ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአደባባይ ንግግርና ዲስኩሮች ብዛት የአፍሪካንና የላቲን አሜሪካንን ሀገራት መሪዎች የሚስተካከል አልተገኘም። ይህ ሪከርድ ለበርካታ ዓመታት ክብሩን እንደያዘ ዘልቋል።የተጠቀሱት የሁለቱ ክፍላተ ዓለማት መሪዎች ለንግግር ወይንም ለዲስኩር አዘውትረው ከአደባባዮቻቸው የማይጠፉት በሁለት ዋና ምክንያቶች እንደሆነ ተመራማሪዎች በጥናቶቻቸው ጠቋቁመዋል፡፡
ተቀዳሚው ምክንያት ተብሎ የሚጠቀሰው ሁለቱም አህጉራት ነባርና ስር የሰደደ የብዝሃ ባህል ባለቤቶች መሆናቸው ነው።የአህጉራቱ ሕዝቦች በሃይማኖቶችም ሆነ በመንግሥታዊና በብሔራዊ ክብረ በዓላቶቻቸው ብዛት ባለጠጎች ስለሆኑ መሪዎቻቸው በየአደባባዩ ከጀማውና ከሕዝባቸው ጋር ለመታደም ቅርብ ናቸው።በዚህም ምክንያት ልማድም ይሁን በጎነት መሪዎቹ በተገኙባቸው አደባባዮች ሁሉ ሹልክ ብለው ተገኝተው ሹልክ ብለው ከመውጣት ይልቅ ሁሌም በተጋበዙበት ምስባክ ላይ ድምፃቸውን እያሟሹ ሳይናገሩ ወይንም ዲስኩር ሳያሰሙ ስለማይሸኙ የግድ መድረክ እንዲይዙ መጋበዛቸው ወይንም እንዲጋበዙ መጠየቃቸውን አጥኚዎቹ በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከዴሞክራሲ ጋር ይጣቀሳል።የሁለቱም አህጉራት ሕዝቦች “ለምግብና ለሥራ ብቻ ሳይሆን” ለዴሞክራሲ ጭምር ፅኑ ርሃብተኛ ስለሆኑ ለአደባባይ ሁከትና ግርግር ቅርቦች ናቸው።በዚህም ምክንያት “ለንግግር የታደሉት የታዳጊ አህጉራቱ መሪዎች” የየሀገራቸውን ብሶተኛ ሕዝብ ለማረጋጋትና ለመገሰጽ በማሰብ፤ በቁጣም ይሁን በዛቻ ወይንም በልምምጮሽ ስሜት ብቅ ብለው ለሕዝባቸው መልዕክትና ተስፋ ለመመገብ አያመነቱም።በእነዚህ ሁለት ሁነኛ ምክንያቶች የተነሳ ተመራማሪዎች የአፍሪካንና የላቲን ሀገራት መሪዎችን የአደባባይ ዲስኩር ወይንም “ንግግር” ወዳጆች የሚል ቅጽል ሰጥተዋቸዋል።ይህንን የጥናት ግኝት ብዙዎቹ በአሜንታ ሲቀበሉት በርካቶች ግን በለበጣ ተሳልቀውበታል።አንባቢዎቼ ሃሳቡን በይሁንታም ሆነ በአሉታ እየገመገሙ ወደኋላም ሆነ ወደፊት እየተንደረደሩ ታሪክ በማጣቀስ የሀገራችንን መሪዎች ቢያነጻጽሩበት ክፋት የለውም::
መሪዎች ሲባል የግድ በቁንጮ ሥልጣን ላይ መንበራቸውን የዘረጉትን ብቻ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል።“መሪዎች” የሚባሉት በቁንጮዎቹ መሪዎች ግራና ቀኝ፣ ቅርበትና ዙሪያ የሚገኙ “ባለ ከመከም” ሹመኞችንም ያጣቅሳል።ሌላውና በጥናቶቹ ውስጥ የተሰመረበት ልዩ “ግኝት” የሁለቱ አህጉራት የአደባባይ ዲስኩረኛ መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ንግግሮቻቸውን የሚያቀርቡት በጽሑፍ ላይ ያዘጋጁትን በማንበብ ሳይሆን በቃላቸው በማነብነብ “ስማ ላልሰማ አሰማ!” የሚል መርህ በመከተል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ትልልቅ አህጉራት ተጋብዘን በአሜሪካዋ ክፍለ ግዛት በሐዋይ ለተሰባሰብነው ሃያ ሰባት ያህል የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ሰልጣኞች ፕሮፌሰራችን ይህንን ጥናት ባስተዋወቁን ዕለት የነበረው ሳቅና ሁካታ ምንጊዜም አይረሳኝም።ሰልጣኞቹ በሙሉ “በመንጋ ሳቅ” እንደዚያ ፍልቅልቅ አያሉ የተንፈቀፈቁት የየሀገራቸው የመሪዎቻቸው የንግግር ባህል በትምህርቱ ውስጥ ፍንትው ብሎ ስለታያቸው ነበር።“የልቡን የነገሩት የኮረኮሩትን ያህል ይስቃል” እንደሚባለው መሆኑ ነው::
እያንዳንዱ ሰልጣኝ ተራው እስኪደርስ ድረስ አላስችል ብሎት እየተሽቀዳደመ የሀገሩን ቀደምትም ሆነ ነባሮቹን መሪዎች የንግግር ወግ ለመግለጽ መጋፋቱ ትዝ ባለኝ ቁጥር ፈገግ ማለቴ አልቀረም።የእኔ ተራ ደርሶ የሀገሬን መሪዎች የንግግር ዘይቤ ለማስተዋወቅ ታሪክ ማጣቀስ ስጀምር ሰልጣኝ ጓደኞቼ በሙሉ ያደምጡኝ የነበረው በሁካታ ስሜት ውስጥ ተመስጠው ሳይሆን በጥሞናና በአግራሞት እየተመለከቱኝ ነበር።ለጊዜው ድባቡ ግር ሳያሰኘኝ አልቀረም፡፡
በኋላ እንደገባኝ ከሆነ የእነርሱን ንግግር የሚያስንቅ ችሎታ ኖሮኝ ሳይሆን ባጣቀስኩት መረጃና ማስረጃ ስለተገረሙ ነበር።ለአብነት የጠቀስኩት ቀደምቱን የሀገሬን መሪ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ሲሆን ይህንንም ያደረግሁት ሆን ብዬ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቹ አፍሪካዊያን ሰልጣኞች ስለ ሀገራቸው ነፃነት ሲናገሩ ደጋግመው ንጉሣችንን በበጎ ያነሱ ስለነበር ጥሩ መንደርደሪያ ይሆነኛል ብዬ በማሰብ የዘየድኩት ብልሃትም እውነትም ነበር፡፡
ከንጉሡ በፊትም ሆነ በኋላ ኢትዮጵያን ከመሩ መሪዎች መካከል ለንግግሩ ይዘትና አቅርቦት የእርሳቸውን ያህል ጥንቁቅ ተናገሪ ኖሮ ወይንም ይኖር ከሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ፈለጋቸውን የተከተለ መሪም ስለመኖሩ አላነበብኩም ወይንም የመረጃ እጥረት ተፈታትኖኛል።ሞጋች ምስክር ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ።እርግጥ ነው ንጉሡ ካከናወኗቸው መልካም ተግባራት በላቀ ሁኔታ በበርካታ ጉዳዮች የሚተቿቸው “ባላንጣዎች” እንደሚበዙ ቢገባኝም “ያለመታደላችን” ፍሬ ስለሆነ ምንም ማለት አይቻልም።ደጋግሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ካለፈው ታሪካችን በጎ በጎውን በምስጋና፤ ክፉዎቹ ደግሞ እንዳይደገሙ በትምህርት ሰጭነታቸው ከማስታወስ ይልቅ የታሪክ ጉድፎቻችንን በየምክንያቱ እየነቀስን የዕለት አፍ ማሟሻ ለማድረግ ባህላችን የበረታ ስለሆነ “በኮናኝነት” ብንፈረጅ አይበዛብንም፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በአብነት የጠቀስኩበትን ምክንያት ላብራራ።ንጉሡ ለጥቂት ሰዎችም ሆነ ለብዙኃኑ ሕዝብ ንግግር ያደርጉ የነበረው ለአገላለጻቸው ብቻ ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ ለሆሄያት አጠቃቀምም ሳይቀር ከፍተኛ ጥንቃቄ ያልተጓደለበት መልዕክታቸው በወረቀት ላይ ሰፍሮላቸው እያነበቡ ነበር።ቁምነገሩ ማንበባቸው ብቻ ሳይሆን የተናገሯቸው ንግግሮች በሙሉ ለወዲያውነት ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በታሪክ ቅርስነታቸው ጭምር እየተሰበሰቡ በህትመት መልክ ለሕዝብ እንዲቀርቡ ይደረግ ነበር።
ንጉሡ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን የመንግሥት እንደራሴ ከሆኑበት ከመስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ጀምሮ በአምባገነኑ የደርግ መንግሥት ተገፍተው አስከወደቁበት እስከ 1966 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ባሉት 58 ዓመታት ውስጥ የጽሑፍ ንግግር ያደረጉት ለ2271 ጊዜያት ነበር።በየዓመቱም ምን ያህል ንግግር እንዳደረጉ ስታትስቲክሱ በሚገባ በዝርዝር ተዘጋጅቶ ይገኛል።ለምሳሌ በ58 ዓመታት ዘመነ ሥልጣናቸው ውስጥ ለሁለት ጊዜያት ብቻ በጽሑፍ ንግግር ያደረጉት በ1909፣ በ1931 እና በ1932 ዓ.ም ሲሆን በርከት ያሉ ንግግሮችን በአንድ ዓመት ያደረጉት ደግሞ በ1956 ዓ.ም ሲሆን ብዛቱም 141 ጊዜ ነበር።
ለምን በዚያ ዓመት በርከት ያለ ንግግር እንዳደረጉ ብቻ ሳይሆን የንግግሮቹ ይዘት በራሳቸው ቢተነተን የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ ፍንትው አድርገው ሊያሳዩን ይችሉ ነበር።ለማንኛውም እጅግ የሚገርመው ነገር ሁሉም ንግግሮቻቸው “ፍሬ ከናፍር” በሚል ርዕስ በተለያዩ ቅፆች በታተሙ መጻሕፍትና በሌሎች የኅትመት ውጤቶች ውስጥ ተዘጋጅተው ለአንባቢያን ቀርበው ስለነበር በአርካይቮቻችን ውስጥ ፈልጎ ማንበብ ይቻላል።የኮሚዩኒኬሽን ሰልጣኝ ጓደኞቼን ያስገረመውና ያስደመመው እውነታ ይህ በስታትስቲክ የተደገፈው ገለጻዬ ነበር፡፡
የመሪዎች ሙሉ ንግግር በጽሑፍ ተዘጋጅቶ ለሕዝብና ለተመራማሪዎች መቅረቡ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም። መሪዎች በአደባባይ በሚናገሯቸው ንግግሮች ውስጥ ለሕዝባቸው የሚሰጧቸው ተስፋዎችና የሚገቡት ቃል ኪዳን የሚፈተሸው በንግግር አዋቂነታቸው ምጥቀት ሳይሆን ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር በመለወጣቸው ብርታት ልክ ነው።የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የንጉሡን ዜና መዋዕልና ገድል ለመተረክ ታቅዶ ሳይሆን ለዛሬው እውነታችን ለትምህርት ይጠቅም ከሆነ በማለት ነው፡፡
በአንጻሩ የዘመነ ደርግ መሪዎቻችን ንግግር በአብዛኛውና በብዛት ከጽሑፍ ይልቅ በተናጋሪው ስሜትና በአደባባይ እድምተኞቹ ብዛትና ሙቀት ልክ እየተቀመመ በቃል ይዥጎደጎድ እንደነበር አይዘነጋም።እርግጥ ነው ለሰዓታት እንደ መጫኛ ይሳቡ የነበሩትና እያሰለቹ ያጥወለውሉን የነበሩት ረጃጅም የአብዮት በዓላትና በፖለቲካ ስብሰባዎቻቸው ላይ ይነበቡ የነበሩት ስንክሳሮች የሚዘነጉ አይደሉም።
ይህ የዘመነ ደርግ መሪዎች ንግግር ከንጉሡ የንግግር ይትባህል ጋር በብዙ መልኩ እንደሚቃረን ለማነጻጸር አይከብድም።የቃል ንግግር ደግሞ ዋነኛ ችግሩ “የየጁ ደብተራ ቅዳሴው ቢያልቅበት፤ ቀረርቶ ሞላበት” እንዲሉ ያልታሰበባቸውና አድማጩን ሕዝብ የሚያስቆጡ ቃላት፣ የማይፈጸሙ ተስፋዎችና ምኞቶች በሞቅታ አፈትልከው ስለሚወጡ መሪዎችን ለትዝብት መዳረጋቸውና ከትዝብትም አልፎ መንበረ ስልጣናቸውን የመነቅነቅ ደረጃ ላይ ለሚያደርስ የሕዝብ አመጽ ሊዳርጋቸው እንደሚችል በገሃድ የተገለጠ እውነት ነው።ምሳሌዎችን የምጠቅሰው እኔ ጸሐፊው ሳልሆን አብባቢዬ እንዲሆን እጋብዛለሁ፡፡
“ነበር ማማሩ!” እንዲሉ ትዝታችንን እዚህ ላይ ገታ አድርገን ወደ ዛሬዎቹ መሪዎቻችን ቀልባችንን ሰብሰብ በማድረግ የንግግር ዘይቤዎቻቸውን በተመለከተ ጥቂት ሃሳቦችን እያመነዠክን በንባባችን እንቆዝም።በግሌ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓይናቸውን በወረቀት ላይ ተክለው ሙሉ ንግግራቸውን ሲያነቡ ያስተዋልኩት ለፓርላማ ወንበረተኞቻቸው በዓለ ሲመታቸውን ሲያስመርቁ ይመስለኛል።(የይመስለኛል ጥርጣሬዬ ይሰመርበት፡፡)
ጠቅላዩ አብዛኛውን ጊዜ በሚዲያ ወይንም በአደባባይ ላይ ቆመው ለሕዝባቸው ንግግር ሲያደርጉ የምናስተውለው የንግግር ነጥቦቻቸውን በጽሑፍ አስፍረው በቃል እያብራሩ እንደሆነ አልፎ አልፎ የሚዲያ ካሜራዎች አትሮኖሱ ላይ ሲያፈጡ አንዳንድ ወረቀቶች ፊት ለፊታቸው ተደርድረው ማስተዋላችን አልቀረም።የሴክሬታሪያት ቢሯቸው ባለሙያዎች ትክክል አይደለም የሚሉ ከሆነ ማረሚያ ቢሰጡን አይከፋም፡፡
የከተማችን ክቡር ከንቲባ ታከለ ኡማን (ኢንጂነር) በተመለከተ ግን የተጻፈ እያነበቡ ለሕዝቡ መልዕክት ሲያደርሱ በግሌ አልገጠመኝም ወይንም በዝንጋኤ አላስተዋልኩም።እኒህ የከተማችን ሁነኛ ሹም ከጽሑፍ ይልቅ ለምን በቃል መናገርን ባህላቸው እንዳደረጉ ከሕዝብ ግንኙነት ክፍላቸው ይፋዊ መረጃ ብናገኝ መማማራችንን ያጎለብት ይመስለኛል፡፡
የዚህ ጽሑፍ መደምደሚያ የመሪዎች ንግግር በሙሉ በጽሑፍ ይቅረብ ብሎ አዋጅ ለማጽናት አለመሆኑ ደምቆ ሊሰመርበት ይገባል።ንግግራቸውንና ዲስኩሮቻቸውን በቃል ማቅረብ መብታቸው የመሆኑን ያህል ለእኛ ተራ ዜጎችም ንግግሮቻቸውን ማግኘት የዜግነት መብታችን እንደሆነ ጭምር መገንዘብ አግባብ ነው።እርግጥ ነው “የጽሑፍ ንባብ” ኋላ ቀር፣ የዘመን ወለድ ቴክኖሎጂ ሚዲያዎች ደግሞ የዘመናዊነት መገለጫ አድርጎ በማሰብ “ዕድሜ ለYOU TUBE”፣ “ዕድሜ ለቴሌቪዥንና ለሬዲዮ” ወይንም በመሰል ዘመናይ ቴክኖሊጂዎች ንግግሮችን በቀላሉ ማግኘት የፈለገ ሰው ሁሉ ዘመነ ሉላዊነት ነገሮችን አልጋ በአልጋ ስላደረገ አጉል መጨነቅ አያስፈልግም ብሎ ነገሮችን ቸል ማለት አግባብ አይሆንም።ዳሩ ይህንን ማን ሊክድ ይቻላል!
ችግሩ ግን ዘመነ ቴክኖሎጂ ሕይወትን የማቅለሉን ያህል ነገሮችንም ለማወሳሰብ መበርታቱ ነው።ለምሳሌ፤ የመሪዎችን ንግግር በምስልና ድምፅ እንደወረደ ማቅረብ የመቻሉን ያህል ምስሉንና ድምፁን በተለያዩ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ጥበቦች አሳሳች ቅንብሮችንና መረጃዎችን በማዘጋጀት በመሪዎች ንግግር ሕዝብ እንዲቆጣ፣ ከበረታም አመፅ እንዲነሳሳ መሰይጠን የሚቻልበት ዘመን ላይ ተደርሷል።መሪው ያልተናገረውን አስመስሎ በማቅረብ፣ በተለየ ሁኔታ ላይ የተናገራቸውን ንግግሮች ለማይገጥም ዐውድ በማዋል ብዙ ጥፋት ለመፈጸም አይገድም።መሪዎቻችን በወረቀት ላይ የተዘጋጀን ኦፊሴላዊ ንግግር ለማንበብ “እንደ መሸበት አሮጌ ፋሽን” ቆጥረው ከወረቀት እንዳይፋቱ ማስታወስ ያስፈለገውም ስለዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ቢወዱትም ቢጠሉትም በየትኛውም የእርከን ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕዝብ መሪዎች የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ብቻ አይደሉም።የሕዝብም ናቸው።የሕዝብም ብቻ አይደሉም፤ በታሪክ ግብዓትነት ለመጠቀስም ቀዳሚዎች ናቸው።የነገ ታሪክ ተሸካሚዎች ብቻም አይደሉም፤ የተመራማሪዎችና የጥናት ርዕሰ ጉዳዮችም ጭምር ናቸው።ስለዚህም የንግግራቸው ይዘትና ትሩፋት ዋጋውም ትርጉሙም ከፍ ያለ ዋጋ አለው።ከነአባባሉስ “ንጉሥ ከተነፈሰ፤ ዓይን ከፈሰሰ” ይባል የለ።ንጉሥ የሚወክለው “ሞዓ አንበሳዊውን ንግሥና” ብቻ ሳይሆን በመሪነት ሥልጣን ላይ ያለን ግለሰብ በማጠቃለል ጭምር መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡
ብዙውን ጊዜ መሪዎች ልብ የማይሉት ጉዳይ ለንግግር መድረክ ሲይዙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዜጎች ጆሮዎች በጥንቃቄ እንደሚከፈቱ ነው።“የምናገረውን አውቃለሁ” በሚል ችሎታና ትምክህት ተማምኖ ያለማስታወሻ ወይንም ተገቢው ዝግጅት ሳይደረግበት ለሕዝብ የሚተላለፉ ንግግሮች ምን ያህል ሕዝባዊ ቅይማት እንደሚፈጥሩ፣ ከበረታም ለቁጣ እንደሚያነሳሱ ለመገንዘብ በሀገራችን የሕዝባዊ መድረክ ማሳዎች ላይ ከእነእንክርዳዱ ተዘርተው የሚታጨዱትን ንግግሮች ልብ ብሎ ማጤን ብቻ ይበቃል።
በቅርብ ጊዜያት እንኳን የአንድ ክልል ጎምቱ መሪ በመስቀል አደባባይ ምስባክ ላይ ቆመው ወደ ኋላ የመቶ ዓመታትን ታሪክ እያስታወሱ ያደረጉት የሞቅታ ንግግር የምን ያህሉን ዜጋ ቅስም እንደሰበረ ማስታወስ ይቻላል።“ከእንዲህ መሰል ዘር በመፈጠሬ ዕድለኛ ነኝ”፣ “የምንትስ ታሪክ ለምንትስ አካባቢ ምኑ ነው” ወዘተ. እየተባሉ የተነገሩ የመሪዎቻችንን ቀደምት የተቃወሰ የአደባባይ ንግግርንም ማስታወስ ይቻላል፡፡
መሪዎች የሚመሰገኑት ወይንም የሚወደሱት በንግግራቸው ይዘት ልክ ነው።“ከአያያዝ ይቀደዳል፤ ከአነጋገር ይፈረዳል” እንዲሉ።ከሥነ ምግባር ያፈነገጠና ያልታሰበበት ንግግር ጉዳቱ ከፍ ያለ ስለመሆኑ በርካታ አብነቶችን እያጣቀሱ ማመልከት ይቻላል።ሥልጣንን መከታ አድርጎ ብቻ በእኔ አውቃለሁ ባይነት ያለ ዝግጅት የሚደረጉ የመሪዎች ንግግሮች ከዕለት ጉዳይነት ከፍ ብለው የታሪክ አካልም እንደሚሆኑ ማወቁ ይጠፋቸዋል አይባልም፡፡
“የአመራር ጥበብ” እና “የጥበባት ጉባዔ” በሚሉ ርዕሶች ባሳተምኳቸው ሁለት መጻሕፍት ውስጥ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በንድፈ ሃሳብ የተደገፉ በርካታ ሃሳቦችን ለማቅረብ ስለሞከርኩ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት መጻሕፍቱን ማንበብ ይጠቅማል፡፡
ሳይታሰብ ከአንደበት ሾልከው የሚወጡ ንግግሮችን ለመቆጣጠር መፍትሔው ንግግርን በጽሑፍ አስፍሮ መያዙ በተቀዳሚነት ይጠቀሳል።ከራስ ጉዳይ ባለፈም መሪዎች በሚናገሩት ንግግሮች ውስጥ ሀገራዊ ርዕዮች፣ ፖሊሲዎችና ወደ ተግባር የሚለወጡ ዕቅዶች ስለሚጠቋቆሙና ለሕዝብ የሚሰጡ ተስፋዎችና ቃል ኪዳኖች መፈጸም ያለመፈጸማቸው ስለሚመዘንበት የታሰበበትን ንግግር በወረቀት ላይ ማስፈሩ በእጅጉ ተመራጭ ነው።
“ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ”
የሚለው “የቅን ዘመን ቅን ግጥም” ለዚህኛው ቆቅ ትውልድ አይሠራም።በመሪዎች ንግግር እና በሀገራዊ ጉዳይ ላይም የሚጠቀስ ማሞካሻ አይደለም።የግጥሙ ዐውድ ትርጉም ይኑረውም አይኑረው አድራሻው ሌላ ስለሆነ የመሪዎች ጆሮ አይስማው ቢባል ይቀላል።ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012