አዲስ አበባ፡- ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ጠንካራ ፓርቲ ብቻ እንዲኖር ፍላጎቱ አለኝ›› ሲሉ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ አስታወቁ፡፡ኢህአዴግ ከእህት ድርጅቶቹና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውህደት ለማድረግ ማሰቡንም በአድናቆት ተመልክተውታል፡፡
አቶ ኦኬሎ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ ኢህአዴግ ባለው ተመሳሳይ አቋም በውስጡ ያሉ እህት ድርጅቶቹን እንዲሁም አጋር ድርጅቶችን ይዞ ውህደት ቢፈጥር ፣ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲሁ ባላቸው ተመሳሳይ አቋም አንድ በመሆን በአገሪቱ ሁለት ጠንካራ ፓርቲዎች ብቻ እንዲኖሩ ይመኛሉ፡፡ኢህአዴግም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየጎራቸው ውህደትን ሲፈጥሩ ግን ባላቸው እሴት፣ ራዕይ፣ዓላማና አቋም ላይ መመስረት አለባቸው፡፡
ኢህአዴግ እህት ድርጅቶቹን ይዞ አጋር ፓርቲዎችን በማካተት ውህደት ለመፍጠር መንቀሳቀሱ መልካም ነው ያሉት አቶ ኦኬሎ፣ ይህ ግን ሊያመሳስሏቸው የሚያስችሏቸውን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።ካልሆነ ግን ውህደቱ በስም ብቻ ይሆንና ወደ ተግባር ሲመጣ ሊጣረስ እንደሚችል ጠቁመው፣በተመሳሳይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲሁ የሚያመሳስሏቸውን ነጥቦች መሰረት በማድረግ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ሆነው መቆም እንደሚኖርባቸውም አስታውቀዋል።
‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገው ሁለት ጠንካራ ፓርቲ ብቻ ነው።›› ያሉት አቶ ኦኬሎ፣ ለዚህ ምክንያታቸው በዋናነት የጠቀሱትም የአገር ሰላም መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ጠንካራ ፓርቲ ሲኖር በሚረባውና በማይረባውም ነገር ብጥብጥ ሊነሳ አይችልም። ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲዎች መብዛት የህዝብ ድምፅ እንዲባክን ከማድረግ ውጭ እምብዛም ፋይዳ የለውም።ስለዚህ በፓርቲ ቁጥር መብዛት ህዝብ እንዳይደናገርም ያግዛል።›› ሲሉም አብራርተዋል።
እንደ አቶ ኦኬሎ ገለጻ፣ሁለት ጠንካራ ፓርቲዎች ብቻ የሚኖሩ ከሆነ የህዝቡ ድምፅ ሁለት ቦታ ብቻ ይሆናል።በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲም የቱንም ያህል ጥሩ ቢሰራ ከሁለት ዙር እንዳይዘል ማድረግ ያስችላል።
አቶ ኦኬሎ እንዳሉት፣የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረንስ አባል የነበሩ ሲሆን፣ ኢህአዴግ የተፎካካሪ ፓርቲ መሆናቸውን እያወቀ ነበር በስልጣን ላይ እንዲቀመጡ የተደረገው።በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አባል መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
አስቴር ኤልያስ