ለውጡን ተከትሎ ከተወሰዱ ወሳኝ እርምጃዎች አንዱና ምናልባትም ግንባር ቀደሙ እንደኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓይነት የዴሞክራሲ ተቋማት በነጻና ገለልተኛ ሰዎች እንዲመራ የተደረገበት አግባብ የሚጠቀስ ነው፡፡ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ፒ ኤች ዲ) የሚመሩት ይህ ኮሚሽን አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ልዩነት ወሳኝ በሚባሉ ሁለት ጉዳዮች ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሰጥቷል፡፡
መታረም ያለባቸው ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲታርሙ አሳስቧል፡፡ ኮሚሽኑ በአካል ጭምር በመሄድ መርምሮ ምክረ ሃሳብ ከሰጠባቸው መካከል ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም «የመፈንቅለ መንግስት» ሙከራ ጋር ተያይዞ በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖችን የሚመለከተው አንደኛው ነው፡፡ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም የወጣው ይህ የኮሚሽኑ መግለጫ የሕገመንግስቱ አንቀጽ 21 ሁለት ንዑሳን ድንጋጌዎች መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ እንዲህ ይላል፡፡
«በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡»
«ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡»
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሌላው ጠንከር ያለ መግለጫ የተሰማው ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ያስከተለውን መጠነ ሰፊና ኢ- ሰብዓዊ እልቂትና ጥፋት በተመለከተ የሚዳስስ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በ11ኛው እና 12ኛው ዙር የሰለጠኑ የመከላከያ መኮንኖችን ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የደቦ ፍትህ ተቀባይነት እንደሌለው መናገራቸው የኮሚሽኑን አቋም የሚያጠናክር ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የደቦ (የመንጋ) ፍትህ እና አላስፈላጊ ሁከት ተቀባይነት የሌለው እና የህግ የበላይነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡
አያይዘውም ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ የተሳሳተ መረጃን መሠረት በማድረግ ለሕግ ቅድሚያ ሳይሰጥ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች እየተገነባች ያለችን ሃገር ከማፍረስ ውጭ ዋጋ የለውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሕግ የበላይነት ለአንድ ሀገር ማህበረሰብ መጠበቅ መሠረት መሆኑንም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻርም መንግስት አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን ከሕግ በላይ የመሆን ዝንባሌ እንደማይታገስም አንስተዋል።
“እንደመር ስንል ባለፍንበት መንገድ ያጣነውን ለመመለስ እንጅ ሃገሪቱን ውጤቱ ለከፋ ቀውስ ለመዳረግ አይደለምም” ብለዋል በንግግራቸው።
መንግስትም እነዚህን ክስተቶች ለመቆጣጠር የመከላከል እና ህግ የማስከበር ስራዎችን እንደሚ ያጠንክር ተናግረዋል፡፡
አዎ!.. የደቦ ፍርድ (ፍትህ) የታለመለትን የፍትህ ጥያቄ ሊመልስ የማይችል፣ ዴሞክራሲንና አብሮነትን የሚጎዳ፣ የእርስ በርስ ግጭትን በማባባስ የሀገር ህልውናን የሚያፈርስ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
የሰኔ 15ቱ የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በባህርዳር የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ ሁለት ጀኔራሎችን የቀጠፈው የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ግድያ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑን ጠቅሰው ሙከራውን በፍጥነት መቆጣጣር ባይችል ኖሮ አስከፊ ነገር ይዞ የሚመጣ አደገኛ ክስተት ነበር ብለዋል።
መንግሥት የሰኔ 15ቱን ክስተት መሰረት አድርጎ የግለሰቦች እና የመገናና ብዙሃንን ድምጽ ለማፈን ሙከራ አድርጓል የሚል ቅሬታ ይቀርብበታል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ ይህ እውነት አይደለም መንግሥት የሰዎችን ደምጽ የማፈን ፍላጎት የለውም፡፡ እንደውም ከዚህ ቀደም በመንግሥት ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እንዲከፈቱ ተደርጓል ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ቅሬታዎች እየተነሱበት እንደሆነ በመጠቀስ መንግሥታቸው በዚህ ረገድ የነበረው አቋሙ ስለመቀየሩ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ጭለማ ቤት የታሰረ የለም፣ ሰው አይገረፍም፣ ጥፍር አይነቀልም ያሉ ሲሆን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለን አቋም አልተቀየረም፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲስፋፋ ነው ፍላጎታችን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ፒ ኤች ዲ) በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም በመጎብኘት መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮችን ለይተው ይፋ አድርገዋል፡፡
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ሥር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ሐይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሁኔታቸውንም ተመልክተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍል በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ታሳሪዎቹ ከ 3 እስከ 4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰረት ሊቀርብ ይገባል›› በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማተሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል›› በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ከ70 በላይ ንጹሃንን የበላው ቀውስ
በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እና ተሃድሶ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስገኘ ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት ይገኛል፡፡ በተለይ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰው ውዝግብ እና ሁከት የተሞላ ነውጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት ከመድረሱ፣ ንብረት ከመውደሙ እና የሰዎች መደበኛ ኑሮ እና ሠላማዊ ሕይወት ከመረበሹ በተጨማሪ፤ የህግ የበላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ላይ የጣለ እጅግ አሳሳቢ ክስተት እንደነበር የኮሚሽኑ መግለጫ ያትታል፡፡
አያይዞም በዚህ ሁከት ምክንያት በሚዲያዎች ዘገባ መሰረት እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አስር ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው የሞቱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሰዎች ግን እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚገመት የግለሰቦች፣ የሕዝብና የአገር ንብረት ወድሟል፡፡ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት መዳረጋቸውን መግለጫው ያስረዳል፡፡
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማናቸውም ዓይነት ቅሬታ ወይም ጥያቄ በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩ ይታመናል፡፡ ለዚህ ውዝግብ መነሻ በሆነው ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሹ ሰዎች ቢኖሩም ሁከት የቀሰቀሱ፣ የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ እንዲሁም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ የሰጡ ሰዎች መኖራቸው ግን አይካድም።
ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታና ጥያቄ በአመፅ እና በእልቂት ማስፈራሪያ ለማስፈፀም የታየው ተግባር እና ያስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የአገር ሠላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ያስከተለ በመሆኑ በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡
ይህን ጥፋት የፈፀሙ እና ወይም የጥፋቱን ተግባር እንደ መልካም ሥራ ያወደሱ ሰዎች ሁሉ በዱላ እና በስለት ተደብድበው በእሳት ተቃጥለው የተገደሉ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለአፍታ እንኳን በራሣቸውና በቤተሰቦቻቸው ተክተው አለማሰባቸው የደረሰውን ጉዳት ይበልጥ መሪር አድርጐታል፡፡ የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሳያወላውል እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ ሲሆን፤ ይህ የመንግሥት ኃላፊነት እና ተግባር በስልታዊ የምርመራ ሥራ እና በሕጋዊ ሥርዓት በአፋጣኝ በሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ ማንኛውም ሰው በመተባበር እና ውጤቱን በትዕግስት በመጠባበቅ፣ በየአካባቢው የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በማጽናናት በመደገፍ እና በመጠገን፤ እንዲሁም የመንግሥት፣ የፖለቲካ እና የልዩ ልዩ ቡድኖች መሪዎች የፖለቲካ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ቆስቋሽ ንግግሮች እና ድርጊቶች እራሳቸውን በመቆጠብ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እና ይህን የመሰለ ጥፋት ዳግም እንዳይፈጸም የሚመለከታቸው አካሎች ሁሎ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል ሲል ምክረ ሃሳቡን ለግሷል፡፡
እንደመውጫ
የኮሚሽኑን መግለጫ መውጣት በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር ተያይዞ ታስረው ከነበሩት መካከል ብዙዎች በመታወቂያ ዋስ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ መወሰኑ እንደተራ ገጠመኝ ማየት አይቻልም፡፡
ከጥቅምት 12ቱ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ተከስቶ አሰቃቂ ሞትና ጥፋትን በማስከተል የተጠናቀቀው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በድርጊቱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እጃቸው ያለበት ወገኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረሃሳብ መንግሥት እያከናወነ ያለውን መሰል ጥረት በማገዝ ረገድ የሚኖረው ድርሻ በቀላሉ የሚወሰድ አይደለም።
የሕግ የበላይነት አንዱ መገለጫ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ነው፡፡ ከሰብዓዊ መብቶች አንዱ ደግሞ አንድ ሰው በነጻ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ጥፋተኛ እንዳልሆነና ነጻ እንደሆነ የሚቆጠርበት የሕግ ሽፋን ነው፡፡ የደቦ ፍርድ ይህንን የሰውን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ አካሄዱ በመንግስት አወቃቀር ሕግ አውጪ ሕግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈጻሚ ያስፈለገው አንዱ አንዱን እንዲቆጣጠርና እርስ በርስ በመተራረም ሕግና ስርዓትን ለማስከበር የተቀመጠውን አሠራር የሚያፈርስና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ በር ከፋች በመሆኑ በየትኛውም ሀገር የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትር አብይ አስተዳደር “ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ ለዘብተኛ አቋም ያሳያል፣ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ተስኖታል” በሚል ከፍተኛ ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ለፓርላማ አባላት “የምንታገሰው የነበረውን ነገር ላለመድገም ነው” ሲሉ የመንግሥትን የበዛ ትግዕስት አግባብነት ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012