ከአስር ለዘለሉ ተከታታይ ዓመታት በሁለት አሃዝ እያደገ እንደነበር የተነገረለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ በሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ቅኝት ጉዞው ከእድገቱ ባሻገር የራሱ ውስንነቶች እንዳሉበት በተለያየ መልኩ ሲነገር ይደመጣል። በቅርቡ ለንባብ የበቃው ‹‹መደመር›› የተሰኘው መጽሐፍም ይሄንኑ ያረጋገጠ ሲሆን፤ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን መፍጠሩን ያትታል። የገበያ፣ የመንግሥትና የሥርዓት ጉድለቶች መኖራቸውም የዚህ ችግር ተደማሪ መገለጫዎች ሲሆኑ፤ የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የሥራ አጥነት፣ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን መዛባት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሙስናን የመሳሰሉ ችግሮችን ፈጥሯል።
በመሆኑም የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት ቢችልም በእነዚህና መሰል ችግሮች ውስጥ እየዳከረ ያለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓቱ የነፃ ገበያ ሂደት ሊፈተሽ እንደሚገባ በመግለጽ፤ ይሄን መሠረት በማድረግም ኢኮኖሚው በእውቀት ላይ ሊገነባ እንደሚገባው ያትታል። እኛም ለዛሬው እትማችን ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ ገለጻዎች መካከል በመጽሐፉ ‹‹ዕውቀት መር ኢኮኖሚን የመገንባት ትልም›› በሚል ንዑስ ይዘት ስር የቀረበውን ሙሉ ሃሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የአገራችንን ኢኮኖሚ ስሪት ምርታማና ተወዳዳሪ በማድረግ በተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ዓውድ ፈጣን፣ መጠነ ሰፊና ተከታታይ ዕድገት ልናረጋገጥ ይገባል። ይህም መሆን ያለበት ከድህነት በፍጥነት መውጣት፣ በምግብ ራሳችንን መቻልና ለወጣቶች አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስፈልግበት ወሳኝ አገራዊ ምዕራፍ ላይ ስለምንገኝ ነው። ከረጅም ጊዜ አኳያ ይሄንን ዓላማ ለማሳካት አገራችን በበቂ የቴክኖሎጂ አቅም ላይ የተመሰረተ እውቀት መር ኢኮኖሚን የመገንባት ትልም ልትይዝ ይገባል። የእውቀት መር ኢኮኖሚ ልማትን ለማምጣት በዘላቂነት በውጭ አገር ቁጠባ፣ ብድርና እርዳታ ላይ ያልተመረኮዘ፤ ራስ ገዝና ከራሱ እየተማረ ራሱን እያረመ የሚያበቃ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት መሆን ይኖርበታል።
በዚህ ራዕይ ስር የአገራችንን ሕዝብ አሰ ልፈን አስፈላጊውን የልማት ፋይናንስና ሀብት ለማሰባሰብ የግዴታ የርዕዮተ ዓለም እስረኛ መሆን እንደማይጠበቅብን የሚያላክት ሃሳብ እናገኛለን። ለአገራችን የሚያስፈልጋት መፍትሔ ግልጽ፣ ሊተገበር የሚችልና ከአገራችን ተጨባጭ ችግሮችና ሁኔታዎች የሚመነጭ መሆን አለበት።
አጠቃላይ ማዕቀፉ ዕውቀት መር ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችሉ ገበያን መሠረት ያደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ክምችትን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ የምርት ኃይሎችን ቅልጥፍናና ምርታማነት ማጎልበት መሆን ይኖርበታል። ይህን ሥርዓት በሂደት ለማጎልበት ጥንቃቄ የተሞላበትን የመንግሥት ንቁ ተሳትፎ የሚፈልጉ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ፖሊሲዎችን መንደፍና መተግበር ያስፈልጋል። እንዲሁም የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዋነኛ መዘውር እንዲሆን የማድረግ ስልት መቀየስ ይኖርበታል።
ቀጣዩ የአገራችን የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ምህዳር የሚፈጥር፣ ማህበራዊ ፍትህን የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ግብ ያለው ሊሆን ይገባል። እነዚህን ዓላማዎች ሊያሳካ የሚችለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ፣ ገበያንና ልማታዊ ጣልቃ ገብነትን አቀናጅቶ የኢኮኖሚ አቅርቦትን ለማስፋፋት የሚወሰድ ነው።
የዚህ ማሻሻያ ማዕቀፍ ዋነኛ ትኩረት የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ መንግሥት መር የነበረውን የኢኮኖሚ እድገት፣ በሂደት በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ እድገት ማሸጋገር ነው። እንዲህ መደረጉ በተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ እድገቱ ወደኋላ ሳይመለስ እንዲቀጥል ከማድረግ በዘለለ የተንሰራፋውን የሥራ አጥነት ለማቃለል እና ሌሎች በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን ለመፍጠር ያስችላል።
የኢኮኖሚ ምርታማነትን፣ ቅልጥፍናን እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ትኩረታችን በዋናነት ገበያው እና የግል ዘርፉ ላይ ቢሆንም የግል ዘርፉ በራሱ ፍትሃዊ የሀብት ድልድልን በተናጥል ይፈጥራል ማለት አይደለም። የግል ዘርፉ ምርታማነት የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን ሀገራዊ ሀብትን በማግዘፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን ያገዘፈውን ሀብት ለሁሉም ሕዝብ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ያከፋፍላል ማለት አይደለም።
ድህነትን ለማስወገድ ያለመ የልማት ውጥን በፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል መነጽር ሲታይ ድህነትን ‹‹ፍጹም›› እና ‹‹አንጻራዊ›› በሚል በሁለት መልኩ መመልከት ይቻላል። በ‹‹ፍጹም ድህነት›› ውስጥ የሚገኙ ማህበረሰቦች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ቋሚ መስፈርቶች መሠረት በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህን ማህበረሰቦች ከድህነት ውስጥ ለማውጣት በዋነኝነት የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። በዚህም ስር ነቀል በሆነ መንገድ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኘውን ዜጋ ከድህነት ወለል በላይ ለማድረግ በመስራት ላይ ያተኩራል።
በሌላ በኩል ደግሞ የ‹‹አንጻራዊ ድህነት›› አረዳድ አካባቢያዊ ንጽጽርን ታሳቢ በማድረግ፣ በኢኮኖሚ እድገት ፍትሓዊ ተጠቃሚ አለመሆን ነው የሚል ብያኔ ይሰጣል። የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በቋሚነት ለማረጋገጥ ምርታማነት እና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች በመፍጠር ላይ ትኩረት ያደርጋል። ዓላማውም ለሥራ ፈጠራና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ የኢኮኖሚ እድገቱን ፍጥነት በመጨመር፣ የኢኮኖሚውን መጠን ማሳደግና አስተማማኝና ጥሩ ክፍያ የሚያስገኙ የሥራ ዕድሎችን በማስፋት ላይ ያተኩራል። ደካማና ዘገምተኛ የኢኮኖሚ እድገት በተዘዋዋሪ ኢፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊፈጥር ይችላል የሚል እሳቤ አለው።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሁለቱም የድህነት ዓይነቶችን የመቀነሻ ስልቶች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ሳይሆኑ በተመጋጋቢነት ሊተገበሩ የሚገባቸው ናቸው። ባለፉት ዓመታት በዋናነት አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምና በሌሎችም ፖሊሲዎች ትግበራ አማካኝነት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። ሆኖም ከፊታችን የተደቀነው ተጨማሪ ችግር ውሱን ምርታማነት ባላቸው ዘርፎች ወይም በምርት ሂደት ውስጥ ጠቅልሎ ያልገባውን ሰፊ የሰው ኃይል ወደ ልማት ለማስገባት መቻል ነው።
ለአብነት ያህል የአገራችንን የአገልግሎት ዘርፍ ብንመለከት የሥራ ዕድልን ጨምሮ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ፈርጀ ብዙ አስተዋጽዖ እየጨመረ ይገኛል። ሆኖም ግን ይህ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የተመረኮዘው በኢመደበኛ ንግዶችና ጥሩ ክፍያ በማያስገኙ መስኮች ላይ ነው። በእነዚህ ዘርፎች የተሰማራው ደግሞ አብዛኛው ድሃው የማህበረሰብ ክፍል በመሆኑ መዋቅራዊ ለውጥ ሲታሰብ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ በዚህ እውነታ አንጻር መመዘን ይኖርበታል።
በመሆኑም በቀጣይ ዋነኛው የልማት ስልት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የምርታማነት እድገት መሆን ይኖርበታል። ይህ ስልት ፈጣንና ተከታታይ እድገት በማስመዝገብ አስተማማኝ የሥራ ዕድል፣ የድህነት ቅነሳና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የቅብብሎሽ እድገት የሚያመጣ ውጥን ነው። ሆኖም ግን ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ የምንከተለው ስልት ፍትሃዊነትን፣ ምርታማነትን እና የዜጎች ደህንነትን የሚያረጋግጥ መሆን ይጠበቅበታል።
ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የምርታማነት እድገት ወይም የአቅርቦት ማስፋፊያ ርምጃዎች በሚከተሉት ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። እነርሱም፡- ጥብቅ የኢኮኖሚ ፍላጎት አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ስብጥርንና ዘመናዊነትን ማጎልበት፣ ፉክክርንና ትብብርን መሠረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ልማት፣ እንዲሁም ትምህርትና ሥራ ፈጣሪነትን ማዳበር ናቸው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ወንድወሰን ሽመልስ