ስትሮክ የሚባለው በሽታ ከልብ ህመም ቀጥሎ የሰው ልጅን ህይወት በመቅጠፍ በ2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እና የሰውን አካል ጉዳተኛ በማድረግ ደግሞ 1ኛደረጃ ላይ ይገኛል። በአገራችን ውስጥ የበሽታው ስርጭት ምን ያህል እንደሆነ እምብዛም ባይታወቅም በየቀኑ ሆስፒታል ውስጥ ለመታከም ከሚመጡት ህመምተኞች እና ለሞት ከሚዳረጉት ውስጥ በዚህ በሽታ የተጠቁት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ከሞት የሚተርፉትም ለኣካል ጉዳት የመጋለጥ ዕድላቸውም በዚሁ መጠን የሰፋ ነው።
ይህ በሽታ የደም አንጎል መርጋት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአንጎል ውስጥ ከሚፈሰው ደም የተነሳ የሚመጣ በሽታ ሲሆን አጠቃላይ ስሙ ስትሮክ ተብሎ ይጠራል። ይህ በሽታ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮችን የሚያጠቃ፣ በአንጎል ውስጥ ደም በትክክል እንዳይዘዋወር በመከልከል የተለያዩ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው። ይህ የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ የሚቋረጠው ከላይ እንደተገለፀው በሁለት መንገዶች ነው።
ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው (80% ስትሮክ የሚያመጣው)፣ ደም በአንጎል የደም ስሮች ውስጥ በመርጋት በአንጎል ውስጥ የሚገኙ ቀጫጭን ደም ስሮች ሲዘጉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን የደም ስሮች ሲጎዱ ደም አንጎል ውስጥ ይፈሳል፤ በዚህም ምክንያት ደም ወደፈለገበት ቦታ መዘዋወሩን ሲያቆም በሽታው ይከሰታል። ይህ የስትሮክ በሽታ በሁለት መንገዶች ይምጣ እንጂ የሚያሳያቸው ምልክቶች ተመሳሳይ በመሆናቸው ጠቅለል አድርገን ለማየት እንሞክራለን።
ለዚህ የስትሮክ በሽታ እንድንጋለጥ የሚያደርገን ምንድ ነው?
ለዚህ በሽታ የሚያጋልጡ ወይም የመያዝ እድልን የሚጨምሩ ነገሮች ተለይተው የሚታወቁ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።
– የደም ግፊት መጨመር፡ ለስትሮክ ከሚያጋልጡ በሽታዎች ወይም ሁኔታዎች ውስጥ ዋነኛ የሆነው የደም ግፊት መጨመር ነው። ስለትሮክ ስናስታውስ ወይም ስናወራ ስለ ደም ግፊት መናገርም ግዴታ የሚሆነው ለዚህ ነው። የደማችን ግፊት እየጨመረ በሄደ ቁጥር በስትሮክ የመያዝ ዕድል ከፍ እያለ ይሄዳል። ለዚህም የመጀመሪያው መፍትሄ የደም ግፊት በሽታ ያለብን እና የሌለብን መሆኑን ምርመራ በማድረግ መለየት ሲሆን ያለብን ከሆነ ደግሞ በቂ ህክምና በማግኘት ችግሩን መቆጣጠር ግድ ይለናል።
የደም ግፊት በሽታ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ይህ በሽታ የሚያጠቃቸው የደም ግፊት በሽታ እያለባቸው ህክምና ያላገኙ እና የሚሰጣቸውን የደም ግፊት በሽታ መድሃኒትን ያቋረጡ ወይም በትክክል የማይወስዱ ታማሚዎችን ነው። አንዳንድ ሰዎች የደም ግፊት በሽታ ያለባቸው መሆኑን የሚያውቁት የደም ግፊት በሽታው ለስትሮክ በሽታ ካጋለጣቸው በኋላ ነው። ስለዚህ በደም ግፊት ከመታመማችን በፊት የደማችንን ግፊት የማስመርመር ልምድ መኖር ከስትሮክ በሽታ ብቻ ሳይሆን በደም ግፊት ምክንያት የሚመጡብን ሌሎች በርካታ በሽታዎችን ለመከላከል ይጠቅመናል።
– ከተፈለገው በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት መኖር እና የአካል እንቅስቃሴን አለማድረግ። እነዚህ ሁለቱም በራሳቸው ለስትሮክ በሽታ የሚያጋልጡ ሲሆኑ በተጨማሪነትም የደም ግፊት በማጣትም ይታወቃሉ።
– ለዚህ በሽታ የሚያጋልጡ ሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ፡ ሲጋራ ማጨስ፣ በሰውነት ውስጥ ስብ ከተፈለገው መጠን በላይ መከማቸት፣ ከመጠን በላይ የአልኮል/አስካሪ መጠጦችን መጠጣት፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ በሽታ እና በስትሮክ በሽታ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ዝምድና መኖር ነው።
– እድሜ፡ የሰው እድሜ እየጨመረ በሄደ መጠን በዚህ የስትሮክ በሽታ የመያዝ እድል እየጨመረ ይሄዳል። በዚሁ መሰረት እድሚያቸው ከ55 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ የመያዝ እድላቸው እድሚያቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ ነው።
የስትሮክ በሽታ ሲይዝ ምንምን ምልክቶችን ያሳያል?
ከዚህ በሽታ ምልክቶች ከሰው ሰው ይለያያሉ። በዋነኝነት ግን ስትሮክ ብዙ ጊዜ ከሚታወቅባቸው ምልክቶች ውስጥ፡ የሰውነት ክፍል በአንድ በኩል መንቀሳቀስ አለመቻል (ሽባ መሆን)፣ ወዲያውኑ መናገር አለመቻል፣ አስቀድሞ ከባድ የሆነ የራስ ምታት ስሜት መሰማት፣ ሽንት እና ሰገራ መቆጣጠር አለመቻል፣ ማስመለስ፣ አፍ ወደ አንድ በኩል መጣመም እና የመሳሰሉት ናቸው። ይህ በሽታ ቀስ በቀስ እየበረታ የሚመጣ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ በድንገት የሚከሰት በሽታ ነው። አንጎል በስፋት የተጠቃ ከሆነ ወዲያውኑ (ሀኪም ቤት ሳይደርሱ) ህይወት ሊቀጥፍ ይችላል።
ይህን በሽታ መከላከል ይቻላልን?
ማንኛውም በሽታ ለበሽታው የሚያጋልጡንን ነገሮች ካወቅን የመከላከያ ዘዴዎቹንም በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። በዋነኝነትም ከታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሽታውን መከላከል ይቻላል።
– የደም ግፊትን በየጊዜው መለካትና ችግሩም ካለ መታከም
– ሲጋራ አለማጨስ እና ከሚያጨሱ ሰዎች መራቅ
– የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፡ ይህንን ስንል ስፖርት ቤት በመሄድ ብቻ ሳይሆን በመራመድ፣ ሶምሶማ በማድረግ፣ ገመድ መዝለል እና ሌሎች ቀላል የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ችግሩን መከላከል እንችላለን። በሳምንት 4 ቀናት ወይም ከዚያ በላይ የስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል።
– የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሰውነት ክብደትን መቀነስ ያስፈልጋል። ለዚህም በዋነኝነት የሰውነት እንቅስቃሴ ማዘውተር፣ የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል። በሌላም በኩል በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ስብ ከፍ ያለ ከሆነ ወደ ሀኪም በመሄድ መታከም ለስትሮክ ከመጋለጥ ይታደጋል።
– የስኳር በሽታ ያለብን ከሆነ መታከም::
– አልኮል አለመጠጣት; የምንጠጣ ከሆነ ደግሞ አሳንሶ መጠጣት እና የመሳሰሉትን በማድረግ ከስትሮክ እራሳችንን መከላከል እንችላለን።
ይህ በሽታ እንዴት ይታከማል? ምን ያህልም ተስፋ አለው ?
የዚህ በሽታ ህክምና በስትሮክ አይነት የሚለያይ ነው። ደም አንጎል ውስጥ መፍሰስ እና ደም አንጎል ውስጥ መርጋትን መሰረት በማድረግ ህክምናው የሚሰጥ የህክምና አሰጣጥ ዘዴውም የአንጎል ራጅ (Brain CT Scan) በሚባል ተለይቶ የሚታወቅ ነው። ይህ የጤና ባለሙያ ድርሻ ሲሆን በአጠቃላይ በአገራችን ውስጥ ለስትሮክ በሽታ የሚደረገው ህክምና በሽታውን የሚያድን ሳይሆን በሽተኛውን ለመንከባከብ (Supportive Care) የሚያስችል ነው።
ማለትም ይህ በሽታ እንደገና እንዳይከሰት የሚደረግ ህክምና ነው። ይህም ህክምና የደም ግፊትን በጊዜው መቆጣጠር፣ መንቀሳቀስ የተሳነውን የአካል ክፍል (ሽባ በሆነው) በማገዝ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ (physioteraphty) እንዲሁም የተጎዳው አካል ባለመንቀሳቀሱ ምክንያት ደም እንዳይረጋ መድሃኒት መስጠት፣ ሽንት የማይወጣ ከሆነ የሽንት ቱቦን በማድረግ በዚያ በኩል እንዲሸና ማድረግ፣ ኢንፌክሽን እና በዚህ ምክንያት የሚመጣውን የሳምባ በሽታ ለመከላከል እና የመሳሰሉትን ድጋፎች ማድረግ ነው። ከዚህ በላይ ያሉት ህክምናዎች ይህንን በሽታ ወደኋላ መመለስ እና መዳን አይችሉም።
እንደ አስትሮኩኣይንት ለረጅም ጊዜ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። እስትሮኩ በድጋሚ እንዳይከሰት የሚረዱ መድሐኒቶችን በኣግባቡ መውሰድ እና ሕክምና ክትትልም አለማቋረጥ ከበሽታው ለማገገም ይረዳል:: ባጭሩ የስትሮክ ህክምና ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ መከላከል በጣም ተመራጭ ነው።
1. Harrison Principles of Internal Medicine: Cerebrovascular Disease.
2. American Stroke Association: Stroke Risk Factors You Can Control, Treat and Improve
3. Mayo Clinic: Overview of Stroke, Signs and Symptoms of Stroke
4. World Health Organization (WHO): Cerebrovascular accident
ዶ/ር ጉርሜሳ ሂንኬሶ
አርሲ ዩኒቨርሲቲ
ሆራ ቡላ
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012