ለረጅም ዓመታት በፍትህ ስርዓት ውስጥ አሳልፈዋል።ከመንፈሳዊውም ከዘመናዊ እውቀትን ቀድተዋል ፤የተለያዩ የሥልጣን እርከኖችን አልፈዋል ።የተለያዩ መጽሔቶችን በዋና አዘጋጅነት መርተዋል፤ የፅሁፍ ስራም አበርክተዋል ።
ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያን ዘመናዊ የዳኝነት ሙያ ጅማሮን ከዘመናዊው ፍርድ ቤቶች አመሠራረትና የየዘመኑ ጉዞ ከታሪክ ሰነዶችና ከደራሲው ልምድና ገጠመኝ ጋር በማዋሃድ ክፍተቶቹ ላይ ተችተዋል፤ ጠቃሚ ያሉትን ሐሳብ ሰንዝረዋል። የዳኝነትን ዓለም አቀፋዊና ዘመናዊ ገጽታና ሚናን ከዳኝነት ሙያ ነፃነት፣ ሕጋዊነት፣ ተጠያቂነትና የዳኞች የሥነ ምግባር መርሆዎች ምን እንደሆኑ በሚገባ የሚፈትሽ መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል።
እኚህ ግለሰብ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ከሁለት አስርት በላይ በቆየው መንግሥታዊ አገልግሎታቸው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የሠሩ ናቸው። ከረጅሙ የስራ እና የኃላፊነት ጉዟቸው እና ከህይወት ተሞክሯቸው እንዲያካፍሉን የዛሬ የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን አድርገናቸዋል- አቶ ግርማሥላሴ አርአያን።
ልጅነት እና ትምህርት
አቶ ግርማስላሴ አርአያ የቁልቢ ገብርኤል ገበዝና ቄስ ከነበሩት ከአባታቸው ከመምሬ አርአያ ወልደ ጊዮርጊስ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ፈትለወርቅ ኪዳነወልድ ጣሊያን ከወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ ታህሳስ 28 ቀን 1935 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ የሐረር ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ልዩ ስሙ ቁልቢ ገብርኤል ገዳም አጥቢያ ቀበሌ ቄስ አምባ በሚባል ሰፈር ውስጥ ተወለዱ።
ዕድገታቸው እንደማንኛው ገጠር ውስጥ እንደተወለደ ህጻን ሲሆን የተወለዱበት ቤተሰብ ቁጥር ብዙ በመሆኑም ወላጆቻቸው በችግር እንዳሳደጓቸው ይናገራሉ።ቤተሰቦቻቸው ጋር ያገኙትን ከቀመሱ በኋላ ለተጨማሪ ምግብ ቤተክርስቲያን በመሄድ “ዘኬ” በመቀበል ይበሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የጨዋታም ፣የመመገቢያም፣ የልጅነት ትውስታቸውም ያለው እዛው ቁልቢ ነው ፤ታዲያ ይህ የመፈንደቂያ ቦታቸው የጥበብ ቦታቸው በመሆን ከፊደል ገበታ ጋር ከመተዋወቅ እስከ ዳዊት መድገም የደረሱበትም ነው።
ዕድሜያቸው 13 ዓመት እስኪሆን ድረስ በዘመኑ የሚሰጠውን የቤተ ክህነት ትምህርት በመከታተል ፊደል ሲቆጥሩ ፣ዳዊት ሲደግሙ፣ ዜማ ሲማሩ በቁልቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አደጉ። በልጅነታቸው በአቡነ ቴፍሌስ ባገኙት የድቁና ክህነት ማዕረግ በቁልቢ ገብርኤል ገዳም በድቁና ለማገልገል በቁ።
የዘመናዊ ትምህርት ትውውቅ
ግርማስላሴ ልክ 13 ዓመት ሲሞላቸው ማለትም መስከረም 18 ቀን 1948 ዓ.ም ከቁልቢ ገብርኤል አጥቢያ ሰበካ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በመዘዋወር የዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመማር በልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ተመዘገቡ። የትምህርት ዕድሉ የተገኘው እንዲህ ነው።ታዳጊ ግርማ በወቅቱ ከቤተክርስቲያኒቱ በድቁና አገልግሎታቸው በሚያገኙት ሳንቲም ለዘመናዊ ትምህርት ቤት መግቢያ ማጠራቀም ጀመሩ። እርሱም ለትምህርቱ በቂ አለመሆኑን ሲረዱ ወተር ወደሚባል አካባቢ በመሄድ በቦታው የሚመረተውን ብርቱካን ፤ማንጎ ፣ሸንኮራና አትክልት ወደ ከተማ በማምጣት እያተረፉ በመሸጥ ለትምህርታቸው ማጠራቀማቸውን ቀጠሉበት።
ልክ እንደወትሮ በዕለተ ሰንበት ቤተክርስቲያን ሊያለግል ይሄዳል ፤ገዳሙ ውስጥ እንደደረሰ ልጃቸውን ክርስትና ሊያስነሱ ከአዲስ አበባ የመጡ አንድ ባላባት ያገኛል።በወቅቱ ደግሞ የመቀደስ ዕጣው የወደቀው ልጅ ግርማስላሴ ላይ ነበር።ታዲያ ከአዲስ አበባ የመጡት ባላባት ፊትአውራሪ ይብርኦ ጋርዴ ከክርስትና በኋላ ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ማብላት ይፈልጋሉ።
ታዲያ እኚህ ባላባት ለምግብ ዝግጅቱ ከውሃ ጀምሮ እስከ እንጨት እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን የሚያቀርብላቸው ሰው ሲፈልጉ የያኔውን ልጅ ግርማስላሴን ያገኙቸዋል።አመለ ሸጋው ዲያቆን ሰውዬው የሚያስፈልጋቸው በማቅረብ ይታዘዛሉ፤ የታዘዙትንም አንዱም ሳይቀር ይከውኑታል፤በዚህ ወቅት ነው ታዲያ የአቶ ግርማስላሴ ታላቅ ወንድማቸው መጥቶ ይህ ሰውዬ ሀብታም ስለሆነ ዝግጅቱን ጨርሶ ሲሄድ ገንዘብ ሊሰጥህ ይችላል፤አንተ ግን ገንዘብ አልፈልግም ነበር ከቻሉ ትምህርት ስለምፈልግ ያስተምሩኝ በላቸው ብሎ መከራቸው እርሳቸውም ይህንኑ አደረጉ።ታዲያ ወቅቱ በ1947 ዓ.ም ሰኔ ወር በመሆኑ የክረምቱ ጊዜ ካለፈ በኋላ ፊት አውራሪ ይብራኦ ጋርዴ አድራሻቸውን ለአቶ ግርማስላሴ በመተው ከጳጉሜ አንድ እስከ አምስት ባለው ጊዜ አዲስ አበባ ቀበና አካባቢ እንዲገናኙ ይቃጠራሉ።
በዚህ መሃል ታዲያ መምህር የሆነው ወንድማቸው ትምህርት ቤት ክረምቱን ዝግ ስለሆነ ለዕረፍት ቤት ይመጣል፤የያኔው ታዳጊ ግርማስላሴም ጉዳዩን ለወንድማቸው ያስራዳሉ፤ወንድምየውም ጉዳዩን ከሰማ በኃላ ስራ ሊያሰሩህ እንጂ አያስተምሩህም ስለዚህ እኔ ድሬዳዋ ሄጄ አናግርልሃለው፤ ድሬዳዋ ሄደህ ትማራለህ ፤ለሚያስፈልግህ ወጪም በወር አስር ብር እልክልሃለው፤ ማደሪያም አክስቶቻችን ጋር ይሆናል ይሏቸዋል እርሳቸውም ተስማምተው ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ድሬዳዋ አቀኑ::
በድሬዳዋ ልዑል መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እጅግ ጎበዝ በመሆናቸው በዕጥፍ በማለፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአራት አመት ውስጥ አጠናቀቁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ከድሬዳዋ እንደገና ወደ ሐረር ጉዞ አደረጉ፤ጊዜው በ1952 ዓ.ም ነበር፤በሐረር ከተማ የመድኀኔያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ::
በ1955 ዓ.ም ከሐረር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርት ክፍል ተማሪ ሆነው ሁለት ዓመታትን አገባደዱ።አቶ ግርማስላሴ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባሉበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ማስታወቂያ ያወጣል፤ በዚህ ጊዜ እርሳቸውም ወደ ህግ ትምህርት ክፍል ተዘዋውረው የሚማሩበትን ዕድል አገኙ።የተማሩበት የሕግ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት ይጠይቅ ነበር።ታዲያ አቶ ግርማስላሴንና ጓደኞቻቸውን ብቻ ታስቦ የተዘጋጀ እስኪመስል ድረስ ትምህርት ክፍሉ ያዘጋጀውን ጠቅላላ መስፈር ያሟሉ ነበር፤አለፉ።በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከንባብ ባሻገር ከጓደኞቻቸው ጋር ውቤ በርሃ በመሄድ ይዝናኑ ነበር።ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ትምህርት ያገኙት 1960ዓ.ም አንደነበር ያስታውሳሉ።
ብሔራዊ አገልግሎት
በወቅቱ የብሔራዊ አገልግሎት የተጀመረበት በመሆኑ ማንኛውም ተማሪ ከተመረቀ በኋላ ወደ ስራ ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት አገሪቱ በምትመድበው በየትኛውም ቦታ አገሩን ለአንድ ዓመት ማገልገል አለበት።በዚህ መሰረት አቶ ግርማ ስላሴ ለሀገራቸው የብሔራዊ አገልግሎት ለመስጠት ወደ አገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤት ገቡ፤ የግብር ቅሬታ እና አቤቱታን በመስማትና መፍትሔ በመስጠት ለአንድ ዓመት አገለገሉ።ከአንድ ዓመት በኋላ በፍትህ ሚኒስትር በሙያቸው ለማገልገል በቋሚነት ተቀጠሩ ።
ታዲያ ታታሪው እና ታዛዡ ግርማስላሴ በስራው ትጉህ በእውቀቱም ሙሉዕ በመሆኑ በወቅቱ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት እና የንግድ ችሎት ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ፍትህአወቅ የሚባሉ ግለሰብ የአቶ ግርማስላሴን ትጋት በማየት የእርሳቸው ምክትል አድርገው ሾሟቸው።በዚያ ወቅት እሳቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት አለቆቻቸውን ማስደመም ቀጠሉ።
በዚህ ስራቸው የተገረመው አለቃቸውም በረዳትነት ከተሾሙ ገና ሶስት ወራቸው ቢሆንም ለዋና ዳኝነት አጯቸው። የወቅቱ የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ ይህ ሰው ወደዚሀ ተቋም የመጣው ቅርብ ጊዜ ነው በዚህ ላይ በጣም ወጣት ነው እንዴት ብዬ ነው ንጉሱ ጋር ሄጄ ሹሙልኝ የምለው ፤ለሹመት ባንቻኮል ጥሩ
ነው፤ትንሽ ይታይ በማለታቸው ሹመቱ ለጊዜው ቀረ።
ለምን አልተሾምኩም ብለው በስራቸው ላይ አንዳች ክፍተት ሳያሳዩ ከአሁን ቀድሞ በነበራቸው የትጋት ልክ ስራቸውን መስራት ተያያዙት፤ለአንድ ዓመት ያክል ከአገለገሉ በኋላ በ1962 ዓ.ም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ተሾሙ። አቶ ግርማስላሴ ከሴቶች እና ህናጻት ችሎት እስከ ቤተሰብ፣ ከወንጀል እስከ ፍትሀብሄር ያላዩት የችሎት ዓይነት፤ ያላስቻሉት ችሎት እና የጉዳይ አይነት የለም።
በዚህ የዳኝነት ሹመት እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተው በዚሁ ዓመት የመንግስት ለውጥ ሲካሄድ በወቅቱ በንጉሱ ተሹመው የነበሩ አፈንጉሶች ደርግ ከኃላፊነት አነሳቸው። በዚያ ጊዜ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩትን እና ወጣቶች የሆኑት የሀገሪቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ዳግመኛ እንዲሾሙ ተደረገ ።
ለአንድ ዓመት ደግሞ በ1968 ዓ.ም በተዘዋዋሪ ችሎት በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫ በመጓዝ ፍትህ በመስጠት አገለገሉ። ከተዘዋዋሪው ችሎት መልስ ለሌላ ግዳጅ ጉዞ ወደ ኤርትራ። በኤርትራ ለአንድ ዓመት ያገለገሉ ሲሆን ወቅቱ ጦርነት እንደነበር የሚያወሱት አቶ ግርማስላሴ ከፍርድ ቤት ወደየትኛው ቦታ መሄድ አይቻልም ነበር፤እንደዛም ሆኖ ግን ችሎት እያስቻሉ ፍርድን ይሰጡ ነበር።ታዲያ በወቅቱ ጋዜጠኛ ሉሌ የተባለ በቦታው በመሄድ እንግሊዞች ከፍርድ ቤት ከወጡ በኋላ ያገኙት ጥሩ ዳኛ ማን ነው ብሎ ህብረተሰቡን በአነጋገሩበት ወቅት አቶ ግርማስላሴ ብለው እንደነገሩት በጋዜጠኛው ማስታወሻ ላይ ለማየት እንደቻሉ ይናገራሉ።
በሹመታቸውም እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ከአገለገሉ በኋላ ደግሞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለሶስተኛ ጊዜ ተሸሙ:: ከስድስት ዓመታት በኋላ ዲግሪያቸውን ከአገኙ ልክ ሃያ ዓመት ሲሞላቸው በ1980 ዓ.ም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ።
በዚህ ማዕረግ አገራቸውን ለአራት ዓመታት እንዳገለገሉ፤ በወቅቱ የነበረው መንግስት ብዙ ሰዎች ማሰር ጀመረ። ዳኞች ያለ ምንም ምክንያት ነው የታሰሩት ብለው ፈቷቸው። ጉዳዩ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወደ ሆኑት አቶ ግርማስላሴ ቀረበ። እሳቸውም “ዳኞቹ የሚሰሩት በህግ ነው። ስለዚህ እነሱን ከህግ ውጭ ስሩ ብዬ ማዘዝ አልችል” በማለት መልሳቸውን ይሰጣሉ። በዚህ የተቆጡት ባለስልጣናት ለአሰራራቸው ያልተመቿቸውን አቶ ግርማስላሴን ጨምሮ ከ70 በላይ የሚሆኑ ዳኞችን አሰናበቷቸው።
አቶ ግርማስላሴ ዕድሜያቸው ለጡረታ ሳይደርስ ፣ የጤና ዕክል ሳይገጥማቸውና ጡረታ መውጣት ሳያሻቸው ሰኔ 1984 ዓ.ም በጡረታ እንዲገለሉ ተደረገ።በዚያ ጊዜ ለኢዮቤልዩ አንድ ዓመት ይጎላቸው ነበር። እሳቸው በወቅቱ በጡረታ ቢገለሉም ቀሪ ዘመናቸውን ስራ በመፍታት አላሳለፉም። በጥብቅና ስራ ላይ ተሰማርተው እስካሁን ድረስ በማገልገል ይገኛሉ።
ሶስት ጉልቻ
ስለ ትዳራቸው ሲያስብ “ብዙ የቤተሰብ ችሎት አይቻለሁ፤ ችግሩንም መልካም ጎኖቹንም አውቃለሁ “ የሚሉት አቶ ግርማስላሴ ሙያቸውን በጣም ስለሚወዱ የህይወት መርሀቸውም ከዚያው የሚቀዳ መሆኑን ይናገራሉ። የሰው ልጆች በዚህ ምድር ላይ በማህበራዊ መስተጋብር እንደ ህብረተሰብ ክፍል ብሎም እንደ ሀገር መኖር የጀመሩበት ጊዜ እና ቦታ ላይ የታሪክ ሊቃውንት በእርግጥ ይሄ ጊዜና ቦታ ባይሉንም ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠሩ ይገልፃሉ። የአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም ዋናው ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ወንድ እና ሴት በሚፈጸሙት ጋብቻ ነው ወንድ እና ሴት ያልኩት ሀይማኖትም በህግም የማይፈቀድ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ስላለ ነው:: ቤተሰብ የህብረተሰቡ ዋና ምሰሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ ሊሰጠው ይገባል። ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ በሕግና እና በስርዓት መመራት ይኖርበታል።
የቤተሰብ መመስረቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ በአወጣው ሕግ መሠረት መመሥረት ይኖርበታል። ስለዚህም እኔ እጅግ በአነበብኩትና በአስተዳደጌም ተጽዕኖ ስር ወድቄ ሴት ልጅን ለጋብቻ መጠየቅ የማይሆንልኝ ጉዳይ ነበር ይላሉ።ታዲያ አንድ ከዚህ ቀደም በቤተክህነት እያለሁ የማውቃቸው በጀረወንድ ተሰማ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው አገኘኋቸው:: ለእሳቸው እባክዎትን ሚስት ፈልጉልኝ ብዬ ጠየኳቸው:: እርሳቸውም በሚሰሩበት መስሪያ ቤት ጸሐፊ የነበረች ወይዘሪት ሮማን ሱራፌልን ስለአቶ ግርማስላሴ የስራ ሁኔታ እና የግል ጠባይ በመንገር ለጋብቻ እንዲጣመሩ ያነጋግሯታል ፤ እርሷም ከመወሰኗ በፊት በአካል አቶ ግርማስላሴን ማየት እንደምትፈልግ ትገልጻለች፤በጅረወንድ ተሰማም አቶ ግርማስላሴንና ወይዘሪት ሮማን ሱራፌልን አገናኟቸው።ከዚያማ መገናኘቱ ቀጠለ፣መዋደዱ ከፍ አለ፤ ፍቅሩ ደራ በ1971 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ጋብቻ ፈጸሙ።ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ሮማን ይሄይስ እና ሶፎኒያስ የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆች አገኙ። ልጆቻቸውን አስተምረው ፣ኩለው ድረው ዛሬ የልጅ ልጅ አይተዋል።አቶ ግርማስላሴ ለ42 ዓመት በትዳር የጸኑም የስራም የግል ህይወታቸውም አስተማሪ የሆኑ ግለሰብ ናቸው።
መፅሐፍ ለንባብ የማብቃት የሀሳብ ጥንስስ
እኚህ የህግ ባለሙያ ከአደጉበትና ከኖሩበት ልዩ ልዩ የህይወት ተሞክሮ፣ በተማሪነት ዘመናቸው ከቀሰሟቸው ዕውቀቶች ፣በስራ ዘመናቸው ካካበቷቸው የስራ ልምዶች፣ ከተሳተፉባቸው ብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ የጉባኤ ልምዶች ለሙያቸው ዕድገት የበኩላቸውን ለማበርከት የተለያዩ የጥናት ስራዎቻቸውን በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የምርምር መጽሔቶች ሲያሳትሙ ቆይተዋል።
ከእነዚህም በተጨማሪ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት “ችሎት”የምትባል መጽሔት እንድትዘጋጅ በማድረግና በመምራት ጽሁፎችን በማበርከት ተሳትፈዋል።በ1997 ዓ.ም በነበሩት የግል የህትመት ውጤቶች ላይ ስለ ህግ ፣ፍትህ እና ተያያዝ ጉዳዮች ይጽፉ ነበር።እነዚህ እና የወንድማቸው ጉትጎታ ታክሎበት የብዙ ጥናቶች ተግባራዊ ልምዶች እና ንባብ ውጤት የሆነው መጽሐፍ እውን ሊሆን በቅቷል።
“ዳኝነት ከጥንት እስከ ዛሬ “መጽሐፍ ዓላማ አድርጎ የተጻፈበት ምክንያት ዓለምአቀፋዊ ይዘት ስላለው የዳኝነት ስርዓት አመሰራረት፣ታሪካዊ ሂደትና ወቅታዊ ሁኔታ ለማመላከት ነው። ዳኝነት በተግባር ላይ መዋል የጀመረው ከጋሪዮሻዊ የኑሮ መልክ መኖር ሲጀምር መሆኑን ታሪካዊ ዳራዎች እንደሚያስረዱ ጠቁመው በዚህም በአብሮነታዊ ኑሮ ውስጥ የተለያዩ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ያድጋሉ።አርሶ አደሩ ከነጋዴው አገልግሎት ሰጪው ከአገልግሎት ተቀባዩ …ወዘተ በሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። ስለዚህም በአብሮነት የኑሮ ዘዬ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ቅራኔዎችን ለመዳኘት በአካባቢው በገለልተኝነታቸው፣ በሕግ አዋቂነታቸው፣ በገላጋይነት ሚናቸው የታወቁ አስታራቂዎችን በመምረጥ አልያም በመንግስት በሚቋቋም ፍርድ ቤቶች አማካይነት ፍትህ እንዲሰጣቸው ያደርጋል።
ይህ የዳኝነት ወይም የግልግል ስርዓት በተለይ እንደኛ በማደግ ላይ ባሉ አገራት በተለያዩ ተዋረዳዊ የስልጣን ማዕረግ ካላቸው ሹማምንት ጀምሮ እስከ ነገስታት እስከሚያዩአቸው የፍርድ ቤት ጉዳዮች ድረስ ይዘልቃል።ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ቀደም ባሉ የግዛት ዘመናት እንኳን የዳኝነት ስርዓት ምን ዓይነት ይሰጠው እንደነበር ይሆናል።
የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጠንን ማደግን ተከትሎ የሚመሰረተው መንግስት የራሱን ብሎም የአባላቱን ጥቅም ከቀሪው የማህበረሰብ አባላት በተሻለ ሁኔታ እንዲጠበቅ ወይም እንዲያስጠብቅ ህግ እንደራሱ ብቻ በሚገለገልበት መልኩ በመቅረጽ የእሱን ትዕዛዝ ብቻ የሚያስፈጽም ዳኞችን በማስፈራራት ፈላጭ ቆራጭ የሆነ መንግስት ሊያቋቁም ይችላል።በዚህ ዓይነት ሰዓት ደግሞ የአብዛኛው ህዝብ መሰረታዊ መብት በዳኝነትም ሆነ በህጉ አይከበርም።ነገር ግን የአስተዳደር መንበሩ የተቆጣጠረው መንግስታዊ አካል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝብ ድምጽ የሚመረት ከሆነ የሚያወጣቸው ህጎችም ሆነ የሚያቋቁሟቸው የፍርድ ቤት ዳኞች የሚሰጧቸው ብይኖች ፍትሐዊ ሊሆኑ ይችላሉ።የህግ የበላይነትም ይከበራል።
በዚህ ስርዓት የመንግስት አካላት መሰረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ህጎችን ቢያወጡ እንኳን በዳኝነት ዘንድ ተቀባይነት አያገኙም፤ ወይም ዳኞች ህጎች በተግባር እንዲውሉ ያደርጓቸዋል።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 የአሜሪካ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ከተለያዩ ዓለም አገራት ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገባቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች ነበሩ።ነገር ግን የፕሬዚዳንቱ ክልከላ ተግባራዊ እንዳይሆን ሻንጣቸውን ገትረው በተሟገቱ ዳኞች አማካይነት የወጣው የክልከላ ደንብ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።
በመጽሐፌ በስፋት የዳሰስኩት እና ለኢትዮጵያ የምመኘው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስርዓት በህዝብ ድምጽ የሚመረጥ መንግስት እንዲኖር ፣ይህ አካልም የሚያቋቁመው የፍትህ ተቋም ደግሞ ነጻ የዳኝነት ስርዓት የሚተገበር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያቆም ተቋማዊ ነጻነት እንዲኖረው ነው።
መልዕክተ ግርማስላሴ
“እናንተ ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ።ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአገር አንድነት፣ ሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እመክራለሁ።”።እውነት ነው ከምንም ነገር በፊት መቅደም ያለበት የሀገር ሰላም ነው ።አረጋውያኑ ተጡረው፤ ቢታመሙ አስታማሚ አግኝተው መኖር የሚችሉት እና ሲሞቱም በክብር የሚያርፉት የሀገር ሰላም ሲኖር ነው።ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት ሀገር ሲኖር ነው፤ሀገር ሰላም ሲሆን ነው።
“በተለይ ወጣቱን የምመክረው ይላሉ አቶ ግርማስላሴ እኔ በትዳሬ 42 ዓመታት አሳልፊያለሁ ወጣቱ ከማንኛውም ነገር ሁሉ በላቀ ሁኔታ ደስታን የሚለግስ አንድ ነገር አለ ፤ ምን ይሆን ? በጣም ቀላልና በእጅ የሚገኝ ነው። ይህን ምስጢር ምን እንደሆነ ገምቱ ቢባል ብዙ ሰው ቁስ ላይ ሊያጠነጥን እንደሚችል እገምታለው ። ብልሆች ብቻ ግን ምንነቱን ሊገምቱ ሊያውቁትም ይችላሉ። አንዳንዶቹ ጤንነት ፣ ወይም ገንዘብ ፣ ወይም ብዙ ወዳጅ ፣ ወይም ይህን ወይ ያን ሃብት ይሉ ይሆናል:: ግን ፣ እነዚህ ሁሉ ተሟልተው ደስታ ሙሉ ላይገኝ ይችላል። ዝናና ሥልጣንም ደስታን አያስገኙም። ጤንነት ፣ ገንዘብ ፣ ባላንጀራ ፣ የሞቀ ቤት … ሁሉም አስፈላጊ ቢሆኑም ደስታ አያጎናጽፉምና ከእነዚህ ሁሉ የሚልቅ አንድ ነገር አለ። እርሱም እውነተኛ ባልንጀራ ሰው የጠፋ ዕለት ሰው የሚሆኑ ሰው የደስታህ ምንጭ ብቻ የሚሆን ሸክምህ የሚገባው ሁሌም ለባልጀራው የሚኖር ሰው የደስታ ምንጭ ነው።እኔ የታደልኩት ይህንን ነው ፤ወጣቱም ከቁስ ተላቆ እውነተኛ ረዳት ይፈልግ ሌላው እዳው ገብስ ነው። ”ስለዚህም እውነተኛ አጋር ካለ ምንም እንኳን ህይወት በፈተና የተሞላችም ብትሆንም ደስታ የጸና ይሆናል።ከዚያ መቻቻል ሌላኛው ቁልፉ ነው። በዚህ ትዳርን ማጽናት ይቻላል።
እነዚህ የአቶ ግርማስላሴ ምክሮች ግልጽ የሆነ ሁሉንም የሚያስማማ ምክሮች ናቸውና ምክራቸውን ተቀብለን እንድንተገብረው ይሁን፤ ለአቶ ግርማስላሴም ቀሪ ዘመናቸው ያለሙትን የሚፈጽሙበት እንዲሆንላቸው እንመኛለን ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
አብርሃም ተወልደ