በኢትዮጵያ የግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ የተገባው በ1994 ዓ.ም ነው። ዋና ዓላማው ጉልበትን በሰፊው በሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር፤ ካፒታልን በመቆጠብ ለኢንዱስትሪው ማንሠራራት መሠረት መጣል ነው። ይህ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና ልማትን እንደ ዋነኛው የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ሽግግር ተመራማሪና የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ውቤ እንደሚሉት፤ በ2004 ዓ.ም የሳይንስ፤ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ፖሊሲው በዋናነት አሁን በዓለም ላይ የኋላ ደራሽ ተጠቃሚነትን (late comer advantage) በመጠቀም ቀልጣፋና ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ያደጉ አገራት የደረሱበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚያስፈልጋቸውና ዋነኛው አማራጭ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
እንደ አቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት፤ እንዲሁም በ40 እና በ50 ዓመታት ውስጥ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ርብርብ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳድረው ማሸነፍ እንዲችሉ በአገር ውስጥ ያለውን ተነጻጻሪ ርካሽ ጉልበት፤ መሬትና ጥሬ እቃ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤታማና ምርታማ በሆነ አግባብ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ የታቀደውን የአምራች ኢንዱስትሪ ግብ ለማሳካት ዘርፉ ፈጣንና ዘላቂ የቴክኖሎጂ ሽግግርና እድገት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ፈጣንና ዘላቂ የቴክኖሎጂ እድገት ማሳካት ለፈጣንና ዘላቂ ኢንዱስትሪ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራ እድገት ፋይዳ ያላቸውን የመንግስት ድጋፍ፤ ማበረታቻና ሬጉላቶሪ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመፈተሽ በዚህ ዘርፍ ከበለጸጉት አገራት ተሞክሮ መቅሰም እንደሚገባም አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ታይዋን፣ ቬትናምና ጀርመን የአምራች ኢንዱስትሪውን ቴክኖሎጂ በመረዳት በኩል የተሻሉ አገራት መሆናቸውን አመላክተው፤ ከአገራቱ ልምድ መቅሰም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ የአገራቱን ተሞክሮ መነሻ አድረገው፤ በኢንዱስትሪ አብዮት ጉዞ በመጀመሪያዎቹ የዕድገት ዓመታት መንግስት ምቹ ፖሊሲዎችን በመቅረጽና ብቁ ተቋማትን በመፍጠር የአንበሳውን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ልማትም ሆነ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሂደት መንግስት የመሪነት ሚና መውሰድ እንዳለበትና የኢንዱስትሪ እድገት ጉዞ ምቹ በሆነ ቁጥር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ስትራቴጂውም በዚያው ልክ መለወጥ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ነባር ቴክኖሎጂዎችን በሳይንስ ፈቃድ ውልና “በተርን-ኪፓኬጅ” መልክ ማግኘት እንደሚቻል፤ ነገር ግን ዘመናዊ የሆኑ ዘመን አፍራሽ የአመራርነት ቴክኖሎጂዎችን በዚህ መልኩ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ፤ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ለማስገባትና ለመማር የተሻለ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ የኮርያን ተሞክሮ መነሻ አድርገው አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ፤ በውጭ ከሚገኙና እውቅና ካተረፉ አምራቾች ጋር ስምምነት በማድረግ የምርት አካላትና ያለቀለት ምርት በማምረትና ለገዢዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ በማቅረብ ቴክኖሎጂን የራስ ማድረግ እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገው የቴክኖሎጂ ፍላጎትና አሁን ያለው ቴክኖሎጂ የመቀበል አቅም ሰፊ ልዩነት አለው የሚሉት ደግሞ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ሴክተር ፖሊሲ ጥናት ባለሙያ ዶክተር አማረ ማተቡ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ ላይ መሠረት በማድረግ ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶች ወይም “ቻናሎች”ን ለይቶ ማስቀመጥ ይገባል።
እነዚህን የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶች በሦስት የዕድገት ምዕራፍ ማለትም፤ አስመስሎ ኩረጃ፤ የፈጠራ ኩረጃና አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ጊዜን ለይቶ ማስቀመጥም ያስፈልጋል። መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በማምረት ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን የውጭ ቴክኖሎጂ መርጦ በማስገባት በመማርና በማላመድ ሥራ የቴክኖሎጂ መሸጋገሪያ ማዕከላት መሆን አለባቸው፡፡
ይህንን በሰፊው ለመስራትም አገሪቱ በምን ዘርፍና በምን ቴክኖሎጂ እስከመሪነትና አፍላቂነት ልትደርስ እንደምትችል፤ በምን ዘርፍ የቴክኖሎጂ ገዥና ተጠቃሚ መሆን ይኖርባታል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በግልጽ መታወቅ እንዳለበትም ዶክተር አማረ ተናግረዋል፡፡ ወደ አገሪቱ እንዲሸጋገሩ የሚበረታቱ ቴክኖሎጂዎችም ተወዳዳሪ የሆኑ፤ አዳዲስ ምርት ማምረት የሚያስችሉ፤ አዲስ ኢንዱስትሪ ወይም አገልግሎት የሚፈጥሩ፤ ኢነርጂ ወይም ግብዓት ቆጣቢ የሆኑ፤ አሊያም በታዳሽ ኃይል የሚሰሩና በሰዎች ጤንነትና ደኅንነት ላይ ጉዳት የማያደርሱ፤ ንጹህና ተስማሚ አካባቢ የሚፈጥሩ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋ የሚከላከሉና የሚቆጣጠሩ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ጥያሩ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአንድ አገር ወይም ድርጅት ህልውና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው፤ የራሱ ቴክኖሎጂ የሌለው አገር ጥገኛ ነው። ያላደጉ አገራት ያለማደጋቸው ዋናው ምክንያት ቴክኖሎጂ የማመንጨትና የመጠቀም አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ያላደጉ አገራት በፍጥነት ለማደግ አዲስ ቴክኖሎጂ ማመንጨት እንደማይጠበቅባቸውና ያደጉ አገራት ያጸደቋቸውን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመጠቀም ወደ በለጸጉት አገራት የተጠጋጋ የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ብዙ አገራት የሚጠቀሙት የእድገት አቅጣጫ ለ“ኢንዱስትሪያላይዜሽን” ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ያለቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ እንደማይቻል የበርካታ ያላደጉ አገራት ተሞክሮ ያሳያል ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር ሲባል ቴክኖሎጂ መቅዳትና ማላመድ፤ በራስ አቅም ዲዛይን ማድረግና የራስ ማድረግን ያካትታል የሚሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ልማት ትኩረት በሰጠችበት የስትራቴጂ ሰነድ ላይ ሽግግርና ልማት አንዱና ዋነኛው የፖሊሲው ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ በራሱ አቅምና ከሌሎች መሰል የአገር ውስጥ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተያዘው በጀት ዓመት አገሪቱ የያዘችውን የለውጥ ጉዙ የሚደግፉ፤ ትርጉም ያላቸው 71 የጥናትና ምርምር ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 16ቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያተኩሩ መሆናቸውንና በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ተመሳሳይ ሀሳብ አፍላቂ ተቋማት ጋር በመተባበር ተቋማዊ የምርምር ብቃትና ደረጃ ያሟላ ተወዳዳሪ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም5/2012
አዲሱ ገረመው