በቀይ ደመ ግቡ መልካቸው ላይ ትህትናቸው ታክሎበት ሳቢ ገጽታን ተላብሰዋል። ሬስቶራንታቸውን አፄ ኃይለስላሴ ብለው ከመሰየማቸው ጋር ተያይዞ አንዳንዶች መልካቸው የንጉሱን ይመስላል በሚል የልጅ ልጅ ወይንም የቤተሰብ ዝምድና እንዳላቸው ይጠይቋቸዋል። እርሳቸው ግን ምንም ዝምድና ባይኖራቸውም የንጉሱን ሥም ለማንኛውም አገልግሎት መጠቀም አይቻልም የሚለውን የተለያዩ ቢሮዎች በህግ ያልጸደቀ ጥያቄ ላይ ብርቱ ክርክር እና ግፊት አድርገው በስሙ እየተጠቀሙበት ይገኛል።
ወይዘሮ ብርሃኔ ዘውዱ ይባላሉ። ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ ናቸው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ ከፍ ብሎ በሚገኘው አልጋወራሽ ግቢ በሚሰኘው አካባቢ ነው ያደጉት። በልጅነታቸው የቤት ውስጥ ስራ አይበዛባቸውም ነበርና ከጓደኞቻቸው ጋር በሰፊው ተጫውተው ማደጋቸውን ያስታውሳሉ።
ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ደግሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለመቅሰም በወቅቱ አምሃ ደስታ በተባለው በአሁኑ ስሙ ሸሮሜዳ ትምህርት ቤት ገብተዋል። ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሳለ ግን እድሜያቸው በግምት 10 እንደደረሰ አብዮቱ ፈነዳና የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት ወረዶ ደርግ ተተካ።
ወቅቱ የግርግር ቢሆንም ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ቀጥለዋል። ይሁንና በትምህርት ቤት ቆይታቸው ግን ወደ ሙዚቃው ማድላታቸውን ያስታውሳሉ። በትምህርት ቤቱ በሚገኘው የሙዚቃ ክፍል ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ማሳለፍ በመምረጣቸው የሚመለከቷቸው ተማሪዎች አንድ ቀን ቤታቸውን አንኳኩተው ለቤተሰባቸው በመናገራቸው ወይዘሮ ብርሃኔ ከፍተኛ ቁጣ አስተናግደዋል።
አባታቸውም ‹‹አዝማሪ ልትሆኚ ነው ወይ?›› በሚል ድጋሚ ወደሙዚቃ እንዳይሳቡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው። በተጨማሪም ቤት ውስጥ ሲሆኑ የሚወዱትንም ማንጎራጎር እንዲተውት በመታዘዛቸው ወይዘሮ ብርሃኔ ወደ ትምህርታቸው ብቻ ማድላታቸው አልቀረም። ስምንተኛ ክፍልን አልፈው ወደ ዘጠነኛ ሲሸጋገሩ ግን ፍጹም ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ።
ወላጆቻቸው ያመጡላቸውን ባል እንዲያገቡት ተጠየቁ። በወቅቱ ስለቀረበላቸው ባል ማንነት እና ምንነት የማያውቁት ወይዘሮ ብርሃኔ ግን አይሆንም ብለው መከላከሉን አልፈለጉም። በቤተሰብ አማካኝነት የመጣው ትዳር በ16 ዓመታቸው አዲስ የሕይወት መስመር ውስጥ ከተታቸው። ባለቤታቸው ደግሞ በህክምና ሙያ ውስጥ የነበሩ እና ኤርትራ አሰብ የሚሰሩ ሰው በመሆናቸው ወይዘሮ ብርሃኔም ትምህርታቸውን አቋርጠው ትዳር መስርተው ወደ አሰብ አመሩ።
አሰብ ያለውን ሙቀት ግን በቶሎ ሊላመዱት አልቻሉም። እናም በየጊዜው አዲስ አበባ እየተመላለሱ መኖሩን ምርጫቸው አድርገውት ነበር። በወቅቱ ደግሞ ያቋረጡትን ትምህርት በቀድሞው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምረው እስከ 12 ድረስ ተምረው አጠናቀቁ።
በመቀጠልም የታይፒስትነት ሙያ ትምህርትን በዚያው መነን ትምህርት ቤት ተከታትለው ወደ ስራ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ሠርተፍኬት ተቀብ ለዋል። ከስልጠናው በኋላ ወዲያውኑ በባህር ትራንዚት ድርጅት ውስጥ የገቢ እቃዎች ክፍል በታይፒስትነት ተቀጥረው ቀድሞ ወደሚያውቋት አሰብ ተመለሱ።
በአሰብም ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ኤርትራ እራሷን ችላ ሀገር ስትሆን በ1983 ዓ.ም በተፈናቃይነት ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ተገደዱ። በወቅቱ ልጆች ተወልደው ነበርና በመዲናዋ በነበራቸው ቆይታ ከቅጥር ስራ ርቀው ህጻናቶችን በማሳደግ ተጠምደው ነበር።
ከጥቂት ጊዜያት ቆይታ በኋላ ግን ልጆቻቸውን በጎን እየተንከባከቡ በአንድ የጤና ተቋም ውስጥ ስራ በማግኘታቸው ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ። ስራው ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ቪዥን በተባለ ክሊኒክ ውስጥ እንግዳ ተቀባይነትን እና የሂሳብ ስራን ያጠቃለለ ነበር። ሳር ቤት አካባቢ በሚገኘው ክሊኒኩ ውስጥ ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል። በነዚህ ዓመታት ሲሰሩ ደግሞ በምሳ ሰዓት ላይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ሻይ እና ቡና የምታቀርብ ደንበኛቸው ጋር በመሄድ ይጠቀሙ ነበር።
ልጅቷ አንዲት ኮንቴይነር ሱቅ ውስጥ ተከራይታ ነበር የምትሰራው። እናም አንዳንዴ ቢሮ ድረስ ሻይ ታመጣላቸዋለች። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ሻይ አምጥታ ሂሳቡን እንኳን በአግባቡ አትሰበስብም ነበርና እንዴት ተከራይታ ያዋጣታል እያሉ እራሳቸውን ይጠይቃሉ። የልጅቷን ሂሳብ በአግባቡ ያለመውሰድ ስንፍና የተመለከቱት ወይዘሮ ብርሃኔ እርሷ በአግባቡ ሳትቆጣጠር ካዋጣት እኔ ደግሞ በአግባቡ ሰርቼና ገንዘቤን ተቆጣጥሬ ብሰራ በተሻለ ሁኔታ መነገድ እችላለሁ በማለት ወደ ግል ስራ መሳባቸውን ይናገራሉ።
የክሊኒኩን ስራ በመልቀቅ አንድ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንዳለባቸው የወሰኑት ወይዘሮ ብርሃኔም አዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ ሱቅ ተከራይተው አነስተኛ ጁስ ቤት ከፈቱ። በወቅቱ ለመነሻ የሚሆናቸውን ገንዘብ ከባለቤታቸው ላይ ተበድረው በ10ሺ ብር መነሻ ‹‹ሀ›› ብለው ንግድን መምራት ጀመሩ።
በጁስ ቤታቸው ውስጥ በመጀመሪያ ከቤት ያገኙትን እንግዳ ማስተናገጃ ወንበር እና ጠረጴዛ እንዲሁም አንዳንድ ቁሳቁሶች ይዘው ነበር ብቻቸውን የሚሰሩት። ከባለቤታቸው ባገኙት ብድርም ለቤት ኪራይ አንድ ሺ ብር ከፍለው አንድ ፍሪጅ ገዝተው ነበር። ፍራፍሬዎችንም ገዝተው በአነስተኛ ማሽን እየፈጩ ለተጠቃሚው ማቅረቡን ተያያዙት። እናም አንድ ሁለት እያለ በየቀኑ ጁስ ተጠቃሚው ቢመጣም የአካባቢው እንቅስቃሴ ግን አነስተኛ በመሆኑ ብዙ ደንበኛ ሊመጣላቸው እንዳልቻለ ያስታውሳሉ።
በወር የሚያተርፉትም ገንዘብ ተጠራቅሞ የቤት ኪራይ እና አንዳንድ ወጪዎችን ከመሸፈን ባለፈ ይሄ ነው የሚባል ትርፍ ባለማምጣቱ የንግድ ቤቱን በመጠኑ ለመቀየር አሰቡ። ለ10 ወራት እንደሰሩም ወይዘሮ ብርሃኔ ጁስ ቤቷን ወደ ምግብ እና የጀበና ቡና ቤት ቀየሯት። ቀለል ያሉ ወጪዎችን የሚጠይቁ ምግቦችን በማዘጋጀት ደንበኞቻቸውን ይጠብቁ ጀመር። አንድ የሻይ ማሽን ተከራይተው የንግድ ቤታቸውን ሬስቶራንት አደረጉት። ይሁንና እሱም አላዋጣ ቢላቸው ማሽኑን ወደመጣበት መልሰው ምግብ መስራቱ ላይ አተኮሩ።
ከንግድ ቤታቸው ጀርባ ያሉ እንጀራ አቅራቢዎች ዘንድ በመሄድ አራትም አምስትም እንጀራ እየገዙ ምግብ እያቀረቡ ደንበኛ ለመሳብ ሞከሩ። ቀስ በቀስም የምግቡን ጥራት እና ጣዕም የተረዱ ሰዎች በብዛት የሚጎበኙት ቤት ለመሆን ወራቶችን ብቻ እንደጠበቁ ወይዘሮ ብርሃኔ ይገልጻሉ።
ስጋ ጥብስ እና የተለያዩ ምግቦችን በማቅረባቸው በርካታ ደንበኞች ይጎርፉ ጀመር። በመሆኑም ታዋቂነታቸው ሲስፋፋ ሬስቶራንታቸው በየቀኑ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ምግብ የሚያቀርብ ቤት ሆነ። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ደግሞ አንድ አስተናጋጅ እና ሶስት የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎችን ቀጥረው ሥራቸውን አሰፋፉ። በተለይ በምሳ ሰዓት በአነስተኛዋ ቤት ውስጥ የሚሰበሰበው ደንበኛ ለስራቸውም ስንቅ እየሆናቸው የተለያዩ ምግቦችን ማቅረባቸውን ቀጠሉበት። ስራው ሲጠናከርም አንድ ሰራተኛ ቀጥረው መከወኑን ተያያዙት።
ከተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች በምሳ ሰዓት የሚጎርፉ ሰዎች ዋነኛ የምሳ ሰዓት ደንበኛቸው ነበሩ። ከምግቡ በተጨማሪ ደግሞ የጀበና ቡና እና ሻይ በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደግ ጀመሩ። ይሁንና ንግዳቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተከራዩትን ቤት የመንገድ ግንባታ ስለሚነካው ቦታ መቀየሩ የግድ ሆነባቸው።
አከራያቸውም አስፓልት ዳር የነበረው ቤት ሲፈርስ ግቢያቸው ውስጥ ቦታ ፈልገው እንዲሰሩ ለወይዘሮ ብርሃኔ ፈቀዱ። ወይዘሮዋም ዳስ ጥለው በመኖሪያ ግቢው ለመስራት ቢሞክሩም ልክ እንደመንገድ ዳሩ ያህል ደንበኛ ግን አልመጣ አላቸው። ይባስ ብሎም ወደ ኪሳራ ማምራት ጀመሩ። ለስድስት ወራት ዳስ ውስጥ ከነገዱ በኋላ ስራውን አቁመው ወጡ።
ወደ ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ሰፈር በማቅናት ለሬስቶራንት የሚሆን ሰፋ ያለ ቤት ሲያፈላልጉ ቆዩ። ምስካየ ህዙናን መድኃኒያለም ገዳም በተማሪዎቸ ኳስ ሜዳ ትሪቡን ስር ያለውን የንግድ ቤት ለኪራይ ጨረታ ሲያወጣበት ልሞክረው ብለው ተሳተፉ። በወቅቱ በስምንት ሺ ብር ጨረታውን ቢወዳደሩም አሸናፊ መሆን ግን አልቻሉም ነበር።
ይሁንና የንግድ ቤቱን ለረጅም ጊዜ ማንም ሳይገባበት ተዘግቶ ይመለከቱታል። እናም የገዳሙ አስተዳዳሪዎቸ ዘንድ ቀርበው ሊከራዩት እንደሚፈልጉ ነግረው ቤቱን በድጋሚ ጎበኙት። የንግድ ቤቱ ለስራ ምቹነት እና ያደጉበት መንደር አካባቢ በመሆኑ እጅጉን ወደውታል። በስምንት ሺህ ብር ቀድሞ የተጫረቱበትን የገመቱትን ቤት በ14 ሺ 300 ብር እንዲከራዩት ጥያቄ ሲቀርብላቸው አላቅማሙም ነበር።
ስድስት ኪሎ አካባቢ የጀርመን ባህል ማዕከል /ጎተ ኢንስቲትዩት/ መግቢያ ላይ የሚገኘውን ቤት አሰማምረው በፍጥነት ወደ ሬስቶራንትነት ቀየሩት። በየቀኑም ከስጋ እና በአትክልት የተሰሩ ምግቦችን በማቅረብ በአካባቢው መታወቅ ችለዋል። የሬስቶራንታቸውንም ስም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ብለው የሰየሙት ወይዘሮ ብርሃኔ ቀስ በቀስ ገበያው እየደራላቸው በትርፍ ላይ ትርፍን መጨመሩን ተያያዙት።
በአጭር ጊዜም ጠቀም ያለ ገቢ በመሰበሰባቸው ከ200 ሺ ብር በላይ በማውጣት ከቆዳ የተሰሩ ያማሩ የእንግዳ ወንበሮችን እና አዳዲስ መገልገያዎችን በመግዛት ሬስቶራንቱን ዘመናዊ አድርገውታል። በተለይ የውስጥ ዲዛይኑን በማሳመር ለገበያ ሳቢ እንዲሆን አድርገው ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። ሬስቶራንታቸውም በአንድ ጊዜ ለ60 እንግዶች የማስተናገድ አቅም እንዳለው ይናገራሉ።
አሁን ላይ በሬስቶራንታቸው እርሳቸውን ጨምሮ 10 ሠራተኞች አሉ። ለሬስቶራንታቸው የሚሆነውን ግብዓት ደግሞ ግማሹ በቤታቸው ይዘጋጃል። በየቀኑ በቤታቸው እንጀራ ያስጋግራሉ። ከአትክልት ተራ ደግሞ ለጁስ እና ለተለያዩ ገበታዎች የሚሆኑትን ምርቶች በመሸመት አብረው ከባለሙያዎች ጋር አብስለው ያቀርባሉ። ከ10 ሺ ብር የባለቤታቸው ብድር የተነሱት ወይዘሮ ብርሃኔ በየጊዜው የቤት ወጪያቸውን ችለው በመቶ ሺዎች ማትረፍ ችለዋል።
ህልማቸው ትልቅ የሆነው ወይዘሮዋ የተከራዩትን የንግድ ቤት ቢሆንም ቤቱን በማሻሻል አንድ ፎቅ ወለል ጨምረውበት ሊገነቡት አቅደዋል። ለዚህ ደግሞ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋቸዋል እናም ግማሹም በብድር ለማሟላት ነው ሃሳባቸው።
ማንም ሰው በውስጡ ይህን ብሰራ ብሎ የሚያስበው ንግድ ይኖረዋል የሚሉት ወይዘሮ ብርሃኔ ማሰብ ብቻ መተግበርም ለስራ ዋነኛው አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ገንዘብ ሳይኖረኝ እንዴት እጀምረዋለሁ ብሎ የሥራ እቅድን መተው ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
እኔ በብድር ጀምሬ ብዙ እጥፍ እንዳተረፍኩ ሁሉ ሌላውም ሰው በትንሽ ገንዘብ ንግዱን ቢጀምረው ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም ይላሉ። በተለይ ሴቶች ያላቸውን ጥቂት ገንዘብም ቢሆን ተጠቅመው ውጤታማ የሚሆኑበትን ድፍረት በመላበስ ቢሠሩ ለተሻለ ህይወት መብቃት ይችላሉ የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
ጌትነት ተስፋማርያም