የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ እና ከሚዛናዊነት የወጡ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን እንዲታረሙ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑን ስለመናገሩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያሳያል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ እንደሚሉት በአገር ደረጃ ከልካይ የነበሩ ህጎችን እና አሰራሮችን ላላ አድርጎ የተሻለ ነፃነት የመስጠት አዝማሚያ ስለነበረ የመገናኛ ብዙሃንም በአንፃራዊ ነፃነት ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይሁንና አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነቱን ከኃላፊነት ጋር አጣምረው በቅጡ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ መታየቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የ2012 እቅድ በተመለከተ ከስራ ኃላፊዎቹ ጋር ሰሞኑን ውይይት አድርጓል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ጥላውን አጥልቷል ያሉት ዶ/ር ጌታቸው ፖለቲካው ሳይጠራ በመገናኛ ብዙሃን ድርሻ ሃይበል ማለት እንደማይቻልም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግን ጭራሽ የማንታገሰውና ግጭት ቀስቃሽ ዘገባ እየተመለከትን ነው፤ ይህም እንዲታረም እያሳሰብን ነው ብለዋል፡፡
እርምት የማይደረግ ከሆነ ግን በህጉ መሰረት እርምጃዎችን መውሰድ እንጀመራለን ሲሉም ለቋሚ ኮሚቴው አረጋግጠዋል፡፡
አክቲቪስትነትና ጋዜጠኝነት በመገናኛ ብዙሃን ተቀላቅሏል ያሉት ዶ/ር ጌታቸው መሬት ላይ ያለውን የፖለቲካ ትግል ወደ መገናኛ ብዙሃን አምጥተው የትግል መሳሪያ እያደረጉት እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ፍፁም ሙያዊ እንዳልሆነ ተናግረው ሆን ተብሎ የተደረገ እንጂ በእውቀት ማነስ እንዳልሆነም እናውቃለን ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የሚያስተዳድሯቸው የክልል መገናኛ ብዙሃን ጭምር እርስ በርስ ቃላት እየተወራወሩ መሆኑን በማስታወስ ቢያንስ ይህንን ድርጊታቸውን በማቆም ምሳሌ መሆን ቢችሉ ምኞታቸው መሆኑንም ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡
ችግሩ ምንድነው?
በማህበራዊ ድረገጾች እና በሜይንስትሪም ሚዲያው መካከል መደበላለቅ መኖሩ ዋንኛ ችግር መሆኑን ብዙ ወገኖች ያምናሉ፡፡ አንዳንድ አክቲቪስቶች በተጨማሪ የሚዲያ ባለቤቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ጠዋት በፌስቡክና በቲውተር የጻፉትን ሃሳብ ምንም ሳይቀይሩ ማታ ላይ በመደበኛው ሚዲያ ላይ ይዘው የሚቀርቡ፣ ትንታኔ የሚሰጡ አሉ፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ በአክቲቪዝም ሥራ ውስጥ በቀጥታ ይሳተፋሉ፡፡ ችግሩ የጋዜጠኞች በአክቲቪዝም ሥራ ውስጥ መሳተፍ ሳይሆን ሁለቱን ሙያዎች እየደበላለቁ መጠቀማቸው ነው፡፡ አንዳንዶች በማወቅም ባለማወቅም ከአክቲቪዝም ሥራዎች ጋር የሚመጋገቡ ያልተረጋገጡ ዘገባዎችና ዜናዎች እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮችን ወደ ማስተናገዱ መግባታቸው እየታየ ነው፡፡ ሚዲያዎች በአክራሪ ብሔርተኞችና የፖለቲካ ፍላጎት ወይንም አጀንዳ አራጋቢ መሆናቸው የሚደበቅ አልሆነም፡፡ በተለይ የክልል ሚዲያዎች በፓርቲዎችና በዘር ፍላጎት ተጽዕኖ ስር መውደቃቸው በግልጽ የሚታይ ሀቅ ሆኗል፡፡
ለመሆኑ ጋዜጠኝነት ምንድነው፣ አክቲቪስት ማንነው? አንድነትና ልዩነታቸው ምንድነው?
ጋዜጠኝነት
ጋዜጠኝነት ፍትሐዊና ታማኝነት ያለው የዜና ሽፋን በመስጠት ሕዝብን ማገልገል ነው፡፡ ጋዜጠኝነት መሠረታዊ እውነትን መሻት እና ያንኑ መዘገብ ነው፡፡ የሙያ ተግባሩ ሕዝቡ ማወቅ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን ማወቅ ያለበትንም ጭምር ማስተማርና ማሳወቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሌሎች ሙያተኞች ስለጥቂት በተለይም ከሙያቸው ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ በጥልቀት ማወቅ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ጋዜጠኞች ግን ለበርካታ ጉዳዮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የማወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፡፡
መሠረታዊ የጋዜጠኝነት መርሆዎች እጅግ በርካታ ቢሆኑም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እውነተኛነትና ትክክለኝነት፣ ታማኝነት፣ ነጻነት፣ ፍትሐዊና ገለልተኝነት፣ ዋች ዶግ (ዜጎችን ከጉልበታሞች መጠበቅ)፣ ለሕዝብ የክርክር/የውይይት ዕድል መስጠት፣ ሰብዓዊነት፣ ተጠያቂነት… ይጠቀሳሉ፡፡
እናም መገናኛ ብዙሀን የጋዜጠኝነት ሥነምግባር ጠብቀው መጓዝ ካልቻሉበት ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ከአክራሪ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የሃሰተኛና የጥላቻ ንግግር እየተስፋፋ መምጣት እንደሆነ ይገመታል፡፡ መንግስት የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ዘንድሮ ለፓርላማ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሕጉ መውጣት ልቅ የሆነ የብልግና ንግግርን ወይንም የጥላቻ ስብከትን ለመቀነስ ይረዳል ተብሎ ይገመታል፡፡
አክቲቪዝም/አክቲቪስት
አክቲቪስት (Activist) በመጀመሪያ ደረጃ ቃሉ የእንግሊዝኛ ሲሆን እንደሌሎች እንደተወረሱና በዘፈቀደ ቀላቅለን እንደምንጠቀምባቸው ቃላቶች ሁሉ ብዙ ጊዜ ንግግር ስናደርግ /Dialogue/ እንዲሁም በብዛት በማህበራዊ ድረገፅ ያሉ ግለሰቦችን “አክቲቪስት” እያልን ቃሉን እንጠቀምበታለን።
አክቲቪስት፦ ማለት ለውጥ አራማጅ ማለት ነው ወይንም ደግሞ ቀለል ባለ ቋንቋ ለውጥ ፈላጊ ማለት ነው። እንዲሁም ደግሞ በተለያየ ሁኔቴ ድምፁን ለማሰማት የሚጥር ማለት ነው። ስለዚህ ማንም በፖለቲካም ይሁን በሌላ ሁኔታዎች ለውጥ ፈላጊ ድምፁን የሚያሰማበት መንገድ ነው።
ድምፁንም የሚያሰማው በማንኛውም ቦታ ሲሆን ለምሳሌ ፣በስብሰባ፣ በማህበራዊ ድረ- ገፅ/ ቲውተር፣ፌስቡክ../ ፣በሰላማዊ ሰልፍ፣ህዝብ በብዛት የሚገናኝበት አካባቢ ሁሉ ለለውጥ ህዝብን የማነሳሳትና ግንዛቤ የማስጨበጥ እንቅስቃሴ ነው።
አንዳንድ አክቲቪስቶች “አክቲቪስትነት ለሰው ልጆች እኩልነትና ፍትህ መታገል ነው፤ አክቲቪስት ማለት የእኩልነትና ፍትህ አቀንቃኝ መሆን ነው” ይላሉ። ዓላማና ግቡም በአንድ አገር ውስጥ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት እንዲገነባና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ ነው ብለው ይህም የሰው ልጆች መሠረታዊ ጥያቄ ነው ሲሉ ፍቺ አስቀምጠዋል።
አክቲቪስትነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን ማስተማር፣ መቀስቀስና ማስተማር ነው። ይህም “ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጠንካራ የፖሊሲ ወይም የተግባር ዘመቻ” ከሚለው የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ትርጉም ጋር የሚሄድ ነው። በአንድ የተወሰነ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ሕዝብን የሚቀሰቅስና የሚያነቃ ሰው አክቲቪስት ሊባል ይችላል።
አንድነትና ልዩነት
የማህበራዊ ድረገጾች መምጣት ተከትሎ በተለይ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ተጽዕኖው እየጎላ መጥቷል፡፡ አክቲቪዝም አንድን ዓላማ ለማሳካት ውትወታን የሚመለከት ነው፡፡ የቆሙለት ወይንም የሚያሳካው ዓላማ አለው፣ ግልጽ ውግንና አለው፡፡
ጋዜጠኝነት የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት የራሱ ሥነምግባር አለው፡፡ ወገናዊ ዘገባን አያበረታታም ብቻ ሳይሆን በጋዜጠኝነት ውግንናን ማንጸባረቅ ጸያፍ ነው፡፡ ሚዛናዊነትን ወይንም የግራ ቀኙን ሃሳብ ማስተናገድ የግድ ነው፡፡
ጋዜጠኝነት እና አክቲቪዝም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ዓለም አቀፋዊ መብትን በመጠቀም ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ አክቲቪስቶች ለደጋፊዎቻቸው ሃሳባቸውን በጹሑፍ፣ በንግግር ደጋግመው መናገር እነሱን የሚያምኑበትን ለማስረጽ ይተጋሉ፡፡
ጋዜጠኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሃሳባቸውን በነጻ የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው አዳዲስ ዜናና መረጃዎችን ይሰጣሉ፣ ይተቻሉ፡፡ እግረመንገድም ያስተምራሉ፣ ያዝናናሉ፡፡ መረጃዎችን ከመስጠት ባለፈ የሰጡትን መረጃ ሌላው ወገን እንዲቀበል አይወተውቱም፤ ምንም ዓይነት ጫናን አያሳድሩም፡፡
ጋዜጠኝነት እና አክቲቪዝም በሀገራችን መቀላቀሉ ችግር ሆኗል ሲባል መገለጫው ምንድነው የሚል ሃሳብ ዘወትር ይነሳል፡፡ አንዱና ዋና መገለጫው የጥላቻ ንግግር መንሰራፋት ነው፡፡ ብዙሀን መገናኛውም ይህን በማራገብ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ መሆኑ ግጭትና አለመግባባት እንዲስፋፋ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ስለጥላቻ ንግግር ሕጉ ምን ይላል?
በኢፌዴሪ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን አስመልክቶ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ በተደጋጋሚ ባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበት አድርጓል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ዘንድሮ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የወጣ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እንዲህ ይላል፡፡
ሰብዓዊ ክብርን የሚገረስሱ እና ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻና ሃሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የጥላቻ ንግግርና የሃስተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሃገራዊ አንድነት፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሃነትና ለእኩልነት ትልቅ ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ፤መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን አላማ ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ፣ተመጣጣኝና በጠባቡ የተበጁ መሆን እንዳለባቸው በመገንዘብ መዘጋጀቱን በመግቢያው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የአዋጁ አላማዎች
ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፤
በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣መከባበር እንዲኖር፤ መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ስርዐት እንዲጎለብት ማድረግ፤
ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መስፋፋትን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከል እና መቀነስ ናቸው።
የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተ ማንም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ያሰራጨ እንደሆነ የጥላቻ ንግግር ወንጀል ፈጽሟል፡፡
የሃሰት መረጃ ስርጭት በተመለከተ ማንም ሰው የሃሰት መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ያሰራጨ እንደሆነ የሃሰት መረጃ ስርጭት ወንጀል ስለመፈጸሙ በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡
ሲጠቃለል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ “ዋልታ ረገጥ” ብለው በሚጠሩት የተካረረ የብሔርና የእምነት ጫፍ ላይ ቆመው ችግሮችን የሚያባብሱ ወገኖች እኩይ ሃሳብና አመለካከት በሚዲያውም የሚንጸባረቅበት ዕድል አሁን.. አሁን ከገጠመኝነት ማለፉ በብዙዎች አእምሮ ላይ ትልቅ አደጋና ሥጋትን ደቅኗል፡፡ በአንድ ወቅት ዶ/ር አብይ “ከራስ ሰፈር ባሻገር መማረክ ከማይችል ዋልታ ረገጥ ፖለቲካ ልንወጣ ይገባል” በማለት ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡
ሚዲያ ትልቅ ሀይል ነው፡፡ ጋዜጠኝነት ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች አንዱ የሆነውን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት (Freedom of Expression) እንዲከበር የማድረግ ግዙፍ ሚና ይጫወታል፡፡
ሚዲያ ይህንን ተልዕኮ ያለምንም ጣልቃ ገብነት በኃላፊነት በማከናወን ሒደት ውስጥ የሚዲያ ባለቤቶች (የግሉ ዘርፍ ወይንም መንግሥት) እጅ ጥምዘዛ በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ የሚዲያዎች የኤዲቶሪያል ነጻነት እንዲጠበቅ ሁሉም አካላት የየራሳቸውን ሚና መጫወት የሚኖርባቸው ሲሆን በተለይ የዘርፉ ተዋንያን ከፍ ያለ ሚና ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠንካራ ለእውነት የወገነ ሚዲያ ባለቤት(ቶች) ፍላጎት የበላይነት ሳይዝና ከሙያው እሴቶቹ ማለትም መረጃን ትክክለኝነት ማረጋገጥ፣ አለማዳላት፣በኃላፊነት ስሜት መስራት እና ጉዳትን መቀነስ ረገድ ሊሰራ ይገባዋል፡፡ ይህን የጸና አቋም የሚያረጋግጥ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እንዲኖር በመታገል ረገድ የዘርፉ ተዋንያን ድርሻ የላቀ ነው፡፡
መገናኛ ብዙሃን (በተለይም የመንግሥት) በግጭት አዘጋገብ ወቅት ግልጽ አድልኦ ያሳያሉ፡፡ በያዝነው ወር በተከሰተው ጥቃት ሆን ብሎ ሽፋን ያለመስጠት (ባለመዘገብ) እና የመንግሥት አካላት ሲናገሩ ብቻ ጠብቆ የመዘገብ አካሄድ ማሳየታቸው በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከተፈለገው በላይ ሽፋን በመስጠት የሚያስጮሁበት አጋጣሚም አለ፡፡ የሰኔ 15ቱን የከፍተኛ አመራሮች የግድያ ወንጀል በተመለከተ ሲሰሩ የነበረውን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሚዛን የሳቱ እና በአድልኦ የታጀቡ የሚድያ ሽፋን አሰጣጥ መገናኛ ብዙሃኑ ሚናቸውን በትክክል እንዳይወጡ እንቅፋት ከመሆን በዘለለ በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተአማኒነት በእጅጉ የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡
በመንግሥት በኩል በየጊዜው የሚዲያ ዘርፉን ዳር ቆሞ ከመተቸት ባለፈ ተከታታይ ውይይቶች እና የሥልጠና መድረኮችን በማመቻቸት በተለይ የሃሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮች በገቢር የሚቀረፉበትን አቅጣጫ ሊከተልና ከእሱ የሚጠበቀውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ጠ/ሚ አብይ በቅርቡ በተናገሩት ሃሳብ ጹሑፌን ልቋጭ “….ከሚድያ አንጻር መገራት ቢፈልግም የተሻለ ሁኔታ አለ፡፡ ሚድያዎች ከተገሩ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡” አዎ!.. በተለይ ዋልታ ረገጦቹ በፍጥነት ሊገሩ ይገባል፡፡ (ማጣቀሻዎች፡ – የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ቢቢሲ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እና የተለያዩ ድረገጾች ላይ የተገኙ መረጃዎች)
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012