በሦስቱ ታላላቅ የዓለም ሃይማኖቶች (ይሁዲ፣ ክርስትናና እስልምና) መጻሕፍት ውስጥ የትራጄዲ ታሪካቸው ከሚተረክላቸው መካከል ቃየንና አቤል የየእምነቶቹ ዝነኛ ተጠቃሾች ናቸው። ከአዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) አብራክና ማሕፀን የተገኙት እነዚህ ሁለቱ ወንድማማቾችና ቀደምት የሰው ልጅ ዝርያዎች ፍጻሜያቸው የተደመደመው በሟችና በገዳይነት ነበር።
ሰበቡ፤
ሁለቱም ወንድማማቾች በአምላካቸው ለመባረክ በመሻት በየፊናቸው ለፈጣሪያቸው መስዋዕት አቀረቡ። ቃየን ምድር ያበቀለችውን ምርጥና መልካም ፍሬ በመሰዊያው ላይ ሲያቀርብ አቤል ደግሞ ከበግ መንጋዎቹ መካከል በኩራት የሰባውን አቀረበ። “ለምን?” ብለን ልንሞግት ሥልጣን ባልተሰጠን ምክንያት ፈጣሪ የአቤልን መስዋዕት በደስታ ሲቀበል ለቃየን መስዋዕት ደግሞ ፊቱን አጥቁሮ እምቢታውን ገለጸ። “ፈጣሪ እኮ ማበላለጥ አልነበረበትም” ብለን እንዳንጠይቅም “አምላክ አይከሰስም፤ ክብሩም አይገሰስም” በማለት ቅዱሳት መጻሕፍት ስለሚጠቁሙን ታሪኩን በአሜንታ ለመቀበል እንገደዳለን። በዚህም ምክንያት በፈጣሪ “አድልዎና” በወንድሙ ሞገስ ማግኘት ቅንዓት የገባው ቃየን ወንድሙን ወደ ሜዳ አታልሎ በማውጣት ደሙን ደመ ከልብ አድርጎ ነፍሱን በግፍ ነጠቀ።
ክህደትና እብሪት፤
“ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ተብሎ በፈጣሪ የተጠየቀው ቃየን፤ “አላውቅም! የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝ!?” በማለት አምላኩን ተዳፍሮ የእብሪት መልስ በመስጠቱ ፈጣሪው እጅግ አዝኖበትና አምርሮበት፤ “የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።. . . በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” በማለት አምላካዊ ውሳኔውን አሳወቀው።
ቃየን በፈጣሪ ዳኝነት ሞት አልተፈረደበትም። “ዐይን ላጠፋ ዐይኑን፣ እጅ ለቆረጠ እጁን” የሚለው የሙሴ ሕግ ገና ተረቅቆና ፀድቆ ወደ ሥራ ስላልገባ ገዳዩ ቃየን በፈጣሪ የተበየነበት የመጨረሻ ውሳኔ የዕድሜ ይፍታህ መቅበዝበዝ ነበር። የመቅበዝበዣውና የመንከራተቻው ማረፊያ ደግሞ “ከኤደን ገነት ምሥራቅ አቅጣጫ ትገኝ የነበረችው የኖድ ምድር ነበረች” ይለናል ቅዱስ መጽሐፍ። “ይህቺ የኖድ ምድር ማን ትሆን?” ለሚለው ጥያቄ የቲዮሎጂ መምህራኖቼ ለምን ምሥጢሩን እንደደበቁኝ አልገባኝም። መጋቤ ዕውቀት አስተማሪዎቼ ብቻ ሳይሆኑ ያነበብኳቸው መጻሕፍትና ኮሜንታሪዎችም “የኖድ ምድርን” የየት ሀገርነት ምሥጢር ሊገልጹልኝ አልቻሉም። በመላ ምት ጥቁምታቸውም አልተስማማሁም።
ገምት ብባል ግን ቃየን ተቅበዝብዞ ያረፈባት ትክክለኛዋ “የኖድ ምድር” ሀገሬ ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደማትቀር ጠርጥሬያለሁ። “ኖድ የሚጠቅሰው ኢትዮጵያን ነው በማለትህ ግዙፍ ስህተት ተሳስተሃል ብሎ በሥነ መለኮት እውቀቱ የሚያስደነግጠኝ ወይንም የሚገስጸኝ “ጠቢብ” ባገኝ በማን ዕድል። “በላ ልበልሃውን የማጧጡፈው” ሽንጤን ገትሬ ነበር።
“የኖድ ምድር የተባለችው ይህቺ መከረኛዋ ሀገሬ ሳትሆን አትቀርም” የሚለው ጨዋ መከራከሪያዬ መሠረት ያደረገው የጥንታዊያኑን የቤተ እምነቶች የብራና መጻሕፍት ወይንም አፈ ታሪክ ምስክር በማቆም አይደለም። በፍፁም። ምሁራን ትንተና ያደረጉባቸውን ማጣቀሻዎችና ኮሜንታሪዎችንም አስደግፌ አይደለም። በጭራሽ። የቀደምት ዓለማትን ዳር ድንበር የሚያሳዩትን ያረጁ የጂኦግራፊ ካርታዎችንም ዋቢ በመጥራት አይደልም። ምን ሲደረግ።
መከራከሪያዬ ነፍስ ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ የቃየንንና የልጆቹን ተግባር የሚመስሉ በርካታ የንፁሃን ደም አፋሳሽ ድርጊቶችን በሀገሬ ስመለከት ስለኖርኩ ምናልባትም ምድሬ በደም አበሳ ስትጠመቅ የኖረችው ያ ተቅበዝባዥ ቃየን አቤልን ገድሎ ያረፈው እዚሁ የእኔው የጉድ ሀገር “ምድረ ኖድ” ሳይሆን አይቀርም ብዬ በመጠርጠር ነው። ያደግነው “ጠርጥር ገንፎ ውስጥ ይገኛል ስንጥር” እየተባለም አይደል!?
የአቤሎችን ንፁህ ደም በሀገሬ ምድር ያፈሰሱ ቃየኖችን ስሰማና ሳስተውል ያደግሁባቸውን የዕድሜዬን መዛግብት ሳገላብጥ እንባና ሣግ እየተናነቀኝ የሚከተሉት ጥቂት መራር እውነታዎች ታወሱኝ።
አንድ፤
“አንተ በተወለድክበት ዓመትና ወር ልክ በሁለተኛው ቀን አራስ ቤት እያለሁ ወንድማማቾቹ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ገርማሜ ነዋይ በቆሰቆሱት መፈንቅለ መንግሥት በርካታ የንጉሡ ባለሟሎችና ንፁሃን ዜጎች ደማቸውን ደመ ከልብ አድርገው ፈጇቸው። በዘግናኙ እልቂት መንስዔነትም የሀገራችን ሕዝቦች በሙሉ ለአርባ ቀናት ሀዘን ተቀምጠን አልቅሰናል። ለአንድ ዓመትም ጥቁር ለብሰን አዝነናል።”
እኒያ ቃየናዊያን መንግሥት ለመፈንቀል የሞከሩት ሹመኞች በንጉሡ አቤላዊያን ላይ ያደረሱትን ደም አፋሳሽ ታሪክ በልጅነት ዕድሜዬ ትተርክልኝ የነበረችው ወላጅ እናቴ ነበረች። የወታደር ሚስትና በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡት መኮንኖች መካከል አንደኛው የአባቴ የልብ ወዳጅና የኮርስ ጓደኛው እንደነበሩም ሰምቻለሁ። ለአንድ ዓመት ያህል በሚኖሩበት የወታደር ካምፕ ውስጥ የሀዘን ጥላ እንዳጠላበትና የወታደር ልጆችም ዕድሜያቸው በሚፈቅደው ጨዋታ እንዳይቦርቁና እንዳይፈነጩ በወታደር ፖሊስ ገደብ ተጥሎባቸው እንደነበር ያጫወቱኝ ታላላቅ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው። በቃየንዊያን ግድያና በአቤላዊያን ሞት ምክንያት። እናስ ተቅበዝባዡ ቃየን ያረፈባት ምድረ ኖድ ይህቺው አሳረኛ ሀገሬ ናት ብዩ ብደመድም ምኑ ያስደንቃል?
ሁለት፤
በባለማንገቻ ቁምጣና በበረባሶ ጫማ እድሜ ላይ በነበርንበት የታዳጊነት ዕድሜያችን ላይ ደግሞ ደርግ የሚባል ጨካኝ የቃየናዊያን ስብስብ የ1953ቱን ዕልቂት ደግሞ ከጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ካራ ያመለጡትን 60 ያህል የንጉሡን አቤሎች በአንድ ሌሊት ለጋራ መቃብር አበቃቸው። ንጉሡንም በአሰቃቂ ሁኔታ ገደላቸው። የኢትዮጵያ እናቶች እንደለመዱት ጥቁር ከል ለብሰው አደባባዩን አጠቆሩት። አባቶችም ዘመኑ የሚፈቅደውን የሀዘን ኮፍያ አጥልቀው እንባቸውን በቁማቸው አዘሩ።
ሦስት፤
የሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ተማሪዎች የመባል ዕድል ላይ በደረስንበት ዕድሜ በተቅበዝባዦቹ ቃየናዊያን ደርጎችና በዘመኑ ለውጥ ናፋቂ “ሳይሞቅ ፈላ” አቤላዊያን ወጣቶች መካከል በተጋጋለው የቀይና የነጭ ሽብሮች ጦስ ምክንያት ታላላቆቻችንና ታናናሾቻችን አቤሎች በፊታችንና በየአደባባዮቹ እንደ እንስሳ እየታረዱ ሲወድቁ እየተመለከተን ደም የተቀላቀለበት እንባ አነባን። በቃየን የተላኩ የሞት መላዕክት የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በግፍ ነጠቁን። የእኛም ሕይወት በፈጣሪ ተዓምር ተረፈች።
በምድረ ኖድ ሀገሬ ላይ የተቅበዘበዘው የቃየን አብዮት “አንድ ትውልድ” ጭዳ በማድረግ እንክት አድርጎ በልቶ የደም ጥማቱን ሲያረካ ዓይናችን ጉድ አሳየን። የንፁሃኑ አቤሎች ደምም፤ “አቤቱ እስከ መቼ አትፈርድልንም!” እያለ ወደ ፀባዖት ቃተተ። ከከተማና ከገጠር የሞት መላዕክት የተረፉት አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶችና ልጆች የደረሰባቸው ግፍ አነሰ ተብሎ በምሥራቅና በሰሜን በተጫሩ ጦርነቶች እየተማገዱ አለቁ። ደም አፍሳሹ ቃየን “በሞት ድግሱ” ጠግቤያለሁ ብሎ ሰይፉን ወደ ሰገባው አልመለሰም። በሀገሬ የኖድ ምድር ዙሪያ ገብ ይበልጥ መቅበዝበዙን አጠናክሮ ገፋበት። ይህንን ግፍ ለመሸከም አቅም ያጡ ወላጆቻችን እንባቸውን እየረጩ እንደ መስዋዕት ልጆቻቸው ሁሉ እነርሱም ተጣድፈው ወደ መቃብራቸው ተሰበሰቡ።
አራት፤
ቃየናዊያን ወያኔ ኢህአዴጎች ሥልጣን ላይ ፊጥ ካሉ በኋላ በተጠናና በታቀደ ዕቅድ ከበደኖ ጀምሮ እስከ መሃል ሀገር በጭካኔና በግፍ የበርካታ አቤሎችን እስትንፋስ በመንጠቅ “ላሌ ጉማ!” እየጨፈሩ በሞት ድግስ ሰከሩ። በቁም ስቃይ ተበቀሉ። በዘረፋ አበዱ። በእብሪት ናላቸው ዞሮ በጥጋብ አተያይ በቆሙበት የሥልጣን ማማ ላይ ከፍ እንዳሉ በእብሪት ሲያገሱ አንገታችንን ደፍትን አለቀስን። ከቃየናዊያኑ ኢህአዴጎች ለማምለጥም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አቤሎች ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዱ፤ ሸሹ። ቀን የከፋባቸውም እንደ ነቢዩ ዮናስ ለባህር አሳነባሪ ተዳረጉ። የኖድ ምድር ሀገሬ በተቅበዝባዥ ቃየኖች ተመሳቀለች። ተዘረፈች። ፊቷን በልጆቿ ደም ታጠበች። በደም የተበከለ አጆቿን በሀዘን ማቋ እያበሰች በቀይ ደሟና በጥቁር ቀለም ታሪኳን አጻፈች።
አምስት፤
መጋቢት 2010 ዓ.ም። በጠቆረው የኖድ ምድር ደመናችን ላይ የተስፋ ጮራ የፈነጠቀ መስሎን በችኮላ እየተጣደፍን “ሃሌ ሉያ!” በማለት ለመዘመር ፈጠንን። የእኛ ዝማሬ ባህርና ውቂያኖስ አቋርጦ በመንጎዱ ባዕዳንም ሳይቀሩ እንዲያጨበጭቡ ተገደው አብረውን ዘፈኑ። ውሎ ሳያድር የደም ጥማተኛው የቃየን ቆሌ ካሸለበበት ባንኖ በመንቃት “ወንድሙ አቤልን ና ወደ ሜዳ እንውጣ በማለት” ሕዝብ ለምስጋና በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ ፈንጂ በማፈንዳት “ሃሌ ሉያ” ማዘመር በጀመረው ኮንዳክተር መሪ ላይ የግድያ ሙከራ አድርገው የንፁሃንን ደም በከንቱ አፈሰሱ።
ከዚያ ዕለት ወዲህም ቃየን ወንድሙን አቤልን በየዕለቱ የሚገድልበትን የረቀቀ ስልት በመጠቀም የግድያውን ሜዳ በሀገር መሪዎች፣ በኮሌጆቻችንና በዩኒቨርሲቲዎቻችን ሜዳዎች ላይ አስፋፋ። እርሱ በግዳዩ ተኩራርቶ ሲፋንን፤ እኛ መከራ ስንጋት የኖርነው የትናንትና ወጣቶች የዛሬ ወላጆች የልጆቻችንን አስከሬን ቤታችን ድረስ ታሽጎ እየመጣልን በሦስት ሥርዓቶች ውስጥ ፈሶ በማለቅ ከተሟጠጠው የእንባ ከረጢታችን ውስጥ እያማጥንና እየጨመቅን ቀለባችን እንባችን ሊሆን ግድ ሆነ።
“እንባ እንባ ይለኛል
እንባ ምን አባቱ፣
ደርቋል ከረጢቱ።” እንዳለው ደራሲያችን ሙሾ እያሞሸን
ተንሰቀሰቅን። ቃየኖች በምድራችን ላይ ፈነጩ። የንፁሃን አቤሎች ደምም ወደላይ አረገ። ሙሾ እንዲቀር ሲወገዝ የነበረውን ባህላችንን ጥሰው የተማሪ አቤሎች እናቶች አልቃሽና አስለቃሽ ሆኑ።
“የተማሪ እናት ተነስተሸ አርግጅ፣
የአስከሬን ሙሽራ ቆሟል ከደጅሽ።”
ይህ በዋሸራ የተገጠመው ግጥም በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ፍሩንዱስ ቅኔ ተተክቶ የጊዜያችን የልቅሶ እንጉርጉሮ ሆኗል።
ቃየኖች አቤሎችን እየተቅበዘበዙ በመግደል በሀገሬ የኖድ ምድር ላይ እንደፈለጉ የሚፋንኑት የእነ አይነኬን ሚዲያ ተቆጣጥረው መሆኑ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። ገዳይ ቃየኖች ዘራፍ እያሉ በመፎከር አቤሎችን እየፈጁ ያሉት የእነ እንደ ልቡን ትዕዛዝ እየተቀበሉም ነው። የሀገሬን ሕግ ምን ነካው? ለህሊናቸው ያደሩ ዳኞች ምነው ራቁን? ደጋግመን ብንጠይቅም መልሱን እስካሁን አላገኘንም። የሀገሬ ሹማምንት እሹሩሩም የበዛ መስሎናል።
“ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር ምልክት እንዳደረገበት” ሁሉ የእኛም ቃየኖች ክፉ እንዳያገኛቸው በልዩ ጥበቃ እንዲከለሉ ተደርገዋል። ልጆቻችንን አቤሎችን በየዕለቱ በግፍ እየተነጠቅን ነው። የፍትሕ ሚዛኑን የጨበጡት ሕግ አስከባሪዎች ይሰሙን ከሆነ “በሕግ አምላክ ሕግ አስከብሩልን”፣ ሕጉ አቅም አጥቶም ከሆነ “በጉልበት አምላክ ጉልበተኞች አደብ ይግዙልን!” የጉልበት አምላክ ዝሎም ከሆነ “በወንጌልና በቁርዓን አምላክ” እንማጠናለን። ወንጌሉና ቁርዓኑ አቅም ካጡም ምርጫችን ምን ሊሆን እንደሚችል መፍትሔውን ለመፈለግ ሕዝባዊ ምክክር እናደርጋለን። ፍትህ ፊቷን ያዞረችበት ምስኪን የሀገሬ ጉዳተኛ እንዲህ አንጎራጎረ አሉ፤
ጨርቄን ጠቅለል፣ ጠቅለል
ላሜን ነዳ ነዳ፣
ምናልባት ሰው ሆኜ ጠላቴን ብጎዳ።
ይህ የተከፋ የባለሀገር እንጉርጉሮ እንኳን የሚያዋጣ አይመስልም። ለማንኛውም ከበቀል ይልቅ በፍትሕ ጉልበት ላይ መደገፉ በእጅጉ ይሻላል። ይመረጣልም። ተቅበዝባዡን ቃየንን ጊዜ ፊት ነስታው፣ ታሪክ አዋርዶት፣ እብሪቱ ተገፎለት የአደባባይ ተረት የመሆን እድሜው ቅርብ እንደሆነ ይሰማኛል። አቤሎች ልጆቻችን ሆይ ተረጋጉ። የትዕግስታችሁ መስዋት መጠኑን ቢያልፍም በፈጣሪም፣ በወላጆቻችሁም፣ በታሪክም ዘንድ ተቀባይነት ስላለው ተስፋ አትቁረጡ። በርቱ። በተሰውት ወንድሞቻችሁ መቃብር ላይ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ዛፍ በቅሎ ፍሬ ማፍራቱ በርግጠኝነት አይቀርም። ቃየኖች ፈሪዎችና ተቅበዝባዦች ናቸው።
ፈሪ ሰው ደግሞ ሰብዓዊውን ፍጡር ብቻ ሳይሆን የሚረግጠውንም መሬት አያምንም። አቤሎች ሆይ ተረጋግታችሁ ትምህርታችሁን ቀጥሉ። አትናወጡ። የሀዘን ቱቢት ሳይሆን የስኬት ገዋን ደርባችሁ በአሸናፊነት እንድናጨበጭብላችሁ ምኞታችንም ጸሎታችንም ነው። የወጀብ ዕድሜው አጭር ነው። ለክፉ ክፉ አትመልሱ። ክፋትን በትዕግስት አሸንፉ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012