የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባርን (ኢህአዴግ) የመሠረቱት አራት ፓርቲዎች ማለትም ህወሓት፣ አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ደኢህዴን የመዋሀድ ወሬ የሰነበተ ቢሆንም መሬት መያዝ የጀመረው ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ነው። ምንም እንኳን አጀንዳው በየጊዜው እየተነሳ ሲወድቅ የኖረ ቢሆንም የግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ በውህደት ጉዳይ ቁርጠኛ አቋሙን ያስቀመጠው በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በሐዋሳ በተካሄደው የግንባሩ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ነበር። በዚሁ ውሳኔ መሠረት ቀደም ሲል ኢህአዴግ “አጋሬ” የሚላቸውን (ሐረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች) ጭምር በማቀፍ ለውህደት የሚያበቃውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ስለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት እየተነገረ ይገኛል።
ይህ ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣት ወይንም የውህደት ሀሳብ የግንባሩን አባል ድርጅቶች ለሁለት ሊከፍል የሚችልበት አዝማሚያም እየታየ ነው። ህወሓት በጉባዔው ላይ የውህደት ሀሳቡን አጽድቆ ቢወጣም ዘግይቶ ግን ሀሳቡን በመቀየር ውህደቱን ወደማብጠልጠል ተሸጋግሯል። የተቀሩት ሶስት ድርጅቶች ማለትም የአማራ ደሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ከሞላ ጎደል በድርጅት ደረጃ አስወስነው ውህደቱን ለመመስረት የሚያስችል ቁመና ላይ ስለመሆናቸው በአመራሮቻቸው አንደበት እየተነገረ ይገኛል።
ውህደቱ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አንዱና ዋናው በአሁኑ ሰዓት ጫፍ የረገጠውን የብሔር ጽንፈኝነት ለማስወገድ የተሻለ መንገድ ይሆናል ብሎ በተዋሀጅ ፓርቲዎቹ መታመኑ ነው። ተጨማሪ ሌሎች ነጥቦችን አለፍ አለፍ ብለን እንቃኝ።
ከተልዕኮ መጠናቀቅ አኳያ፣
ኢህአዴግ በሚመሠረትበት ወቅት የብሔር ጭቆናን ለማስቀረትና የብሔር ጥያቄ ለመመለስ የተፈጠረ ስትራቴጂካዊ ግንባር ነበር። የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ፀድቆ ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት እውን ከሆነ በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች እራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ቋንቋ፣ ባህል እና በማንነት የሚኮሩበት ህገ- መንግሥታዊ መብቱ ተረጋግጧል። ስለዚህ ግንባሩ የተፈጠረበት ዋንኛውን ዓላማ አሳክቷል ማለት ይቻላል። ብሄር ብሄረሰቦች በዚህ ሕገ-መንግሥት መነሻ እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በመጎናፀፋቸው በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ይኸው ተግባራዊ ሆኗል። የሥርዓቱ ዋና መለያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን ያልተገደበ መብታቸውን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሰራር ማቋቋሙ ነው።
በአብዛኛው የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው መሰል አደረጃጀቶች ማለትም (የግንባር፣ ንቅናቄ፣ ነፃ አውጭ ወዘተ) ባለው ሥርዓት ላይ በማመፅ በትጥቅ ትግል ወይም በሌላ አግባብ የሚታገሉ ናቸው። ከዚህ አኳያ ኢህአዴግም የደርግ ሥርዓት በትጥቅ በማስወገድ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መመስረት ነበር። አደረጃጀቱ በዚያን ወቅት ተገቢ ቢሆንም ላለፉት 27 ዓመታትም በዚሁ መቀጠሉ በተለያዩ ጉዳዮች አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው። ስለዚህ የግንባር አደረጃጀቱ ተልዕኮውን አሳክቶ የጨረሰ ብቻ ሳይሆን ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይራመድ በመሆኑ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ መምጣት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ጭምር ነው።
– ፌዴራል ሥርዓቱ እና የፓርቲ ውህደት ተያያዥነት የሌላቸው መሆኑ ፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ ህገመንግሥቱን መሠረት በማድረግ የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መሠረትም ዘጠን ክልሎች የተዋቀሩ ሲሆን እነዚህን ክልሎች መሠረት በማድረግም ብሄራዊ ድርጅቶች እየመሯቸው ይገኛሉ። በፌዴራላዊ ስርዓት እያንዳንዱ ክልል የራሱ ድርጅት ይኑረው የሚል አሰራርም ሆነ ህግ የሌለ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ አገራት ልምድም ይህን አያሳይም። ስለሆነም ብሄራዊ ድርጅት መኖርና የአገራችን ፌዴራል ስርዓት የተሳሰሩና የግድ የሚል አይደለም።
አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መፍጠር ማለት ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጋር ምንም የሚያጋጨው ነገር ፈፅሞ የለም ። በጣም ግልፅ መሆን ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር ፓርቲን አንድ እናድርግ ሲባል በህገ-መንግስቱና በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ማዕቀፍ ብቻ ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግና አጋሮቹ ብቻ ህገ-መንግሥቱንም ይሁን ፌዴራላዊ ሥርዓቱን መቀየር አይችሉም። ይህ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል ኢህአዴግና አጋሮቹ ወጥ ፓርቲ የሚሆኑት ፌዴራሊዝሙን ለማፍረስ ሳይሆን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም እውን ለማድረግ ነው። ይህ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት በእኩል የሚወስንበት፣ ፍትሃዊ እና አካታች የፖለቲካ ውህደት ለመፍጠር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በአግባቡ አስታርቀው ለማስተናገድ ነው።
ይህ ብዥታ ከሁለት መሠረታዊ መነሻ ሊነሳ ይችላል። አንደኛው ከዚህ በፊት የነበረው የኢህአዴግና አጋሮቹ አደረጃጀት በብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ ሲሆን ፌዴራሊዝሙም ከዚሁ ጋር የሚሄድ የፓርቲው አደረጃጀት ሲለወጥ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሊለወጥ ይችላል በሚል የውህደቱን አጠቃላይ ይዘት ካለመረዳት የሚመነጭ ሲሆን ይህ ውይይት በሚደረግበት ወቅት የፓርቲ ውህደትና የፌዴራሊዝም አደረጃጀት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው እንዲያውም በፌዴራሊዝም ላይ የሚነሱ ጉድለቶችን በተሻለ ደረጃ በማረም ማስቀጠል መሆኑን ሲረዱ ግልፅ መሆን የሚችል ነው።
በዓለም ላይ ያለውም ተሞክሮ እና ልምድ ሁሉም ፌዴራሊዝም የሚከተሉ ሀገር የብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም በየክልሉ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎች የሉም። ሥርዓቱ ፌዴራላዊ አወቃቀር ኖሮት ሲያበቃ ፓርቲዎቹ ግን ሀገራዊ ፓርቲዎች ናቸው። የእኛም የውህደት አካሄድ ዓለም አቀፍ ልምድን ከግንዛቤ የወሰደ የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በተሳካ አግባብ አስታርቀው ፌዴራሊዝሙን በተሻለ ለማስቀጠል ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ውህደቱ እንዳይሳካ በብሔር አጥር ውስጥ ተሸጉጠው የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥና ተስፋ እንዳይቀጥል ማንኛውንም መልካም ነገር ህዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከተው የሚሠሩ ኃይሎች ናቸው። እነዚህን ለማስረዳት ጊዜ ማቃጠል አይገባም ይልቁንም ውህደቱን በማፋጠን በተጨባጭ አሉባልታውን ማምከን ነው።
እራስን በራስ የማስተዳደርና የብሔር ብሔረሰቦች መብትን በሚመለከትም ከውህደቱ ጋር ብዥታ ለመፍጠር የሚሞክረው ሌላው ገፅታ ነው። የውህደቱ ዋናው ዓላማ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በእኩል የሚስተናገዱበት ውሁድ ለመፍጠር ነው ሲባል የብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብት የተቀበለ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ የሚያከብር ነው።
የድርጅት መዋቅርና መንግሥታዊ መዋቅር ልዩነት በግልፅ የተሠመረ ነው። አዲሱ ውሁድ ፓርቲ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ስለሚያካትት በምርጫው ድርጅቱ በየአካባቢው ብሔር ተወካዮችን በህዝቡ ተቀባይነትን ያተረፉትን ያቀርባል፤ ህዝብ በምርጫ ሲመርጠው እዚያው የራሱን አካባቢ ያስተዳድራል ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር ተይዘው ልክ እንደ መጀመሪያ ነጥብ የብዥታ መነሻ ያለው ሲሆን መረዳትም ያለብን ከላይ በተቀመጠው አግባብ መሆን ይኖርበታል።
ሌላው የብዥታ ገፅታ ደግሞ ከቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው። በጥናቱ መሠረት የፓርቲው የሥራ ቋንቋ ‘’multi lingual‘’ ወይም በርካታ ቋንቋዎች ሲኖሩት በየአካባቢው የሚነገረው ቋንቋ እና በሀገር ደረጃ ለሥራ ቋንቋነት ከተመረጡት ያሻውን ወስደው ይሠራሉ ማለት ነው።
ስለዚህ ቋንቋዎችን የሚያቀጭጭ ሳይሆን እንደውም በሀገር ደረጃ ፓርቲው የሥራ ቋንቋዎችን በርካታ በማድረግ ቋንቋዎቹ ይበልጥ እንዲያደጉ እድል ያጐናፅፋቸዋል።
አጋር ድርጅቶችን በተመለከተ፣
የኢህአዴግ አደረጃጀት በአራት ክልሎች በሚገኙ አባል ብሄራዊ ድርጅቶች በመያዝ የተመሰረተ ነው። ግንባሩ አጋር ድርጅቶች ያላቀፈ በመሆኑ በሀገሪቱ ወሳኝ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ አምስቱን ክልሎች የሚመሩ አጋር ድርጅቶችን የማያሳትፍ እና አካታች ያልሆነ አደረጃጀት ነው።
ይሁንና እነዚህ ድርጅቶች በውሳኔው ሂደት ሳይሳተፉ ነገር ግን የኢህአዴግን ውሳኔ የሚተገብሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በውሳኔ ሂደት ክልሎችን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ እንዲተላለፍ በማድረግ ክልሎቹ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መድረስ ከሚገባቸው ደረጃ እንዳይደርሱ የራሳቸው ውስጣዊ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ከዚህም የላቀው ጉዳይ በሀገራዊ ጉዳይ እኩል የሚመክሩበት እድል ማነሱ ለሀገራቸው ባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጥርባቸው በተለያየ ጊዜ ወደ ግንባሩ አባል ለመሆኑ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በማቅረብ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። አደረጃጀቱ አካታች ካልሆነ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጋር የሚጋጭ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለሆነም አንድ አገራዊ ድርጅት ቢኖር በነዚህ ክልሎች ያለ ማንኛውም ዜጋ በሌሎች ክልሎች ካሉ ዜጎች እኩል የመሳተፍ እድልን የሚያሰፋና ፍትሃዊና ሚዛናዊ ውክልናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም አደረጃጀቱ ሁሉንም የሚያሳትፍ በሆነ አግባብ አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት ወቅታዊና ተገቢ ያደርገዋል።
በህወሓት በኩል የሚነሳው የልዩነት ኀሳብ ምንድነው?
“በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የተዋሀደ ፓርቲ ጥያቄ ለምን?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ባለ 43 ገጽ ሰነድ በመጋቢት ወር 2011 .ም በህወሓት በኩል ወጥቶ ነበር። ሰነዱ ህወሓት ለምን ውህደቱን እንዳልፈለገው በዝርዝር በወይን መጽሔት በማስፈር አባሎቹ እንዲወያዩበት አድርጓል። ከሰነዱ ጥቂት ኀሳብ ልጥቀስ።
“….አሁን የኢህአዴግን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከተው በጥገኛ መበስበስ አዘቅት ውስጥ እየዳከረ የሚገኝ ሲሆን የሚወስዳቸው የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎች ደግሞ ሞቱንና ቀብሩን በማፋጠን ላይ ናቸው። ኢህአዴግ አሁን ባለበት የመከነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ “አገር አቀፍ የውህደት ፓርቲ ለመተግበር መፍጨርጨር መጀመሩ” ከንድፍ ሃሳቡ፣ ከመርሆዎቹና ከመስመሩ ጨርሶ መውጣቱን ያመላክታል። ኢህአዴግን በአቋራጭ አንድ ፓርቲ ለማድረግ የሚፈልገው ሀይል ዓላማውና ህልሙ ኢህአዴግን ማጠናከር ሳይሆን ጨርሶ በማፍረስ ግብአተ መሬቱን በመፈፀም አብዮታዊ ዴሞክራሲና መሪ ድርጅቱን የማጥፋት ተልዕኮ ያነገበ መሆኑ ግልፅ ነው። …”
አቶ ረዳኢ ሓለፎም የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል ናቸው። በቅርቡ ከትግራይ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢህአዴግን ውህደት አጥብቀው ተችተዋል። እንዲህ ይላሉ። “የኢህአዴግ ውህደት አንዱ ተበልቶ አንዱ ሊወጣ ካልሆነ በቀር የአሃዳዊነት መንገድ ስለሆነ የራሱ ህልውና አደጋ ውስጥ ከቶ የሚወክለው ህዝብንም ለጉዳት ይዳርጋል።”
ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የህወሓት ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ህወሓት ከውህደቱ ለምን ሊወጣ እንደቻለ ያስረዳሉ። “… በፕሮግራም አንድ እስከሆንን ድረስ በውህደቱ ላይ ተቃውሞ የለንም። አንድ ዓይነት ፕሮግራም ስላለን ለመዋሃድ ጥናት እንዲደረግ በሐዋሳው ጉባኤ ተስማምተን ነበር። አብዮታዊ ዴሞክራሲ የድርጅቱ ፕሮግራም ሆኖ እንዲቀጥልም ተስማምተናል። አሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አያስፈልገንም ተብሏል። ስለዚህ ከሐዋሳው ጉባኤ በኋላ የፕሮግራም ለውጥ አለ ማለት ነው። ውህደቱ ከሐዋሳው ጉባኤ ውሳኔዎች ውጪ እየተከናወነ ነው። የኃይል አሰላለፍም ተቀይሯል። በሐዋሳው ተወስኖ የነበረው ተጥሷል። የፕሮግራም ልዩነት ተፈጥሯል።”
ይህን ሀሳባቸውን ሲያብራሩም “…አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የቋንቋ ልዩነት እንጂ የፕሮግራምና የይዘት ልዩነት ስላልነበራቸው አራት ሆኖ ከመቀጠል ወደ አንድ መዋሃድ እንደሚኖርብን ወስነናል።
የመወሀድ ሃሳብ ከሐዋሳ ጉባኤ በፊትም የነበረ በመሆኑ ለሙከራ ያህልም በፌዴራል ደረጃ ባሉ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የወጣትና የሴት የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊጎች እንዲወሃዱ ተደርጓል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ግን ሐዋሳ በተገናኘንበት ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው። አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች በፕሮግራም ይዘት መለያየታቸው በገሃድ እየታየ ነው።
የስም ለውጥ ያደረጉ ብሄራዊ ድርጅቶች በሐዋሳው ጉባኤ ላይ ፕሮግራማቸውን ቀይረው መጥተው ቢሆን ኖሮ በጉባኤው ተስማምተን የምንወጣበት አይሆንም ነበር።
በወቅቱ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ተነስቶ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን ነው ብለን አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች ተስማምተን የወጣነው። ፕሮግራሙ በተግባር ተፈትኖ ለውጥ ያመጣ በመሆኑ ይህንን እናስቀጥላለን የሚል ውሳኔ ነበር ያሳለፍነው።
በአሁኑ ወቅት ግን በብሄራዊ ድርጅቶቹ መካከል የይዘት ለውጥ ተፈጥሯል። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ወገኖች ስላሉ አንድ መሆን አይቻልም ነው።
ፕሮግራም የሚቀየረው በጉባኤ በመወያየት እንጂ በአደባባይ በማወጅ አይደለም። በአዋጅ አንድ እንሁን የሚለው ነገር አይሰራም። በፕሮግራም አንድ ባልሆንበት በአሁኑ ወቅት ውህደት አጀንዳ መሆን አይችልም “ በማለት የድርጅታቸውን ህወሓት አቋም አንጸባርቀዋል።
ውህደቱ ተሳካ እንበል፤ ከዚያስ?
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሶስቱ ኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውህደቱን በመደገፍ ወደተግባር ሊሸጋገሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፋ ብሎ ይታያል። ይህ ከተሳካ ህወሓት ከአዲሱ ውሁድ ፓርቲ በመውጣት መጪው ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ራሱን ወደተቀናቃኝ ፓርቲነት ሊያሸጋግር ግድ ይለዋል ማለት ነው። በገዥው ፓርቲ/ መንግሥት ውስጥ የሚኖረው ትልቁን የወሳኝነት አቅም/ ድርሻ ሙሉ በሙሉ ያጣል ማለት ነው።
ሌላው የውህደቱ ትልቁ ዕድል ሁሉም ክልል ቋንቋው ማንነቱ ተጠብቆለት ራሱን በራስ ማስተዳደሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ውህዱ ፓርቲ ለአንድ ብሔር ወይም አመራሮች በተናጠል እወክለዋለሁ ለሚሉት ክልል/ብሔር ብቻ የመቆማቸው አጀንዳ ተዘግቶ፤ ሁሉም ወገን በኢትዮጵያ፣ በሀገሩ ጉዳይ ወሳኝነትን ያጎናጽፈዋል።
ይህን አካሄድ “አሀዳዊነት ነው፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ያጠፋል…” የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች በተለይም ከብሔር ተኮር ፖለቲካ አራማጅ ኃይሎች ቢገጥመውም የማታ ማታ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር በተለይ በኢትዮጵያዊነት አጥብቀው የሚያምኑ የብዙ ዜጎች እምነትና ተስፋ ሆኗል።
(ማጣቀሻዎች፡- የኢህአዴግ ይፋዊ ድረገጽ፣ ወይን የህወሓት የንድፈ ሀሳብ መጽሔት፣ የትግራይ ቲቪ፣ የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትወርክ /ኦቢኤን…)
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012