<< አምኜን>> ለምኜ ስዘራ እንዳልነበር
ጎረቤቴ ጅሩ አቀበለኝ ምክር
ብሎ የገጠመው የሰሜን ሸዋው የሞጃና ወደራ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ነው። በአካባቢው ያለው ጥቁር አፈር በክረምት ቢዘራበት ፍሬ አልይዝልህ ቢለው በመስከረም እየዘራ ለቀለቡ የምትሆነውን ጥቂት ሰብል ብቻ ያገኝ እንደነበር አይዘነጋውም። አሁን ይህ ተቀይሯል። ምክንያቱም በደለቡ በሬዎቿ ከምትታወቀው ሞረት እና ጅሩ ወረዳ የመጡ አርሶ አደሮች ቀድሞ በሰለጠኑበት የኩታ ገጠም የጥቁር አፈር አንጠፍፎ የመዝራት ስልት መሰረት ለጎረቤቶቻቸው ሞጃና ወደራ አካባቢዎች ልምድ አካፍለው ተመልሰዋል። ከዚያ ወዲህ አገሩ ሁሉ ሰፋፊ እርሻ ይመስል ከዳር እስከዳር በአንድ አይነት ሰብል በኩታ ገጠም ዘርቶ ለዓይንም የሚያጠግብ ፍሬ የያዘ ሰብል አድርሷል።
አቶ ከፈለኝ በርሶማ በሰሜን ሸዋ ዞን የሞጃና ወደራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ በላ የሚዘራው <<አምኜ>> የተሰኘውን አዘራር ተከትሎ እንደነበር ያስታውሳሉ። አምኜ የተባለውም አመራረት የአካባቢው ጥቁር አፈር በክረምት ወቅት ውሃ እየያዘ ሰብል አላበቅል ስለሚል መስከረም ሲጠባ ተጠብቆ የሚዘራበትን ሁኔታ ያመለክታል። ክረምት ካለፈ በኋላ በመዘራቱ ሊያፈራም ላያፈራም ስለሚችል፣ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል የሚለውን ይዞ አምኜ የሚለው ስም የሚሰጠው አመራረት በአካባቢው የኖረ መሆኑን ይናገራሉ።
ከክረምቱ በፊት ግን የወረዳው አመራሮች ከግብርና ባለሙያዎች በተጨማሪ ከክላስተር አስተራረስ እና በጥቁር አፈር ምርታማነት ላይ ስልጠና ወስደው ማሳቸው ላይ የተገበሩ 10 አርሶ አደሮችን ከሞረትና ጅሩ አካባቢዎች አምጥተው ለሀገሬው ሰው ሁሉ እየዞሩ እንዲያሰለጥኑ ብሎም ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።
የጅሩዎቹን የልምድ ተሞክሮ ተግባራዊ አድርገናል የሚሉት አቶ ከፈለኝ፣ በዘንድሮው የክረምት ዘመንም ሁሉም አርሶ አደር ለ60 እና 70 በመሆን አንድ መሪ እየመረጠ በመሰባሰብ በተመሳሳይ ሳምንት በማረስ፣ ስንዴ በመዝራቱ እና በመንከባከቡ ኩታ ገጠም መሬቱ ላይ ያማረ ሰብል ማግኘቱን ይገልጻሉ።
እንደ እርሳቸው፤ ፓላስ የተሰኘውን ጸረ አረም እና ሌሎች ግብዓቶችን በመጠቀምም በጋራ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሲከላከሉ ቆይተዋል። ይህም ልምድ ውጤታማ መሆኑን አርሶ አደሩ በማየቱ ከዚህ በኋላ ያለጎትጓች በጋራ እየሰራ ከፍተኛ ምርት ለማምረት ብሎም ለሌሎች አካባቢዎች ልምዱን ማካፈል ይፈልጋል።
ወይዘሮ አሰገደች ወልደሃዋርያት ደግሞ በአካባቢው ሴት አርሶ አደር ናቸው። ሁለት ጥማድ መሬት ቢኖራቸውም ከአራቱም ወገን ያለውን የእርሻ መተላለፊያ መሬት በኩታ ገጠም በማረስ በህብረት እያመረቱ ነው። አሁን ምርቱም በጋራ ፓላስ ጸረ ተባይ እና የተለያዩ ግብዓቶች እየተጠቀሙ በመስመር በመዘራቱ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ተስፋ ሰንቀዋል። <<ከዚህ ቀደም አምኜን ስንዘራ ትደርስ አትደርስ ይሆን ተብሎ ከአንድ ጥማድ አምስት እና ስድስት ኩንታል ይገኝ ነበር። አሁን ግን እስከ 30 ኩንታል በጥማድ የሚደርስ የስንዴ ምርት እንደማገኝ ተማምኛለሁ>> ይላሉ።
ከጅሩ የመጡ አርሶ አደሮች ጥቁር አፈርን በወጉ ስለማንጠፈፍ እና ስለጋራ ሥራ ጠቀሜታ ያቀበሉን ምክር ተግባራዊ አድርገናል የሚሉት ወይዘሮ አሰገደች በቀጣዩ ደግሞ አስተማማኝ ፍሬ የያዘውን ሰብል በአግባቡ የሚሰበስቡ እና የሚወቁ ዘመናዊ ማሽኖችን ስለማሰማራት ሊታሰብ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
የአንድ ባለሃብት ወይም የመንግሥት ሰፋፊ እርሻ የሚመስለውን በኩታ ገጠም የታረሰ የአርሶ አደር ማሳ ምርት እንዳይባክን ከተፈለገ አንድም ሁለትም እያሉ የግብርና ማሽኖችን ቢቀርቡ የበለጠ ምርት ይገኛል ባይ ናቸው።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ ደግሞ ከፌዴራል እና ከክልል የመጡ ባለስልጣናትን አስከትለው ማሳውን ከጎበኙ በኋላ እንዲህ አሉ፤ አርሶ አደር ከአርሶ አደር አገናኝቶ በተደረገው ልምድ ልውውጥ ከቀድሞው ሶስት እጥፍ እና ከዚያ በላይ ምርት ማሳደግ ተችሏል። ይህን ቦታ የተግባር ማዕከል በማድረግ ደግሞ ለተቀረውም አካባቢ ሁሉ ልምዱን ማዳረስ ያስፈልጋል።
እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ፣ በወረዳው በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች በኩታ ገጠም እና በቅንጅት አሰራር ሄክታር ላይ አምርተዋል። በዚህ ሥራ 1ሺ645 አርሶ አደሮች በፈቃደኝነት መሬታቸው ላይ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሰርተዋል። በዚህም ከፍተኛ የስንዴ ምርት ከአካባቢው እንደሚገኝ ይጠበቃል።
የጅሩ እና አካባቢው አርሶ አደሮች ያሳዩት ተሞክሮ የማካፈል ልምድም የሚደነቅ ነው። በመሆኑም በሰሜን ሸዋ እየተገኘ ያለውን ሰፊ የግብርና ምርት በዘላቂነት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲሆን ለመጠቀም የአግሮ ፕሮሰሲን ፋብሪካዎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ጌትነት ተስፋማርያም