ተማሪዎች ቀያቸውን ለቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያቀኑበት ዓላማ እውቀትን በመሻት ነው፡፡አሁን አሁን የፖለቲካ መጠቀሚያ በመሆን ሕይወታቸውን እስከማጣት ሲደርሱ ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል፡፡በዚህ ዙሪያ ከወላጆችና ከተማሪዎች ያሰባሰብናቸውን አስተያየቶች ለንባብ በሚመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
‹‹እንደዛሬው ሳይሆን በፊት አንዱን ልጄን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር አንድም ቀን እንዲህ ይሆናል ብዬ አልተጨነቅኩም፡፡የሚሄድበትን ገንዘብ አስቤ ካዘጋጀሁለት ሀሳቤን የጨረስኩ ያህል አስብ ነበር። በዚህ ሁኔታ ተምሮና ተመርቆ አሁን በሥራ ላይ ይገኛል›› የሚሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን በደምበጫ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ ወይዘሮ እመቤት ስንሻው ናቸው፡፡
ወይዘሮ እመቤት እንደሚሉት፤ትንሹ ልጃቸው ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱ ሲሆን ነቀምቴ ዩኒቨርሲቲ እየተማረ ነው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ባለመሆናቸው ደስታ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡መንግሥት በተገቢው የመማሪያ አካባቢዎቹን ሰላም መጠበቅ አለበት። ወላጆች በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን ሲልኩ በመጥፎ ድርጊት ውስጥ ልጄ እንዳትሳተፍ አደራህን ብለው ጡታቸውን አስይዘው አስምለው መላክ አለባቸው፡፡ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ድሮው ሰላም ተመልሰው ልጆቻችን በሰላም እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ችግሩ የሚብሰው ለእኛ ለእናቶች ነው ሲሉ ወይዘሮ እመቤት እንባ እየተናነቃቸው አጫውተውናል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ልጃቸው እንደሚማር የገለጹልን የአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ በቀለ ስዩም ናቸው፡፡እርሳቸው እንደሚሉት፤ በዚህ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እውቀት መገበያያ መምሰላቸው እየቀረ ነው፡፡ወጣቶች በሚሰባሰቡበት ጊዜ አስገራሚ ባህል፣አመጋገብና አለባበስ በማየት ኢትዮጵያ ለካ እንደዚህ ነች በሚል ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ በጉጉት ያወሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
‹‹እኔ ዩኒቨርሲቲዎች ግርግር እየተፈጠረባቸው ነው ብዬ ልጄን ማስቀረትን አልመረጥኩም፡፡ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች ልጆቻቸውን ከላኩ በኋላ እንዲመለሱ የሚያደርጉም እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ነገር ግን መፍትሄው ልጅን ማስቀረት እና ማስመለስ ነው? ይልቁንስ ልጆቻችንን በተገቢው መምከር አለብን፡፡ሌላው ቀርቶ ችግር ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ በግቢያቸው ሲመለከቱ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አካላት ፈጥነው ማሳወቅ አለባቸው፡፡
‹‹ሰላምን ማምጣት የሚቻለው ወጣቶቹ ስሜታቸውን በመቆጣጠር ወላጆቻቸውን እና አላማቸውን እንዲሁም አገራቸውን ማሰብ ሲችሉ ነው፡፡ይህን ያህል ጊዜ የለፉበትን ትምህርት ፍሬ በሚያዩበት በመጨረሻው ወቅት የሚፈጠሩ እንዲህ ዓይነት ብጥብጦችን በብልሃት ማለፍን መልመድ አለባቸው፡፡ሆን ብለው ሕይወታቸውን ሊያበላሹባቸው የሚሞክሩትን በጥበብ ማለፍ ይኖርባቸዋል›› ሲሉ አቶ በቀለ ይናገራሉ፡፡
አቶ በቀለ እንደሚገልጹት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲዎችን የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ስልክ ቁጥር በደንብ ይዘው መንቀሳቀስ አለባቸው። በተጨማሪም ለወላጆቻቸው ስልክ ቁጥሮቹን ሊሰጡ ይገባል፡፡ዩኒቨርሲቲዎችም የእነዚህን ስልክ ቁጥሮች መስራት እና አለመስራት በየቀኑ ማረጋገጥ አለበት፡፡ስልክ ቁጥሮቹ 24 ሰዓት የሚሰሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ይሄ ከሆነ ልጆቻችንን የሚያሰጉ እንቅስቃሴዎች በሚመለከቱበት ጊዜ ቢያንስ ለወላጆቻቸው ማሳወቃቸው አይቀርም፡፡
ወላጆችም በእነዚያ ስልክ ቁጥሮች የችግሩን መኖር ለሚመለከተው አካል ፈጥነን የሚያሳውቁ ይሆናል፡፡የከፋ ችግርም ሳይፈጠር ሁኔታውን ማረጋጋት ያስችላል ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ (እህት፣ ወንድም፣ እናትና አባት) በአንድ ተሰብስቦ ከሄደበት የመማር ዓላማ በስተቀር በምንም ድርጊት ውስጥ ልጆቹ እንዳይሳተፉ ሊመክር ይገባል ይላሉ፤ አቶ በቀለ፡፡ሌላ ዓላማ ይዘው ፖለቲካን በማራመድ ሌላ ሥራ የሚሰሩትም በዚህ መንገድ ክትትል ከተደረገ ተለይተው መውጣታቸው አይቀርም፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ተማሪው ወጣት ታደለ የሻነው ሀይለመስቀል እንደሚለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓላማቸውን ብቻ መስራት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል ባይ ነው፡፡ለዚህ ግን ቤተሰብ የሚያደርገው ክትትል አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ትምህርት ቤቱ የሚያደርገው ክትትል ደግሞ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በውል መለየት አለበት። ያን ማድረግ ሲቻል በሰላም መማር ማስተማሩ መቀጠል ይችላል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ለረብሻና ለብጥብጥ ዋና ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱት አካላት ዋና የትኩረት ኢላማቸው በውጤታቸው ደካማ በሆኑ እና በሚሰናበቱ ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ራሳቸው ጭምር የተማሪ መታወቂያ አመሳስለው መስራት እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡ስለዚህ ማንኛውም በሰላም መማር እና መመረቅ የሚፈልግ ተማሪ በማደሪያ አካባቢዎች የሚከናወኑትን ተግባራት ተከታትሎ ማሳወቅ አለበት፡፡
ተማሪው ራሱን ነቅቶ የሚጠብቅ ከሆነ እነሱ መላዕክት አይደሉም እኮ ከሰማይ አይወርዱም፡፡በአካባቢው ውለው አድረው ተከታይ መልምለው ሲያጠናቅቁ ነው ወደ ረብሻ ውስጥ የሚገቡት፡፡የሚነሱ ሀሳቦችን ምክንያታዊ ሆኖ መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡በስሜት የመነዳት ሁኔታ ካለ ዓላማን ማሳካት ቀርቶ የትም መድረስ አይቻልም፤ ብዙ እንቅፋቶች አሉ፡፡ስለዚህ ሰከን ብለን ማሰብ አለብን ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
‹‹ተማሪዎች ራሳቸው ዓለም የደረሰበትን ሁኔታ የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡በዚህ ዘመን የሚመራቸውን ተከትለው ለምን ይነዳሉ? እያንዳንዱ ተግባር በተማሪዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል›› የሚለው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ባበው አዝመራው ነው፡፡
በመሆኑም በሚፈጠረው ችግር የሚባክነው የእኛ የመማሪያ ጊዜ፣ የሚጠፋው ሕይወት ከግጭቱ የሚተርፈው በቀልና ጥላቻ መሆኑን ካሳለፍናቸው ዓመታት መማር ነበረብን።፡ወጣት አስተዋይና በደመነፍስ የሚመራ መሆን የለበትም፤ ምክንያታዊ በመሆን ማንሳት የሚፈልጉት ጥያቄ ካለም በውይይት መጠየቅና ተነጋግሮ መተማመን ይቻላል፡፡በተማሪዎች መካከል እርስ በርስ መዋደድና አንድ መሆን ካልቻልን እንደዚህ አይነት ችግሮች እየተፈጠሩ ሊቀጥሉ ይችላሉ በማለት ባበው ስጋቱን ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በዩኒቨርሲቲዎች እንዲኖር ተማሪዎች በራሳቸው ሐሳብ መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ ልዩነት ቢፈጠር እንኳን ከስሜታዊነት ነፃ ሆኖ በምክንያትዊነት በማመን ችግሮችን መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡በሰከነ መንገድ አላማቸውን ማሰብ አለባቸው፡፡ወላጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማሰብ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2012
ሙሐመድ ሁሴን