– ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ተጠየቀ
አዲስ አበባ፡- ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩን የሰላም አስተምሮት እንደ አርአያ በመከተል ከሌሎች ወንድም ወገኖቹ ጋር በመተባበር ለሰላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ። 1494ኛው የነብዩ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል በድምቀት ተከበረ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ በታላቁ አንዋር መስጅድ የነብዩ መሀመድ 1494ኛው የልደት በዓል ሲከበር ለእምነቱ ተከታዮች እንደገለጹት፤ ነብዩ በመልካም ፀባያቸው፣ ለአንድነትና ለሰላም ሳይታክቱ ማስተማራቸው እንዲከበሩ አድርጓቸዋል። ለሰውና ለሀገርም የሚጠቅመው በሰላምና በአንድነት መኖር ነው። ሕዝበ ሙስሊሙም የነብዩን አስተምሮት በመከተል ለሰላምና ለአንድነት መትጋት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
“በአሁኑ ወቅት የእርስ በእርስ ግጭትና አለመተማመን ከመቸውም በላይ ተበራክቷል፤ በርካቶችንም ለሞትና ለመፈናቀል ዳርጓቸዋል። በመሆኑም ፈጣሪ የማይወደውን ክፉ ሥራ በመተውና ለፈጣሪ በመታዘዝ ሕዝበ ሙስሊሙ የሰላም ፈርቀዳጅ መሆን አለበት። በተለይ ደግሞ የተሳሳቱትን በማረምና በማስተማር ሁሉም የሙስሊሙ ህብረተሰብ ለሀገሩ ዕድገት መጣር አለበት” ሲሉ ገልጸዋል።
“ ጠንካራ የነበረው አንድነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ነው” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ከምንጊዜውም በላይ ለአብሮነትና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ቀድሞ የነበረውን ሰላም ማጠንከር እንደሚገባ ተናግረዋል። እንዲሁም በዓሉ ሲከበር ለሌላቸው በማካፈል፣ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሙስሊም ህብረተሰብ ድጋፍ በማድረግ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ላሉ ወገኖች ፀሎት በማድረግና ከኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በጋራ ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ አሊ መሀመድ ሽፋ በበኩላቸው ለህዝበ ሙስሊሙ እንዲህ ሲሉ መልዕክታውን አስተላፈዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ እርስ በእርስና ከእምነቱ ውጪ ካሉ ወገኖቹ ጋር ሀገርን እስከነ ሰላሟ ማቆየት አለበት። የሃይማኖት አባቶችም ሰላምን ሳይታክቱ በመስበክና ሌት ተቀን ፀሎት በማድረግ፤ ሙሑራንና አክቲቪስቶች ሥራቸውን በአግባቡ በመሥራት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
በቅርቡ በሀገራችን በደረሰው ጥቃት ምክንያት የንብርት መውደም፣ክቡር የሆነው የሰው ሕይውት መጥፋት፣ መፈናቀልና በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን መቃጠል ምክር ቤቱ አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጸው፤ ይህ እኩይ ተግባር ድጋሚ እንዳይፈጠርና ሁሉም ዜጋ ሳይሸማቀቅ በሀገሩ ሠርቶ እንዲኖር ሕዝበ ሙስሊሙ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2012
ሞገስ ፀጋዬ