወይም ጥያቄ የሕገመንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም:: ሲል ምላሽ ሰጥቷል::
ዶክተር ነጋሶ ከጉባኤው የተሰጣቸውን ምላሽ ‹‹ተገቢ ነው›› ሲሉ አልተቀበሉትም:: በሕገመንግሥቱ ላይ የተጠቀሱትንና የእሳቸውን መብትና ጥያቄዎች የገደቡ ነጥቦችን በመዘርዘር አጣሪ ጉባኤው የሰጠውን ውሳኔ ተቃውመው ‹‹ይግባኝ.. ሲሉ አመልክተዋል::
የይግባኝ ባዩ የቅሬታ ነጥቦች
*አዋጅ ቁጥር 255/94 የሕግ አወጣጥ ሥርዓትን ሳይከተል የወጣና ሕገመንግሥቱን የሚቃረን ሆኖ ሳለ ተፈጻሚ መሆን የሚገባው ለወደፊቱ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እንዲታገድ በሚስማሙ ፕሬዚዳንቶች ላይ መሆን ሲገባ ከሕግ ውጪ እኔም ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ተደርጓል:: ይህ የተደረገው ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሳይሻሻል ነው::
* በአዋጅ ቁጥር 255/1994 አንቀጽ 7 ‹‹ፕሬዚዳንቱ የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላም ወገንተኝነት ካላቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የመገለል ኃላፊነት ይኖረዋል›› የሚለው ድንጋጌ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኖ ያገለገለ ሰው በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29 ፣30፣31 እና 38 ለዜጎች በተጠበቁ ዴሞክራሲዊ መብቶች እንዳይጠቀም የሚገድብ ስለሆነ ከሕገመንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረን ነው:: ከሕገመንግሥቱ ጋር የሚቃረን ሕግ ደግሞ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በሕገመንግሥቱ ንዑስ አንቀጥጽ 9/1 / ላይ ተደንግጓል::
የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ‹‹በፌዴራል መንግሥት የወጣ ሕግ ከሕገመንግሥቱ ጋር ይቃረናል›› በሚል የቀረበለትን ጉዳይ መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ከማቅረብ በስተቀር ውሳኔ መስጠት አይችልም እንጂ ‹‹ይችላል›› የሚባል ቢሆን እንኳን አመልካቹ ውሳኔውን ተረድቶ ይግባኝ ማቅረብ እንዲያስችለው ውሳኔው በዝርዝር ሊሰጠው ይገባል::
ዶክተር ነጋሶ የአዋጅ ቁጥር 255/1994 አወጣጥና አዋጁ ይዟቸው የወጣው ድንጋጌዎች በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 84/4/መሠረት ሕገመንግሥታዊ ክርክር ያለበት ስለሆነ ጉዳዩ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 84 /4/መሠረት እንዲታይልኝ ሲሉ መስከረም 20 1997 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ ለሕገመንግሥቱ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ማመልከታቸውን ይጠቅሳሉ::
ይሁን እንጂ ጉባኤው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ጉዳዩን መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ማቅረብ ሲገባው ጥያቄው የሕገመንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም በማለት የሰጠው ውሳኔ አግባብነት የለውም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል:: ከዚሁ ጋር በማያያዝም አዋጅ ቁጥር 255/ 94 ሕገመንግሥቱን የሚቃረኑ ድንጋጌዎችን ይዞ የወጣ ስለሆነ በሕገመንግሥቱ ንዑስ አንቀጽ 9/1 መሠረት ተፈጻሚነት አይኖረውም ተብሎ እንዲሻርልኝ ሲሉ ጠይቀዋል::
አቤቱታ አቅራቢው በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የመተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 255/94 ውስጥ ያሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች ሕገመንግሥቱን የሚቃረኑ ስለሆነ አጣሪ ጉባኤው ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክርቤት ያሳውቅልኝ ባሉት መሠረት የኢፌዴሪ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ በቀረበባቸው ጉዳዮች ላይ በመወያየት በተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ውሳኔውን ለማሳለፍ መክሯል::
ጉባኤው የአመልካቹን ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ በኅዳር ወር 1997 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የቀረቡትን ጉዳዮች በዝርዝር ተመልክቶ ይሆናል ያለውን የመጨረሻ ውሳኔ አሳልፏል:: በዚህም መሠረት
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላ ወገንተኝነት ባላቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ እንደሌለበት፣ የሚሳተፍ ከሆነ ግን በሁለቱ ምክርቤቶች አፈጉባኤዎች ውሳኔ ወይም በአፈጉባኤዎቹ በሚጠራ ልዩ የጋራ ስብሰባ በሚወሰን ውሳኔ መሠረት በአንቀጽ 13 የተገለጹ መብቶች ሊቋረጡ እንደሚችሉ በአዋጁ አንቀጽ 14 ተደንግጓል:: ሲል ይጠቁማል::
በሕገመንግሥቱ 29 እንደተደነገገው አመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ እንዲሁም በአንቀጽ 30 ላይ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታን የማቅረብ መብቶች በአንቀጽ 31 የመደራጀት መብት፣ በአንቀጽ 38 የመመረጥና የመምረጥ መብት የሚገድቡ ወይም የሚያግዱ አይደሉም::
አዋጅ ቁጥር 255/1994/ በግልጽ የሚያስቀምጠው የቀድሞ ፕሬዚዳንት በአዋጁ የተገለጹት መብትና ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት ከፈለጉ በአዋጁ የተደነገጉትን ግዴታዎች ማሟላት እንደሚያስፈልግ እንጂ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጥቅማጥቅማቸውን አስከተዉ ድረስ በፖለቲካ እንቅስቃሴ መሳተፍን አይከለክልም::
በአዋጁ የተደነገጉት መብትና ጥቅማጥቅሞች ሕገመንግሥታዊ ሳይሆኑ በአዋጁ የተሰጡ በመሆናቸው የአዋጁ ተጠቃሚ ለመሆን በአዋጁ የተጠቀሱትን ግዴታዎች ማሟላት ግዴታ ይሆናል::
በመሆኑም የአዋጁ ድንጋጌዎች ከሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29፣30፣31 እና 38 ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን ገልጾ ይህንኑ በውሳኔው ላይ አስፍሯል::
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክርቤት የሰጠው ውሳኔ
ምክርቤቱም በበኩሉ የአዋጅ ቁጥር 255/1994 ድንጋጌዎች ይግባኝ ባይ ከጠቀሷቸው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29፣፣30፣31 እና 38 ጋር አይቃረንም:: ስለዚህ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የወሰነው ውሳኔ ሕገመንግሥታዊና ትክክለኛ በመሆኑ ይግባኙ ተቀባይነት የለውም ሲል ምላሽ ሰጥቷል::
ምክርቤቱ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መጋቢት 28 ቀን 1997 ዓም የጻፉትን የይግባኝ ቅሬታን መሠረት በማድረግ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ባቀረቡት ማመልከቻ ላይ ያተኩራል::
ምክር ቤቱ ባስተላለፈው የውሳኔ ሀሳብም ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ገለልተኛ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 70 ንዑስ ቁጥር 2 መሠረት ፕሬዚዳንትነቱን የሚቀበል ዕጩ ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ድርጅታዊ ግንኙነት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ይገልጻል::
ፕሬዚዳንቱ በሥራ ዘመኑም ሆነ የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላ ወገንተኝነት ካላቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ገለልተኛ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲደነግግ የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 70 ንዑስ ቁጥር 3 ደግሞ የምክርቤቱ አባል ፕሬዚዳንት ሆኖ ከተመረጠ የምክርቤቱን መቀመጫ መልቅቀ እንዳለበት ይደነግጋል::
ከነዚህ ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው ፕሬዚዳንቱ እንደተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳና ገለልተኛ ሆኖ መላውን የአገሪቱን ሕዝቦች የሚወክልና የሚያገለግል ስለመሆኑ ነው::
ፕሬዚዳንቱ እንደ አንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ትልቅ የሀገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ተቋም በሁሉም ዘንድ ክብርና የመልካም ስም አመኔታ ኖሮት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ሳያደርግ ወይም ሳይታይበት መላውን የአገሪቱን ሕዝቦች እንዲያገለግል፣በሥራ ዘመኑም ሆነ የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላ መብትና ጥቅሞቹ እንዲጠበቁ ሲባል አዋጁ ወጥቷል::
የሥራ ዘመናቸው ያበቃ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ልዩ መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ጊዜ እንደነበሩት ወገንተኝነት ሳይኖራቸው ገልተኛ ሆነው ለአገርና ለወገን ማገልገል ያልፈለጉ እንደሆን ፣ የተሰጣቸውን ልዩ ጥቅምና መብት ትተው እንደማንኛውም ዜጋ በግልም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅተው ወገንተኝነት ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም ሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 መሠረት የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ:: አዋጁም ይህን ዓይነት ክልከላን አላስቀመጠም::
በአጠቃላይ የአዋጅ ቁጥር 255/1994 ድንጋጌዎች ይግባኝ ባዩ ከጠቀሷቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29፣30፣እና 38 ጋር አይቃረንም:: ስለዚህ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የወሰነው ውሳኔ ሕገመንግሥታዊና ትክክለኛ በመሆኑ ይግባኙ ተቀባይነት የለውም:: ሲል የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ላቀረቡት የ‹‹ይግባኝ›› ማመልከቻ ተገቢ ነው ያለውንና የመጨረሻውን ፍትህ ሰጥቷል::
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
መልካምስራ አፈወርቅ