ሰሞነኛ ከሆኑትና የብዙዎቻችንን ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች መካከል ኢህአዴግ ወደ ውህድ ፓርቲነት ሊለወጥ ነው የሚለውን ያህል የህዝብ ጆሮ የተሰጠው ጉዳይ ያለ አይመስለኝም። በተለይም ጉዳዩ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ ፓርቲዎች መካከል ተመሳሳይ አቋም ያልተያዘበት መሆኑና ጽንፍ ተይዞ ድንጋይ የሚወራወሩበት የፖለቲካ መድረክ መሆኑ ብዙዎቻችን ትኩረት እንድንሰጠው አስገድዶናል።
የኢህአዴግ ውህደት እንደዚህ ዋነኛ የውዝግብ ማዕከል የሆነበት ጉዳይ ምንድን ነው ? ለምን ከአንዳንድ ወገኖች በዚህ መጠን ተቃውሞ ገጠመው? ውህደቱ በቅጽበት የታሰበ ነው ወይ? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎች መመልከቱ አግባብ ነው። የኢህአዴግ ውህደት መነጋገሪያ ከሆነ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ጉዳይ ነው። ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ውህደት ያስፈልገዋል የሚለው ጉዳይ በ5ኛው የግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ተዘግቦ እናገኘዋለን።
ስለዚህም እንደሚባለው አዲስ ክስተት አይደለም። በኢህአዴግ ጉባኤ ሲሳተፉ የቆዩ አንዳንድ ነባር አመራሮች እንደሚያስረዱትም ይህ የውህደት ጥያቄም ከ5ኛው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ በተደረጉ ጉባኤዎች ሳይነሳ የማያልፍ ጥያቄ ሆኖ መቀጠሉንና በሁሉም የድርጅቱ አባላት ጭምር የግንባሩ የውህድት አስፈላጊነት ጉዳይም በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ መሆኑን ነው የገለጹት። የውህደት ጥያቄው የበረታበት ኢህአዴግም በመቀሌ ከተማ ባደረገው 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥያቄው ተጠንቶ ምላሽ እንዲያገኝ በማለት አቅጣጫ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት አግኝቷል።
በተለይም በሀዋሳ በተደረገው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ከዚህ በኋላም ውሳኔው ወደ ውጤት ይቀየር የሚለው ጉዳይ ተደጋጋሚ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች እና እህት ድርጅቶች ጥያቄ ሆኖ መቀጠሉን ድርጅቶች በተደጋጋሚ ከሚሰጡት መግለጫና ቃለ መጠይቅ ለመረዳት አያዳግትም። ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ለግንባሩ ጥንካሬና ለሀገሪቱ ካለው ፋይዳ አንፃርም ኢህአዴግ በሀዋሳ ከተማ ባካሄደው 11ኛው ጉባኤ ላይ ውህደቱ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል። እኛም በአካል ባንገኝም እንደማንኛውም ዜጋ ትዕይንቱን በሚዲያ ተከታትለናል። ታዲያ አራቱም የኢህአዴግ ድርጅቶች በጋራ በኢህአዴግ ውህደት ላይ በጋራ ከወሰኑ በኋላ ውህደቱ አሁን ለምን በአንዳንድ ወገኖች ተቃውሞ ገጠመው የሚለውን ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል።
በጉዳዩ ዙሪያ በአንዳንድ ወገኖች የሚወጡ መግለጫዎች መረር ያሉና ውህደቱ ሀገርን የመበታተን አደጋ አለው የሚል መልዕክትን ያዘለ ነው። ‹‹በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተበራከቱ፣ ጥፋት በጥፋት ላይ እየተደራረበና የጥፋቱ ከፍተኛ መጠን በየቀኑ እየጨመረ ወደ ከፋ አገር የመበተን ደረጃ ደርሷል የሚለው የኮሚቴው መግለጫ፣ አደጋው ወደከፋ ደረጃ እንዲሄድ እያደረገ ካለው አንዱ ምክንያት የፓርቲ ውህደት ለመፈጸም እየተደረገ ያለው የችኮላ እንቅስቃሴ ነው›› የሚል መግለጫ መውጣቱን እናስታውሳለን። ለመሆኑ ከ5ተኛው ደርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ ሲታሽ የመጣን ጉዳይ ዘገየ ሊባል ካልሆነ በስተቀር በምን መመዘኛ ነው የተቻኮለ ሊባል የሚችለው።
እንደውም ኢህአዴግ መወቀስ ካለበት ይህን ሁሉ ዓመታት ጉዳዩን ችላ ብሎ በመዘግየቱ ነበር። የብሶተኞችን ጩኸት ቀምቶ ነው እንጂ አጋር ድርጅቶችን ባገለለ መልኩ ይህን ሁሉ ዓመታት ብቻዬን አስተዳድራለሁ ብሎ አግላይ አካሄድን መከተሉ ሊያስወቅሰውም ይገባ ነበር። ስለሆነም የአሁኑ ውሳኔ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር የተዋከበበት መንገድ ለእኔ አይታየኝም።
ውህደቱ ያስጨነቃቸው አካላት ለምን ይህን ያህል መቃወም አስፈለጋቸው ብለን ስንጠይቅ የለውጥ አመራሩን ህዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣት የሚደረግ እሩጫ ሆኖ እናገኘዋለን። ውህደቱ ህብረ ብሄራዊነትን ይደፈጥጣል፤ አሀዳዊ መንግስትን ያነግሳል የሚሉ ከጉዳዩ ጋር አብረው የማይሄዱ አሉባልታዎች ሲሰነዘሩ ይደመጣል። በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ባለፉት 27 ዓመታት ሲተገበር የቆየው ፌዴራሊዝም ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር አሀዳዊ ባህሪ የነበረውና ከአንድ ማዕከል በሚወርድ የዕዝ ሰንሰለት አድርግ አታድርግ የሚሉ ቀጭን ትዕዛዞች በሁሉም ክልሎች ሲተገበሩ ቆይተዋል።
ስለዚህም በምንም አይነት መልኩ ከቀድሞው በከፋ መልኩ የጌታና የሎሌ ግንኙነት ሊፈጠር እንደማይችል እየታወቀ እና ይደረግም ቢባል አሁን ካለው የለውጥ አስተሳሰብና ከህዝቡ ንቃተ ህሊና አንጻር ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልጽ ሆኖ ሳለ ይህንን አመክኒዮ ይዞ መቅረብ ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኘሁትም።
ይልቁንም የኢህአዴግ ውህደት በሀገሪቱ ለ27 ዓመታት ያህል ሰፍኖ የቆየውን የአዛዥ ታዛዥ ድራማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ የሚያደርግና የሴራ ፖለቲካ አራማጆችን ግብዓተ መሬት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለአንዳንዶች ላይዋጥ ይቸላል። የሆኖ ሆኖ ግን የኢህአዴግ ውህደት ላለፉት 27 ዓመታት ከፖለቲካ መድረኩ ዕርቀውና የበይ ተመልካች ሆነው የቆዩትን የአፋር፤ የሶማሌ፤ የሀረሪ፤ የቤኒሻንጉልና የጋንቤላ ህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህም ውህደቱ ኢትዮጵያዊነት በበለጠ መሰረት እንዲይዝና ሁሉም በእኩል መጠን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ኢህአዴግ የጀመረውን የቤት ስራ በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።
በኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙ አባል ፓርቲዎችም ድንጋይ ከመወራወር ወጥተው ህዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል። ወደድንም ጠላንም ይህችን ሀገር እያስተዳደረ የሚገኘው ኢህአዴግ የተባለው ፓርቲ በመሆኑ ጉዳዩ ከፓርቲ መጠላለፍ ወጥቶ ህዝብንና ሀገርን መሰረት ባደረገ መልኩ በውይይትና በምክክር ችግሮችን መፍታት ሀገርን ከሚያስተዳድር ፓርቲ የሚጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
መምህር ይስማው ኃይሌ- ከቤኒሻንጉል