ማለፊያ ብዕራቸው ሞገስ ይሁንላቸውና ደራሲ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ‹‹አርአያ›› በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፋቸው የእድሜና አመለካከትን ምንነት በሚገባ እናስተውል ዘንድ ጠቅሰውታል።
ዓቢይ ገጸ ባሕርይ ያደረጉት ‹‹አርአያ›› ከሀገረ ፈረንሳይ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሥራ ምደባ ይሰጠው ዘንድ እንደ ወጉ በቤተ መንግሥት ደጅ ሲጠና በነበረበት ወቅት ‹‹አንድ ሽማግሌ ሀብታም መኮንን›› እዚያ ከደጅ ጠኚዎች ጋር አግኝተውት ነበርና አናግረውት የውይይታቸውም መልክ ምን ሊመስል እንደቃጣ ሳያስገነዘቡን አልቀሩም።
‹‹ለመሆኑ የቱን መሰል ግንዛቤ ጨበጣችሁ?›› ተብሎ ቢጠየቅ አረጋዊው መኮንንና ወጣቱ ኢትዮጵያዊ የምድረ አውሮፓ ምሩቅ ተመላሽ በተለዋወጧቸው ቃላት ውስጥ የተቀናቃኝነት፣ ‹‹ለእኔ ይገባል›› ባይነት የጎለበተ የባላንጣነት አመለካከት እውን ሊሆን የበቃበትን ኩነት ደራሲው በግሩም አኳኋን ያሰመሩበትን ጽሑፍ ለገጸ ንባብ አብቅተዋል።
ከአዛውንቱ ቀዳሚ ጥያቄ እንኳ ብንነሣና ከዚያ ‹‹አርአያ›› የሰጠውን መልስ ብንመለከት ያን ሰምተው ደግሞ አረጋዊው መኮንን ያስደመጡትን የመልስ መልስ ለአፍታ ብናይ መልካም ነውና እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ለመሆኑ ምን ተምረህ መጣህ?››፣
‹‹የእርሻ ትምህርት››፣
‹‹የእርሻን ትምህርት ምን ትምህርት ትለዋለህ! እኛ የትም ሳንሄድ ማንም ሳያስተምረን ዐውቀን እንሠራበት የለምን? ለዚህ ለምን ሰው ሀገር አስኬደህ ልጄ?!››
ይህ አባባል እንግዲህ በትክክል የባላንጣነት ማንደርደሪያ የሆነውን፣ ቀንቶ መናቅ›› የሚባለውን አሳምሮ ያረጋግጥልናል።
‹‹ወጣቱ አርአያ›› ከኒያ ‹‹ሽማግሌ መኮንን›› ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አካሂዶ ትምህርት ለግብርናውም ቢሆን ወሳኝነቱን ለማስመስከር ብዙ ቢጥር እንኳ ሳይሳካለት እንደቀረ ደራሲው አስረድተውናል። እሳቸው ግን ለዚህ የአርአያ መልስ ምንም ሳይበገሩ ይበልጡንም በሐሳባቸው እንደገረሩ፣ በዚያው አቋማቸው እንደተገተሩ መቅረታቸውን እናያለን።
‹‹እባክህን ተወኝ የእናንተ ትምህርት ሲረባ አላየንም። የምታውቁት ትምባሆ መጠጣትንና ይህችን ኮት ብጤ መልበስን፣ በጦም መብላትን እንጂ አንድ ሥራ ስትሠሩ አላየንም። ከብሪትና መርፌ እንኳ አትፈጥሩ! እንዲያው ይብላኝ! ይብላኝ! እኛስ አርጅተናል ትተንላችኋል። ብቻ መጨረሻችሁን አይተን ጉድ አሳይቶን!›› እያሉ ምሬትና ቁጭት በመላበት ቋንቋ ሲናገሩ ‹‹አርአያ ተገረመ›› ይላል የደራሲው ጽሑፍ።
የሁለቱን ገጸ ባሕርያት የንግግር ልውውጥ ደራሲ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት በዚህ ከደመደሙ በኋላ ‹‹ይህ›› እነርሱ እኛን እንደ መደገፍና ዐውቀው ቦታ እየለቀቁልን በማበረታታት ፈንታ የባላንጣነት መንፈስ ካደረባቸውም ይህ ከፍ ያለ ጉዳት የሚፈጥር ነው እኮ›› ሲሉ ይህን የባላጋራነት አቻ የሆነውን ‹‹ባላንጣነት›› በብርቱ ኮንነውታል። ይህን መሰል አመለካከት መኖሩን ደራሲው በማያወላውል አኳኋን ያረጋገጡት መጽሐፉ አደባባይ በዋለበት ዘመን የዛሬ ስድሣ ሰባት ዓመት ገደማ ነው።
ዛሬስ? የለም? እንዲያው አፍ ሞልቶ ‹‹የለም›› ለማለት እና ያለ አንዳች ማንገራገር ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም። ‹‹መንፈሳዊ ቅናት›› ቢኖር ኖሮ ከተፈጥሯዊ ባሕርይ የሚሰርጽ ነውና እንደ አመጣጡ መቀበል እንችል ነበር። ‹‹ቀንቶ መናቅ›› ግን አዘንባይነቱ ወደ ምቀኝነት ወደ ፍጹም ባላጋራነት ወይም ወደ ፍጹም ባላንጣነት ያጋድላልና በሳቅና በደስታ ማስተናገዱ ለብዙዎቻችን ሲቸግር እናያለን።
ሌላው ቀርቶ እንደ ነገሩ የእድሜ ባለጸጋነቱን ፈጣሪ ቸሮት ለጡረታ የበቃ ሰው እንኳ ያን እድሜ ያበደረ ፈጣሪ አመስግኖ ለዘመን አረጋዊነት በመብቃቱ ሐሴት አድርጎ ለሌላው ማለፊያ ምሣሌ ሆኖ መታየት ሲገባ ‹‹እኛ እንግዲህ በቅቶናል፣ እስቲ እንግዲህ እነ እገሌ፣ እነ እገሊት ሲሠሩ እናያለን›› በማለት የጠላትነት ባሕርይውን ለማወጅ ይነሣል።
ይህም ብቻ አይደለም። በተግባር ምድብ ዘመኑ ካካበተው ትንሽ ዕውቀት ወይም ልምድ እንኳ እንዲለግስ ቢጠየቅ ‹‹ለማን ብዬ…..›› የተሰኘ ነገር ያስደምጣል። እንግዲህ ሀገሪቱ መኖርም፣ መበልጸግም ያለባት እርሱ በሥራ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑ ነው። እርሱ ሲታመምም ታማ፣ ሲሞትም ሞታ፣ ሲቀበርም ተቀብራ መገኘት አለባት ማለት ነው። የእንደዚህ ያለ ክፉ አመለካከት የአንድን ሀገር ልማትና እድገት ወደ ኋላ የሚጎትት፣ በማናቸውም ሁኔታ ወደፊት ትጓዝ ዘንድ የማይፈቅድ ስለሆነ ለአንድ የኅብረተሰብ አነዋወር እና ብልጽግና ጨርሶ የተድላ ብሥራት አይደለም።
‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው የጋማ ከብት ዓይነት መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ አህያ ይህን ስትተርት በጆሮው የሰማ ሰው የለም። ሰው የራሱን ባሕርይና ምቀኝነት፣ ራስ ብቻ ወዳድነትና ‹‹ሁሉን ለእኔ -ሌላው ለምኔ›› ባይነት እንደ ክፉ አመሉ በጉያው ሸሽጎ በአጋሰስ ላይ ጭኖ እያላከከ ዘመኑን ቆጠረ እንጂ!!
በርግጥ የዘመናችን ‹‹ወጣት ነኝ›› ባይም የሚያጠፋው ሞልቷል። የንቀት አስተያየት የበረከተ ነው። በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ እንኳ ብናይ የአረጋዊውን የጠራ ስልተ ልሳን እንደ አላቂ አሮጌ ጨርቅ ይቆጥረዋል። እንደ ቡትቶ ይንቀዋል። ይህ ሲባል ግን በተለይ በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ በሽማግሌው ጎራ በሚደመጠው ሮሮ ወጣቱ ተደስቷል ማለትም አይደለም። የእድሜ ባለጸጋው በፊናው የራሱ ክፉ አመለካከት አለበት። በዕውቀት ጥልቀት፣ በምርምር ምጥቀት፣ በተግባር ርቀት እና በአሠራር ብልኃት በአነዋወር ለውጥና ምጥቀት የተፈጠሩትን የአነጋገር ፈሊጦች ሲሰማ ‹‹የዛሬ ልጅ አማርኛ ምኑ ተይዞ! አበላሽቶታል!›› እያለ ያጥላላዋል።
ለምሳሌ የዜማውን፣ የሙዚቃውን ነገር እንኳ ብናነሳ ‹‹ዜማ›› የሚለው ‹‹ዘየመ›› ከሚለው ግሥ ‹‹ሊመጣ መቻሉን›› ሙዚቃም ‹‹ሞዘቀ›› ከተሰኘው ግሥ ‹‹በስምምነት እንዲያገለግል›› መፈጠሩን የሰማ ወይም ያነበበ እኔን መሰል ወይም እኔን አለፍ እድሜ ጠገብ ‹‹ይሄ ግሥ ደግሞ ከየት መጣና ነው›› ሲል አንጃ ግራንጃውን ይያያዘዋል። የቀድሞዎቹን የብላታ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስን ወይም የመምህር ተክለ ማርያ ፋንታዬን መጻሕፍተ ሰዋሰው ግሥና ርባታ በምስክርነት ቆጥሮ ሊሟገት ይነሣል።
ቋንቋ ከጊዜ ጋር እየተራመደ ሊሄድ መብቃቱንም ማመን አይፈቅድም። እንግዲህ በእርሱ ቤት ቋንቋ አያድግም፣ አይለወጥም፣ አይጎላም፣ አይኮስስም ማለት ነው። ያው እንደ አንቺ፣ አንተ፣ እኔ፣ እርሱ፣እርሷ እንደሚሉት ተውላጠ ስሞች በጉብልና ይኖራል ማለት ነው። ይህ እጅግ የከበደ ስሕተት ሆኖ ሳለ ብዙ ጊዜ ሲታረም እና ወደ ተሻለ ሁኔታም ሲረማመድ ያየንበት ወቅት የለም ማለት ይቻላል።
እዚህ ላይ ግን ‹‹ወጣት ነኝ›› ባዩ በየቀኑ በየጫት መቃሚያው የሚፈጥሯቸውን ስድብ አከል፣ ዘለፋ አዘል ሰው አዋራጅ ልቅ የባለጌ አባባሎች ለማለት ፈጽሞ እንዳልተሞከረ ልብ ልንል ይገባል። የእንዲህ ዓይነቶቹ ወጣቶች አባባል እና ቋንቋ ጭርሱን እንኳን ልብ ሰጥቶ ለግንዛቤ ለማብቃትና ለወቅትም ቢሆን ለአፍታ ጆሮ ሰጥቶ መገኘት የሚያስፈልግ አይደለም።
በጥቅሉ ሲታይ ግን በበርካታ ሊቃውንት አስተሳሰብ ወጣቱ ትውልድ የሚችለውን ያህል ዕውቀት የሚገበይበትን ስልት መርጦ ከዘመኑ ሥልጣኔ ጋር ቢያዋህደው ፍኖተ ሕይወቱን የተመቻቸ እንደሚያደርገው ብዙዎቹ ማእምራነ ልሳናት ይስማሙበታል። ወጣቱ ግን ይህን መሰል አመለካከት ይዞ ለመጓዝ ይፈቅዳልን? ይህ እራሱን የቻለ አጠያያቂ ጉዳይ ነው።
አረጋዊውና አረጋዊቷ ደግሞ የወጣቱን፣ የጎልማሳውን ዘመን ወለድ ተክህኖ ተቀብለው ለሽበት ማለምለሚያ ተካፍለው፣ ራሳቸውም ካካበቱት አካፍለው ለመኖር ቢፈቅዱ እድሜያቸውን በደስታ ከዳር ያደርሱታል የሚል ትርጓሜ ያለው በእጅግም ተቀባይነቱ የሚያጠራጥር አስተሳሰብ ብዙ ጊዜ ይደመጣል።
በማንኛዎቹም ወገን መናናቅ ከተከሰተ ግን ያው መራራቅን ፈጥሮ የመጨረሻው ውጤት ሕይወታቸውን ውሃ እንደጠማው ተክል አጠውልጎ መቅረት ብቻ ይሆናል። እናስ ይህ ለምን እንዲሆን ይፈቀዳል? ነገሩ እጅግ የሚያሳስብ መሆኑን በበርካታ ጊዜያት ምሁራን ባገኙበት መድረክ የሁኔታውን አስጊነት ጭምር ከማስገንዘብ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም። ሆኖም አስጊነቱ በብዙዎች እየተነገረ ቢገኝም የሚረዳው ወይም ለመረዳት የሚፈቅደው በጣም በቁጥር ያነሰ ነው።
ይሁንና አንድን ነገር እንደሚያደምጡት ሁሉ ወዲያውኑ ደግሞ ለውጦ ወይም በሌላ ተክቶ ለመገኘት ያስቸግራልና አሁንም ቢሆን በተስፋ ከመጠባበቅ ወደ ኋላ ማለት የሚገባ አይደለም። ስለዚህ ጥረቱ ይቀጥል ዘንድ የሁላችንም ምኞት ሊሆን የተገባው ነው። በተረፈ ግን ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አለች አህያ እየተባለ ያንኑ ‹‹የአጋሰስ ተረት ይዞ መኖሩን አንፈቅደውም። በነገራችን ላይ ‹‹አህያ እንዲህ አለች›› ሲባል እድሜ ልካችንን ስንሰማ ሁለት ጸጉር አውጥተናል። ለመሆኑ ‹‹አህያን መሆን የሚፈልግ›› ይቅርና ‹‹አህያን መምሰል የሚከጅል ሰብዓዊ ፍጡር›› ይገኝ ይሆን? ይህንን ጥያቄ ለአንባቢ እንተወዋለን።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012