አዲስ አበባ፡- በ2012 በጀት ሩብ ዓመት በከተሞች ለ142ሺ 372 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግሥቱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በ2012 በጀት ሩብ ዓመት በከተሞች 270 ሺ 184 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 142ሺ 372 ለሚሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንጻር 52 በመቶ ብቻ ቢሆንም ካለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር 21 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
በሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እንዲሁም ከስደት ተመላሾች እንደሚ ገኙበት አመልክተው የሥራ ዕድሉ ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከልም እንጨትና ብረታ ብረት፤ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ግንባታ፣ እንሰሳት ማደለብ ፤ የጓሮ አትክልት ልማት፣ ንግድና ትራንስፖርት እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡
የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራ ፈላጊዎች የመመዝገብ ሥራ የሚሠራበት፣ ስልጠና የሚሰጥበት፣ ብድር የሚመቻችበት፣መስሪያና መሸጫ ቦታ ዝግጅት የሚደረግበት፣ ወዘተ መሆኑ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: ሆኖም በመጪዎቹ ወራት ዕቅዱን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አቶ በቀለ ተናግረዋል::
መረጃዎቹ ከሚሰበሰቡባቸው ከሁለት ሺ ከተሞች በላይ የሐሰትና የተጋነኑ ሪፖርቶች ለመቆጣጠርም በ270 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ከሚመለከተውን የመንግሥት አካል ምልሽ እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
በከተሞች በ2011 ዓ.ም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ ከአንድ ሚሊዮን 594ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ የዚህ ዓመት አፈጻፀሙም ካለው ከፍተኛ የሥራ ፈላጊ ቁጥር አንጻር ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን እንደሚያመላክት ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012
ጌትነት ምህረቴ