ባለፈው ሳምንት ፅሁፌ፣ ሚስቶች በባሎች ላይ የማይወዷቸውን ነገሮች ምንነት ለመዳሰስና ለማሳሰብ ሞክሬ ነበረ። በዚህኛው ሳምንት ጽሑፌ በዚያኛው ሳምንት ያልኩትን ግልባጭ ላነሳባችሁ አልፈልግም። ይሁንናም ሁለቱም የሚጋሩት አዳማዊ ባህሪ አለና፤ ሁለቱም ሥጋ ለባሾች ናቸውና የሚወራረሱት ነገር አይጠፋም።
ውድ ባል ሆይ! ወደ ትዳር ዓለም የመጣኸው በእውነት ከእርሷ ጋር መኖር እንደሚያስደስትህ አምነህ ግን ከስሜት በላቀ እውነት ተገፍተህ ከሆነ እድለኛ ነህ። በዚህ ሳቢያ ብዙዎቹን ችግሮች በሚያስደንቅ ትዕግስትና ቻይነት ልታልፋቸው ብርታት ይሆንሃልና መልካም ነው ። ይሁንናም በአብሮ መኖር ውስጥ ከእርሷ የምትጠብቃቸው መሰረታዊ እውነቶች አሉና እንዲህ ብለህ አስረዳት።
ውዴ ሆይ! የሚከተሉትን ባህሪያዊ ሁነቶች አብዛኛዎቹን ካንቺ ጠብቃለሁ።
ባደረግሺልኝ ነገሮች ከቶውንም በሰው ፊት አትገበዢ። ይህንና ያንን ያደረግኩልህ በዚህና በዚያ ምክንያት ነው፤ እያልሽ በሶስተኛ ሰው ፊት አትናገሪ። ለመናገር የሚያስገድድሽ ነገር እንኳን ቢገጥምሽ በትህትና ሌላ ሰው ያደረገለትን ነገር አስታውሼ ያደረግሁት ነው እንጂ፤ የራሴ አይደለም በይ።
በምንም ምክንያት ልትዋሺኝ አትሞክሪ። ያጋጠመሽ ነገር ከፈቃድሽ ውጭ በክፉ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንናም ጉዳዩን በእውነት ሳትቀንሺና ሳትጨምሪ ንገሪኝና ለጉዳዩ በጋራ መፍትሔ እንፈልግለት።
የኔ የሆነው ነገር ያንቺ ነው ግን አንዳንድ ነገሮች ግን ፈቃዴን ይጠይቃሉና ጠንቀቅ በይልኝ። ለምሳሌ ያህል ማስታወሻዎቼ፣ ጽሑፎቼ፣ ፎቶዎቼ፣ ሽልማቶቼ ፤ ከምሰራበት ሥፍራ ለስራ አገልግሎት የተሰጡኝ ንብረቶች፣ ወዘተ…. እስቲ ልንገረውና ላውሳችሁ ወይም ላበድራችሁ በይ እንጂ ለጠየቁሽ ሰዎች ካደረግሽ በኋላ አትንገሪኝ።
ከዝምድና ውጭ በሆኑ ሰዎች ላይ ጥንቃቄ ይኑርሽ። ዘመድ ያልሆንን ሰው በተለይም ጾታው ወንድ የሆነን ሰው ስታስተዋውቂኝ ምንም ዓይነት የአቀራረብ ሆነ የአነጋገር አሳሳች ለውጥ ላይብሽ አልፈልግም። በጨዋ አቀራረብ፣ በጨዋ ቋንቋ አናግረሽው እንድትጨዋወቱ ነው፤ የምሻው። የባልና ሚስትነት ድንበራችንን የሚያደፈርስ ቃልም ቅብጠትም መፍቀድ ይቸግረኛልና፣ ራስሽን ግዢ።
ኦቴሎ ላይ (ዊሊያም ሼክስፒር ጽፎ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በውርስ የተረጎመው ነው) አንድ ቦታ ላይ፡-
የኢያጎ ሚስት ኤሚሊያ የኦቴሎን ሚስት ዴዝዴሞናን ታገኛትና ፣ “እመቤቴ ፣ ወንዶች እኮ “ከርሳሞች ናቸው” ይበሉን ይበሉንና ሲጠግቡ ባይፈልጉም እንኳን ሌላ ሰው የወደደን ሲመስላቸው ይቀናሉ። ኦቴሎ ላይ ይህን ጠባይ አላየሽበትም ?” ስትላት ፣ “የኔ ኦቴሎ ይህን ዓይነት ፀባይም አልፈጠረበት፤ እንዲያውም አማልክቱ ከውስጡ አሟጠው ለት ነው መሰለኝ ፤ አላየሁበትም።” ትላታለች።
ኤሚሊያ ታዲያ፣” ቅናት መቼ በአማልክት ቁጣና ፈቃድ ሆነ ፤ ያለፍሬ ተጸንሶ ያለማህፀን የሚወለድ ጭራቅ እኮ ነው!” ትላታለች። እና ለማስቀናት ብለሽም ባይሆን በምንም ምክንያት ለቅናት በር የሚከፍቱ ነገሮችን ባለማድረግ ተባበሪኝ። ያኔም ጤናማ ትዳር ይኖረናል።
የአደጋ ጊዜ ተጠሪሽ እኔ እንጂ እናትሽ እንኳን አይደለችም፤ አንቺም ለእኔ። እቃ በወደቀ፣ መብረቅ በበረቀ፣ ቁጥር ”ካልዳኔ ድረስልኝ” እያልሽ በቤትና ቤተዘመድ መሐል የሌለ ስም አትጥሪ። ከዚህ ሌላ፣ በአስፈላጊ ሥፍራ የዋስ ፊርማ በሚያስፈልግበት ስፍራ ካንቺ የማስቀድመው ስም እንደሌለ ሁሉ ከእኔም የሚቀድም ስም እንደሌለ ተገንዘቢ። በመከራም ሆነ በህመም የተባለውን እንዳትረሺ።
አስቤ ያደርግኩልሽን በምስጋና ቋጪው። የመጠኑ መለያየት ምንም ዓይት ይሁን ውድ ይሁን ርካሽ የማይገኝ ይሁን የሚገኝ ነገር ሳደርግልሽ አነሰ ብለሽ ማንኳሰስ ፣ ገዘፈ ብለሽ ማጋነን ሳይኖር አመሰግናለሁ ማለት ብቻ በቂ ነው። በተረፈ ይህንን አረግሁ ብሎ ያንን ሰራሁ ብሎ ዝም ብለው አኮረፈ ብሎ ወሬ ማንዛረጥ ከመጣ ፣ ባላለቅስም አልስቅም፤ “ማርያምን” ይከፋኛል ።
የድሮውን ግንኙነት ማድነቅ አሁንን ማንኳሰስ መሆኑን አትርሺ። ከዚህ ጋብቻ በፊት የነበረውን ግንኙነት እያደነቅሽ ያሁኑን ቸል ማለት፣ አሁንን ማንኳሰስ ነውና ደጋግመሽ በማንሳት ልቤን አታቁስይው። ምናልባት በሞት ተለይቶሽም ከሆነ ልብሽን ከመቃብሩ በታች አድርጊው እንጂ ከመቃብር በላይና በታች የሆነ ልብ አያስፈልገኝም። ይህ የአድናቆት ስሜትሽ የሚገልጠው ካንተ ይልቅ የሞተው ይሻለን ነበረ፤ የሚል መልዕክት አለውና ጠንቀቅ በይ። በህይወት ካለ ደግሞ ጥሪውና “አጣሁህ እንጂ አላጣኸኝም” ብለሽ ንገሪውና ይውጣልሽ።
በግጭት ወቅት ነገር ከሚያባብስ ነገር ተቆጠቢ። በተለይ የችግሩ ምክንያት አንቺ ከሆንሽ ጉዳዩን በሰከነ ልብ እንድንፈታው ሁሉንም የማቃለያ ዘዴዎች ለመጠቀም ሞክሪ እንጂ ፣ ግጭቱን አባብሶ ወደ አስከፊ ውጤት የሚወስድ ቋንቋ ላለመናገር አንደበትሽን ተቆጣጠሪው።
“ድሮም ካንተ ጋር መግባባት አይቻልም።”
“የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ”
“አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው”
“የእምዬን እከክ ወደ አብዬ ልክክ” ወዘተ…የሚሉ ነገር አጋጋይ ተረትና ምሳሌዎችን በመጠቀም ነገር አታጋግሚ። ጉልበት ወደመጠቀም ገፍተሽ፤ ጡንቻ ራስ አትበይኝ።
ዘረኛነት ካለብሽ ቁርጡን በጠዋት ንገሪኝ። በምንም መለኪያ የጥፋቴም ሆነ የልማቴ ምክንያት የተወለድኩበት ዘር እንደሆነ አድርገሽ የነገርሽኝ እለት የኔና ያንቺ አህል ውሃ ያበቃለታል። ማንኛውም የሰው ልጅ አመልክቶ እንዳልተወለደ ሁሉ መርጦ አይጋባም፤ መንደርተኛ/ ዘረኛ ካልሆነ በስተቀር። የጋብቻችሁ ምክኒያቱ ፍቅር ካልሆነ መለኪያችሁም እርሱ ይሆንና ወደጎሳና ነገድ ጸብ ያወርዳችኋልና አደራሽን ዘረኛነት ካለብሽ ከውስጥሽ ግደይው። ዘረኛ ሰው፤ ላላዋጣበት አክሲዮን ድርሻ የሚጠይቅ ዋሾ “ማህበረተኛ” ነው። ከዚያ ቤተሰብ ለመወለድ ያዋጣሽው ንኡስ ህዋስ የለምና።
ውዷ ሆይ ! ውልደቴ፣ በምርጫ ቢሆን ኖሮ ጃፓናዊ/ ጀርመናዊ… ሆኜ ነበረ፤ የምወለደው። ገባሽ!? እንዲህ ስልሽም በተወለድሽበት ቤተሰብ ማንነት እፈሪ ማለቴ አይደለም፤ አትመኪ እንጂ። ከእኔና አንቺ የሚወለዱት የሰው ልጆች በሄዱበት የምድር ዳርቻ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ተጋብተው በማያውቁት ምድር፤ ባልጠበቁት ቋንቋ ውስጥና መስተጋብር ሊያልፉ እንደሚችሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራዎች እንጂ እኛ ጠፍጥፈን እንደጋገርናቸው ቂጣዎች ሆዳችን ውስጥ መልሰን የምናስገባቸው የእጅ ስራዎቻችን አድርገሽ እንዳታስቢያቸው። እኛ ከጌታ እረኞች ሆነንና ጠብቀን እንድናሳድግ ተሰጡን እንጂ እንዳላመጣናቸው ሁሉ መድረሻቸውን ልንወስንላቸው አልተፈጠሩምና አጥብበሽ ዓለምን አታሳያቸው። ምድር ሁሉ የእነርሱ ናትና !!ተባረኪልኝ ።
ሁሉ አማረሽ አትሁኚ! ወደገበያም ሆነ ወደጉባኤ ባለሁበትም ቦታ ሆነ በሌለሁበት ልትናገሪና ልታናግሪ ስትወጪ በአንደበትሽ ቁጥብ በአሰራርሽ ምጥን ስትሆኚ መልካም ይሆንልሻልና ሁሉን በአግባቡ አድርጊ። ሁሉን ልናገርና ሁሉን ላድርግ ባይ አትሁኚ። ልትናገሪ ስትፈልጊም አስፈቅደሽና አመስግነሽ ጀምሪ። ስትጨርሺም በአድናቆት ዝጊው እንጂ አትራቀቂ፣ አትዘባርቂ፣ አማረልኝ ብለሽ ያልተገባ ነገር ስትናገሪ በንግግርሽ እርዝማኔ ውስጥ ምስጢር ልታወጪ ትችያለሽና አስቢበት። ብዙ ሰዎችን ከመጉዳትሽም ብዛት አንቺንም ግምት ላይ ይጥልሻልና ።
አለኝ በምትይው ነገር አትመኪ፡- ባለን ንብረት፣ በያዝነው ገንዘብ፣ በዝናሽና ባገኘሽው ጊዜያዊ ክብርም ሆነ በውበትሽ አትመኪ። ሁሉንም ያገኘነው ከጊዜ በኋላ የመሆኑን ያህል ከጊዜ በኋላ ገንዘቡም ያልቃል፣ ንብረቱም ያረጃል፤ ዝናም ይረግባል፣ ውበትም ይረግፋልና በፍጹም በአንዳቸውም ነገር አትገበዢ። ያለፍሽበትን መንገድ ያሳለፈሽ እግዚአብሔር መሆኑን አትርሺ። በዕውቀትሽም ቢሆን ከቶውንም ሌሎች አልደረሱበትም ብለሽ በልዩነት አትኩራሪበት፤ አታቅራሪበት።
ገንዘብ ስታወጪም ሆነ ስታስወጪ ነትራካ አትሁኚ። ገንዘብን እንድንጠቀምበት እንጂ እንዲጠቀምብን በእጃችን አልገባምና ገንዘብ ስታወጪ፣ “ስቄ ያመጣሁት አይደለም” “ለማንም እና ለምንም አላወጣም” አትበይ። አልቅሰሽም ቢሆን እንኳን የተቀበልሺው ደስ ብሎሽ ልትጠቀሚበት ይገባሻል እንጂ፤ በስስት ራስሽን እየጎዳሽ ልትደብቂው አልተፈጠረም። ይልቅ መስጠት የሚወዱ ብዙ እረፍት ሲኖራቸው የሚወስዱ እንቅልፍ የላቸውምና ፤ ከሰው በግፍ ለመውሰድም አታስቢ ሲኖርሽም ለባሰበት ለመስጠት አታመንቺ። ይህም ማለት ግን በትኚው ማለት አይደለም፤ ገንዘብን ከሰው አታስበልጭ ማለት እንጂ። እንዲህ ስትሆኚልኝ ልቤ በሀሰት ትሞላለች፤ ካንቺ ጋር የኖርኩባቸውንም ቀኖች አመሰግናለሁ፤ ገና የምኖርባቸውን ቀናት እናፍቃለሁ።
እንባሽን መሳሪያ አታድርጊ፡ -የጠፉብኝንና የተጠራጠርኳቸውን ነገሮች ስጠይቅሽ በአግባቡ መመለስ እንጂ ለምን ተጠየቅሁ ብለሽ እንባሽን አታስቀድሚ። በእንባሽ ልትሸፍኚው የፈለግሽው ነገር እንዳለ ድጋሚ ስለምጠረጥር ነገሮቻችንን ያበላሽብናል። በቀጥታና ዓይኖቼን እያየሽ መልሺልኝ ። አላምንም ካልኩሽ የራሴ ጉዳይ ነው፤ በእንባሽ ማእበል ነገሮችን ለማስቆም መሞከር ግን አደጋ አለው። ሳትቆጪ በእርጋታ ሳታለቅሺ በቀጥታ መናገርን ተለማመጂልኝ። ያኔም አካሌን እርፍ ፤ ሃሳቤን ዝርግፍ አድርጌ አዳምጥሻለሁ፤ እንግባባለንም።
የምታስቢውን ላስብ የምትገምቺውን ልገምት እንደምችል አትጠራጠሪ፡- በምንም መለኪያ አያውቅም፣ አይደርስበትም፣ አይገለጽለትም፤ ብለሽ በምስጢር እኔ ሳላውቅ ምንም ነገር ለማድረግ አትሞክሪ። የገጠመሽን ክፉ፣ የሰራሽውን ቀሽምም ሆነ ያዋጣኛል ብለሽ አድርገሽ የወደቅሽበት ጉዳይ ካለ ሳትደብቂ ንገሪኝ። አንዳንዴ በሙከራሽ ያሸነፍሽበት ጉዳይ ቢኖርም እንኳን አንዳንዴ መልካም ዜናም ፣ የክፋት ያህል ያስደነግጣልና ቅድመ ፍንጭ ለመስጠት ሞክሪ። ከሌላ ሶስተኛ ወገን ሰምቼ የክፉውን እውነትነቱን ካረጋገጥኩ፤ የደጉንም በወሬ ከሰማሁ ፣ በቤቱ ውስጥ ደባል ሰው መሆኔን ስለሚያሳየኝ ልታጪኝ እንደምትችይ ገምቺ።
ይህን ሁሉ የምነግርሽ ፣ ስለምወድሽና ላጣሽ ስለማልፈልግ እንደሆነ አውቀሽ ተጠቀሚበት። ለማንም ያልሰጠሁትን ማንነቴን አሳልፌ የሰጠሁት ላንቺ መሆኑን አትርሺ። ባንቺ ውስጥ እኔ አለሁ በእኔ ውስጥ በአካል እንኳ በሌለሽበትም ሥፍራ አንቺ አለሽ። ኧረ ይቺን ሴት አንድ በሏት ከማለቴ እና ሶስተኛ ወገን ከመጋበዜ በፊት ይህን አልኩሽ፤ ብለህ ንገራት ፤ ትሰማለች!!
ትዳር ማለት የተንደላቀቀ መኖሪያ ቤት፣ የተሟላ ማዕድ፣ ውድ ጌጣጌጦች፣ አስገራሚ መኪና፣ ድንቅ የመዋኛ ገንዳና ተለዋጭ የክረምት ቤት መስራት ማለት አይደለም። ትዳር ማለት ትንሽ ንትርክ ፣ ትንሽ ወቀሳ ፣ ትንሽ ለቅሶ፣ ትንሽ እጥረት፣ ትንሽ ዋ! ዋ!፣ ትንሽ አንተ ነህ አንቺ ነሽ መባባል ያለበት መነፋፈቅ ነው። ክብርና ዝና ብቻ መልካም መልካም ብቻ የሚጠበቅበት የመላዕክት ጥምረት አለመሆኑን መረዳት አስተዋይነት ነው።
በአጠቃላይ ጋብቻ ወይም ትዳር በሁለት ተጋቢዎች መካከል የሚፈጸም የእድሜ ልክ ልባዊ ውል እንጂ በወረቀት የሚታሰር አክሲዮን አይደለም ። የሃሳብ ፣ የአካል ፣ የንብረትም በሉት የህልምና መንፈስ ጥምረት ያለበት የመውጣትና የመውረድ ህይወት እንጂ የሙከራ ላቦራቶሪ አይደለም። ሲሆን ሲሆን ይሄዳል፤ ሳይሆን “ጥንቅር ብሎ ይቀራል” ተብሎ በኮንትራት ለመለያየት እስከመገንጠል ድረስ ተብሎ የሚጻፍና በሸንጎ አብላጫ ድምጽ ውሳኔ ህዝብ የሚሰጥበት ረቂቅ አይደለም።
እነሱው 50%–50% ሆነው ገብተው መቶ ሆነው የሚጨርሱበት ቤት ነው ፤ ቤተሰብ፣ የህብረተሰብ መሰረት የትልቋ ሀገር መንግስት ተምሳሌት ነው!! በነገራችን ላይ፣ በኣመት አንዴ የቤተሰብ ሳምንት ተብሎ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለምን አይከበርም? ማነህ ደግሞ የዚህ ሃሳብ ባለቤት ነኝ ባይ። ከአሁኑ አስታውቅ። ነገር መሬት ሲይዝ፤ ሰው በሥራ ሲያዝ፤ ደርሰህ እያለቃቀስክ ፣ ሃሳቤን ሰርቀውኝ እንጂ ሃሳቡ ፤ የኔ ነበር፤ እንዳትል።
መልካም የቤተሰብነት ሳምንት!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ