ብቻዬን ይህንን አደረኩ ብለው አይኩራሩም። ለሥራ አጋሮቻቸው ቀዳሚውን ቦታ ይሰጣሉ። በዚህ ባህሪያቸው ብዙዎች ይወዷቸዋል። ትልቅ ትንሹን በሙያም ሆነ በሰውነቱ አክባሪ ናቸው። ይህም በሰዎች ዘንድ ትልቅ አክብሮት እንዲኖራቸው አድርጓል። ብዙዎችም “የቡና ልማት አባት” ሲሉ ያደንቋቸዋል። እርሳቸው ግን “ከእኔ በላይ ብዙ የሰራ አለ” የሚሉ ናቸው። ቢሆንም እሳቸው በኢትዮጵያ ቡና ልማት ዘርፍ ከ40 ዓመት በላይ የሰሩ ባለሙያ ናቸው ።
እነቬትናምን ሳይቀር በቡና ምርታቸው የተሻሉ እንዲሆኑ ብዙ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ራሳቸውም በአንደበታቸው ይመሰክራሉ።አሁንም በቡና ልማት ላይ ዓይናቸውን አልነቀሉም፤ አገሪቱ በቡና ምርቷ በዓለም እንድትተዋወቅ ያደረጉ እንቁ ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው ይመሰከርላቸዋል። የተሰሩ ምርምሮችን ዳግም ሥራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ እንደ ወባና የእንስሳት በሽታ ፍቱን መድኃኒት ያስገኙም ናቸው የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ይልማ የማነብርሃን። ይሄ ልምድና ተሞክሯቸው ትምህርት ይሆነን ዘንድ ለዛሬ የ‹‹ህይወት እንዲህ ናት›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ።
ልጅነት
የካቲት 16 ቀን 1927 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ይልማ ለአባታቸው የመጨረሻ ልጅ ለአክስታቸው ደግሞ በቤት ውስጥ ብቸኛ ልጅ ሆነው ነው ያደጉት። እናት እርሳቸውን ወልደው ይህችን ምድር በመለየታቸው እናትም አባትም ሆነው ያሳደጓቸው አክስታቸው ናቸው። በእርግጥ አባታቸውም እኔ ላሳድገው ብለው ነበር። የእናት እህት ግን ለምን በወንድ እጅ በእንጀራ እናት ብለው በመውሰድ ተንከባክበው አሳደጓቸው። አደግ ሲሉ ደግሞ አባታቸው ጋር ሄደው መኖር ቀጠሉ።
‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ከአክስታቸው ጋር አዲስ አበባ ያደጉት አቶ ይልማ፤ ሸገር ተወልደው እስከ አስር ዓመታቸው ድረስ የኖሩት ካዛንቺስ ነበር ። አክስት እንደ እናትና አባት ባይሆንም በቤት ውስጥ ብቸኛ ልጅ በመሆናቸው የፈለጉት ነገር እየተሟላላቸው አድገዋል። ጨዋታ ሲፈልጉ እንዲጫወቱ፤ እቤት ውስጥ ማንበብ ሲፈልጉም እንዲያነቡ ይፈቀድላቸዋል። ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በቤተክርስቲያን ነው። ይሄ ደግሞ ሰፈር ውስጥ እንዳይውሉ ከልጆች ጋርም እንዳይጋጩ አግዟቸዋል። በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ጨዋው ልጅ እስከመባል እንዳደረሳቸው ይናገራሉ።
ጸጥ ያለ አካባቢን አጥብቀው የሚወዱት የትናንቱ ህጻን የዛሬው አዛውንት አቶ ይልማ፤ በባህሪያቸው ተጫዋች፤ ለአካባቢው ሰው ሁሉ ታዛዥና ማንበብ የሚወዱ ናቸው። በዚህም ሁሉም ሰው ይመርቃቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወት የሚወዱት የእግር ኳስ ነው። ለጨዋታውም የጨርቅ ኳስ ሰፍተው እርሳቸው የአጥቂነት ቦታን በመተካት ብዙ ጎል ማስቆጠር ያስደስታቸዋል። ብዙ ጊዜም የተለያዩ ቡድኖች የእነሱ አባል እንዲሆኑ ይመርጧቸው እንደነበር አይረሱትም።
አቶ ይልማ በቤት ውስጥም ቢሆን የተለያዩ ነገሮችን በመስራት አክስታቸውን የሚያግዙ ሥራ ወዳድ ልጅ እንደነበሩ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ በስፋት የሚያስታውሱት ለዛሬው መሰረት የሆናቸውን የቡና ማፍላት ሥነሥርዓት ነው። ቡና አፍልተው ጎረቤት ተሰብስቦ ሲጠጣ በጣም ይደሰቱ ነበር። እርሳቸውም አንድ ስኒ ቡና ይጠጣሉ። ጣዕሙ በጣም ያስደስታቸው እንደነበር ይናገራሉ።
‹‹ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት ቡና ማህበራዊ ህይወትን ከማጠናከሩ ባለፈ ጣዕሙና መዓዛው ዘላለም ከአዕምሮ የሚጠፋ አይደለም። ለቡና ምርምር ሥራም እንድገባ የረዳኝ ይህ የልጅነቴ ልምድ ነው›› ይላሉ። መቼም ቢሆን በቡና ልማት ላይ የሚሰራ ሰው እሆናለሁ ብለው አስበው እንደማያውቁ የሚናገሩት አቶ ይልማ፤ በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት የሚያደንቋቸውንና የሚወዷቸው መምህር ጥላሁን ዳምጤን ነበር። ብዙዎችም እርሳቸውን መሆን ይሹ እንደነበር ያነሳሉ። ምክንያቱን ደግሞ ሲያስረዱም የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን የሚያስተምሩት ሥነምግባርና ታሪክ በመካከል እየቀላቀሉ ነውና በስነምግባር የተሞረዱ ልጆች እንዲሆኑ እንዳደረጓቸው አጫውተውናል።
ሌላው ከአቶ ይልማ የልጅነት ህይወት ሳይነሳ የማያልፈው ጉዳይ ከአስር ዓመታቸው በኋላ ያሳለፉት ህይወታቸው ነው። ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ሲሉ የሚወዷቸውን አክስታቸውን ትተው ወደ አዳማ የሄዱበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ ያስታውሳሉ። አባት ‹እኔ ጋር ከሆንክ ጊዜ ሳትፈጅ ዘመናዊ ትምህርት ትጀምራለህ› ሲሉ ተናግረዋል። የገቡላቸውን ቃል ለመጠቀምና ይህንን እድል ላለማጣት ሲሉ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ጓዛቸውን ጠቅልለውም ከአዲስ አበባ አዳማ ገቡ።
በወቅቱ አክስት በጣም ተከፍተው እንደነበር የሚያነሱት አቶ ይልማ፤ እንጀራቸውን መቅበር ስለማይፈልጉ ፈቅደውላቸው አባታቸው ጋር እንዲሄዱ ይገልጻሉ። በእርግጥ አክስታቸው ቄስ ትምህርት ቤት አስገብተዋቸው ዳዊት ከመድገም አልፈው ዜማን እስከማወቅ አድርሰዋቸዋል። ግን ማን እንደዘመናዊ ትምህርት ያሉት አቶ ይልማ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ቆርጠው ተነስተዋል። የቅርብ ጓደኞቻቸው ዘመናዊ ትምህርት ተምረው ሲመጡ በእንግሊዘኛ ትምህርት ከእርሳቸው እንደሚበልጡ እያሳዩ ያስቆጯቸው ነበርናም ከእነርሱ እኩል ለመሆን በማሰብ ጭምር ነበር በቁጭት አባታቸው ጋር ሄደው መማሩን የጓጉት።
የአዛውንቶችና የትልቅ ሰዎች ምርቃት ትልቅ ቦታ ያደርሳል የሚለው አባባል በአቶ ይልማ ልብ ውስጥም ሀሳቡ ታትሟል።እናም ለምርቃት ሲሉ በአካባቢያቸው ለሰወች መላላክን ያዘወትራሉ። በአባታቸው ቤት ትንሹ በቤት ውስጥ ብቸኛ ልጅ ሆነው ነው ትምህርታቸውን የተማሩት። የእንጀራ እናታቸው ደግሞ ከእናት ባልተናነሰ ትንከባከባቸው ነበር። ብዙ ጊዜም ለትምህርታቸው ትኩረት የሚሰጡ ልጅ ሆነው ነው ያደጉት። የቤት ውስጥ ሥራ እንኳን እንዲሰሩ እንደማትፈቅድላቸው የሚናገሩት አቶ ይልማ፤ በሥራው ፋንታ እንዲያነቡና እንዲጫወቱ ትገፋፋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬም ድረስ ውለታዋን እያሰቡ ያመሰግኗታል።
አቶ ይልማ ይልማ ተብለው ስም የወጣላቸው በምን ምክንያት እንደሆነ በደንብ ባያውቁም አንድ ልጅ ስለሆኑ “ይብዛ፣ ይበርክት፣ ቤተሰቡ ሙሉ ይሁን” ለማለት ታስቦ ስማቸውን እንደወጣላቸው ይገምታሉ። አድገው በሥራ ላይ እያሉ ደግሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው ይልማ የሚለውን ስማቸውን ከቡና ልማት ጋር ያስተሳስሩት እንደነበርና “ቡናው ይልማ” እያሉ ይጠሯቸው እንደነበርም አጫውተውናል። ይሄ መጠሪያቸው ያስደስታቸዋል።
ትምህርት
ፊደል የቆጠሩት በቄስ ትምህርት ቤት ኡራኤል ነበር ። በዚህ ቤት እንደቄስ ተማሪነታቸው ከሀሁ ጀምረው አቦጊዳንና መልዕክተን አልፈው ዳዊት ደግመዋል። ከዚያ ልቀውም ዜማንና ንባብንም ተምረዋል። ከዚያ በኋላ ነው አዳማ ሲገቡ ይህንን ትምህርት ያቋረጡት። ምክንያቱም የትናንቱ አዳማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የዛሬው አጼ ገላውዲዎስ እርሳቸውን የመሰለ ጎበዝ ተማሪ ይፈልጋል። ስለዚህም እዚያ ገብተው ዘመናዊ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ቀጠሉ።
በገቡበት ትምህርት በጉብዝናቸው ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው በመሆናቸው ከሌሎች ተማሪዎች ተመርጠው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አመሩ። ጉብዝናቸው አልቀነሰምናም 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ። በዚያ ዘመን ደግሞ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠትና ለማስተማር የሜክሲኮ መንግስት ቃል ገብቶ ነበር። እርሳቸውም ከአምስቱ ምርጥ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ በመሆን በነጻ የትምህርት ዕድል ወደ ሜክሲኮ ቻፒንጎ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ።
በቻፒንጎ ዩኒቨርሲት የእርሻ ትምህርት እንደተማሩ የሚገልጹት አቶ ይልማ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀቁ። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ጃንሆይ ሲሆኑ፤ ወደ ውጪ ከመሄዳቸው በፊት ለአገር የሚጨነቁት ጃንሆይ ቃል አስገብተው ልከዋቸዋል። ጃንሆይን ለመሰናበት በሚሄዱበት ወቅት የገቡት ቃል አለ። ያ የገቡት ቃል በውስጣቸው የነበረው ስሜት ዛሬ ድረስ እንዳልተለያቸውም ይገልጻሉ። ቃልኪዳኑ ላይ ሁለት ነገሮች በዋናነት ተነስተዋል የሚሉት አቶ ይልማ፤ ‹‹ ስንልካችሁ ለአገር የሚጠቅም ትምህርት ተምራችሁ እንድትመጡ ነው። የአገራችሁን ስም በምንም መልኩ በከንቱ እንድታስጠሩ አንፈልግም›› የሚል ነበር። ይህንን ቃል መሰረት አድርገውም ለሀገራቸው በጣም ወሳኝ የሆነውን የእርሻ ትምህርትን መርጠው ተምረዋል። ጎን ለጎንም የቡና ትምህርትም እንደተማሩ አጫውተውናል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም የያዙት ከዚሁ መስክ ሳይወጡ በቻፕንጎ ዩኒቨርሲቲ ነው። የሚያስመሰግን ውጤት ለማምጣትም ጥረት አድርገው እንደተሳካላቸውም ያስታውሳሉ። ከዚያ ቃል እንደገቡት ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ከሁለተኛ ዲግሪ በኋላ ትምህርታቸውን እንዳልቀጠሉ የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ምክንያታቸው ሁለት ነገር እንደነበር ያነሳሉ። የመጀመሪያው የጊዜ ያለመመቻቸት ሲሆን፤ ሁለተኛው የሚበልጠውን በመምረጣቸው ነው። የመረጡት ጉዳይም በእውቀት ላይ እውቀት ለመጨመር በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰድ ነው። ጎን ለጎንም ስልጠናዎቹን በመስጠት ትምህርት እያገኙ መሆኑን ያምናሉ።
በተጨማሪ በጅማ እርሻ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ያስተምሩ ነበርና በዚያም እውቀታቸውን ያጎለብቱ እንደነበር ይናገራሉ። ” በእርግጥ” ይላሉ አቶ ይልማ ‹‹በእርግጥ መማር መቼም ቢሆን አይናቅም። የሚጨምረው አንድ ነገር አለ። ሆኖም ምቹ ጊዜ ስላልነበረኝ ሦስተኛ ዲግሪዬን ልማር አልቻልኩም። ዛሬ ደግሞ አርጅቻለሁ። ስለዚህ እንዳመለጠኝ አስባለሁ። ነገር ግን ሁሌም የምማርበት ሁኔታ ስላለ ከእውቀት አራቅኩም ብዬ አላስብም›› ብለውናል።
ሥራን በቡና ልማት
ለትምህርት በሄዱበት የውጭ ሀገር ቀርተው የመስራት እድሉ ቢኖራቸውም ማን እንደ አገር ብለው የገቡትን ቃል አክብረው ከሜክሲኮ ወደ አገራቸው ተመልሰው በጅማ እርሻ ትምህርት ቤት በማስተማር ነው ሥራ የጀመሩት።ሥራቸው ጠንካራ ነውና ጎን ለጎን የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ ሆኑ ። ስምንት ዓመት ከስድስት ወር ያለምንም እረፍት የእርሻ ትምህርት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት፣ ተማሪዎች በቂ እውቀት ከእርሳቸው እንዲቀስሙ በማድረግ አሳለፉ።
ውጤታማነታቸው ከትምህርት ቤቱ አልፎ አገር ሲያውቃቸው ደግሞ ይህ ሰው በስፋት ያግዘናል ሲሉ አዲስ አበባ በትናንቱ ቡና ቦርድ በዛሬው ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቀላቀሉ። እዚህ ከገቡ በኋላም ሥራ ወዳድነታቸው እንዳለ ነውና የቡና ልማቱ ላይ አሻራቸውን ማሳለፉን ተያያዙት። በእርግጥ ቦታው ላይ ሲመጡ የመምሪያው ኃላፊ ሆነው ነበር። ይህንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቀን ከሌሊት ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። በቆይታቸው ምስጋናን ያስገኙ ሥራዎች ሰርተዋል።
በአንድ ተቋም 20 ዓመታትን በተለያዩ ኃላፊነቶች ማሳለፍ ቀላል አይደለም የሚሉት አቶ ይልማ፤ ቡናና ሻይ በአቅም እንዲጎለብት ያልቆፈሩት ድንጋይ እንዳልነበረ ይናገራሉ። በዚህም ፍሬያማ ተግባራትን ከውኛለሁና ደስ ይለኛል ብለውናል። ከዚህ መስሪያ ቤት ሲለቁም በቀጥታ የተቀላቀሉት የግሉን ዘርፍ ነበር ። ከሼህ መሀመድ አል አላሙዲ ጋር ለመስራት ሜድሮክ ኢትዮጵያ ውስጥ ገቡ። ‹‹ኢትዮ አግሪ ሴፍት›› የሚባል ድርጅት አቋቁመውም በተለይ በቡናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲሰሩም ሆኑ።
ሥራ ወዳዱ እንግዳችን፤ ድርጅቱ የሜድሮክ ቢሆንም ብዙ መሰረት እንዲይዝና እንዲመሰረት ያደረጉ ሰው ናቸው። ከቡና አልፎ የአበባ፣ የእህል እንዲሁም የሻይ እርሻ እንዲኖረው ሰርተዋልም። ከዚህ በፊት በምርምር ውጤት ያመጡ እንደ እንዶድ አይነቶች ዳግም ተሞክረው ለተለየ ተግባር እንዲውሉ በማድረግ ዙሪያ ብዙ ሰርተዋል። ለአብነት ለወባና ከውሀ ጋር ወደ ከብቶች በመግባት እንስሳትን ለጉዳት ለሚዳርገው አልቅት መድኃኒት የመሆኑን ምስጢር በባለሙያዎች ተመርምሮ እንዲቀርብ አድርገው ውጤታማ መሆኑን ያረጋገጡ ናቸው። በዚህም ሥራቸው ሰውንና እንስሳትን
ከገዳይ በሽታ አድነዋል።
እንግዳችን ከብዙዎቻችን ለየት የሚያደርጋቸው በሄዱበት ስፍራ ለማዳና ተቋሙን ለመለወጥ የሚሰሩ መሆናቸው ነው። ከሜድሮክ ኢትዮጵያ ሥራውን ከለቀቁ በኋላ እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲቀጠሩ ምንም ሳይቸገሩ ነበር ወደ ተግባር የገቡት። በእርግጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያሰራቸው በፈለጋቸው ጊዜ እየጠራ ነው። ቢሆንም ግን ሥራው በአገር ውስጥ አይደለምና ማደናገሩ አይቀርም ነበር። እርሳቸው ግን ሙያውን ተክነዋልና ሳይደናገሩ አሰልጣኝነታቸውን ይወጣሉ።
አቶ ይልማ በድርጅቱ እውቅና ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት ያመሩት ወደ ቬትናም ነው። በዚያም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለገበሬዎቻቸውና ለተለያዩ የእርሻ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥተዋል። ለሶስት ጊዜም እየተመላለሱ አገሪቱ ከነበረችበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሦስተኛ እንድትሸጋገር አሻራቸውን አሳርፈዋል። በተመሳሳይ ይኸው ድርጅት በሜንማር ወይም በርባን ልኳቸው ለሶስት ወር ያህል ስልጠና ሰጥተው ብዙ ለውጦች በአገሮቻቸው ላይ እንዲመጣ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በዩጋንዳና በአገር ውስጥም ይህንኑ ተግባራቸውን በመከወናቸው ለውጦች እንዲመጡ አስችለዋል።
እንግዳችን እንደሚሉት፤ በዓለም ደረጃ ለቬትናም በቡና ምርት መታወቅ ምክንያቱ የእነሱ ስልጠና ብቻ አልነበረም። ሦስት አበይት ነገሮች ናቸው በዋናነት ውጤቱ እንዲታይ ያደረጉት። የመጀመሪያው የመልክአምድር ምቹነት ፤ ሁለተኛው የገበሬው ጥንካሬና የመንግሥት እገዛ ሲሆን ሶስተኛው ገበሬዎቹ የሚይዙት ሰፊ የእርሻ ቦታ በሰለጠነ ቴክኖሎጂ ታግዞ መልማት መቻሉ ነው። በዚያ ላይ የዘሩ ምርታማነትና በመስኖ መልማት ትልቅነቷን እንድታሳይ አግዟታል።
ቡና ችግርን መፍቻ፤ ማንነትን ማወቂያ፣ ቤተሰብ መመስረቻ፣ ስለ አገር፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ ማወቂያ ነው። ስለዚህም በአገር ውስጥም ማሳደግ ይገባል። በአገራቸውም ይህ ተግባር እውን ይሆን ዘንድ እየሰሩ ይገኛሉ። አሁን ባሉበት ደረጃ ተመልሰው ሜድሮክ ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባት የማማከር ሥራ እየሰሩም ነው። ዘወትር መፈክራቸው ‹‹ጉልበት እንጂ አዕምሮ አይደክምም›› ነውና እስከ ህልፈታቸው ድረስ እውቀታቸውን በማካፈል አገራቸውን በማገልገል ላይ ናቸው።
አቶ ይልማ በቡና ዙሪያ የተለያዩ ጽሁፎችን ለህትመት አብቅተዋል። አንድ መጽሐፍም ታትሞ ለንባብ በቅቷል። ይህ መጽሀፍ ብዙ የቡና ልማትን የሚያፋጥኑ ሀሳቦች ቢኖሩትም በእንግሊዝኛ በመጻፉ የአገር ውስጥ ገበሬዎች ሊያነቡትና በተግባር ሊያውሉት አይችሉም። ስለሆነም በቅርቡ ለህትመት የሚበቃ በአማርኛ የተጻፈ መጽሐፍ ለማሳተም ጥራዙን እንደጨረሱ አጫውተውናል።
የመልካም ሥራ መታወቂያ
በተለያዩ አካባቢዎችና አገራት ተዘዋውረው ንግግር በማድረጋቸውና ስልጠናዎችን በመስጠታቸው በርከት ያሉ ሰርተፊኬቶችን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ከሁሉም የሚልቅባቸው ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች ያሰባሰበው ‹‹የኢትዮጵያ ቡና ሳይንስ ሶሳይቲ›› የሰጣቸው ሽልማት ነው። ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ቡና ብዙ የለፋና አስተዋጽኦ ያደረገ ሲል ነው ከብዙዎች መካከል አንተ ትበልጣለህ ብሎ የሸለማቸው። በዚህ ደግሞ ክብር ይሰማኛል ይላሉ። የኢትዮጵያ ቡና በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ተግባራት ምቹነቱ ከመቶ ዓመት በላይ ቆይቷል። ይህንን ያደረጉ በዘመናዊም ሆነ በልምድ ቀደምት አባቶች ናቸው። እናም ይህንን ተክቶ በአገር ልጅ እውቅና ማግኘት ከማስደሰት በላይ እንደሆነም ይናገራሉ።
የአገር አበርክቶ
አቶ ይልማ መምህር በመሆናቸው ብዙዎችን በእርሻ ትምህርት የተሻሉ ተማሪዎች አብቅተዋል። በቡና መስክ የሚሰሩ ገበሬዎችንም ሆነ ባለሙያዎችን በማሰልጠንም ምርቱ ውጤታማ እንዲሆን ለፍተዋል። የቡና ቦርድ ላይ በኃላፊ በተቀመጡበት ወቅትም አቅሙን ለማሳደግ ከውጭ ድርጅቶች ጋር ሳይቀር በማገናኘት ሥራ ሰርተዋል። በተለይም እስከዛሬ ድረስ ከአገሪቱ ሳይነጠል በተለያየ መልኩ የሚያግዘውን አውሮፓ አንድነት ማህበር ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ያደረጉት ጥረት ሁሌም እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል።
የቡና ልማት ማጠናከሪያ ሥራን በስፋት የሚሰራውን ኮፊ ኢምፕሩቭመንት ፕሮጀክት /ሲፕ/ የተባለ ፕሮጀክትንም ወደ አገር ውስጥ ገብቶ እንዲሰራ ሀሳብ ያቀረቡት እርሳቸው ነበሩ።
መጀመሪያ በሜክሲኮ በትምህርት ላይ እያሉም ቢሆን አገራቸውን በመልካም ለማስጠራት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። ለአብነትም ጤፍ ሳር ነው መባሉ አንገብግቧቸው ጤፍ የተሻለ ንጥረ ይዘት ያለው ምግብ መሆኑን ለማስረዳት ያደረጉት በዋናነት ይጠቀሳል። ሜክሲኮ ቻፒንጎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ መምህራኑም ጭምር የጤፍን ጥቅም በሚገባ አልተረዱምና ሳር ነው እያሉ ያበሳጯቸው ነበር። ኢትዮጵያውያን ሳር ነው የምትመገቡት ይሏቸውም ነበር።
አንድ ቀን ይህ እንዳልሆነ ለማሳየት በፖስታ ቤት ጤፍ እንዲላክላቸው አደረጉ። እፍኝ የማትሞላዋን ጤፍም ዘርተው ሰባት ኪሎ አደረሷት። ከዚያ በዩኒቨርሲቲው ሙሉ የቤተሙከራ መሳሪያ ነበርና በብዙ ትግል አስፈቅደው እንዲመረመር አደረጉ። ውጤቱ አስደንጋጭ ነበር። እስከዛሬ የተሻሉ ናቸው ከሚሏቸው የእህል ምርቶች የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ነበር። እናም መምህራንም ሆኑ ተማሪዎቹ በዚያ ውጤት አፈሩ። የተሻለ ተመጋቢ መሆናቸውንም መመስከራቸውን ቀጠሉ። ይህ ደግሞ ለተማሪው ይልማ የምስራች ነበር። የአገር ጀግና እንደሆኑ እንዲሰማቸውም አድርጓቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ሌላው ለአገሬ አበርክቻለሁ ያሉት ነገር የቡና በሽታ አገር ውስጥ ገብቶ ብዙ ችግሮችን በመፍጠሩ ያንን መታደግ መቻላቸውን ነው። ይህ የሆነው ደግሞ የመፍትሄ አቅጣጫን በማመላከት ሲሆን፤ ዶክተር ዳኛቸው ከሚባሉ የሥራ አጋራቸው ጋር በመሆን ኬንያ በመሄድ ስለ በሽታው አጥንተው በመምጣታቸው ነው። በእርግጥ ኬንያ ውስጥ የተከሰተው ችግር ከአገሪቱ ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም በእነሱ የአየር ሁኔታ አጥንተው ስለሆነ የሰሩት አገር ውስጥ አምጥተው መተግበር አይችሉም። ግን አመላካች ነገሮችን ጠቁሟቸዋልና ወደ አገራቸው መጥተው አገራዊ መፍትሄን አፈላለጉ። በተለይ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሰጡት ደግሞ ተመራማሪዎች በመሆናቸው እነርሱን እያማከሩ እንዲሰሩ አድርገው ውጤቱን ማምጣት ችለዋል። በሰራሁትና ለውጤት ባበቃሁት በእያንዳንዱ ሥራ ውስጥ የአጋሮቼ ድርሻ ቀላል አይደለም። ሁሉም የሆነው ከእነርሱ ጋር ነው ይላሉ። መንግሥት ያስተማረኝም ሆነ አገር አስቀምጣ የምትመግበኝ ሰርቼ እንዳገለግላት መሆኑን አምኜ መስራቴ ከሁሉም ይበልጥ ሰራሁ እንድል አድርጎኛል።
ትዳርን ለ50 ዓመታት
ከባለቤታቸው ጋር ትዳር ከመሰረቱ ከሃምሳ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። በቤት ውስጥ አንድም ቀን ተጨቃጭቀውም ሆነ ተጣልተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ የተማሩ በመሆናቸው ልጆቻቸውን በፕሮግራም ነበር የሚያስጠኗቸው። ለራሳቸውም ጊዜ ይሰጡ እንደነበር ያነሳሉ። ይህ ደግሞ ችግሮች ቢኖሩም በውይይት እንዲፈቱ እንዳስቻላቸው ያስረዳሉ። ስለዚህም ባለቤታቸውን ‹‹የችግሬ ደራሽና ፈቺ፤ ድክመቴን ሸፋኝ ነች›› ይሏታል።
አቶ ይልማ ባለቤታቸውን ያገኟቸው ለሥራ ግብርና ሚኒስቴር በሚመላለሱበት ወቅት ነበር። እርሷ ደግሞ ጸሐፊ ስለነበረች ወደ ኃላፊው ጋር ከመግባታቸው በፊት እርሷን ማውራት ግድ ይሆንባቸዋል። እናም ሰው ወዳድና ተጫዋች በመሆናቸው ልቧን ይረቱታል። መቀራረባቸውም ይጠነክራል። ከዚያማ ጓደኝነታቸው አደገና ትዳር ተመሰረተ። ዛሬ የአራት ሴት ልጆች ወላጆች፣ የስድስት የልጅ ልጆች አያቶች ሆነዋል።
‹‹ልጆቻችንን ቀበቷችንን ጠበቅ አድርገን ነው ያሳደግናቸው። ስነምግባርና ጉብዝናም እንዲኖራቸው አድርገን በቻልነው መጠን ኮትኩተናቸዋል። ያ ደግሞ በውጤት ስለተደገፈ አምላካችንን እናመሰግናለን›› የሚሉት አቶ ይልማ፤ ሁሉም ልጆቻቸው ሁለት ሁለት ዲግሪ ሰርተዋል። አግብተው ልጆችን አፍርተውም ኑሯቸውን በአሜሪካ አገር አድርገው በደስታ ይኖራሉ።
መልዕክተ ይልማ
‹‹አሁን እድሜዬም ገፍቷል። ብዙ ለአገሬ የማበረክተው ነገር የለኝም። ሆኖም ቁጭ ማለት አልወድም። በተቻለኝ ሁሉ መልካም ዘር ዘርቼ ማለፍን እፈልጋለሁ። አሁን በሜድሮክ ኢትዮጵያ በአማካሪነት ባገለግልም ለአገሬ ያስፈለኩበት ቦታ ድረስ እየሄድሁ መስራትን እሻለሁ። ጉልበቴ ደከመና ልምዴ ሞተ ብዬ አላምንም›› የሚሉት አቶ ይልማ፤ አሁንም ለትውልዱ አደራ የሚሉት አላቸው።
በምንም ጉዳይ ላይ መጡልን እንጂ መጡብን መባልን አይሹም። ሁልጊዜም መጡልን ስባል ነው ከ40 ዓመት በላይ በቡናው ዘርፍ የሰራሁት። ይህ ደግሞ ሽልማቱ ከላይ ብቻ ሳይሆን ከሰዎችም ጭምር እንዲዘንብልን ያደርገናል። በመሆኑም ለራስ የአዕምሮ እርካታና ለሰዎችም የሚታይ ነገር ለመስራት ይህንን አድርጉ ይላሉ። የታላላቆችን ምክር የሚሰማ፤ ልምዳቸውንም የሚቀስም ሰው በነጻ የመማር እድል አለው። ከዚያ ካለፈ ግን ዋጋ ይከፍላል። በመሆኑም እናንተ በዋጋ ሳይሆን በነጻ ለመማር ሞክሩ ባይ ናቸው። ሌላው ምክረሀሳባቸው ራስን መመልከት ህዝብን ብሎም አገርን ማየት እንደሆነ አስቦ መስራት ልምዳችሁ ይሁን የሚለው ነው። ለዚህም የምትከተሉትን አርአያ የሚሆን ሰው ምረጡ፤ አርአያችሁ የተለያየ አቅጣጫዎችን እንዲያሳያችሁ ፍቀዱለት። ከዚያም በመራችሁ ቦታ በመጓዝ ውጤታማ ሆኑ ይላሉ።
‹‹ይህችን አገር ለማዳን በተለይ በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዙሪያ ሁሉም ሊሰራ ይገባል። ተፈጥሮ ሰውንም አገርንም ይታደጋል። ›› የሚለው ደግሞ የመጨረሻው ምክራቸው ነው። እኛም ምክራቸውን በተግባር እናውል በማለት ለዛሬ እንሰናበት። ሰላም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው