በዚያ ሰሞን በአንድ መድረክ ያመኑበትን ከመናገር ወደኋላ የማይሉት የአደባባይ ሙህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “ …የለውጡ ግንባር ቀደም ተግዳሮት ፖለቲካዊ ማባባል political appeasement ነው ።… “ ሲሉ ተደምጠው ነበር። ሰሞነኛው ውሎና አዳራችንም ሆነ ያለፉት 19 ወራት አክራሞታችን ይሄን አባባል የሚያፀኑ ናቸው ማለት ይቻላል ።ሆኖም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ሆነ የሀገር ቤት ፖለቲካው ማጠንጠኛ ማባበል ፣ ማቆላመጥና ማብሸልሸል የሆነው በምክንያት ነው ፡፡
ከቅርቡ ታሪካችን እንኳ ብንጀምር ቀዳማዊ ኢህአዴግ ሆነ ደርግ ከጎረቤት ሀገራት ጋርም ይሁን በሀገር ቤት የሚነሱ ግጭቶችን ሆነ አለመግባባቶችን በኃይል በጠብመንጃ ለመፍታት ያደረጉት ሙከራዎች ችግሮችን ይበልጥ አወሳስቧቸው እንጂ አልቋጯቸውም ፡፡
ደርግ ከእነ ኢህአፓ ጋር የነበረውን ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት በማባበል መፍታት ቢችል በዚች ሀገር ታምር ሊሰራ የሚችል አንድ ትውልድ ባላለቀ ነበር። የትውልድ ክፍተትም ባልተፈጠረ ።እናትና ሀገር ከል ባለበሱ ፊታቸውን ባልፈጁ ።ከአማፅያኑ ከእነ ሻእብያና ህወሀት ጋር ልዩነቱን በዲፕሎማሲ በማባበል በማግባባት መፍታት ቢችል ኖሮ በመቶ ሺዎች የሚገመት ወጣት ባላለቀ አካል ጉዳተኛ ባልሆነ ።የሀገር ፣ የህዝብ ሀብት ባልወደመ ።እድገት ልማት ጭዳ ባልሆነ ።እርሀብ ፣ እርዛት ፣ ጉስቁልና ባልገነነ ።ይቺ ታላቅ ሀገር ባህር በር አልባም ባልሆነች ።
ይሄ ከፋፋይ ፣ ጠባብና ዘራፊ ቡድንም በየይስሙላ ፌዴራሊዝም መንበር ላይ ባልተቀመጠ ።ለዚህ ውስብስብና ውጥንቅጥ ፖለቲካዊ ድባብ ባልተዳረግን ።ቀዳማዊ ኢህአዴግም ላለፉት 27 አመታት የገጠመውን ተቃውሞ በውይይት በማግባባት መፍታት ቢችል ኖሮ ያ ሁሉ ግፍና ስቃይ በዜጋ ላይ ባልተፈፀመ ።ጥላቻ ልዩነት መጠራጠር የተራቆተ ካዝና ባልወረስን ።ለእርስበርስ ግጭት ባልተዳረግን ።ከኤርትራ ጋር የነበረው አለመግባባት በማባበል በማግባባት ቢፈታ ኖሮ ከ100ሺህ በላይ ወጣት ባላለቀ ከዚህ በላይ አካል ጉዳተኛ ባልሆነ ።ይሄ ቡድንም በመማፀኛ ከተማው መሽጎ ቀኑን ባልተጠባበቀ ፡፡
ይህን የታሪክ ጠባሳ ጠንቅቀው የሚያውቁት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ መንገድ እንደማያወጣ አበክረው ተረድተው ላለፉት 19 ወራት ጉምቱው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ እንደሚለው “ ያልተሄደበትን መንገድ “ ማለትም ልዩነትን አለመግባባትን በማባበል ፣ በማግባባትና በሆደ ሰፊነት ለመፍታት ሞክረዋል ።በዚህ ረገድ ላለፉት 20 አመታት ምሽግ ይዘው ቃታ ስበው በጠላትነት በአይነ ቁራኛ ሲተያዩ ሲጠባበቁ የነበሩት የኤርትራና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከምሽጋቸው ወጥተው በወንድማዊ እህታዊ ናፍቆት እንዲተቃቀፉ አድርገዋል።
የመንግስት ለመንግስት ሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መልሶ እንዲያንሰራራ አስቸለዋል ።የሰላም ስምምነት በመፈራረም ድንበሩ ቀጣናው ከግጭት ስጋት እንዲወጣ ውጥረቱም እንዲረግብ ጥረት አድርገዋል ።በሱዳን ሰላም ወርዶ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል ።ሶማሊያን ከኬንያ እንዲሁም ጅቡቲን ከኤርትራ ለማስታረቅ በደቡብ ሱዳንም ዕርቅ ለማውረድ እየተጉ ይገኛል ።ለጥረታቸውም አለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ምዕራባውያን እውቅና ሰጥተዋቸዋል።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በመሆን በሰላም የኖቤል አሸናፊም ተሸላሚም ሆነዋል ።ከወጪ ቀሪ ሲሰላ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በማባበል ላይ የተዋቀረ የውጭ ግንኙነት ስልት ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል ።ሆኖም ይህ ስኬት ከአለም ታሪክ ጋር ሲመሳከር የማባበል ዲፕሎማሲ አባት ተደርጋ የምትወሰደው የቅድመ ሁለተኛው የአለም ጦርነት እንግሊዝ በአንደኛው የአለም ጦርነት ያየችው ዕልቂትና ውድመት እንዳይደገም አዶልፍ ሒትለርን ለማባበል ያደረገችው ጥረት በናዚው እብሪተኛ እንደ ፍርሀት ተቀጥሮ እንዴት እንደፈረሰና ይህን ተከትሎም የማባበል ዲፕሎማሲም ሆነ ፖለቲካ እንዴት እንደማርያም ጠላት መታየት እንደጀመረ አይተን ስናበቃ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የሀገር ቤቱን ፖለቲካዊ ማባበል ፖሊሲያቸውን እንቃኛለን ፡፡
እንግሊዝ የ1ኛው አለም ጦርነት ያስከተለውን ዘግናኝ ዕልቂትና ውድመት በማሰብ እንዲሁም ፋሺዝምን ኮምኒዝምን ለማዳከም እንደመሳሪያ ለመጠቀም በማሰብ አዶልፍ ሒትለርን ፖለቲካዊና ቁሳዊ ንጣፍ concession በመስጠት ለማባበልና 2ኛውን የአለም ጦርነት ለማስቀረት ያልተሳካ ሙከራ አድርጋለች ።እንደ ቅደም ተከተላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሮቿ ራምሲ ማክዶናልድ፣ ስታንሊ ባልዲዊንና ኔቭል ቻምበርሊን የጀርመኑን ናዚና የኢጣሊያውን ፋሽስት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1930 እስከ 1939 በዲፕሎማሲያዊ / ፖለቲካዊ ማባበል ለማግባባት ሞክራለች ።ይህ ጥረቷ ተሳክቶ እ አ አ ፣ በመስከረም 1938 የሙኒኩ ሰነድ የተባለውን ስምምነት ለመፈራረም ችላ ነበር ።በወቅቱ ይህን የማባበል ፖሊስ ሌበር ፓርቲ ፣ ግራ ዘመም ኃይሎችን ጨምሮ የቶሪዎቹ ዊንስተን ቸርቸልና ዳፍ ኮፐር አምርረው ተቃውመውት ነበር ።
የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ ሒትለር ውሉን ተፈራረሞ አመት እንኳ ሳይሆነው ቺኮዝለቫኪያን በመውረር ስምምነቱን ጣሰ ።የማባበል ዲፕሎማሲም አብሮ ተቀበረ ።የእንግሊዝ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሪት ታቸር በቅፅል ስማቸው iron lady / ብርቱዋ እንስት / በአንድ መድረክ” የማባበል ዲፕሎማሲ እንደ ክርፋት ሳይገለማኝ አልቀረም ።“ ሲሉ መደመጣቸው የማባበል ፖሊሲ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳልነበረው ያረጋግጣል ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 70 አመታት በዩኒቨርሲቲዎች በልሒቃን ወንበር መነጋገሪያ መሆኑ ግን አልቀረም ።ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሟቹን የማባበል ዲፕሎማሲ በምስራቅ አፍሪካ የሕይወት እስትንፋስን በአፍንጫው እፍ ብለው ዳግም ሕይወት እንደዘሩበት የኤርትራው ፣ የሱዳኑ ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፣ ወዘተ . ስምምነቶች ሕያው ምስክሮች ናቸው ፡፡
ይሁንና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የማባበል ፖለቲካ በሀገር ቤት የተፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑን ልብ ይሏል ።ችግሩ ከፅንሰ ሃሳቡ ይሁን ከሕዝባችን የስነ ልቦና ውቅር ለዘርፉ ልሒቃን የምርምር ርዕስ እንዲሆን ትቸዋለሁ ።ለውጡ ከባተ ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገራችን በውሃ ቀጠነ እና በሰበብ አስባቡ ግጭት፣ ሁከት ፣ ብጥብጥና ግፍ በየአይነቱ ያልተከሰተበትን ክልል መጥቀስ ይከብዳል። በዚህ ሰሞን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አንዳንድ ከተሞች የተፈፀመውን ዘግናኝ ግፍ ጨምሮ በአማራ፣ በሶማሊያ፣ በአፋር ፣ በጋምቤላ ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ፣ በሐረሪና በድሬዳዋ የተከሰቱ አጉራ ዘለል ሁከቶች የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲሁም ካለፈው ሀንጎቨር ለመላቀቅ ሲሉ ያሳዩት ልበ ሰፊነት በሚፈለገው ደረጃ አለመሳካቱን ያሳያል።
ሒትለር የእነ እንግሊዝንና ፈረንሳይን ማባበል እንደ ፍርሀት እንደቆጠረው ሁሉ ሕገ ወጦች የመንግስታቸውን ትዕግስትና ማስተዋል እንደ ፍርሀትና ደካማነት ተቆጥሮ የሕግ የበላይነትን ከመገዳደር አልፎ ቀይ መስመሩን በተደጋጋሚ እየጣሰ ይገኛል። ሰሞነኛውን አረመኔአዊ ድርጊት ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀዩ መስመር ታልፏል እንዳሉት ።በተለይ በመማፀኛ ከተማው መሽጎ የሚገኝ የተጠርጣሪ ቡድን በወቅቱ ለሕግ አለመቅረቡ የበሬ ወለደ መረጃ እየነዛ ፣ ሴራ እያሴረ ፣ ደባ እየጎነጎነ ፣ ግጭት እያባዘ ፣ ወዘተ ሀገሪቱን በተደጋጋሚ ወደለየለት ቀውስ ለመክተት ሌት ተቀን እየተጋ ይገኛል ።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሰሞኑን መግለጫቸው መረር ብለው በቃ ! ለማለት የተገደዱትም ለዚህ ነው ።የመጣንበት የአፈና፣ የመገዳደልና የመጠፋፋት ፖለቲካ አዋጭ እንዳልነበር ከቀደመው ታሪካችን የተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተከተሉት ልበ ሰፊነት እንዳለ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በመግለጫቸው ቃል ገብተዋል ፡፡
እንደ መውጫ
በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻል ሁሉ በአንድ ወገን ልበ ሰፊነት ፣ ትዕግስትና ጥረት ሰላምን ማስፈን አይቻልም። በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የፖለቲካም ሆነ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋትም የሚታሰብ አይሆንም። ዴሞክራሲስ በሕዝብ ለሕዝብ ስለሕዝብ አይደል ! ? የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም ።በወንጀል የተጠረጠሩ ቡድኖችን በጉያው ሸሽጎ ፤ ሽማግሌ ፣ የሃይማኖት መሪ ፣ አባ ገዳ ፣ ወላጅ የሌለ ይመስል ልጅን መረን ለቆ ፤ ከሀገር ህልውና ቀዬን ፣ ፓርቲን እያስቀደሙ ፤ የአክቲቪስትን ግንባር እያዩ፣ ምርጫን እያሰቡ ፤ ወዘተ እዚያና እዚህ እያጣቀሱ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አይቻልም ፡፡
እኛም ኮሽ ባለ ቁጥር ወደ መንግስት ጣታችንን ከመቀሰራችን በፊት እንደ ዜጋ ባለንበት ማህበረሰብ በምናገለግለው ተቋም ምን ሰራን ብለን አራቱን ጣቶቻችንን ወደ ራሳችን ማመልከት አለብን ።ታላቁ መፅሐፍስ አንተ ግብዝ በባልንጀራህ አይን ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ከማለትህ በፊት የራስህን ምሰሶ መጀመሪያ አውጣ አይደል የሚለው ።እንዲሁም በአደባባይ የምናወራውንና በጓዳችን ከምንፈፅመው ጋር አንድ ሊሆን ይገባል ።በአውደ ምህረቱ ፣ በመስጊዱ ፣ በመልካው የምንሰብከውን ሆነን መገኘትም ይጠበቅብናል። በኑሮአችን ልናሳይ ይገባል፡፡
በተረፈ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሕንዱ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “ ሃይማኖታዊ ያልሆነው secular የመንግስቴ መርህ ፍትሕ ለሁሉም። ማባበል ለማንም ።“ የሚል ነው እንዳሉት ።ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሁላችን ጠቅላይ እስከሆኑልን ድረስ አያባብሉን ፣ አያቆላምጡን ፣ አያሽበልብሉን። አለመደብንም ።ተፈጥሮአችንም አይደለም። የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ማርክ ኪርክ” ከ1930ዎቹ ማባበል ያተረፍነው ጦርነትን ነው ።“ እንዳሉት እኛም የእርስ በእርስ እልቂትን ፣ ብጥብጥብን ፣ በቁም መፍረስን ማትረፍ ስለማንፈልግ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እደግመዋለሁ ግዴለዎትም ማባበሉን ለሌላ ጊዜ ያቆዩልን።
ለጊዜው ይለፈን። የአራዳ ልጆች እንደሚሉት ይብራብን። ያው አያባብሉን ስል የሕግ የበላይነትና የሕግ የበላይነት ያስከብሩልን ለማለት ነው ።ፓርላማው፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ ልሒቃን ፣ ወላጅ ፣ ወዘተ የሕግ የበላይነት ይከበር ሲሉ በገደምዳሜ እሹሩሩ ይቅር ማለታቸው እምአይደል ።ሆኖም በውጭ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ እየተጠቀሙት ያለው የማባበል ፖሊሲ ውጤታማ ስለሆነ ይበልጥ አጠናክረው ይቀጥሉበት ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012