ግዙፍ ተክለ ሰውነታቸው ግርማ ሞገስን አላብሷቸዋል። የሁለት ልጆች አባት እና የ74 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ቢሆኑም መጦርን ሳይሆን አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ ሰርቼ አሰራለሁ በሚል መንፈስ ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ረጋ ያለው ሰብዕናቸው በርካታ የህይወት ልምዶችን ማሳለፋቸውን ያስረዳል። ጥንቁቅ እና ሰው ወዳድ መሆናቸውን ደግሞ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።
አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ ይባላሉ የዛሬ እንግዳችን። ትውልድና እድገታቸው በወላይታ ሶዶ ከተማ ነው። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በ1938 ዓ.ም የተወለዱት እንግዳችን አባታቸው የህክምና ሙያ ነበራቸውና አሁን ላሉበት የሥራ ዘርፍ የአባታቸው ሙያ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ።
አቶ ብርሃኑ በልጅነታቸው ትምህርቱንም ይወዱ ነበርና መጽሐፍትን እያነበቡ በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ተከታትለዋል። ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ ግን አባታቸውም ለሥራ ጉዳይ ወደ ይርጋለም በመዛወራቸው ቤተሰቡን ይዘው ሲሄዱ እርሳቸውም ወላይታ ሶዶን ተሰናብተው አቀኑ። ይሁንና ከአዲሷ የገጠር መንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መከታተል ያልቻሉት አቶ ብርሃኑ የሰዓታት ጉዞ አድርገው ወደሚያገኟት ይርጋዓለም ከተማ መማራቸው አይቀሬ ሆነ።
ከመኖሪያቸው እየተመላለሱ መማሩ እንደማያዋጣቸው በመገንዘባቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ቤት ተከራይተው በይርጋዓለም ራስ ደስታ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በወቅቱ ማንም ከአጠገባቸው አልነበረምና ምግብ እያበሰሉ የሚያሳልፉት ጊዜ አይረሳቸውም።
በትምህርት ቆይታቸው ደግሞ በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚያተኩሩ ተግባራትን ይወዱ ነበርና ሶሻል ወርክ የተሰኘው ትምህርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ነበራቸው። ይህን ተግባራቸውን ደግሞ የሚታዘቡ ሰዎችም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ከትምህርት ቤቱ እርሳቸው እና አንድ ሌላ ተማሪ ተመርጠው ለማህበረሰብ ልማት / community Development/ ትምህርት ወደ ሐዋሳ አቀኑ።
በሐዋሳ ከተማ የህዝብ እድገት ሰራተኞች ማሰልጠኛ እና ሰርቶ ማሳያ ማዕከል ውስጥ ለሁለት ዓመታት እንዲሰለጥኑ ተደረገ። በወቅቱ ትምህርቱ ተግባር ተኮር በመሆኑ አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ እየሄዱ ስለምርት ማሻሻል እና ስለማህበራዊ፣ ጤና እና የተለያዩ ጉዳዮች ህብረተሰቡን ያሰለጥኑ ነበር ።
ህብረተሰብ ዘመናዊነትን እንዲቀስም እና የተሻሻለ ኑሮ እንዲመራ በየአርሶ አደሩ ቤት በመዋል ውጤታማ ሥራ በማከናወናቸው ምስጋናም አገኙ ፤በትምህርታቸውም በመበርታታቸው በዲፕሎማ ተመረቁ። ከምርቃት በኋላ ወዲያውኑ የተመደቡት አርጡማ ፋርሲ በተባለ አካባቢ ነው። ከከሚሴ ከተማ የአንድ ሰዓት እግር ጉዞ ከሚርቀው የስራ ቦታቸው አካባቢ ቤት ተከራይተው በዙሪያቸው ያለውን ማህበረሰብ ስለ ማህበረሰብ ልማት ሥራዎች አሰልጥነዋል።
በተመደበላቸው አነስተኛ ብስክሌት አስፓልት በማያውቃት የገጠር መንገድ እየተዘዋወሩ አለፍ ሲልም በበቅሎ እየተንቀሳቀሱ ለሶስት ዓመታት ሰርተዋል። ከዚያ በመቀጠል ተዛውረው ወደ ነቀምቴ ከተማ ነበር ያመሩት። የአካባቢው እድገት ሰራተኛ ሆነው ከህብረተሰቡ ጋር አብረው እየኖሩ እርሻ እና ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ህይወት እድገት ላይ እየሰሩ በነቀምቴ ለሁለት ዓመታት ቆይተዋል።
ከነቀምቴ በኋላ ግን የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለማሳደግ በሚል ሥራውን ትተው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በዩኒቨርሲቲው የሶሻል ወርክ ትምህርታቸው እየተከታተሉ ሳለ የወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ይህንኑም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት እና ጫና ስላሳሰባቸው ትምህርታቸውን ከአንድ ዓመት በኋላ አቋርጠው ባላሰቡት የሕይወት አቅጣጫ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅን ተቀላቀሉ።
አንድም ቀን ፖሊስ እሆናለው ብለው አስበው የማያውቁት አቶ ብርሃኑ በፖሊስ ኮሌጅ የሚሰጠውን ፈታኝ የአካል እና የአዕምሮ ስልጠና ለሁለት ዓመታት ተከታትለው በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ቻሉ። ወዲያውም የወቅቱ የጅማ አውራጃ ፖሊስ አዛዥ በመሆን ነበር የተመደቡት።
በጅማ ቆይታቸው ጠንካራ አመራር መሆናቸውን በማሳየት ለአንድ ዓመት እንደሰሩ እርሳቸው ሳያውቁ አንድ በቴሌግራም የተላከ መልዕክት በሚመሩት ቢሮ በኩል መጣላቸው። የቴሌግራሙን መልዕክት ተቀብለው ሲያነቡት ደግሞ በ24 ሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባ እንዲገቡ እና ለአስቸኳይ ሥራ እንደሚፈለጉ የሚገልጽ ነበር።
በቤታቸው ያገኟቸውን የተወሰኑ እቃዎች በመያዝ በአፋጣኝ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ስለጉዳዩ ሲጠይቁ በሲቪል አፌይርስ በተባለ የሥራ መደብ በኩል ወደ አስመራ ተጉዘው ህዝቡን የማረጋጋት ሥራ እንዲያከናውኑ ተነገራቸው።
በኤርትራ በተከሰተው ጦርነት ህዝቡን ከማረጋጋት ባለፈ የኤርትራ፣ የጎንደር እና የትግራይ መልሶ ማቋቋም መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። የተለያዩ ቦታዎች ላይ የእርዳታ ማስተባበሪያ እና ማቋቋሚያ `ኃላፊ ሆነው በአስመራ ለ10 ዓመታት የዘለቀው የሥራ ዘመናቸው ተጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
አዲስ አበባ ሲመለሱም የ1977ቱ ድርቅ ተከስቶ ነበርና የእርዳታ ማስተባበሩን ሥራ ሲመሩ ቆየ። በዚህ ውጤታማ ሥራቸው የተወደሱት አቶ ብርሃኑ የከተማ ልማት ኮርፖሬሽንን በኃላፊነት ተረክበው ተቋሙን የማደራጀት ሥራ አከናውነዋል። በኋላም የዕቃ አቅራቢ ድርጅት መንግሥት ሲያቋቁም አሁንም በኃላፊነት ተመድበው ለበርካታ ግንባታዎች ግብዓት የሚያቀርብ ድርጅት አዋቅረው በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት በኃላፊነት ሰርተዋል።
አቶ ብርሃኑ ከዚህ ሁሉ የመንግሥት ኃላፊነት እና የማህበራዊ ሠራተኝነት አገልግሎት በኋላ የግል ሥራቸውን ጀምረው በእራሳቸው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ደረሱ። በመሆኑም በሥራ አጋጣሚ ከሚያውቁት አንድ ጀርመናዊ ፈረንጅ ሐኪም ጋር በመነጋገር በጥምረት ክሊኒክ ለማቋቋም ንግግር ያደርጋሉ።
ከብዙ ውይይቶች በኋላ የጋራ ሥራ ስምምነቶችን በማድረግ አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ህንጻዎች ውስጥ አንዱን ተከራይተው ሥራው ተጀመረ። በገንዘብ ረገድ ጀርመናዊው ጥሩ አቅም ነበረውና ሥራውን ለማስኬድ አልተቸገሩም ነበር። አቶ ብርሃኑ ደግሞ ያካበቱትን የአስተዳደር ልምድ በመጠቀም የክሊኒኩን ሥራ ሲወጡ የህክምና ሥራውን ደግሞ ጀርመናውያን እየከወኑ ለአንድ ዓመት ሥራቸውን ቀጠሉ።
ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የተከራዩት የዲፕሎማቶች ህንጻ በመሆኑ እና ለክሊኒክ ሥራ እንደማይሆን ስለተነገራቸው አዲስ ግቢ መፈለግ ነበረባቸው። ግንፍሌ የተባለው አካባቢ አንድ ሰፊ ግቢ በመገኘቱ ተከራይተው ሥራቸውን ቀጠሉ።
ሰንሻይን የጨጓራ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ክሊኒክ በሚለው የህክምና ተቋማቸው ውስጥ 15 ሠራተኞችን ቀጥረው ታካሚዎቻቸውን ማስተናገዱን ተያያዙት። አንድ ብሎ የጀመረው የታካሚ ቁጥር በየቀኑ ከአስር በላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜያት አልወሰደበትም።
ጀርመናዊው ሐኪምም በሙያው በአካባቢው እየታወቀ ሲመጣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ህክምናውን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ተበራከቱ። ለአሥር ዓመታት በጥሩ ግልጋሎት ከሰሩ በኋላ የአቶ ብርሃኑ አጋር የሆነው ፈረንጅ ህይወት አለፈ።
በዚህ ወቅት አቶ ብርሃኑ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ የተመሰረተው የክሊኒክ ሥራቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ሆነ። ይሁንና የስፔሻሊስት ክሊኒኩም የአስተዳደር ሥራውን በከፍተኛ ብቃት ሲመሩት የቆዩት አቶ ብርሃኑ በጀርመናዊው ምትክ ሶስት ዶክተሮችን አፈላልገው በመቅጠር ሥራቸውን ቀጠሉ።
በየጊዜው ለሚያስፈልጉ የላብራቶሪ እቃዎች እና የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን እያሟሉ መስራቱ አልከበዳቸውም። በመሃልም ሥራቸውን ለማሳደግ በማሰብ ሶስት የውጭ አገር ሐኪሞችን ከአውሮፓ አስመጥተው አሰርተዋል።
በወቅቱ ለፈረንጆቹ ቤት መኪና እና አስፈላጊውን ግብዓት እያሟሉ ቢያሰሩም ወጪው ግን ከባድ ሆነባቸው። ለእያንዳንዱ ሐኪም በአጠቃላይ ከ100ሺ ብር በላይ እያወጡ ሲሰሩ ወጨው በመክበዱ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ፈረንጆቹ ልምጃቸውን ለኢትዮጵያውያን አካፍለው ወደመጡበት ተመለሱ። አሁን አቶ ብርሃኑ ከአሥር ዓመታት በላይ ከአጋራቸው ጋር የጀመሩትን ሥራ በእራሳቸው ሥር አድርገው በብቃት እየሰሩበት ነው።
በስፔሻሊስት ክሊኒካቸው ውስጥ 20 ሠራተኞች ቀጥረው እያሰሩ ነው። ሶስት በሙያቸው የተመረጡ ዶክተሮች ደግሞ አብረዋቸው ይሰራሉ። እያንዳንዱ ዶክተር ከአጠቃላይ የህክምና ወጪ 70 በመቶውን እየወሰደ አቶ ብርሃኑ ደግሞ ሰላሳ በመቶውን ድርሻ ይዘው ያሰራሉ።
በዚህም ለእያንዳንዱ ዶክተር በወር ከ70 እና ከ80 ሺህ ብር በላይ የሚከፍሉበት ወቅት አለ። ታካሚዎችም በቂ አገልግሎት አግኝተው በከፈሉት ገንዘብ ተደስተው ሲሄዱ እንደሚረኩ የሚናገሩት እንግዳችን ትልቅ ቪላ ቤት እና ለምርመራ የሚሆኑ የተለያዩ ሰርቪስ ቤቶች ያሉትን የስፔሻሊስት ክሊኒካቸውን ግቢ ጽዱ እንዲሆን ሁልጊዜም ጥረታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
የክህምና ሥራ በአብዛኛው የገንዘብ ትርፉ ሳይሆን የአእምሮ እርካታው ነው የሚበልጠው የሚሉት አቶ ብርሃኑ ይሁንና በዚህ ሥራ ከእራሳቸው አልፈው 20 ሠራተኞችን መቅጠር ያስቻለ ሃብት መፍጠራቸው ለማንም ግልጽ የሆነ የስራ ትጋት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።
በአባታቸው የህክምና ሙያ ተጽእኖ ምክንያት ወደዚህ ዘርፈ እንደገቡ የሚናገሩት እንግዳችን ከዚህ በዘለለ ደግሞ በአገር ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ተቆርቋሪነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ከስፔሻሊስት ክሊኒካቸው የዕለት ተዕለት ሥራ ቀንሰው በሚያገኙት ጊዜ በአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ውስጥ በአባልነት ተካተው ስለአገራዊ ጉዳዮች በየጊዜው ምክክር በማድረግ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።
<<እኔ አሁን እድሜዬ እየገፋ ቢሆንም ሥራዬን የበለጠ አስፋፍቼ ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ነው ፍላጎቴ>> የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ ወጣቱ በላቡ ጥሮ ግሩ የሚያገኘውን ሃብት በአግባቡ እየተጠቀመ በሰላም መኖር ይገባዋል የሚል እምነት አላቸው።
በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሰላም እጦት በቀጥታ በሥራ እና ንግድ ጋር የተያያዘ ክፉ ተጽእኖ ስላለው ወጣቱ ለእራሱ እና ለአገሩ የሚያተርፍበትን ጠንካራ የሥራ ባህል ስለማሳደግ ማሰብ እንዳለበት ይገልጻሉ።
ሥራ ሳይመርጡ በመስራት እንጂ ንብረት በማውደም ትርፍ እንደማይገኝ አውቆ ወጣቱ በየሙያው ተሰማርቶ ቢሰራ ነገ የተሻለች ሀገር መፍጠር ይቻላል የሚል መልዕክት አላቸው። መንግሥትም በበኩሉ ለወጣቱ ገንዘብ በማቅረብ በእውነተኛ መንገድ ከረዳ ወጣቱ የማይለወጥበት ምክንያት አይኖርም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
ጌትነት ተስፋማርያም