ኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የጀመረችው በ1954 ዓ.ም እንደሆነ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ምርቱን በአገር ውስጥ በስፋት በማምረት የስንዴን ፍላጎት ለማሟላት ቆላማ አካባቢዎችን ለመጠቀም የግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ያሉበት የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም በ2011 ዓም ሦስት ሺ ሄክታር መሬት በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሶማሌ ቆላማ ቦታዎች ከባለሀብቶችና ከአርሶአደሮች ጋር በመሆን ለማምረት ተችሏል፡፡
በቀጣይም በቆላማ አካባቢዎች ያለውን ለመስኖ ተስማሚ የሆነውን መሬት ከውሃ እና ቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት ስንዴን በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን የመተካት አቅም ያለ መሆኑ የተረጋገጠበት ነው፡፡ ይህንንም ለማስፋት ትልቅ ተሞክሮ የተቀመረበት እንደሆነ ግብርና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡
ባለፈው የምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ ችግሮች በ2012 ዓ.ም እንዳይደገሙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ የምርጥ ዘር ብዜት መንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶቹ አባዝተው ያቀረቡት ዘር ጠቅላላ ከሚታረሰው መሬት ከ30 በመቶ በላይ እንዳልሸፈነ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስታውሰናል፡፡ የምርት ብክነትን እና ጥራት የሚያሻሽል ሜካናይዜሽን የአቅርቦት እና የዋጋ ችግር ያለበት እንደሆነም በአጽንኦት የተገለፀ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በአንዳን የአገሪቱ ክፍሎች የስንዴ ምርጥ ዘር እጥረት እየተስተዋለ ያለበትን ሁኔታ አርሶአደሮች ይናገራሉ፡፡
አርሶ አደር ወሰና ኡርጌሳ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ዋሙራ ሰቆ ቀበሌ አንድነት በሚል ስያሜ በክላስተር /ኩታ ገጠም/ የተደራጁ ከ66 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ያስተባብራሉ፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ከኋላ ቀር አሠራር ተላቆ ዘመናዊ አሠራሮችን እየተከተለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የግብርና ሙያተኞች እገዛም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አርሶአደር ወሰና፣ አርሶ አደሩ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ምርታማነቱን የሚያሳድጉ አዳዲስ አሠራሮችን በመቀበል ተነቃቅቶ እየሠራ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በበጋው ወራት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ስንዴን በመስኖ ለማምረት በሀገር ደረጃ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር የአካባቢው አርሶአደሮች ዝግጁ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶአደር ወሰና ዕቅዱ ገበሬው የመኽር ምርቱን ከሰበሰበ በኋላ ያለሥራ የሚያሳልፈውን ረዥሙን የበጋ ወራት በሥራ የማሳለፍ አዲስ ባህል እንዲያዳብር ከማገዙ በተጨማሪ የስንዴ ምርትን በሚፈለገው ደረጃ አምርቶ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለሟሟላትና ለስንዴ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡ ዕቅዱን ለመተግበር ግን የምርጥ ዘር ግብአትን ማሟላት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አርሶ አድር ስሜ ሄዪም በበኩላቸው እንዳስረዱት አርሶአደሩ በአካባቢው የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ በመስኖ ስንዴን ለማምረት ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ አርሶአደሩ መሬቱን አርሶ ለዘር አዘጋጅቶ ምርጥ ዘር ባለማግኘቱ የዘር ጊዜ ያልፍበታል፡፡ በምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት ከዕቅድ ውጭ ሌላ አዝርዕት ለመዝራትም ይገደዳል፡፡ ይህ ደግሞ ምርታማነትን ይቀንሳል፡፡ ችግሩ በበጋው ለሚከናወነው የመስኖ ልማት እንዳይደገም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
አቶ ከበደ ደበሎ የምዕራብ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በበጋው በባህላዊና በዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎች በመስኖ በመጠቀም ስንዴን ለማምረት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ አገራዊ ዕቅድን ለመተግበርም መንግሥት ምርጥ ዘርንም ሆነ የተለያየ የግብርና ግብዓቶች ለመሟላት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ተጠቅሞ ውጤት በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው አርሶአደር የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብ ማገዝ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
የአርሲ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው የምርጥ ዘር አቅርቦት በየዓመቱ መጨመሩንና ባለፈው የምርት ዘመን ብቻ 180 ሺ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደተሰራጨ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ አቅርቦትና ፍላጎት እንዳልተጣጣመ ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት ስንዴን በመስኖ ለማምረት በተያዘው ዕቅድ መሰረት አመችነት አላቸው በተባሉ አምስት ወረዳዎች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና በዕቅዱ መሰረትም የአርሶ አደር ስልጠናና የመሬት ልየታ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በበጋ ወቅት ስንዴን ማምረት በኢትዮጵያ አዲስ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ ምርጥ ዘርን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል፡፡ ዕቅዱ ከተተገበረ በ2011 /12 ዓ.ም የምርት ዘመን የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብና ኤክስቴንሽንና ኮሙኒኬሽን ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደረሰ ተሾመ በበኩላቸው ስንዴን በበጋ በመስኖ ለማልማት በሀገር ደረጃ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አዲስ ተሞክሮ እንደሆነና ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚስማማና ለመስኖ የሚሆን ምርጥ ዘርን የማዘጋጀት ክፍተት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት በዋናነት የዋቤ ፣ የአዋሽና የኦሞ ተፋሰሶችን እና ቆላማ ቦታዎችን መሰረት ያደረገ የምርጥ ዘር አቅርቦት የሚያደርግ ቢሆንም በደጋማ ቦታዎች የከርሰምድር ውሃ ተጠቅመው ስንዴን ማምረት የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ቀደምሲል የሚጠቀሙትን ምርጥ ዘር መጠቀሙ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
በበጋ ወቅት የሚዘራ ምርጥ ዘር ሙቀትን መቋቋም የሚችልና ለመስኖ ተስማሚ መሆን እንደሚገባው የተናገሩት ዳይሬክተሩ ፌደራል መንግሥት በዕቅድ ከያዛቸው ቆላማ ቦታዎች ውጭ በበጋ የሚዘራ ምርጥ ዘርን ለሁሉም አካባቢ ለማዳረስ አልሞ እንዳልተዘጋጀ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ደረሰ እንዳሉት በመስኖ ልማቱ 32 ሺ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም በሚቀጥለው ዓመት እስከ መቶ ሺ ሄክታር ሊሸፍን የሚችል ምርጥ ዘር ለማባዛት መንግሥት በጀት ይዞ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2012
ኢያሱ መሰለ